‹ታሪክ›ን መሣሪያ ያደረገ የፖለቲካ አካሄድና ያስከተላቸው ችግሮች

0
1069

በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚታዩ የፖለቲካ አሰላለፎች የኋላ ‹ታሪክ›ን መሰረት ያደረጉ ይመስላሉ። አንዳንዶችም እንወክልሀለን ያሉትን ሕዝብ ለማሳመንና መሪውን ለመጨበጥ፣ ተከታይ ሕዝብ በመስመራቸው ለማዥጎድጎድ ታሪክን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ይህንን ሀቅ የሚሳዩም እልፍ አእላፍ ማስረጃዎች አሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው የቀደሙ ታሪኮችን በተዛባና በተጋነነ መንገድ እየተረኩ የልዩነት መነሻ አጀንዳ በማድረግ የሚለያየውን እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ይልቁንም ውስጣዊ ችግሩን ተረድቶ ፍላጎቱን የሚዳምጠው መሪ እንደሚሻ ግልጽ ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚታየው የፖለቲካና የ‹ፖለቲከኞች› አካሄድ የቀደሙ ታሪኮችን በማንሳት የትግል ስልት ማድረግ ነው። በዚህም ታሪክን ከጥቅሙ ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግጭትና የቀውስ መንስኤ እንዲሆን አድርገውታል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ እስከ አሁን የነበሩና አሁንም የሚታየው የፖለቲካ አካሄድ ታሪክን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ክፍተቶችን በመሙላት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ አይደለም። በአንጻሩ በፖለቲከኞችና በአንዳንድ ቡድኖች ፍላጎትና አረዳድ አንድ ታሪክ ኹለት እና ከዛ በላይ ታሪካዊ ትርክቶች፣ እንደየቡድኑ ተሰጥቶት ይታያል።

የታሪክ ምንነትና የታሪክ ጥቅም ምን እንደሆነ የተገነዘቡ የማይመስሉት እነዚህ ፖለቲከኞች፣ የታሪክ ጠቀሜታ ዘንግተዋል በሚል ትችቾችን ሲያስተናግዱ ይታያል። በተጓዳኝ ምሁራን እንደሚያስረዱት ታሪክ የጥንት ክስተቶች ጥናት በተለይም በሰው ልጆች ጉዳይ ላይ የተደረገ ጥናት ነው።

ታሪክ በተለያዩ የታሪክ ተመራማሪዎች የተሰጠው በተለያየ መንገድ የተገለጠ ትርጓሜ አለ። ከነዚህም ውስጥ ‹አልፋ ሂስቶሪይ› የተባለ ታሪክ ላይ ትኩረቱን አድጎ የሚሠራ ድርጅት ታሪክን ‹ታሪክ ያለፈው ዘመን ጥናት ሲሆን፣ በተለይም በሰዎች፣ ማህበረሰቦች፣ ክስተቶች እና ችግሮች ለመረዳት የተደረገ ሙከራ ነው። ለሁሉም የሰው ልጅና ማህበረሰብ የተለመደ ነግር ነው።›› ይለዋል።

የታሪክ ጠቀሜታን በሚመለከትም ታሪክ ሊጠቅም የሚችለው በእውነታውና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ሲተረክና ካለፈው ለመማር ሲያገልግል የሰው ልጆች የቀድሞ ታሪካቸውን እንዲያውቁና መልካም ባህሎችንና ተሞክሮዎችን በማስቀጠል በአንጻሩ ከቀደሞ ስህተቶች በመማር በነባራዊ ሕይወታቸው ላይ ታሪክን በማገናዘብ የተሻለ ነገ ላይ እንዲደርሱ ማድረጉም ሌላውና ወሳኝ ጥቅሙ እንደሆነ በታላላቅ የታሪክ ጸሐፍት ተመዝግቦ ይገኛል።

ታሪክ ጉልህ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ሁሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት ብለው የሚሞግቱም አሉ። ይህንንም በኢንግሊዘኛ <The Advantage and disadvantage of History for life> በሚል ርዕስ በሃኬት ክላሲስ የተጻፈ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት ተተንትኖ እናገኘዋለን። እንዲህ ያለ ዕይታ አንድም መነሻው የተጻፉ ታሪኮች ሁሉ እውነት ላይሆኑ ይችላሉ የሚለው ዕይታ ነው። ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ በኢትዮጵያ አንዳንድ የቀድሞ ታሪኮች ላይ የሚታዩ ኹለት ጽንፍ የያዙ ትርክቶችን ማንሳት ይቻላል።

ትልቁና በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከሚታየው ታሪክ ጠቀስ ግጭታ መሠረት ሆኖ የሚታየው የታሪክ አረዳድና እውነትነት መሳት ጉዳይ ነው። ይህም ራስ ወዳድነት፣ ታሪክን በተወሰኑ የቡድን ምኞቶች መሰረት ማስካከል፣ ለራስ ጥቅምና ሥልጣን ለማግኘት እንዲያመች አድርጎ መተረክ ወዘተ ያመጡት ጣጣ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ በጉዳዩ ሐሳባቸውን የሚሰጡ ባለሞያዎች ይጠቅሳሉ።
ከላይ የተጠቀሰውንና የተጻፉ ታሪኮች ሁሉ እውነት ላይሆኑ መቻላቸው የሚያመጣው ጉዳት በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋል ሁነት መሆኑ ሀቅ ነው። ይህ አይነት የተዛባ የታሪክ አዘጋገብ የአሁኑ ትውልድ ትክክልኛ ታሪኮችን እና አኗኗሮችን እንዳይረዳ እንዳደረገው የዓለማችን እውቅ የታሪክ ባለሙያዎች ያስቀምጣሉ።

ከሳምንት በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ አሁናዊና የወደፊት እጣ ፋንታ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮረ ውይይት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂደዋል። በዚህ ስብሰባ ወቅት ታሪክንና ተረክን መሠረት ያደረገ ውቅቅስ የታለመውን ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ፈተና እንደሚሆንና ጭራሽ ወደ ሌላ ችግር የሚከት፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ መሆኑ ተነግሯል።

በውይይቱ እለት ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡ መካከል መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ያቀረቡትና ወደኋላ አጼ ምኒልክን በማንሳት ያሰሙት የወቀሳ ቃል ከብሔራዊ መግባባት ይልቅ ሌላ ችግር የሚወልድ ሐሳብ ተብሎ በብዙዎች ተተችቶም ነበር። መረራ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቅሬቸውን በማሰማትም ኮንነው አልፈዋል።

ፕሮፌሰሩ በበኩላቸው ‹ባቀረብኩት ጽሑፍ ላይ ቅር የተሰኙ አካላት እምየ ምኒልክን አትንኩብኝ አይነት ሐሳብ ያላቸው ናቸው።›› ሲሉ ከበርካታ አካላት ለቀረበባቸው ወቀሳ ምላሽ ነው ያሉትን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። መረራ አክለውም እውነቱን የማወቁ አስፈላጊነት የማያጠያይቅ ሀቅ ነው ይላሉ። ‹‹ችግሩ ግን እሱ አይደለም፣ የቀረበው ታሪክ ላይ መስማማት አለመቻሉ ነው።›› የሰጡት አስተያየት ነው።

አዲስ ማለዳ በዚሁ ጉዳይ ላይ የታሪክ ባለሙያዎችን አነጋግራለች። የአሀዱ ራድዮ ዋና አዘጋጅ፣ አንጋፋ ጋዜጠኛና ታሪክ አዋቂ ነው፤ ጥበቡ በለጠ። ጥበቡ በመረራ ጽሑፍ ዙሪያ ለአዲስ ማለዳ ሐሳቡን ሲያጋራ ‹‹ትላንት በሆነ ታሪክ/ትርክት ላይ መሠረት አድርጎ የፖለቲካ መሣሪያ ማድረግ ትክክል አይደለም።›› ይላል። ጥበቡ አክሎም ታሪክ በአንድ ወቅት ሆኖ ያለፈ ክስተት መሆኑን በመግለጽ፣ ትናንት የሆነ ክስተትና ኹነትን ዛሬ ላይ እያነሱ መከራከር ለዘመኑ የሚመጥን አይደለም ሲል ይሞግታል።

ከመቶ ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ተመልሶ ለዛሬ ብሔራዊ መግባቢያ ሐሳብ ላይ የጥንት ታሪኮችን ከማንሳት ይልቅ በአገሪቱ አሁናዊ ችግር ላይ መምከሩና የመፍትሔ ሐሳብ ማንሳቱ የሚበጅ ጉዳይ መሆኑን ጥበቡ አጽንዖት ሰጥቶ ተናግሯል።

ሌላኛው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሥማቸው እንዳይጠቀስ በማሳሰብ ሐሳባቸውን ያጋሩ የታሪክ መምህር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ታሪክን እንደ ታሪክነት ሳይሆን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ እየተጠቀሙት ነው ባይ ናቸው። በዚህም ታሪክን መሰረት ያደረጉ የብሔር ፖለቲካን በማቀንቀን የቀደሙ ታሪኮችን በተዘባ መንገድ ሳይቀር በመተረክ፣ አንዱ ማኅበረሰብ በአንዱ ማኅበረሰብ ቂም እንዲይዝ የተደረገበት መንገድ የታሪክ ግጭቱን አባብሶታል ይላሉ፣ መምህሩ።

ጋዜጠኛ ጥበቡ የታሪክ መምህሩን ሐሳብ ይጋራሉ። ፖለቲከኞች ታሪክ ውስጥ ገብተው ታሪክ ለግጭት መንስኤ እንዲሆን ምክንያት ሆነዋል ወይም አድርገዋል በሚለው ሐሳብም ይስማማል። ‹‹በተለይም…›› ይላል ጥበቡ፣ ‹‹በተለይም የብሔር ፖለቲካ አሁን ላይ ለሚታዩት የታሪክና ሌሎች ተያያዥ የኢትዮጵያ ችግሮች ዋነኛ የችግር ምንጭ ሆኗል።››

ታሪክ መምህሩ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲከኞች መካከል የሚታየው የታሪክ ግጭት በዋናነት በኦሮሞ እና በአማራ ፖለቲከኞች መካከል ነው። ለዚህም እንደ ማሳያ በአፄ ምኒልክ ታሪክ ላይ የኹለቱ የብሔር አቀንቃኝ ፖለቲከኞች ለዘመናት የዘለቀ ስምምነት የጠፋበት የግጭትና የጥላቻ መንስኤ ሆኗል ሲሉ የታሪክ መምህሩ ይጠቅሳሉ።

የታሪክ ግጭቶቸን ለማስቀረት በፖለቲከኞችም ሆነ በአንዳንድ የታሪክ ባለሙያዎች በታሪኮች ላይ በመስማማት ወደ አንድ አቅጣጫ የመምጣቱ ጉዳይ አስቸጋሪ መሆንና በታሪክ ላይ አንድ ደምዳሜ ላይ ለመድረስ የፍቃደኝነት ጉዳይ እንደሚጎድልም የታሪክ መምህሩ ይናገራሉ።

ሁሉም የየራሱን አረዳድ የሚከተልበት የታሪክ አተራረክ ዘይቤ አገር ላይ የታሪክ ስምምነት የማይታሰብና የማይቻል ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች የሚያነሱትም የሚስማሙበትም ሐሳብ ነው።
በኢትዮጵያ የሚበጀው የቀድሞ መንግሥታትን ችግር እያነሱ ከመገዳድል ይልቅ ችግሮቻችን ምንድን ናቸው ብሎ ለይቶ ማውጣትና መፍትሔው ላይ መምክር ትልቁ አማራጭ መሆኑን የአፋር ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሙሳ አደም አስቀምጠዋል። ሙሳ አክለውም ‹‹በታሪክ ከታየ ያልተጎዳ ኢትዮጵያዊ የለም። ቢሆንም እውነቱን ማወቁ ነውር አይደለም። ነገር ግን ታሪክን በመናገራችን መርዝ የምንዘራ ከሆነ ትናንትን ትተን ዛሬ ላይ ማተኮረ ነው የሚበጀን›› ሲሉ ጠቁመዋል።

ጋዜጠኛ ጥበቡ በበኩሉ የታሪክ ግጭትን ለማስቀረት ዋናው መፍትሔ ለግጭቱ መነሻ የሆነውን የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎችን ሰብሰብ አድርጎ በአንድ በሚወክሉት የብሔር ፓርቲ ማደረጃት ነው ይላል። ጥበቡ እንደሚለው በታሪክ መጋጨትን ማስቀረት ካልተቻለ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ዘመናትና የመንግሥታት ታሪክ፣ ከአፄዎቹ ዘመን እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥትት ድረስ በርካታ መልካም ነገሮች እንዳሉ በርካታ መጥፎ ነገሮች መከሰታቸውን ያወሳል። እናም አጀንዳው እሱ መሆን የለበትም ይላል።

ይልቁንም አጀንዳ መሆን ያለበት ጉዳይ እንዴት ኢኮኖሚያዊ ችግራችንን እንፍታ፣ እንዴት በጋር እንደግ፣ እንዴት አንድነታችንን እናስከብር የሚለው መሆን አለበት ባይ ነው። ድሮ በአፄዎቹ ዘመን የሆነው ታሪክና ትናንት የተፈጸመውን አጸያፊ ድርጊት እያነሱ አጀንዳ ማድረግ የማይበጅ በመሆኑ፣ መንግሥትም አሁን ላይ የሚታየውን የችልተኝነት ዝንባሌ በመተው ሕግን ማስከበር እንደሚገባ ጥበቡ አመላክቷል።

በአንድ የታሪክ ክስተት ላይ በተለያየ አረዳድ የተተረኩ ታሪኮችን ለማረምና እውነቱን ለመፈለግ የታሪክ ምሁራንን ማወያየትና እውነቱን ተንትኖ ማስቀመጥ አንዱ ወሳኝ ነጥብ መሆንን ጥበቡ ጨምሮ ጠቅሷል።

የታሪክ መምህሩ እንደሚሉት ደግሞ የታሪክ ግጭትን ለማስቀረት እውነቱን በትምህርት ከመረዳት ባለፈ በአሁናዊ ፖለቲካዊ ሁነቶች ጋር ከማገናኘት ማውጣት እንደሚስፈልግ ነው። ታሪክን ማጥናትና እውነቱን መፈለግ ለታሪክ ባለሙያዎች ቢተው መልካም ይሆናል ሲሉም አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here