የጎሳ ፖለቲካ ሲተገበር ለዘመናት ተቀብሮ የነበረው ፈንጂ ፈነዳ

0
922

ጌታቸው ካሳ (ዶ/ር) የሥነ ሰብዕ (‹አንትሮፖሎጂ›) መምህርና ተማራማሪ ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሥነ ሰብዕ የሠሩ ሲሆን ጥናታቸውንም አርብቶ አደር በሆነው እና የዘር ሀረጉ ከሐውያ ሶማሌ እንደሚመዘዝ ከሚነገርለት ገሪ ማኅበረሰብ ላይ አካሒደዋል። ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ‹ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ› ከሚባል የትምህርት ተቋም በሥነ ሰብዕ አግኝተዋል። የሥራ ተመክሯቸውን በተመለከተ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ውስጥ ከጀማሪ ተመራማሪነት እስከ ምክትል ድሬክተርነት ሰርተዋል። እንዲሁም ላለፉት ዐሥር አመታት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናት ማዕከል መምህር፣ ተማራማሪ እና የሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር አስተባባሪ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ብዙ ምሁራን በማይደፍሩት በሶማሌ እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በሚገኙት በባሕልና ታሪክ ስለተሳሰሩት ገሪ እና ቦረና ጎሳዎች ታሪካዊ የግንኙነት ዳራ፣ ግጭቶች እና መሠረታዊ መንስኤዎች እንዲሁም በዘላቂነት ሠላምን ለማስፈን መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ከአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የተጎራባቾቹ ገሪና ቦረና ጎሳዎች ታሪካዊ አመጣጣቸው በትውፊቶቻቸው ያለው አረዳድ ምን ይመስላል?
እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች መንግሥታት ከመፈጠራቸው በፊት ለረጅም ዘመናት አብረው የኖሩ ናቸው። ቦረና ከደቡባዊ ሶማሊያ እና ሰሜን ኬኒያ ከፈለሱበት ጊዜ ጀምሮ ከገሪ ጋር ተገናኝተዋል። ገሪዎች ደግሞ በቦረና ሥር ይተዳደሩ ነበር። ገሪዎች አርብቶ አደር ነጋዴዎች (‹ኮመርሻል ፓስቾራሊስት›) ናቸው።
እንግሊዞች ለቅኝ ግዛት እስኪመጡ ድረስ ቦረና፣ አጁራን፣ ገብራ፣ ገሪ እና ሌሎች እዛው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የሶማሌ ጎሳዎች አንድ ላይ በኅብረት (‹አሊያንስ›) ይኖሩ ነበር። ከሌሎች ቡድኖች ራሳቸውን ለመከላከል ሕግ አውጥተው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ይኖሩ ነበር።
የሁለቱ ጎሳዎች መሠረታዊ ልዩነቶቻቸው ምንድን ናቸው?
ገሪ የበለጠ የዘር ሐረጋቸው ከሶማሌ የሚመዘዝ ሲሆን ለእኔ የሚመስለኝ ግን የኦሮሞም የሶማሌም ቅልቅል ይመስሉኛል።
በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ምን ያሳያሉ?
ፖለቲካው እየተካረረ ሲመጣና እንግሊዝ ገሪዎችን ‹‹እናንተ ማን ናችሁ?›› ብሎ ሲጠይቅ ያኔ ነው ሱማሌ ነን ማለት የጀመሩት፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ የዘር ሀረጋቸውን ከአረብ ጋር ያያይዙታል። ይህ እንግዲህ የሚሆነው የጎሳ መሬቶች መፍጠር ሲጀምሩ ማለት ነው። በአብዛኛው ቦረናዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሱቅ ያሏቸው ገሪዎች ናቸው።
ቦረና ደግሞ የራሳቸውን ባሕል ይዘው፣ ገዳ ስርዓት ጠብቀው ባሕላዊ ሃይማኖት የሚከተሉ ናቸው። አሁን ግን ሙስሊሞችም ክርስቲያኖችም አሉ። የኑሮ ዘያቸው ትኩረት ከብት ማርባት ላይ ብቻ ነው። ቦረናዎች ፈረስ ሲጠቀሙ ገሪዎች ደግሞ ግመል ይጠቀማሉ።
እንግሊዝ ኬኒያን በቅኝ ግዛት በያዘችበት ወቅት ኢትዮጵያም በምኒልክ ጊዜ ግዛቷን እያስፋፋች ነበር። በወቅቱ አካባቢውን በሠላም ያስተዳድር የነበረው ቦረና ነበር። እያንዳንዱ በቦረና ኅብረት ውስጥ የገባ ጎሳ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ልክ እንደፌደሬሽን ይጠበቃል፣ ይከለላል።
ቦረና በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ስለሆኑ የማስተዳደሩን ሥራ ሲሰሩ ገሪ ደግሞ በኢኮኖሚ ጠንካራ ስለሆኑ ግብርንና ለገዳ የሚከፈለውን ይከፍሉ ነበር። ሁለቱም የሚገለገሉበት የጋራ ባሕላዊ ሕግ ነበራቸው። ቦረናም ሆነ ገሪ ሲያጠፉ ፍትሕ የሚሰጥበት ስርዓት ነበር፤ ሁለቱም ተከባብረው ይኖሩ ነበር። ገሪዎችም ቦረናዎችም ራሳቸውን ቦረና ነን ይሉ የነበረ ሲሆን ገሪዎችን ገፍቶ ለሚጠይቃቸው ብቻ ገሪ ነኝ ይሉ ነበር።
ምንም እንኳን የቦረናዎች የበላይነት ቢታይም የቦረና እና የገሪ መሬቶች ይጠበቃሉ፣ ከብቶቻቸውንም ሣር ማስጋጥ ይችላሉ። ይሁንና ቦረናዎች መሬት በደረቀ ቁጥር ሣር ወዳለበት ደጋ ቦታዎች ይዟዟራሉ፤ ገሪዎቹ ደግሞ ቦረናዎቹ ለቀው በሔዱት በረሃማ ቦታን ለግመሎቻቸው ይጠቀሙበታል። በዚህ ዓይነት መንገድ ነው እየተገፋፉ የመጡት፣ ከዚህ በኋላ ነው ወደ ግጭቱም የተገባው።
መሠረታዊ የግጭት መነሻቸው ምንድን ነው ማለት ይቻላል?
የመሬትና የውሃ አካላት ዋናው መነሻ ሆነው የኢትዮጵያ እና የኬኒያ መንግሥታት እ.አ.አ 1907 የድንበር ውል ሲያስሩ ቦረና የነበረውን ሥልጣን ወይም የበላይነት እያጣ መጣ ምክንያቱም በኬኒያ በኩል ገዢው እንግሊዝ የነበረ ሲሆን በተቃራነው በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በመሆኑ ነው።
ከዚህ በኋላ ትንንሽ ግጭቶች እየበዙ በመምጣታቸው፣ ሱማሌም እንዲሁ እየተስፋፋ በመምጣቱ የእንግሊዝ ቅኝ ገዢ አስተዳደሩን በሠላም ለማስተዳደር በሚል መሬትን ከፋፍሎ መስጠት ጀመረ። በሶማሌ ክልል አካባቢ ያሉ ቦታዎችን ደግሞ ሽንሽኖ ለትንንሽ የሱማሌ ጎሳዎች ከፋፍሎ ሰጠ። በዚህም ምክንያት ገሪዎችም የራሳቸውን ድርሻ በኬኒያ በኩል አገኙ።
ቦረናዎችን ደግሞ በፊት ያስተዳድሩ የነበረውን ቦታ አስትተዋቸው አሁን ሞያሌ የሚባለው አካባቢ ድረስ አመጡት ትንሽ መሬትም ኬኒያ ውስጥ እንዲኖራቸው ተደረገ፤ ብዙ የግጦሽ መሬት ጥበት ግን አለባቸው።
በፊት ጊዜ እንደዚህ መለያየት አልነበረም። መሬት በጋራ እየተዳደረ ይጠቀሙ ስለነበር ከከብት መሰራረቅ ከሚነሱ ትንንሽ ግጭቶች በስተቀር እምብዛም ችግር አልነበረም።
ገሪዎች ምኒልክን ከተቀበሉት የሱማሌ ማኅበረሰቦች መካከል ሲሆኑ አዲስ አበባ ድረስ ተጋብዘው መጥተዋል።
ስለሆነም ገሪን ብንወስድ መጤ ሳይሆን ከመጀመሪያው ጀምሮ እዚሁ የነበረ ጎሳ ነው። የኢትዮጵያና ኬኒያ ድንበር ሲሰመርም ገሪዎች ኢትዮጵያ የያዘችው ቦታ ውስጥ እንዲካተት ያደረጉ ናቸው። ኢትዮጵያም ስትወረር ኢትዮጵያን በመከላከል የተሳተፉ ናቸው።
ግጭቶች እየበዙ ሲመጡ የሲዳማ ጠቅላይ ገዢ የነበሩት ራስ ደስታ ልክ እንግሊዝ አድርጎት እንደነበረው የጎሳ መሬት መስጠት ጀመሩ። የአሁኑ መሠረታዊ ግጭቱ መንስኤ የግጦሽ መሬትና ውሃ ነው።
በ1925 ራስ ደስታ የእንግሊዝን በጎን መምጣት ለማስቆምም ሆነ በጎሳዎቹ መካከል የነበሩትን ግጭቶች ለማስቀረት የቦረናንም የገሪንም ጎሳዎች ባላባቶች ሰብስበው ውሳኔ ሰጡ። የግጦሽ መሬትና ውሃ ተሰምሮ ተሰጥቷቸዋል። በውሳኔው መሠረት ከተሰጠው መሬት ወጥቶ ወደ ሌላኛው ጎሳ መሬት መሔድ ያስቀጣል፤ የጎሳ መሪዎቹንም በእስራት ያስቀጣ ነበር። ይህ ስምምነት የተደረገው በጎሳዎቹ መካከል ምክክር ተካሒዶ ነበር።
ይሁንና ከሕይወት ዘያቸው ባፈነገጠ መልኩ የመሬት ድልድሉ የጎሳዎቹን እንቅስቃሴ ገደበ፣ ገሪዎችም ንግድ እንደልብ ለማካሔድ አልቻሉም። በዚህ ምክንያት ግጭቶች መስፋፋት ጀመሩ። በጊዜ ሒደትም ግጭቶቹን መፍታት ያለመቻል ሁኔታዎች ተፈጠሩ።
በጣሊያን ወረራ ወቅትም ገሪዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን የተሰለፉ ቢሆንም ከሽንፈቱ በኋላ አቋማቸውን ለውጠው ለጣሊያን አድረዋል። ቦረናዎች ግን በወቅቱ በብዛት እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል። ኢትዮጵያ በጣሊያን ሥር በነበረችበት ቆይታ ወቅት የድንበር ውሎች ፈርሰዋል። ሁሉም በጣሊያን ቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ከጣሊያን መውጣት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ገሪን ጨምሮ ሌሎች የሱማሌ ጎሳዎችን ለጣሊያን አድረዋል በሚል መግፋት ጀመረ። በዚህም ምክንያት ቦረናዎች ታማኝ ናቸው በሚል ሥልጣን ተሰጣቸው፤ ገሪን ጨምሮ ሱማሌዎች ያሉበት አካባቢ ቦረናዎች አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በዚህ ምክንያት የግጭቱ ጉዳይ ፖለቲካዊ የሆነ መልክ ያዘ። በአጠቃላይ የሶማሌ ጎሳን ታማኝ አድርጎ ያለማየትና ቦረናዎችን ደግሞ በተቃራኒው ታማኝ ማድረግ ናቸው፣ ድንበር ጠባቂ ናቸው በሚል ብዙ አድሏዊ እገዛ ከመንግሥት እንዲያገኙ ተደርጓል። እዚህ ላይ መሰመር ያለበት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ድንበሩንም ሆነ አገሩን ከጠላት የሚጠብቀው ቦረና ነው የሚል አመለካከት ተፈጠረ። በመሆኑም የቦረና ጥያቄዎች በቶሎ መልስ ይሰጣቸዋል፣ ትንንሽ ሥልጣኖችን ለቦረናዎች መሥጠት ተጀመረ፣ ዘመቻ ሲኖርም ከወታደሮች ጋር አብረው የሚዘምቱት እነሱ ነበሩ። ይሁንና ገሪዎች ይህንን ለቦረና የተሰጠውን አድሏዊ ድጋፍ መቃወም ጀመሩ። እኛም ይህቺን አገር እኩል ጠብቀናል በማለት ለምንድን ነው መድሎ የሚደርስብን በሚል ገሪዎች መቃወም ጀመሩ።
በዚህም ወደ 1950ዎቹ ዓመታት ከታላቋ ሶማሊያ ጋር ለመቀላቀል የእንገነጠላለን ትግል ማድረጋቸውም ይታወሳል።
ከቀዳሚዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ የሦስቱ መንግሥታት የሁለቱን ጎሳዎች አያይዝን በተመለከተ ምን ማለት ይቻላል?
ራስ ደስታ በ1925 ያደረጉትን ጎሳዎቹ አብረው እንዲኖሩና ግጭትን ለመከላከል ዓይነት ስምምነት የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ የጎሳ መሪዎችና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምሮ ድንበር መካለል ተደርጓል።
ይሁንና የመንግሥት ጥሩ ያልሆነ አመለካከት ገሪን ለአገሩ ታማኝ አድርጎ ያለማየት ፤ ቦረናን ግን ታማኝና ድንበር ጠባቂ አድርጎ መመልከት በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ጦርነቶች ከሶማሊያ ጎን እንዲቆሙ አድርጓቸዋል።
እስከ 1969 ድረስ ገሪም እንደ ገሪ ፤ ቦረናም እንደቦረና ነበር የሚታዩት ከዛ በኋላ ነው ኦሮሞ እና ሶማሌ የሚለው ነገር የመጣው። ይሁንና እነዚህ ሁለት ጎሳዎች እርስ በርሳቸው ተዋልደዋል፤ ግጭት እንኳን ቢኖር በባሕላዊ መንገድ እየፈቱ ኖረዋል።
ደርግም ቢሆን ቦረናን በግልጽ ይደግፍ ነበር። ገሪዎችን እንደዜጋ ሳይሆን እንደሽፍታ በመቆጠራቸው ራሳቸውን ማስታጠቅ ጀመሩ።
ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ቦረና ባለፉት ሦስት መንግሥታት ሲደገፍ፣ ሲታጠቅና ድንበር ጠባቂ የሚል አመለካከት ተፈጥሯል። ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ግን ቦረና የቀድሞ አስተዳደሮች ደጋፊ ነው በሚልና ሌሎች ምክንያቶች ገሪን መደገፍ ጀመረ። በአጭሩ ተራው የገሪና የሱማሌ ሆነ። ከዚህም ጋር በተያያዘ የሱማሌና የኦሮሞ አካባቢ ተፈጠረ። ገሪ ወደ ሶማሌ ክልል እንዲካለል ሲደረግ ቦረና ደግሞ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተካሏል።
ትልቁ ችግር ፖለቲካዊ መሆኑ ነው። የጎሳ ፖለቲካ ሲተገበር ለዘመናት ተቀብሮ የነበረው ፈንጂ ፈነዳ፤ ግጭት ተቀሰቀሰ። ሁለቱም፡- ገሪም ሆነ ቦረና ይተዋወቃሉ፣ አብረው ኖረዋል፣ መጤ አይደሉም፣ ተዋልደዋል ነገር ግን ፖለቲካው ፍትሓዊ ስላልነበር ወይም የአስተዳደር ፍትሕ ስላልነበረ፣ የአገሪቱ አንድነትም የሚጠብቅና የማይጠብቁ በሚል መድሎ ስለነበረ ነው።
በ1997 ስለተካሔደው ሕዝበ ውሳኔስ ምን ይላሉ?
ሕዝበ ውሳኔው ሊበን ዞን የሚባለው ቦታ ላይ ነው የተካሔደው። ሕዝበ ውሳኔ እስኪሰጥበት ጊዜ ሁሉም በየፊናው የመሬት ቅርምት ማካሔድ ነበር የተያያዘው። በዚህም ግጭቱ ተፋፋመ፤ በዛው ልክ ቦረናን ማሳደድና መግፋትም ተደርጓል።
ሱማሌ ነን የሚሉት ቦታውን ከያዙት በኋለ ሕዝበ ውሳኔው ተካሔደ፤ ፍትሓዊ የሆነ ሕዝበ ውሳኔው ግን አልነበረም። ይህም የሆነበት ምክንያት እዛ አካባቢ ትርምስ እንዲፈጠር ስለሚፈለግ ነው። ከሱማሌና ኦሮሞ ምረጡ የሚል ግዴታ መኖሩ በራሱ ችግር ፈጣሪ ነበር።
አሁን ብዙ ሰው የተፈናቀለበት ቦታ ብትሔድ አንዱ ኦሮሞ ነኝ ሌላው ሱማሌ ነኝ ይልኻል። እነዚህ ማኅበረሰቦች ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋል። ይህ እንዲሆን የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት ለከፋፍለህ ግዛ ሥልጣን ማስጠበቂያ ሥልት ነው።
ለምንድን ነው የለውጥ ተስፋ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እየመጣ ባለበት ሁኔታ ግጭቱ እየተባባሰ፣ ማፈናቀሉ እየጨመረ የሔደው?
ግጭት ማባባሱ ላይ አሁንም የሕወሓት እጅ ያለበት ይመስለኛል። ከኮንትሮባንድ ንግዱ ጋርም ይያያዛል። ሌላው በገሪና ቦረና መካከል ያለው ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉት የፖለቲካ ልኂቃን ለፖለቲካ ትርፍ ትንንሽ ልዩነቶችን በማጦዝ እንዳይበርድ አድርገውታል። በአጭሩ አሁን ቦታው የሁለት መንግሥታት ጦርነት ሆኖ ቁጭ አለ።
በአካባቢውና በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?
አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዕርቀ ሰላም እንዲሁም የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽኖች በሚል የጀመሩት ነገር በጣም ጥሩ ይመስለኛል።
ዋናው ነገር የተጣሉ ሰዎችን ማስታረቅ እንጂ ያልተጣለውን ለምን ታስታርቃለህ? በቦረና እና በገሪ መካከል ብዙ እርቅ ተካሒዷል። እዛ እርቅ ላይ የነበሩት ሰዎች ግን የክልል መንግሥት ባለ ሥልጣናት ነበሩ። ይሄ ማለት ያልታመመን ሰው ወይም በሽተኛ ይዞ የመጣን ሰው እንደማከም ማለት ነው። እንዲህ የተደረጉ የእርቅ ሒደቶች ትክክለኛ አልነበሩም። የከተማ ልኂቃን ማስታረቁ ፍይዳ የለውም።
ግጭቱ ወይም ፀቡ በቦረናና ገሪ መካከል ሆኖ ሳለ የኦሮሚያ እና የሱማሌ ክልሎች ግጭት ተደርጎ መወሰድ ትክክል አይደለም። ትልቁም ክፍተት ያለው እዚህ ላይ ይመስለኛል።
የሽምግልና ስርዓቱ መበላሸት፣ በአካባቢው ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴዎች አለመኖር፣ የፌደራል መንግሥቱ በቶሎ ጣልቃ አለመግባቱ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።
በአጭሩ አሁን የተጀመረው ሥራ በትክክል ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ዘላቂ ሠላም ለሁለቱም፣ ለአገሪቱም ያመጣል ብዬ አስባለሁ።
ይህ እንዲሳካ በተጨባጭ ምን መደረግ አለበት?
እርቁ ውስጥ የሚካተቱትን በጥንቃቄ መምረጥ ያስፈልጋል። የሕዝቡ ትክክለኛ ተወካዮች፣ የሌሎች አካባቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ጉዳዩን በጥልቀት የሚያውቁ ምሁራን መካተት አለባቸው። በተጨማሪም ጉዳዩ የቀጣናው በመሆኑም ኬኒያና ሶማሊያ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) መካተት ይገባቸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here