የአብነት ትምህርት ቤት ትውፊቶች ዘላቂነት በምንና እንዴት?

0
2167

የኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ስርዓት ከአገረ ሰብ ወግ እና ልማዶች ጋር መዋሐድ ያንሰዋል እየተባለ ይተቻል። ሙሉጌታ ገዛኸኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ የትምህርት ስርዓት በመጥቀስ እንዴት እናዘምነው ብለው ይጠይቃሉ።

 

 

ትምህርት ለአንድ አገር ማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና መሻሻል መሠረት ነው። ሰው ልማድና ወጉን ይከተላልና አገርኛ ዘይቤ እንዲኖረው ለራስ ባሕልና ወግ ክብር መስጠት ፈፅሞ አያጠያይቅም። መላው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በአውሮፓ ቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር በዋሉበት የታሪክ አጋጣሚ የባዕድ ቋንቋን ለመጠቀም ተገደዋል። በውሕደ ንሳት የሌላን አኗኗር ዘይቤ እንደወረደ መቀበላቸውም ሁለንተናዊ የመዘበራረቅ ውጥንቅጥ አስከትሏል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነውን ወግና ልማድ ጠብቃ በማፅናት ጥረት ማድረጓ ምንግዜም ያስመሰግናታል። የእኛን ሥልጣኔ ለመቋደስ ቁጥራቸው የትየለሌ የውጭ አገራት ተመራማሪዎች የብራና ጽሑፎች ወደሚገኙባቸው ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት በየጊዜው ይጎርፋሉ።
ባሕላዊ ትምህርት በኢትዮጵያ ከተጀመረ ሰባት ሺሕ ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ። በዚህ ረገድ የቤተ ክሕነት ሊቃውንት ፊደል ቀርፀው ሥነ ጽሕፈት ከነ ባሕሪቱ ለትውልድ የሚበጅ መልካም አርኣያነት አበርክተዋል። በተለምዶ አጠራር ደብተራ ነገር ግን በማዕረግ ደረጃቸው ትልቅ ሰው የሚል ተቀፅላ በደቀ መዛሙርቶቻቸው ዘንድ ልዩ ክብርና ሞገስ ይቸራቸዋል። የነገሥታቱ መዋዕለ ዜና ዘጋቢም ናቸው። ብሒለ አበው ወ እመው ‘አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው’ እንዲሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በረጅም ዘመን ታሪኳ ለዕውቀትና ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍ ያለ ውለታ አላት። ቤተክህነት ወጣቶች መልካም ስብዕና እንዲገነቡና አገራቸውን እንዲያውቁ ባሳየችው አስተዋፅዖ ነቀፌታ የለባትም። በብራና የእጅ ጽሕፈት አጣጣል የመጻሕፍት ትርጓሜን፣ ሃይማኖታዊና የነገሥታት ታሪክ መገኛ ማዕከላት እኚሁ ገዳማትና አድባራቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ባብዛኛው ተበታትነው ልብ የሚላቸው የማጣቱ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ለአእምሮ ቅርስነት የተስፋ ማንቂያ ደወል ሆነው እንዲዘልቁ የሁሉንም ትኩረት ይሻሉ።
ማስተዋል የአዋቂዎች ልጓም ናት እንደሚባለው መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ጥበብ የሚገለጠው በትምህርት የሕሊና ትጋት መሰላልነት ነው። ሊቃውንት አእምሮአቸውን ማበልፀግ የቻሉት በጥንቱ የአብነት ትምህርት አማካኝነት መሆኑ ያኮራል። በዓለማዊው ዕውቀታቸውም ቢሆን የበቁ ምሁራን እንደ ዶክተር ስርጉ ሐብለ ሥላሴ፣ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ዶክተር አያሌው ሲሳይ ወዘተርፈ ሥረ መሠረታቸው ይኸው የአብነት ትምህርት እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት በሰጡዋቸው ቃለ መጠይቆች መስክረዋል። ባሕላዊው ትምህርት ሳይንኳሰስ ከዘመናዊው ሥልጠና ሳይፋለስ ስኬታማ የመሆን ምሥጢር ከእማኝነታቸው ብዙ መማር ይቻላል።
ዛሬ ‘አደጉ’ በሚባሉት አውሮፓ እና አሜሪካ አህጉራት አድባራትና ገዳማት የሥነ መለኮት አስተምህሮ ማዕከላት ብቻ ሳይሆኑ የዕውቀት ዓይነተኛ መፍለቂያ በመሆን ወደ ዘመናዊ ሥመ ጥር ትምህርት ተቋም ራሳቸውን ለመቀየር ቻሉ። በእኛም አገር አክሱም፣ ዋሸራ፣ ዋድላ፣ ላስታ፣ በጌምድር፣ ሸዋ ወዘተርፈ ታላላቅ ገዳማት ባላቸው ሊቃውንት ብዛት ስብስብና እምቅ ዕውቀት መሠረታቸውን ሳይለቁ የጥናትና ምርምር ማዕከላት ሆነው ማጠናከር ይበጃል። የሥልጣኔ ጀማሪዎች ሆነን ወደኋላ እንደ ጭራ መቅረት ሊያስቆጨን ይገባል። ትውፊት (tradition) ከዘመናዊው ትምህርት ጥበብ (rationalism) ጋር ሳይጣረስ እንዴት ጠብቆ ማቆየት ይቻላል? የሚለው ጉዳይ ተገቢውን ምላሽ እስከዛሬም ቢሆን የተሰጠ አይመስልም።
በአገራችን ዘመናዊ ትምህርት እንዲስፋፋ በአዋጅ የወጣው በ1898 በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነበር። አዋጁም እንዲህ ይላል፡- “እስከ አሁን ማንም የእጅ ሥራ አዋቂ የነበረ ሰው በውርደት ሥም ይጠራ ነበር። ስለዚህም ማንም ሰው ለመማርና ለመሠልጠን የሚደክም አልነበረም።…ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ለወደፊትም ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ሁሉ ከስድስት ዓመታቸው በኋላ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይሁን።” የዐፄ ምኒልክ አዋጅ አንድምታው ግልጽና የማያሻማ ነው። ከዚያ ዘመን አልፎ እስከ አሁን ድረስ ለተማረ ሰውና ለትምህርት የሚሰጠው ግምት አናሳ እየሆነ ሙያ ትልቅ ትንሽ የሚናቅበት አጋጣሚ ሰፊ ስለነበር ነው። ዳሩ ግን መማር ብቻም ሳይሆን አዳዲስ ነገሮች ለመሥራትና የአስተሳሰብ ለውጥ ቶሎ ለማምጣት ቀላል አልነበረም። በአንፃሩ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል ሊባል ይችላል።
ኃይለ ገብርኤል ዳኜ “Education and Society: the Case of Ethiopia” በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ የአንድ አገር ትምህርትና ማኅበረሰብ ቁርኝት ምን እንደሚመስል የጠቆመ ሲሆን በኢትዮጵያም ይኸው ቁርኝት የማኅበረሰብና አካባቢ ጠባይ ይዘት መጠንሰሻ መሆን እንዳለበት ያብራራል።
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጥንታዊ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሁኔታን ስንቃኝ ተቋማቱን ማጠናከር አገራዊ ችግር መፍቻ አቅም ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፤ ግብረ ገባዊ አስተዋፅዖዋቸው የማይናቅ ነውና። ቁጥራቸው እየተመናመነ የሔደውን የቀለም ቀንድ ሊቃውንት መታደግ ማለት የቆሎ ተማሪ በየደብሩ የነጠረ ዕውቀት ይቀስማል ብቻ ሳይሆን የአገር ዕድገት ኅልውናን መታደግም ጭምር ነው። የአብነት ትምህርት የሥነ ጥበብ አገራዊ ጥበብና ዕውቀት እንዲዳብርም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
መምህር ኪዳነ ማርም ጌታሁን “ጥንታዊ የቆሎ ተማሪ” በተሰኘ መጽሐፍ የቆሎ ተማሪን ሲገልፁት ‘ዘአልቦ ጥሪት’ ርስት የሌለው ይሉታል። ዳሩ ግን ብል የማይበላው የነጠረ የቅኔ ዕውቀት ባለቤት መሆኑ እሙን ነው። እንዲያው ለነገሩ የቆሎ ተማሪ ሕይወት ከዘመድ አዝማድ ቀዬ ርቆ በየመንደሩ ዞሮ ቁራሽ ኮቸሮ እንጀራ ለምኖ ከየኔታው ተቆራኝቶ ይገኛል። ‘የቆሎ ተማሪ ፈሪ ነው’ የሚል ብሒል ደግሞ አለ። ቅኔውን እንደ ማር ጠጅ ሲያንቆረቁረው ሌላ ነው። ተረቱም እንዲህ ነው፣
‘የተማሪ ነገር ይቅር ምን አባቱ፤
ዱላ ሲያነሱበት ይላል ባዛኝቱ’
ገዳማትና ገዳማውያን በተሰኘ አንድ ጽሑፍ ላይ ለግእዝ ፊደላት መልክና ቅርፅን በመስጠት የሥነ ጽሕፈት ዕውቀት እንዲስፋፋ ያደረጉት የቤተ ክሕነት ሊቃውንት መሆናቸው የታወቀ ነው ሲል ያትታል። የአገራችን ሥልጣኔ ከዚሁ ትምህርትና ስርዓት መሠረቱን የጣለ ነው። ኢትዮጵያዊው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታላቅ ሥራ አበርክቶ ሲታወስ ይኖራል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕይወት ተፈራ “Mine To win” በሚል በእንግሊዝኛ ያበረከተችው በአቀራረቡ ልቦለድ ቀመስ መጽሐፍ “ኀሠሣ” ተብሎ በሞክሼዋ ሕይወት ታደሰ ግሩም ሆኖ ተተርጉሞ ለአንባቢ ቀርቧል። ትኩረት የተነፈገው የአብነት ትምህርት ቤት የቆሎ ተማሪ መፃዒ ዕድሎች ጉዳይ ላይ በልቦለዳዊ አተራረክ የማይሰለች አቀራረብ ተጽፏል። ስለ ጥንታዊ የአብነት ትምህርት ቤቶች የቅኔ ተማሪ፣ ሊቃውንተ ጉባዔ ትምህርት ቤቶች የዘመናት ውጣ ውረድ፣ የትውልዱ አረዳድ፣ ትውፊቱን የመጠበቅ ኃላፊነት ከምዕራቡ ዓለም አስቀድሞ የአገራችን ጥንታዊ ትምህርት፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሕፈት፣ አገረ ሰብ ዕውቀት፣ ግብረ ገብ ማስተማሪያ ምንጭ ሆና ቤተክርስቲያን ዘልቃለች። ይህንኑ መሻት፣ ማፈላለግ ላይ ኀሠሣ ያውጠነጥናል ብሎም ብዙዎች በትዝታ ምናብ ያነጉዳል።
ቤተክሕነት በአብነት ትምህርት ቤቶቿ አማካኝነት ትውልድን በማስተማርና በመቅረፅ በርካታ ሊቃውንትን፣ ምሁራንን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከማብቃት ባሻገር ለቤተ መንግሥቱ አዘማኝ ፋና ወጊ የሆኑ ሀገር አስተዳዳሪዎች መፍለቂያነቷም ትታወሳለች። ዘመናዊነት እየተስፋፋ በመጣበት ወቅትም ወጣቶች ለሀገር ፍቅር ስሜታቸው መቀዛቀዝ ተግዳሮት እንዳይሆን የበኩሏን እገዛ ኃላፊነት እየተወጣች ዘመናትን ትሻገራለች። ስንፍናን አጥብቃ የምታወግዘው ቤተክርስቲያን የሥራ ባሕል እንዲዳብር በገዳማውያን አበው ወ እመው ለመላው ዓለም አስመስክራለች። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሰምና ወርቅ ከቋጠሩት ስንኝ ይህንን ሐሳብ ያጠናክርልናል፦
“ሁሉን ተሸክማ የምትኖረው ዓለም፤
ከሰነፍ ሰው በቀር የሚከብዳት የለም።”
መልዕክቱ ያላንዳች ማብራሪያ በልቦና ይሰርፃል።
ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር ባሳተሙት “ባሕልና ክርስቲያናዊ ትውፊት በኢትዮጵያ” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ሲገልጹ የሥልጣኔ ምንጩ ትምህርት ነውና የአብነት ትምህርት ቤቶች ነባሩን ባሕልና ወግ ጠብቀው እንዲሻገሩ ከዘመናዊው ትምህርት ጎን ለጎን ትኩረት ተሰጥቶ ሊቀጥል ይገባል ይላሉ። የአብነት ትምህርት የራሱ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ንባብ ቤት፣ ጸዋትወ ዜማ፣ የግዕዝ ቅኔ፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ፣ የሕግ ትምህርት፣ የቁጥር ትምህርት(አቡሻኽር) እዲሁም የጽሕፈትና ሥነ ስዕል-ቅርፅ ቅርፅ ትምህርትን በውስጡ ያካተተ ይዘት አለው። እነዚህ የጥንት ሥልጣኔ አሻራዎች ናቸውና ሊጠበቁ ይገባል። የአብነት ትምህርት ቤቶች ቀጣይ ተስፋና ተግዳሮቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደፊት ሰፊ ዳሰሳ ማካሔድ አስፈላጊ ይመስለኛል። በምዕራቡ ዓለም የማዘመን ተፅዕኖ ጫና ውስጥ የሚወድቀው ባሕላዊ ትምህርት ጨርሶ ተረስቶ እንዳይከስም መታደግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።
ስለ አብነት ተማሪ ቤትና የቆሎ ተማሪ ምንስ ተባለ ከተቋጠሩ በርካታ ስንኞች ጥቂቱን እነሆ በማለት እሰናበታለሁ።
“ይማርልኝ ብየ ዋሸራ ሰድጄ፤
ቀለም ገባው አሉ እሳት ሆነ ልጄ።”
“ተማሪ በሞተ በሰባት ዓመቱ፤
ተምሮ ይመጣል ትላለች እናቱ።”
“ይኸው ተሠራልህ ተማሪ ቤትህ፣
እሳትና ውኃ አቀረብኩልህ፤
በርታ ተመራመር አስብ በራስህ።” “
መጽሐፍ ዘርግቶ እንደማስተማር፤
እኔን ተከትሎ ይላል ብር ብር።”

ሙሉጌታ ገዛኸኝ የታሪክና ቅርስ ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው gezahegn.mulu@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here