የከተማ ፖለቲካ (ክፍል አንድ)

0
393

ከተሞች የፖለቲካ ማዕከል ናቸው የሚሉት ኢሳያስ ውብሸት፥ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ሒደቶችን በመቃኘት በሚጀምሩት በዚህ ጽሑፋቸው ከተሞች የፖለቲካ ዕሳቤዎች የሚጠነሰሱባቸው መድረኮች ናቸው በማለት ይህንን ባሕሪያቸውን በነባራዊው ዐውድ አስደግፈው ያስነብቡናል።

 

 

የቅርብ ጊዜው የፖለቲካ ለውጥ
በ1967 ኢትየጵያ እንደ አገር በሌሎች ዘንድ የተሳለችበት የ“ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት”ን በመመርኮዝ ተመሥርቶ የነበረው ዘውዳዊ መንግሥት ምንም እንኳ ብርቱ ተቋውሞ ከአርሶ አደሮች መግጠሙ የቁልቁለት ጉዞውን ቢያፈጥነውም በከተሞች አካባቢ (በተለይም በአዲስ አበባ) ሲካሄዱ የነበሩ ህዝባዊ አመጾች ግን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ-መሬቱ እንዲፈፀም ዋንኛ ምክንያት ሆኗል። እንደ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ገለጻ “የታኅሣሥ ግርግር” በመባል የሚታወቀው የ1953 መፈንቅለ መንግሥት “አይነኬ” ተብሎ የሚታሰበውን የንጉሡን ሥልጣን የነቀነቀ እና ተከትለው ለመጡ አመፆች በር የከፈተ ነበር። ይኼንን እውነታ ደግሞ የሚያጠናክርልን የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ የነበሩት ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ በግልበጣው ሙከራ ወቅት በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች መካከል ተገኝተው “እኛ መስኮቱን ከፍተናል፤ በሩን የምትከፍቱት እናንተ ናችሁ” (ጥላሁን፣ 1996) ብለው መናገራቸው ለተማሪው ንቅናቄ መጠናከር ፈር የቀደደ እና ሌሎችንም ለማንቃት ‹ሀ› ተብሎ ግስጋሴ የተጀመረበት የማንቂያ ደውል ነበር። የ1960ዎቹ የተማሪ እንቅስቃሴ የጊዜውን ፖለቲካ ከመለወጥ አኳያ የአንበሳውን ሚና ተጫውቷል። በወቅቱ ሥር በሰደደው እና ወጣቶችን ባካተተው ተቃውሞ በመንግሥት አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የዘውዳዊውን መንግሥት አሰናበተ።
የንጉሡን ዘመን ተከትሎ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በርዕዮተ ዓለም ተመሳሳይ ዓላማን ያነገቡ ኃይሎች በጥቃቅን ልዩነቶች ራሳቸውን በጎራ በመከፋፈል ወደለየለት የእርስ በርስ መጠፋፋት የገቡበትን ሁኔታ እናገኛለን። በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የከተማ ትግልን በማራመድ ባለሥልጣኖች እና የመንግሥት መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስን እንደ እንድ ስትራቴጂ መጠቀም ጀመረ፤ ታሪኩ ሰፊ እና ውስብስብ ቢሆንም መጨረሻው ግን ዓላማው መክኖ የተሸነፈበት ሁኔታ እናያለን። በጊዜው የወታደራዊ መንግሥት ደርግ በኢሕአፓ ላይ ጊዜያዊ ድል ቢቀዳጅም ኃይሉንም እጅጉን የተገዳደረ እና ከሕዝቡ ጋር የሚያቃቅር እርምጃዎቹንም እንዲወስድ ምክንያት ሆኗል፤ ይህንንም ተከትሎ በሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚመራ ኃይል በተራው ሥልጣንን በአፈ ሙዝ ለመረከብ ቻለ።
ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ኢሕአዴግም ቢሆን ክፉኛ ደዌ እየሆነበት ያለው በከተሞች የሚዘወሩ ተቃውሞዎች እና የአመፅ ትግሎች ናቸው። በተለይም ደግሞ የምርጫ 97 ውጤትን ተከትሎ የተከሰተው ፀረ ኢሕአዴግ ተቃውሞ እና ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በከተሞች አካባቢ መሠረታቸውን የጣሉ ነበር። በአፀፋው የታጠቁ የመንግሥት ወታደሮች የወሰዷቸው “ተመጣጣኝ ያልሆኑ” የኃይል እርምጃዎች መንግሥትን ከሕዝብ ያራራቀ ሁናቴን ፈጥሯል። ችግሩን ከምንጩ በመረዳት አስፈላጊውን የመፍትሔ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ “የፖለቲካ ትርጉም” በመስጠት መሸፋፈኑ ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል እንጂ በፍፁም የሐሳብ ልዕልና አምጥቶ የሕዝብ ድምፁን ሊያዳፍን አይችልም። እንዳለመታደል ሆኖ ደግሞ የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ዕሳቤ የተመሠረተው በእንደዚህ ዓይነት የተሳሳተ ግምት ላይ ነው።
በእርግጥ በ1998 የፀደቀው “የከተማ ልማት ፖሊሲ” በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው እና ከከተማ ጋር ተያይዞ ለሚስተዋሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ፋይዳ ይሰጣል ተብሎ የታመነበት እና ገጠርን ማዕከል ባደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለሚመራው የያኔው ኢሕአዴግ መንግሥት መልካም እርምጃ ተደርጎ የተወሰደ ነበር። ሆኖም ግን በከተሞች የሠላም አየር የነፈሰው በጣም ጥቂት ለሚባል ጊዜያት ነበር፤ ይልቁንስ የኑሮ ውድነት እና የመልካም አስተዳደር እጦት የአገሪቷ ስንክሳር ከመሆን ባለፈ መልኩ በዜጎች ለሚነሱ “መሠረታዊ” ጥያቄዎች መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱን አጠንክሮ ቀጠለ፤ ሕዝብ የውስጥ ስሜቱን የሚተነፍስበት መድረኮች ተከረቸሙ። የተስፋ ጭላንጭል የነበሩት ጥቂት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን አዋጆችን እና የሕግ አንቀፆችን በመጠቃቀስ ወደ እስር ቤት ማጎሩን ተያያዘው። በሕጋዊ መንገድ ድምፁን ማሰማት ያልቻለው ፍትሕን እና ዴሞክራሲን ያነገበ ሕዝብ በአስገዳጅ ሁኔታ የአመፅ ተቃውሞ መንገድን እንዲጠቀም ዋንኛ ምክንያት ሆነ።
በታኅሣሥ ወር 2004 በሃይማኖት ጉዳይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም የእስልምና እምነት ተከታዮች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እንቅስቃሴ ጀመሩ፤ ብዙም ሳይቆይ ‘የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን’ን ምክንያት ባደረገ መልኩ በኦሮሚያ በሚገኙ በአንዳንድ የትምህርት ማዕከላት የተጀመረው ሕዝባዊ ቁጣ ቀስ በቀስ መላ ክልሉን አዳረሰ፤ በትግራይ ክልል በተካተቱ አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄን (ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ) በማንሳትና እና በኦሮሚያ ክልል የሚካሔደውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አጋር በመሆን የአማራ ክልል ሕዝብም ተቃውሞውን ተቀላቀለ፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተለያዩ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ እና የማንነት አጀንዳዎችን በመያዝ ሕዝባዊው ተቃውሞ በደቡብ ክልል እንደ ሰደድ እሳት ይቀጣጠል ጀመር።
ከጠቅላላው ሕዝብ ብዛት አኳያ ጥቂት የሚባሉ ሆኖም ግን “የወገኖቻችን መብት እኛም ያገባናል” በሚሉ የከተማ ሊቆች እና ነዋሪዎች አቀንቃኝነት የተካሔዱ ሕዝባዊ ጥሪዎች እና ተቃውሞ በሥልጣን ላይ ያለውን የኢሕአዴግ መንግሥት ድጋፍ በመሸርሸር ብቻ ያላቆመ እና ከፍ ሲልም በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት ተቋማት እንዲፈራርሱ ምክንያት የሆነ ጭምር ነበር። መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ከአንዴም ሁለቴ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታሰበለትን ዓላማ ያላሳካ ብቻ ሳይሆን እንደውም በተቃራኒው እንደ ‘ሂዩማን ራይትስ ዋች’ ሪፖርት (2017) ከሆነ ኢሰብኣዊ ድርጊቶች የተፈፀሙበት እና ችግሩን ያባባሰ ታሪካዊ እርምጃ ነበር። በዚህም መሠረት ኢሕአዴግ ስንት ጊዜ በተሐድሶ እና ጥልቅ ተሐድሶ ሰበብ እርምት ለመውሰድ የዳከረ ቢሆንም፥ ያ አልሆን ሲል ከፍተኛ በሚባል ደረጃ የአመራር እና የሐሳብ ለውጥ የወሰደበት እርምጃ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
“ከተማ” እና “ፖለቲካ”
እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2018 (እኤአ) ሪፖርት 55 በመቶ የሚሆኑት የዓለም ሕዝብ በከተሞች የሚኖሩ ሲሆን ከ30 ዓመታት በኋላ በ13 በመቶ ልቆ 68 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡ በቁጥር ስንገልፀው ደግሞ 2.5 ቢሊዮን ሕዝቦች ኑሮዋቸውን በከተሞች ማድረግ ይጀምራሉ ማለት ነው። ወደ አፍሪካ ስንመጣ በአማካይ 43 በመቶ ሕዝቦቿ በከተሞች ይኖራሉ። በተያያዘም ምንም እንኳ ከሌሎች አፍሪካ አገራት ጋር ስትወዳደር ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየከተመች (urbanized) ያለች አገር ናት ብትባልም አሁንም ቢሆን ግን የከተማ ሕዝቦቿ ድርሻ ከ20 በመቶ ሊዘል አልቻለም።
ከተሞች የባሕል፣ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ማዕከል ከመሆናቸው በዘለለ የአገራት አንቀሳቃሽ ሞተር ጭምር ናቸው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአገራት መንግሥት አወቃቀር/አስተዳደር፣ ፖሊሲዎች እና ሕግጋት የከተሞች ነፀብራቅ ናቸው፤ ትላልቅ ፍብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች የሚያካትቱ በመሆናቸው የኢኮኖሚ ሳንባ ሊባሉም ይችላሉ።
በፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ አንኳር ጉዳይ ሥልጣን ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም “መርሕ” ወይም “ብሔር/ዘውግ”ን መሠረት ባደረገ መልኩ በመደራጀት፥ ደጋፊዎቻቸውን በማብዛት ይኼንን ሥልጣን የሚያገኙበት ዕቅድ ይነድፋሉ። ስልቶቻቸው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መንገድ የተከተለ አልያም ደግሞ ኃይል መጠቀምን መሠረት ያደረገ ሊሆን ይችላል። ከብዙ አገራት ልምድ ማየት እንደሚቻለው ከተሞች የፖለቲካ ዕሳቤዎች የሚጠነሰሱበት እና ዓላማ ተኮር ትግል የሚካኼደባቸው ዋነኛ መድረክ ናቸው። የተቀየጠ ኅብረተሰብ፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም እና የተማረ የሰው ኃይል፣ የተሻለ የመገናኛ አውታር እና ሥራ አጥነት መኖሩ በእኔ አመለካከት ከተሞች ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አመቺ እንዲሆኑ ያስቻሉ ምክንያቶች ናቸው።

ኢሳያስ ውብሸት በደብረ ብርሃን ዮኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት ሳይንስ መምህር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው isawub@gmail.com ሊያገኟቸው ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here