የ97ቱ “ቅንጅት“ እና “አዲሱ ውህደት” ምንና ምን ናቸው?

0
986

በ1997 አገራዊ ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘት ችሎ የነበረው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በወቅቱ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍን ለኢትዮጵያዊያን ማስተዋወቁ ዛሬም ድርስ የሚነሳለት ጉዳይ ሆኗል። ከዛሬ 13 ዓመት በፊት እንደ ክስተት ሆኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቅ ያለው ፓርቲው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግን ከሚጠብቀው በላይ ፈትኖታል ይባላል። ቅንጅት የአዲስ አበባን የምክር ቤት መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍም በቅቶም ነበር፤ ምንም እንኳን በውጠቴ መሠረት አዲስ አበባን ተረክቦ ባያስተዳድርም።
1997ን በኢትዮጵያ የኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የመድብለ ፓርቲ ማቆጥቆጥም ለመጀመሪያ ጊዜ መሬት ወርዶ የታየበት ነው ሲሉ የሚገልጹትም አሉ። በ2002 በተካሔደው አገራዊ ምረጫም ሆነ 2007ቱ ምርጫ 97 ላይ የነበረውን ቅንጅትን ያህል ጠንካራ ፓርቲ ማየት አለመቻሉን የሚያነሱ ወገኖች ‹በታሪካዊው ምርጫ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል፤ ብዙዎችም ፍርሰዋል እንደ ቅንጅት ጠንክሮ የታየ አልነበረም›› ሲሉም ይገልጹታል።
ቀስተደመና፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሊግ (ኢዴሊ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የተባሉ ፓርቲዎች ጥምረት የነበረው ቅንጅት መስከረም 14/1998 ውሕድት ለመፍጠር ያደረገው ስብሰባ ሳይሳካ መቅረቱም በምርጫው ውጤት የያገኘውን ወንበር እንዳይጠቀምበት አድርጎታል። በወቅቱ በጥምረቱ ውስጥ በነበረ የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት ግብአተ መሬቱ መፋጠኑን ብዙዎች በማንሳት ዛሬም ሲቆጩ ይደመጣሉ። በዚህም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከሕዝብ ይልቅ ራሳቸውን ለሥልጣን ስለሚያስቀድሙ ተመሳሳይ ርዕዮት እንኳን ኖሯቸው በተለያየ ስያሜ ብዙ የፖለቲካ ምኅበራን መመስረትን እንደሚመርጡም ይወቀሳሉ። ይህም በውስጣቸው ያለውን የዴሞክራሲ እጦት ማሸነፍ ሳይችሉ ሲቀሩም እየተበተኑ አዳዲስ ፓርዎችን መመስረትንም ለምደዋል በሚል ይተቻሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፓርቲዎችን ከመብዛት ይልቅ ሰብሰብ ብሎ ሞጋች ሆኖ መቅረብን በየመድረኩ ሲመክሩ ይደመጣል። ሌሎች ፖለቲከኞች በበኩላቸው ኢሕአዴግ ሲያፈርስና ሲሠራቸው የኖሩ ፓርዎች ስለበዙ እንጂ ከፓርቲ ሊቀመንበሮቻቸው ብቻ መታወቅ ባለፈ አባላታቸው የሚታወቁና በሕግ በመመራት ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ፓርዎቸ ቢቆጠሩ 10 እንደማይሞሉ በማንሳት ይሞግታሉ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ ተፎካካሪ ከሚሏቸው 82 አካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በነበራቸው ውይይት ከተናጠል የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመውጣት በአንድነት ሥራዎችን ቢሠሩ ለፓርቲዎቹ ጥቅም እንዳለው ሲመክሩ ነበር። ይህ ማድረግ ከቻሉ እሳቸውም ሆኑ መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። ይህንን ሐሳብም በመቀበል አንዳንዶች በጥምረት፣ ሌሎች ደግሞ በውህደት ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን ስምምነት ለመፈጸም መግባባት ላይ እየደረሱ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ከዚህም አልፈው ተዋህደናል የሚል መግለጫን እየሰጡ ነው።
ይሁን እንጂ ውህደትን በሚመለከት በፓርቲዎች መካከል የሚሠሩ ሥራዎች አጥጋቢ እንዳልሆኑ የፖለቲካ ልኂቃን ያነሳሉ። መራራ ጉዲና (ዶ/ር) “party politics, political polarization and the future of Ethiopian democracy“ በሚለው ጽሑፋቸው ፓርቲዎች ብዙ ጊዜ ጥቅምን ተመርኩዘው መመስረታቸውና ውህደት መፈጸማቸው የሥልጣን እሽቅድድም ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን ያትታሉ። ብሔር ላይ የተንጠለጠለ አጀንዳ የሚያራምዱ ፓርቲዎች መበርከትና ሌሎች ችግሮች ተዳምረው የሚፈልጉትን ያህል ርቀት እንዲሄዱ እንዳላስቻላቸውም ያነሳሉ።
የፖለቲካ ምሑሩ አለን ዋሬ እንደሚገልጹት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ከአንድ በላይ የሆነ ማኅበረሰባዊ ጥቅምንና ትላልቅ እሴቶችን የያዙ ተቋማት ናቸው። በሥራቸውም ለሚያስተዳድሩትና ለሚመሩት የሕብረተስበ ክፍልም አቋማቸውን በግልጽ ማስረዳት እንደሚጠበቅባቸው ይመክራሉ። ይህም ግን በተግባር አለመገለጹን በመጥቀስ ፓርቲዎች መርህ ተኮር አለመሆናቸውና በግለሰቦች መካከል የሚፈጠር የፖለቲካ መጠላለፍ ትልቁ ችግር ሆኖ መምጣቱን ይጠቅሳሉ።
ሰሞኑን በአገር ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት ሰማያዊ፣ ኢዴፓና የቀድሞ የመድረክ አመራሮች እንዲሁም ሠላማዊ የትግል ስልትን ለመከተል ትጥቅ ፈትቶ ወደ አገር ውስጥ የገባው አርበኞች ግንቦት 7 ውሕደት ለመፈጸም መስማማታቸውን በሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች አረጋግጠዋል።
ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት ሲካሄዱ የነበሩ የጥምረትና የውሕደት ሒደቶች በሥራ አስፈጻሚና በሊቀ መናብርት ደረጃ ከላይ ብቻ የሚሠራ እንደነበርም ይነሳል። ይም መርህ አልባ ግንኙነትም ለፓርቲዎች በቶሎ መፈረካከስ አንዱ ምክንያት ነበር የሚሉት የአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈጻሚ አባል ቸኮል ጌታሁን አሁን ላይ የሚደረገው ውሕደት ከወረዳ መዋቅር ጀምሮ የተሠራበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳለ ንጉሴ ውሕደት የሚፈጽሙ ፓርቲዎች ቶሎ እንዲፈርሱ የሚደርጋቸው ምክንያት የግለሰብ ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚንጸባረቅባቸው ነው ይላሉ። እንዳለ ‹‹ውሕደት መፈጸም ጥሩ ነው በጋራ የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴም ጠቀሜታው የጎላ ነው፤ ግን የሚደረግው ውሕደት ሳይንሱን የጠበቀ ነው ወይ የሚለው ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው›› ይላሉ።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በአንድ ማሕተም አርማና ስያሜ እየተዳደሩም ብዙ ጊዜ በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ፓርቲዎች ለሁለት ሲከፈሉ፣ በምርጫ ቦርድ ሲሰረዙና እውቅና ሲነፈጋቸው ማየት የተለመደ ነው። ለዚህ ማሳያ ከሚባሉት ውስጥ በቅርቡ ይህ እጣ ፈንታ የደረሰው ኢዴፓ አንዱ ነው። ብዙ ጊዜም ፓርቲዎች በሚያጋጥማቸው ውስጣዊ አለመስማማት ምክንያት በህዝቡ አመኔታቸውን ያጣሉ።
የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ አካሉ ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም፤ ከባለፈው የቅንጅት መፈራርስ በመነሳት ውሕደቱ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል መላምትም ሲሰነዘር እንሰማለን፣ ውሕደታችን በሕግና መርህ ላይ የተመሰረተ እስከሆነ ድረስ ችግር ይገጥመናል የሚል ሐሳብ የለንም›› ይላሉ።
መምህር እንዳለ እንደሚሉት ውሕደትን የፈጸሙም ይሁን በተናጠል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕዝቡ ያላቸውን ተቀባይነት የሚቀንሰው የሕዝብን ጥቅም በማሰብ አለመነሳታትውና የፖለቲካ መርሆዎቻቸውን ጠብቀው አለመሥራታቸው ነው። ፓርቲያችው ባለፉት ወራት ለሁለት ተከፍሎ ውዝግብ ውስጥ እንደነበር በማስታወስ አሁን ላይ ለምታደረጉት ውሕድት ችግር አይፈጥርም ወይ? ስንል የጠየቅናቸው የኢዴፓ ሊቀ መንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ‹‹ላለፉት 18 ዓመታት ሕጋዊነታችንን ጠብቅን እየሠራን ነው በምርጫ ቦርድ ተመዝግበን ሕጋዊነታችንን ስላረጋገጥን ውሕደቱ ላይ የሚፈጥረው ችግር አይኖርም›› ብለዋል።
ውሕድትን ከመፈጸም በፊትም አንድ ፓርቲ ብዙ መስራት እንዳለበት በመጥቀስ በውሕደት ወቅትም በፊት ላይ የነበረ የፓርቲዎች ስያሜ፣ ዓርማና ርዕዮት ዓለም በአዲስ መልክ እንደሚዋቀር ይጠበቃል የሚሉ ወገኖች፣ ለዚህም በስነ ልቡና ረገድም ራስን ዝግጁ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
ውህደት በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግም እንዳልተከናወነና እስካሁንም ግንባሩ የአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ጥምረት እንደሆነ የሚያነሱት አበበ አካሉ ሰማያዊ ፓርቲም ላለፉት ሁለት ዓመታት በየክልሉ ካሉ አባላቱ ጋር የቤት ሥራዎቹን ቀድሞ እንዳከናወነ ገልጸዋል። ምንም እንኳን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ለቡድን (ለብሔር፣ ብሔረሰቦች) መብት ቅድሚያ የሚሰጥ ቢሆንም አሁን ላይ ውሕድት ለመፈጸም የተስማሙት ፓርቲዎች የዜግነት ፖለቲካ ዋና ማጠንጠኛቸው እንደሆነ ይገለጻል።
መንግሥትም የፖለቲካ ምሕዳሩን በማስፋት የፓርቲዎች ሕጋዊ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ከማድረግ በዘለለም፣ አሳታፊ የምርጫ ስርዓትን እያበጁ በሕዝብ ድምጽ ለሚያሸንፍ የፖለቲካ ፓርቲ ሥልጣን የማስረከብ ልማድ ሊኖረው እንደሚገባ ምሁራን ይመክራሉ። ይህ ሲሆን የመድብለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ስርዓቱ እያበበ እንደሚመጣ በመጥቀስም ለዚህ ስኬት ሁሉም በኃላፊነት ሊሠራ እንደሚገባ ነው የሚገለጸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here