‘‘ዴሞክራሲ ከጠመንጃ አፈሙዝ ልትወለድ ትችላለች?’

0
597

የትጥቅ ትግል አሸናፊዎች ሁሉንም የሚወስዱበት፣ ተሸናፊዎች ሁሉንም የሚያጡበት (አሸናፊ-ተሸናፊ ግንኙነት የሚመራው) ስርዓት ለመውለድ የሚመች መንገድ ነው። ዴሞክራሲ ደግሞ በተቃራኒው የብዙኃኑን ይሁንታ ያገኘው የሚመራበት እና የኅዳጣን መብቶች የሚከበሩበት (ብዙኃኑን የአሸናፊነት ስሜት፣ በቁጥር ያነሰውን ደግሞ ቢያንስ የመከበር ስሜት እንዲሰማው የማድረግ መርሕ ላይ የቆመ) ስርዓተ መንግሥት ነው። ከዴሞክራሲያዊ መርሖች ውስጥ አንዱ ማመቻመች (‘ኮምፕሮማይዝ’ ማድረግ) ነው። ሁለት የታጠቁ ኃይሎች ዴሞክራሲያዊ ድርድር ማድረግ አይችሉም፤ የሚችሉም ከሆነ የጦር ኃይላቸው የሚመጣጠን ካልሆነ በስተቀር በተመጣጠነ ደረጃ አይደለም። ለዚህም ነው ‘ዴሞክራሲ ከጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን፣ ከሕዝብ ድምፅ መስጫ ሳጥን ነው የምትገኘው’ የሚባለው።
በዓለማችን ብዙዎቹ ዴሞክራሲን በትጥቅ ትግል ለማምጣት የሞከሩ ቡድኖች አልተሳካለቸውም። ይህ የሚሆንበት ምክንያት በጠመንጃ አፈሙዝ የሚገኘው ሥልጣን በሕዝባዊ ይሁንታ የተገኘ ስለማይሆን እና የዴሞክራሲ እስትንፋስ የሆነው ሕዝባዊ ተሳትፎ በጠመንጃ ፊት ነጻ ስለማይሆን ነው።
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ኖሮ አያውቅም፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት እያየነው ያለነው ሽግግር ወይም ለውጥ በሕዝባዊ አመፅ ግፊት የመጣ ቢሆንም በሕዝባዊ ምርጫ የመጣ ስላልሆነ ዴሞክራሲያዊ ነው ማለት አይቻልም። ይሁንና ለውጡ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችል መድረክ እየፈጠረ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን መድረክ ለማምጣት እንዲችል ግን አሁን የገጠሙት ፈተናዎችን መሻገር አለበት፤ ከነዚህ ተግዳሮቶች ዋነኛው በድርጅት ሠራዊትነት (በተለይም የኦነግ ሠራዊት መኖር) የታጠቁ አካላት መኖር ጉዳይ ዋነኛው ነው።
በዴሞክራሲ ውስጥ ገለልተኛ የሆነ አንድ ሠራዊት ብቻ ይኖራል። ነገር ግን ሠራዊቱ ለገዢም ይሁን ተቀናቃኝ ቡድኖች መወገን የለበትም። ይህ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ዜጎች በነጻነት፣ በድምፃቸው ይወስናሉ ማለት አይቻልም። በሒደቱ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ተካሒዶ ተሸናፊው ቡድን የራሱ ሠራዊት ያለው ከሆነ፥ ሽንፈቱን ይቀበላል ብሎ ማሰብ ይቸግራል። ሠራዊት ያላቸው ቡድኖች ፖለቲካዊ ድርድር የሚያደርጉት በመሣሪያ አቅማቸው እንጂ በሕዝቦች ድምፅ እና ባላቸው ድጋፍ መሠረት አይደለም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ምርጫዎች ቢካሔዱ ሠራዊት የሚጠብቀው የሕዝቡን ደኅንነት ሳይሆን የድርጅታቸውን ጥቅም ስለሚሆን፥ ራሳቸው የግጭት መነሻ ይሆናሉ።
በአንድ ስርዓተ መንግሥት የኃይል የበላይነት (‘ሞኖፖሊ ኦፍ ቫዮለንስ’) ኃላፊነት በሚሰማው መንግሥት እጅ ብቻ መሆን እንዳለበት ይታመናል፤ ይህ ካልሆነ ግን ግጭት መቀስቀሱ አይቀሬ ነው። ዴሞክራሲ በሠላማዊ የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር እንጂ ሁሉንም ተቀናቃኝ ድርጅቶች በማስታጠቅ አይመጣም።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here