የ2012 ኹነቶች እና ስንብት

0
994

2012 ዓመት አዲስ የነበረበትን ሰሞን በ365 ቀናት ተሻግረን 2013 ላይ ተገኝተናል። ‹የማያልፍ የለም!› እንዲሉ 2012 እጅግ አሳዛኝና አስከፊ፣ አስጊና አስጨናቂ ሁነቶች በተወሰኑ የተስፋ ፍንጣቂዎች ውስጥ ሆነው አልፈውበታል። በፖለቲካው፣ በማኅበራዊ ሕይወት፣ በምጣኔ ሀብትና በዓለም ዐቀፍ ግንኙነቶች ኢትዮጵያ ብዙ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ተንከባለው ዓመት የተሸገሩና ለ2013 በተስፋና በስጋት የተላለፉ ጉዳዮችም ብዙ ናቸው።
አዲስ ማለዳ እነዚህን ኹነትና ክስተቶች ገጿ በፈቀደመ መጠን ሙያዊ ስርዓቶችን ተከትላ ስትዘግብ፣ ስትከትብ ቆይታለች። የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታም እነዚህን የ2012 አይረሴና ወሳኝ ኹነቶች በመንቀስ፣ ከቀደሙ ዘገባዎች በማጣቀስና ቅርብ የሚመስለውን ግን ያለፈውን የ2012 የተለያዩ ክስተቶች ለይቶ በምልሰት በማስቃኘት ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉይ አድርጎታል።

ዓመታት ሲቀያየሩ እና ዘመን በአዲስ ዘመን ሲተካ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ርዕይ፣ አዲስ ትሩፋት ይዞ ይመጣል በሚል በአሮጌው ዓመት ላይ ያልተሳኩ እና የተከሰቱ ተግዳሮቶች በአዲሱ ዓመት መልካም ይሆናል በሚል የተስፋ ስንቅን አገር ትሰንቃለች። ለዚህም ደግሞ ሕዝብና መሪ የመጪውን ተስፋ አሻግሮ ከመመልከትም ሆነ ምንም አይነት ብርሃን በማይታይበት እና በጭላንጭል የኩራዝ ብርሃን ወጋገናማውን ቀን በመናፈቅ፣ አነሳሽ መሪ ቃልን ይጠቀማሉ። እንደ አገርም ይህ ጉዳይ የብዙኀኑን ልብ የሕዝብን ሞራል ከፍ እንዲያደርግም ይታመናል።

ከእነዚህም መካከል ከ2008 ወደ 2009 በመሸጋገር ላይ የነበረችውን ኢትዮጵያን እናስታውሳለን። ‹‹የከፍታ ዘመን፤ የብርሐን ሕይወት›› እያልን በዋና ዋና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለ ከፍታ እና ስለ ብርሃናማው ሕይወት ስንዘምር ነበር። በዛም መረዳት ውስጥ ሆነን ነው 2008 የጎመን ድስት ውጣ ብለን 2009 የገንፎ ድስት ግባ ያልነው።

ይሁን እንጂ ብርሃን በዘፈን፣ ከፍታም በዳንኪራ አይመጣም ኖሮ 2009 ከድጡ ወደ ማጡ የተሔደበት ሆነ። ኢትዮጵያም በ2008 የተሳቀቀችበትን ዘመን በ2009 ተደግሞ በኹለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ዓመቱን አጠናቀቀች። በርካቶች ሕይወታቸውን በግፍ አጥተው እና ወደ ማጎሪያ ተግዘው እንዲሁም አንዳንዶች አገር ጥለው የተሰደዱበት ዓመት ነበር።

ከፍ እና ዝቅ ሲል የነበረው ይኸው የኢትዮጵያ የየወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ታዲያ ወርሃ መጋቢት 2010 ላይ ስር ነቀል የተባለ ለውጥ በማምጣት እነሆ የለውጥ አመራር የሚል ስያሜን ያነገቡ አመራሮች ወደ ፊት መጡ። እነርሱም ጥቂት ዓመታትን ለፈጀው የኢትዮጵያ ውጥንቅጥ መፍትሔ የምናበጀው እኛው ነን የሚል ተልዕኮን ያነገቡ ነበሩ።

ኹለት ዓመታትን ከመንፈቅ በአፍታ ፉት ያለው ይኸው የለውጥ አመራር ታዲያ በርካታ አዳዲስ ኹነቶችን እያስመዘገበ ቀጠለ። አዲስ ማለዳም እነዚህን ኹነቶች ከታሪክ ምዝገባው ባሻገር ከስር ከስር በመዘገብ ለአንባቢዎቿ ትኩስ መረጃዎችን እና ጥልቅ ትንታኔዎቿን ስታደርስ መቆየቷ የሚታወስ ነው።
በ2013 ዋዜማ ላይ ሆነን ተሰናባቹን ዓመት 2012ን ምን ምን አበይት ጉዳዮች ተካሔዱበት? ምንስ ዋነኛ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ላይ ተከናወኑ የሚሉ ጉዳዮችን በማንሳት እንዳስሳለን።

ብልጽግና ፓርቲ እውን ሆነ
የአራት እህት ፓርቲዎች ግንባር እና የአጋር ድርጅቶች ስብስብ የነበረው የ27 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው ግንባሩ ኢሕአዴግ ወደ ፓርቲነት ሳያድግ ከስሞ ወደ ብልጽግና ፓርቲ የተለወጠበት ጊዜ ያሳለፍነው ዓመት በ2012 ነበር። እጅግ ለበዛው የትችት ያውም ደግሞ በራሱ ከፍተኛ የፓርቲ ሥራ ኃላፊዎች ዘንድ ‹‹ኢሕአዲግ ከአናቱ ነው የተበላሸው›› ሲባልለት ነበር። እንዲሁም ስር ነቀል ያልሆነ፣ ያለውን ችግር በጥልቀት ለውይይት ከማቅረብ ይልቅ ‹እንዴት ተብሎ ይነካል!› በሚል ያረጀ ያፈጀ አካሔድ አንድ ጊዜ በጥልቅ ታድሰናል ሌላ ጊዜ ደግሞ በወጣት ተተኪ ትውልድ ተተካክተናል በሚል የዕለት ዕለት መፍትሔ መስጠት መካከል፣ እንቅስቃሴው አመርቅዞ ነበር ለውጡን የወለደው።

የሆነው ሆኖ ከአራቱ መሥራች ድርጅቶች ውስጥ ትግራይን ክልል በዋናነት እያስተዳደረ የሚገኘው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አሻፈረኝ ብሎ ሲቀር ቀሪዎች ሦስቱ ድርጅቶች እና አጋር ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ነበረው ተገድበውበት የነበረው ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ተነስቶ ሙሉ አባል የሆኑበት አጋጣሚ በተሰናባቹ 2012 ከተከናወኑ ጉዳዮች አንዱ ነው።

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ፍልስፍና ሲመራ የቆየው ኢሕአዴግ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የሶማሌና የሐረሪ ክልል ገዢ ፓርቲዎችን በማቀፍ አንድ ወጥ ፓርቲ ሆነው ለመውጣት የፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብና ለኢትዮጵያ ብልጽግናን ያመጣሉ ተብለው ተስፋ የሚጣልባቸውን የፓርቲውን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በወጣት ምሁራን በማስረቀቅ ሒደት ላይ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች በወቅቱ አረጋግጠው ነበር።

ከመስከረም 8/2012 ጀምሮ ለአምስት ቀናት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩበት ዓመት 2012 ሲሆን፣ በጉባዔው አብዮታዊ ዴሞክራሲን በመተካት የአዲሱ ፓርቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ይሆናል በተባለው የመደመር የፖለቲካ ቀመር ላይ ውይይት ተደርጎበት እንደነበርም አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ የቻለችው ጉዳይ ነበር። የመደመር ፍልስፍና ላይ በባህር ዳር፣ በአዳማ እና ሐዋሳ ከተሞች ላይ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ወጣቶችንና ምሁራንን ያሳተፈ ዝግ ስብሳባ ተደርጎበትም አልፏል።

ተዋህዶ ወጥ ፓርቲ ስለመሆን ማውራት ከጀመረ ከ17 ዓመት በላይ የሆነው ኢሕአዴግ በ1994 የቀድው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባደረጉት ስብስባ ላይ በተሳታፊዎች ተጠይቀው ጉዳዩን አንስተውት እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ ሐሳቡን አንድ ዕርምጃ እንኳን ወደፊት ሳይንቀሳቀስ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ በተደጋጋሚ ጉዳይን ከመገናኛ ብዙኀንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተውበታል።

ውሕደቱ መቼ ይፈጸም የሚለው ጉዳይ ላይ ካልሆነ በቀር ውሕደቱን የሚቃወም የኢሕአዴግ አባል ድርጅት የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውም ይታወሳል። ይሁን እንጂ በምስረታ ላይ ባለው ወጥ ፓርቲ የሕወሓት ተሳትፎ አጠያያቂ ሆኖ ነበር። በኋላም ላይ በይፋ ፍቺ መፈጸሙ እና ‹አሻፈረኝ! ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሞት ብቻ ነው› የሚለየኝ የሚል አቋሙን ይፋ ያደረገው ሕወሓት የራሱን ርዕዮት ዓለም በመከተል 2012 ተደምድሟል።

የ2012 አዲስ ዓመትን መባቻ ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ የጨዋታ እንግዳ ሆነው በቀረቡበት ወቅትም ‹‹ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚወስድ አንድ ፓርቲ ይመሠረታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ሲሉ ተናገሩ። አስከትለውም በጉዳዩ ላይ ዘርፈ ብዙ ውይይቶች እንደሚደረጉ መናግራቸው ይታወሳል።

‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሕደቱን እንዴት ማከናወን ይቻላል የሚለው ላይ እየተወያየን ነው›› በማለት ያከሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹‹ዴሞክራሲን በውስጥ [በኢሕአዴግ ውስጥ] ካልተገበርነው በውጪ ልንፈጽመው ስለማንችል ብዙ ውይይት እናደርግበታልን። ስለዚህ ውይይታችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቋጭተን በቅርቡ አንድ ዜና ይዘን እንመጣለን ብለን እናስባለን።›› ሲሉም የተናገሩት በተሰናባቹ 2012 መባቻ ላይ ነው። እና ይህንንም በዓመቱ መገባደጃ ላይ ዞር ብለን ስንመለከተው እውነትም ተግባራዊ መደረጉ እና ብልጽግናም ዕውን መሆኑን እንታዘባለን።

ወርሃ ጥቅምት 2012 ኢትዮጵያን ያመሰ እና ዜጎችን ልብ በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት የተከናወነበት እና ከባድ የሀዘን አሻራ ጥሎ ያለፈ ወቅት ነበር።
ከጥቅምት 11/2012 ጀምሮ ለቀናት የዘለቀው የተሰናባቹ ዓመት የአስከፊው አሻራ ክስተት ከፊል የአዲስ አበባን አካባቢዎች በጥቂቱ የዳሰሰው እና በአብዛኛው የኦሮሚያ ከተሞች የተከሰተው ነው። መንግሥት ባመነውና ባስታወቅው መሰረት የ86 ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት የቀጠፈው ችግር የመንግሥት ቸልተኝነት የሚታይበት አጋጣሚ እንደሆነ በርካቶች የተስማሙበት ጉዳይም ነበር።

በተለይ ደግሞ በአዳማ ከተማ በውል የሚታወቁ 16 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ግጭት በስፍራው ለነበረው የጸጥታ መዋቅር ከአቅሙ በታች እንጂ በላይ እንዳልነበር ሥሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ የአዳማ ከተማ ነዋሪ አዲስ ማለዳ በስፍራው ተገኝታ ላቀረበችለት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ የሚታወስም ነው። ስለ ሁኔታው ሲናገር ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት የከተማው ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ኃይሎች ዳር ሆነው ይመለከቱ እንደነበር በዐይኑ የተመለከተውን ተናግሯል። ‹‹መንግሥት ብጥብጡን ይፈልገዋል እንዴ? የሚል ሐሳብም በብዙ ሰዎች ሲታሰብ ነበር›› ሲል የተገለጸው የ2012 መጥፎ ትዝታ ነው።

አዲስ ማለዳ በዚሁ ወቅትም ‹‹የጸጥታ ስጋት ፍልቅልቅነቷን የነጠቃት ድሬዳዋ›› በሚል ርዕስ ስር ወደ ምሥራቃዊ ፈርጧ የጨዋታ አዋቂዎች አገር ድሬዳዋ ባቀናችበት የ2012 ወርሃ ጥቅምት እጅግ በደበዘዘ እና በቆዘመ አቋም የተቀበለቻት እና ልጆቿን በእድ አዳር፣ በሜንጫ ያጣችበት 2012 ክፉ ዓመት እንደሆነባትም አስነብባ ነበር።

በተለይ ደግሞ አዲስ ማለዳ በድሬደዋ በተገኘችበት ቀን ሦስት ቀናትን አስቀድሞ ብሔር እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን አስተናግዳ በትንሹም ቢሆን የአለመረጋጋት ዓውድማ ሆና ሰንብታ ነበር። ለዚህም ይመስላል የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ኃይል፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የከተማዋ የፖሊስ ኃይል በንቃትና በተጠንቀቅ የነዋሪውን እንቅስቃሴ የሚቃኙት።

በአዲስ አበባ የተወሰኑ አካባቢዎች እና አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ አዋሳኝ ከተሞች ተነስቶ የነበረው ግርግር ታዲያ ብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ትኩሳቱ ደርሶ ኖሮ ጨዋታዋን ነጥቆ ለጭምትነት ትቷት የሄደው ግጭት በድሬዳዋ ተከስቶ እንደነበር የ2012 የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ወራት ጊዜ መቁጠሪያ ምስክር ነው።
ድሬዳዋን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ዳፋውን የጣለው ይኸው ጉዳይ ታዲያ የ2012 መጥፎው ትዝታ እንደሆነ የብዙዎች አስተያየት ለመሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። አያልፍም ወይ?፣ አይነጋም ወይ እና የመሳሰሉት ጥያቄዎችን ያስተናገደው 2012 ላይመለስ ተሰናብቷል። ተፈጥሮ ዑደቷን አታቆምም ጊዜም ባለበት አይቆምም፤ ትሩፋትም ሆነ ዳፋ ያለበት ዓመትም እንደዛው እንደሆነ አይቀጥልም። እናም 2013 ሊገባ ግድ ሆነ። እኛም 2012ን ተሰነባብተነዋል።

ኮቪድ 19
ዓለም በአንድ ሰንደቅ እንድትታወቅ አድርጓታል ይሉታል፣ ‹‹ማስክ›› የፊት ጭንብልን ማለታቸው ነው፤ ስለ ዓለም ዐቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 ሲገልፁ። ያሳለፍነው 2012 ታዲያ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከቻይናዋ ዉሃን ግዛት የተነሳው ወረርሽኝ እልፎችን ለአፈር ሲያበቃቸው ቀሪዎችንም ከሞት ሽረት ትግል በኋላ እንዲያገግሙ ያደረገበት ዓመት ነበር 2012።

ዓለም ዐቀፉ ወረርሽኝ ኮሮና ኮቪድ 19 በተለያዩ የዓለም አገራት በተለይም ደግሞ በምጣኔ ሀብት ደርጅተዋል በተባሉ አገራት ላይ ቁጣ ሽመሉን አጠንክሮ የሰነዘረበት እና በእኛዋ የድሃ ድሃ አገራትን ከፊት በምትመራው ኢትዮጵያችንም ይህ ሽመል አከርካሪዋን ለመስበር የዳዳው ነበር፤ ባሳለፍነው ዓመት። ይህንንም ተከትሎ ችግሩ በስፋት የተከሰተባቸው የዓለም አገራት በርካታ እንቅስቃሴዎቻቸውን እና የዕለት ተዕለት ክንውኖቻቸውን እንዲገቱ ተገደዋል።

በተለይ ደግሞ ታላላቅ አየር መንገዶች ከወረርሽኙ ጅማሬ ጀምሮ ወደ ቻይና የነበራቸውን በረራ በማቆም ቢጀምሩም ቀስ በቀስ ግን የበረራቸውን ዕገዳ ወደ ሌሎች ዓለም አገራት መዳረሻዎችም አዙረው በባተሌነት ይታወቁ የነበሩ ዓለም ዐቀፍ ታላላቅ አየር መንገዶች በዝምታ ውለው ሲያዛጉ ማደር የታየባቸው ታሪካዊው ዓመት ነበር፤ 2012። ለዚህ ደግሞ በርካታ አገራት ውስጥ ወረርሽኙ በመዛመቱ መሆኑ ግልጽ ምክንያት እንደሆነ ይፋ ሆኗል።

ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ አገራት የየራሳቸውን እና ያዋጣናል ያሉትን የመከላከያ እርምጃዎችን ሲወስዱ ተስተውሏል። በዚህም ከማኅበራዊ ፈቀቅታ እና ከንጽህና አጠባበቅ ባለፈ ለሳምንታት ምናልባትም ለወራት የሚዘልቅ፣ ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡና ቤታቸው እንዲቀመጡም አዝዘዋል። ያንንም ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህን ተከትሎ በበርካቶች ጉዳዩ በአፍሪካ በተለይም ደግሞ እምብዛም የማያወላዳ የጤና ስርኣት ያላትን አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ወረርሽኙ አንድ ጊዜ ካፈተለከ መመለሻው እንደሚቸግር እና የብዙዎችን ሕይወትም ሊቀጠፍ እንደሚችል ያስቀመጡበት እና የተነበዩበት ዓመት ነው። ይሁን እንጂ ከነጠላ አሃዝ ጀመረው የሟቾች ቁጥር በአማካኝ በቀን ከሦስተ አሃዝ ወደ አራት አሀዝ የተሻገረበት ዓመትም ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህንንም ምክንያት በማድረግ እንደ ሌሎች አገራት መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ መንቀሳቀስን ከእነ አካቴው በመከልከል ቤት ውስጥ እንዲቀመጥ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ይኖርበታል። እንዲሁም ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ መገታት ይኖርበታል በሚልም ምክረ ሐሳብ የተቀመጠ ቢሆንም ቅሉ፣ ተግባራዊነቱ ግን ከመንግሥት ቁርጠኝነት ውጪ በሰው ዘንድ እምብዛም ለመሆኑ የታዘብነው ጉዳይ ነበር።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ማንኛውንም አይነት ወደ ክልላቸው የሚደረጉትን የሰዎች እንቅስቃሴ እና የሕዝብ መጓጓዣዎችን በማገድ ለመንፈቅ የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ2013 ዋዜማ ላይ በይፋ ተነስቶ ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት እንዲመለስ ሆኗል። የኮቪድ ጉዳይ 2012ን አይሻገርም ችግሩ እያለ እንመነጠቃለን፣ ወደ ነበርንበት የእንቅስቃሴ ሁኔታ ተመልሰን የጀመርነውን ብልጽግና ጉዞ እናሳልጣለን የተባለ በሚመስል አኳኋን ነገሮች ቀድሞ መልካቸውን ይዘው እነሆ 2013 ገብተናል።

በተመሳሳይም በመዲናችን አዲስ አበባ የመንግሥት ሠራተኞች ቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ መንግሥት ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከግማሽ በመቶ በላይ ሠራተኞቻቸውን ቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዘው ከተተገበሩ ድንጋጌዎች ውስጥ በስፋት እና በሚገባ የተተገበረ ጉዳይ በሚመስል መልኩ አዲስ ማለዳ ለሥራ ጉዳይ በተንቀሳቀሰችባቸው የመንግሥት ተቋማት የተራቆቱ ሰው አልባ ቢሮዎችን መመልከት የተለመደ ነበር።

የሀጫሉ ግድያ
ክስተቱ 2012 መገባደጃ የክረምት ወራት በአንዱ ጎዶሎ ቀን የሆነ ነው። የኦሮሞ ድምጽ ሆኖ ሲታገል የኖረው ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሠኔ 23/2012 በምሽት መገደሉ የተሰማበት መሪር ዓመት። ከዚች ቅጽበት የጀመረው የኹከት እና ብጥብጥ እንቅስቃሴዎች በርካቶችን ለሕልፈት ያውም በአሰቃቂ ሁኔታ ገሚሶችን ደግሞ ዕድሜ ልካቸውን ያፈሩትን ንብረት በአንድ ሽራፊ ሰከንድ ዶግ አመድ ያደረገ ጉዳይ ነበር።

ከሻሸመኔ እስከ አሳሳ፣ ከዝዋይ እስከ ባሌ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ሕይወት እና ንብረት ጠፍቶ በሕይወት የተረፉት ደግሞ በቤተ ዕምነት ተጠልለው የክረምቱን ዶፍ እና ቁር ለመጋፈጥ የተገደዱበት፤ 2012።

በ30ዎቹ አጋማሽ ይህችን ዓለም የተሰናበታት የምዕራብ ሸዋው ፈርጥ ሀጫሉ በርካታ ውጣ ውረዶችን ከእስር እና ከሌሎች ተግዳሮቶች ጋር እየተጋለ ያሳለፈ ብርቱ ወጣት ነበር። እንኳን ኦሮምኛ ተናጋሪን፣ ያልሆነውን እንኳን በምትሀታዊ ድምጽ ቅላጼው እና በፍጹም የሙዚቃ ችሎታው የሚማርክ ድንቅ የጥበብ ሰው ባሳለፍነው ዓመት ላይመለስ ያሸለበበት ጊዜ ነበር።

ሰሚን ግራ ያጋባ፣ ታአማኒነትን ለማግኘት እጅግ ያከራከረ እና በኋላ ግን መራራውን እውነት ወዳጅ ዘመድ፣ አድናቂ እና የሙያ አጋሮቹ ሊቀበሉት ግድ ብሏቸዋል። ከአብሮ አደጎቹ እስከ ታላላቅ አገሪቱ ከፍተኛ ሥራ አመራሮች ድረስ በእምባ የሸኙት ሀጫሉ በተሰናበትነው ዓመት ነበር ይህችን ምድር የተሰናበታት።

ሩቅ ለማደር አስቦ ሲሠራ የኖረው እና ቅርብ ያደረው ሀጫሉ በዚች ምድር ላይ በኖረባቸው ጥቂት ዓመታት የማያልፍ ሥራዎችን በሕዝብ ዘንድ ቀርጾ ያለፈ ድንቅ ጥበብ ሰው ነበር። በጀግንነት እና በወኔ የተቃኙት የሀጫሉ ሙዚቃዎች ዛሬም ሆነ ነገ ከሀጫሉ ህልፈት በኋላም እየተደመጡ ተተኪውን ትውልድ ሲያንጹ እና ሙዚቃን እንዴት ለተገቢው ዓላማ ማዋል እና ሐሳብን ማስተላለፍ እንደሚቻል ብሎም ለውጥን ማምጫ መንገድም እንደሆነ ማሳያ መሆኑን ይማሩበታል።

ሠኔ 23/2012 ለልበ ሙሉው እና ለከያኒው ሀጫሉ እንደማንኛውም ቀን የሥራ እና ባተሌነት ቀን ነበር። ነገር ግን ጠዋት በቀኝ አውለኝ ላለው ሀጫሉ ማታ መሽቶ በተደጋጋሚ እንደሚገልጸው በትልቅ ናፍቆት ለሚጠብቁት ልጆቹ ሊበቃ ሳይችል ከመንገድ ቀርቷል። የፌዴራል ፖሊስ ስለ ድምጻዊው አሟሟት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ልዩ ሥሙ ገላን ኮንዶሚኒየም በተባለ ስፍራ ሀጫሉ የሚያሽከረክራትን ተሽከርካሪ አቁሞ ወርዶ ተመልሶ ወደ ተሸከርካሪዋ በገባበት ወቅት ገዳይ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች የተሽከርካሪውን በር በመክፈት በጥይት እንደመቱት አስታውቋል።

ሕይወቱን ለማትረፍም በተደረገው ርብርብ ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተወስዶ የነበረ ቢሆንም መጥፎ አጋጣሚ ሀጫሉን ከሚወደው ሙዚቃ፣ ከአድናቂዎቹ እና ከሚወዳት ኢትዮጵያ ነጥቃዋለች።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳም በሀጫሉ ሁንዴሳ ድንገተኛ ሞት ከገቡበት ድንጋጤ እና ብስጭት በወጉ ሳይወጡ ነበር ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫቸውን ያስተላለፉት። ‹‹በፊንፊኔ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጀግናው ወንድማችን፣ ደማችን፣ የትግል የለውጥ ምልክት የሆነው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በመሳሪያ መመታቱን ሰማሁ›› ሲሉ ጀምረው፤ ‹‹በሀጫሉ ሕልፈተ ሕይወት እንደ አንድ አብሮ አደግ እንደ ትግል ጓድ እና እንደ ጀግና የተሰማኝ ሀዘን ከፍተኛ ነው፤ ለእኔ ደግሞ ወንድሜ አማካሪዬ ነው፤ ይህን ጀግና ነው ያጣነው›› ሲሉም ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም ርዕሰ መስተዳደሩ በሀጫሉ ላይ የተፈጸመው ግድያ ታስቦበት የተፈጸመ ግድያ እንደሆነ እና እንደ ተራ ነገር የሚታለፍ እንዳልሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
ከዚሁ በተመሳሳይም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርብ የሚያውቁት እና የትግል አጋራቸው የሆነውን ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው እንደሰሙት ተናግረዋል። የሀጫሉን ታጋይነትንም በተመለከተ ‹‹የእኛ መታወቂያ አይኑረው እንጂ ወይም ዩኒፎርም አይልበስ እንጂ እንደኛው ታጋይ ነበር›› ሲሉም ተናግረዋል።

በሦስቱ ሠኔዎች የተካሔዱትን አገራዊ አስደንጋጭ ክስተቶችን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀዳሚ ኹለት ሠኔዎች የተደረጉትን ግድያዎች እና በሦስተኛው ሰኔ ማለትም በሀጫሉ ግድያ ዙሪያ ‹‹ምንም ጉዳዩ የማይመለከተውን›› ሲሉም ጠቅሰዋል።

የሀጫሉ መሞት ኢትዮጵያን በዋናነት ኦሮሚያ ክልልን የተለየ መልክ እንዲኖረው ያደረገ እና እዚህም እዛም የሚሰሙት ወሬዎች ልብን የሚያዝሉ እንጂ ሰላም የሚተነፈስባቸው አልነበሩም። ሻሸመኔ ከተማን ለአብነት በማንሳት እንኳን ሕንጻዎች እና የትምህርት ተቋማት እንዳልነበሩ ወደሙበት፣ ዕልፎች ይህን ሽሽት የቻሉት ወደ አጎራባች ክልል ሐዋሳ ከተማ ሲያቀኑ ያልቻሉት ደግሞ በዛው በቤተ እምነቶች ተጠልለው ችግሩን አሳልፈዋል። ይህ ጽሑፍ እስከተሰናዳበት ጊዜም ወደ ቤታቸው የተመለሱት ጥቂቶች ናቸው።

እስር
ከድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተከሰተውን ግርግር እና ኹከት ምክንያት ተደርጎ ለጠፋው የሰው ሕይወት እና ንብረት ተጠርጣሪ ናችሁ በሚል የፖለቲካ አመራሮችም በቁጥጥር ስር የዋሉበት ዓመት ነበር፤ 2012።

በኦሮሞ ወጣት ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው የሚባለው እና ከአክቲቪዝም ወደ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት የተዘዋወረው ጃዋር መሐመድ እና በቀድሞው ኢሕአዴግም ዘመን በእስር የነበረው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ላዕላይ አመራር በቀለ ገርባ በቁጥጥር ስር ውለዋል። በተመሳሳይም ይህን ጉዳይ በሚመለከት በአዲስ አበባም ኹከትን በማነሳሳት ፖሊስ ጠርጥሬዋለሁ ያለውን አዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ዋና ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ በቁጥጥር ስር የዋለበት የዓመቱ መገባደጃ ወራት ነበር።

በድምጻዊው ሕልፈት ማግስት እስር ቤትን የተዳበሉት እነዚሁ ጉምቱ የፖለቲካ ዋናዎች በደጋፊዎቻቸው በኩል የይፈቱልን እና መብታቸው ይከበር ጥያቄ በማኅበራዊ ሚዲያው በኩል ሲናፈስ የነበረበት ጊዜም ነበር። ይሁን እንጂ በውጫዊው እና ውስጣዊው ጫና ሳይበገር የሕግን የበላይነት ለማረጋገጥ እየሠራሁ ነው የሚለው መንግሥት፣ በያዝነው ዓመት 2013 የመጀመሪያ ቀናት ክስ ለመመስረት ቀን ቆርጧል። በ2012 የተጀመረው ጉዳይ እየተንከባለለ እነሆ ለአዲስ ዓመትም የክርክር እና የመካሰስ አየርን ሊያጥን እነሆ ብሏል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት ነበር ጉዳያቸውን ሲታዘብ የኖረው። እነሆ ታዲያ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ ዐስር ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ሕግ መስከረም 8 ቀን 2013 በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰርት ችሎቱ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ 2012 ሊገባደድ የቀናት ዕድሜ ላይ ነበር። እስከዚያ ድረስ ግለሰቦቹ ባሉበት ሁኔታ በፖሊስ ማረፊያ እንዲቆዩ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ አቃቤ ሕግ ሃምዛ አዳነ፣ ሸምሰዲን ጣሃ፣ መለሰ ድሪብሳ እና ቦና በተባሉ አራት ተጠርጣሪዎች ላይ በአምስት ቀናት ውስጥ ክስ ይመስርት ብሏል፤ ችሎቱ።
ችሎቱ በአራቱ ተጠርጣሪዎች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜው ሊያጥር የቻለው ዐቃቤ ሕግ በግለሰቦቹ ላይ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ስላላሰማ እና ክስ ለመመስረት የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በቂ ነው በማለቱ እንደሆነ ታውቋል።

ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በዐስር ተጠርጣሪዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ በጠየቀው መሰረት የቀዳሚ ምርመራ የምስክሮች ቃል የተሰማበት መዝገብ ለክስ ዝግጅት እንዲረዳው ከጳጉሜ 2 እስከ ጳጉሜ 5 ባሉ ጊዜያት የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሬጂስትራር ሠራተኞች ግልባጩን እንዲያደርሱ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ከተቃወመባቸው ምክንያቶች አንዱ ግለሰቦቹ ፈፀሙት የተባለው ወንጀል ሞት ያስከተለ በመሆኑ እና ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ15 ዓመት በላይ በሚሆን ጽኑ እስራት የሚያስቀጣቸው በመሆኑ ሕጉ የዋስትናን መብትን ይከለክላል የሚለው ነው።

የሹመኞች ስንብት
የበርካቶችን ልብ ሰልቦ እንዴት ነው ነገሩ ያስባለው ጉዳይ ባሳለፍነው ዓመት የሹመኞች ፈጣን የሆነ የሥራ መልቀቂያ ጉዳይ ነበር። ከጤና ሚኒስቴር እስከ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ብሎም እስከ ሥራ ፈጠራ ኮሚሽነር አድርጎ የፖሊስ ጥናት ስትራቴጂ ዋና ደይሬክተር ድረስ ድንገት ተነስተው ከዚህ በኋላ አንገናኝም አይነት መልቀቂያ ያስገቡበት ዓመት ነበር፤ ይኸው 2012።

ለአብነት ያነሳናቸው የሥራ ኃላፊዎች እነዚህ ሆኑ እንጂ በርካቶችም እንዲሁ ነጉደዋል። የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔዋ ኬሪያ ኢብራሒም ወደ መቐለ ለሥራ ምክንያት በሔዱበት ነበር መልቀቂያቸውን አስግበተው ከእንግዲህ ይበቃኛል የሚል ውሳኔ ላይ የደረሱት። የኬሪያ በግልጽ ወደ መገናኛ ብዙኀን በመምጣት ለመልቀቃቸው አለኝ ያሉትን ምክንያት ያስቀመጡ ቢሆንም፣ ቀሪዎች ግን ሾላ በድፍን በሆነ መንገድ ነበር የነጎዱት።

በኢትዮጵያ ባለፉት ኹለት ዓመታት የታዩትን የሽግሽግ የሥልጣን እርካብ የሹመኞች መቀያየር በአብዛኞች ዘንድ ትዝብትን የጣለ እና በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ተቀምጠው ነገር ግን ቀጣይነት በሌለው ሁኔታ የካቢኔው ሽግሽግም ሆነ ከአንዱ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላው መዘዋወር በውጤታማነት ላይ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ ለመሆኑ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ካለፉት ረጅም ኢሕአዲግ ጉዞ ላይ ታይተው የማይታወቁ ግን ደግሞ በቅርብ ለውጥ በሚል አካሔድ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ወደ አራት ኪሎ የገባው የዐቢይ መንግሥትን ተከትሎ ታዲያ በካቢኔው ውስጥ የተዋቀሩት መንግሥት ተቋማት በበርካታ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች እንዲመሩ መደረጋቸው የሚታወቅ ነው።

ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ መንበር ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙገሳን ከተቸሩበት አንዱ የሆነው ግማሽ እና ከዛ በላይ የሆነውን የካቢኔያቸውን በሚኒስትር ደረጃ ግን በግማሽ ሴቶችን ማድረጋቸው አንደኛው ጉዳይ ነበር።

በዚህም ጋር ተያይዞ ታዲያ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዐይታው የማታውቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዘዳንት ሴት መሆናቸው ደግሞ አድናቆትን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተናኘበት አንዱ እና ዋነኛው ጉዳይ ነው። ሴቶችን ከማብቃት ጋር ብቻም ሳይሆን ወደ ውሳኔ ሰጪነት በማምጣቱም ረገድ የማይናቅ አሰራሮች መከናወናቸውን በርካቶች በዓለም አደባባይ የመሰከሩት ጉዳይ ለመሆኑ መገናኛ ብዙኀን ምስክር ናቸው።

ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በመምራት እና ሕዝብን እንዲሁም የመንግሥትን ኃላፊነት በመሸከም በተመደቡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አልረጋ ባለ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ዝውውር እና መተካካትም የሚስተዋልበት እንደሆነ ለመታዘብ የሚከብድ አለመሆኑ ደግሞ የዶክተር ዐቢይን ካቢኔ በስፋት ከሚያስተቹበት ሁኔታዎች ውስጥ መሆኑ ይነገራል።

ዓባይ ‹‹ግድቡ የኔ ነው››
የትውልድ ቁጭት ፣ የአገር ኪሳራ ከዘፈን ግጥም ማሳመሪያ የዘለለ ፋይዳ ያልነበረው በዓለም በርዝመቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ዓባይ ከዘመናት ውዝግብ እና ከውሃ የፖለቲካ ውጥረት በኋላ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተገደበበት የኢትዮጵያ የድል ዓመትም ነበር 2012። ቀደምት ነገስታት እና ሹማምንት ይህ እንዲሆን ቢተልሙም የልጅ ልጆቻቸው ግን እንደሚጨርሱት እና ውጥናቸውን ከግብ እንደሚያደርሱት ያምኑ ነበር እና ይህም ዕምነታቸው ከ2012 በኋላ ስጋ ሳይለብስ ማለፍ አልቻለም። ከዋሽንግተን ዲሲ እስከ ካይሮ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ካርቱም ድረስ የአገርን አደራ እና የሕዝብን ኃላፊነት አንግበው በሚንቀሳቀሱ ተደራዳሪዎች ዕጅ አልሰጥም ባይነት የመጀመሪያው የውሃ ሙሊት እነሆ በ2012 የክረምት ወራት ነበር የተከናወነው።

አገር ከዳር ዳር በደስታ ኢትዮጵያዊነትን የዘመረበት፣ የነገን ብርሃን አይቶ የዛሬውን የፋኖስ ጭላንጭል በደስታ የኖረበት ‹‹ግድቡ የኔ ነው›› በሚል መርህ በአንድ ልብ የተመመበት ጊዜ ተሰናባቹ ዓመት ነበር። ምንም እንኳን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ የጣር ዓመት የነበረው 2012 ኢትዮጵያ ግን የዘመናት ህልሟን በልጆቿ የተባበረ ክንድ የመጀመሪያውን ድል የተቀናጀችበትም ዓመትም ነበር።

ከሰከላ እስከ ሜዲትራኒያን ያለከልካይ ከዘፍጥረት ጀምሮ ሲነጉድ የነበረው ባዕዳን ቀላቢው ዓባይ፤ በአገሩ እና በቀየው ሊተጋ አይኑን የመለሰበት ታሪካዊ ጊዜ ነው። ከእንግዲህ ወገን በኃይል ዕጦት በጭስ ታፍኖ ላይሞት፣ እናቶች በማገዶ እንጨት ለቀማ ትከሻቸው ላይጎብጥ የናፈቁትን የቅንጦት የሚመስል ግን መሰረታዊ ፍላጎታቸው በኃይል አቅርቦት ሊሟላ ዓባይ የመጀመሪያ ጉዞውን በአገሩ ባሳለፍነው ዓመት ጀምሯል።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here