በእርግጥ ምርጫው ሪፈረንደም ሆኗል!!

0
800

በ2012 ዓመት ማብቂያ በጳጉሜ ወር በትግራይ ክልል ምርጫ ተካሂዷል። የዚህን ምርጫ ቅድመ ሁኔታ እንዲሁም ተካሂዶ ውጤቱ እስኪሰማ ድረስ የነበረውን ሂደት የሚያወሱት ግዛቸው አበበ፣ የምርጫው ውጤት አስቀድሞ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ይሆናል የተሟገቱና ተቃዋሚዎች ቢያንስ ወንበር ያገኛሉ ብለው ተስፋ ያደረጉትን ጨምሮ ብዙዎችን ምን ያህል እንዳስደነገጠ አንስተዋል። ይህም የሕወሓትን እውነተኛ መልክ ለቀሪዎቹ ያመላከተ መሆኑን በዳሰሳቸው አሳይዋል።

በ2012 መካሄድ የነበረበትን አገር ዐቀፍ ምርጫ በሚመለከት በተነሳው ውዝግብ ውስጥ ሕወሐት መጀመሪያው ላይ ይዞት የነበረው አቋም ስህተት ነበር ማለት አይቻልም። የብልጽግናና የሌሎች በርካታ የፖለቲካ ቡድኖች አቋምም ተቀባይነት ያለው እንደነበረ መዘንጋት አይገባም። ምክንያቱም ውዝግቡ ብልጽግናና አንዳንድ ቡድኖች ምርጫው እንዲሁ መራዘም እንዳለበትና ብልጽግናም መሪ ሆኖ እንዲቀጥል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አቋም የያዙበት ሲሆን ሕወሐትና አንዳንድ ቡድኖች ደግሞ ምርጫው በመሰረዝና ባለመሰረዙ፣ ከተሰረዘም ቀጥሎ ሊኖር ስለሚገባው አገርን የማስተዳደር ጉዳይ ቁጭ ብለን ተነጋግረን መወሰን ይገባናል የሚል አቋም ነበራቸው።

ቀድሞውንም ቢሆን በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ከተቃዋሚዎችም ሆነ ከኅብረተሰቡ አብዛኛው ክፍል ከምርጫው አገር ማረጋጋቱ ይቅደም፣ ጸጥታ ማስከበር ባልተቻለባቸው በርካታ አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ አይታሰብም ባይ ነበር። በኋላ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጨምሮበት ምርጫው መራዘሙ በብዙዎች ዘንድ እንደ ስህተት የሚቆጠር ጉዳይ አልነበረም።

ስህተቱ የተፈጠረው ብልጽግናና ሕወሐት ‹እኔ መሰማት አለብኝ› ብለው በየራሳቸው ፍላጎት መንጎድ በመጀመራቸውና ሌሎች ብዙ ቡድኖች ደግሞ ከኹለቱ የአንዳቸው ጀሌ የመሆን ዓይነት አዝማሚያ መያዛቸው ነው። በመጨረሻም ልዩነቱ ብልጽግናዎች ምርጫ አይካሄድም ከማለት አልፈው በውድም ሆነ በግድ እኛ ገዥዎች ሆነን እንቀጥላለን የሚል፣ ሕወሐቶች ደግሞ ምርጫ ማካሄድ ማንኛውም ምድራዊ ኃይል የማያቆመው መብታችን ነው ብለው አቋም ይዘው በለየለት መፋጠጥ ውስጥ ገብተው አለመግባባቱ ወደ ስህተት፣ ስህተቱም ወደለየለት አጥፊነት አድጓል።

በዚህ ልዩነት ላይ ሕወሐት የንቀት አካሄድ አክሎበትና ብልጽግናዎች ደግሞ በተረኛ አለቃነት መንፈስ በማን አለብኝነት አካሄድ ቀጥለውበት፣ አጥፊነቱ በጠላትነት ወደመተያየትና ወደመዘላለፍ ብሎም ወደመዛዛት ወስዷቸዋል። እየቆዩ ኹለቱም ቡድኖች በጣም የወረዱና ደረጃቸውን ያልጠበቁ እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብን እየመሩ መሆኑን የረሱ አንዲመስሉ ያደረጋቸውን የቃላት ቀዝቃዛ ጦርነት ከፍተዋል።

ለዚህ ቀዝቃዛ ጦርነት መጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከበርካታ የፌዴራልና የክልል ብልጽግና ቡድን አመራሮች ጋር ሆነው በትግራይ ይካሄዳል የተባለውን ምርጫ በሚመለከት ዛቻ፣ ነቀፌታና ውንጀላም ጭምር መሰንዘራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህን የብልጽግናዎች ዘመቻ ተከትሎ ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳና ሌሎች የሕወሐት አውራዎች በበኩላቸው ጠቅላዩንና ተባባሪ አጋሮቻቸውን በመወረፍና በማቃለል ቀዝቃዛውን ጦርነት አግመውታል።

በዚህ ግርግር ግን ሕወሐት ከትግራይ ሕዝብ ጥቂት የማይባለውንና በትግራዩ ምርጫ እንወዳደራለን የሚሉ ተቃዋሚዎቹም ጭምር በእልህ ተነሳስተው ‹ምርጫ ወይም ሞት!› ባይ ሆነው ከጎኑ እንዲሰለፉ ማድረጉ ተሳክቶለታል። ‹ለ17 ዓመታት መራር ጦርነት ያካሄድነው በጨፍላቂ፣ አሃዳዊና አምባገነን ቡድን ወይም ግለሰብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታችንን ለመነጠቅ አይደለም› ባዮች በዝተው የታዩትም ለዚህ ነው። በዘርና በክልል መቦዳደን የብዙ ዓመታት ልምምድ እየተደረገ በቆየበት አገር ጠቅላዩ የተከተሉት መንገድ የሚያዋጣ አይደለም።

ምርጫና ውዝግቡ
ብልጽግናዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫ ያራዘሙ አገራትንና መንግሥታትን በመጥቀስ፣ ምርጫ ያካሄዱ መንግሥታትና አገራት የሌሉ የሚያስመስሉ ፕሮፓጋንዳዎችን በመሥራት ትክክለኛ አቋም እንደያዙ ለማስረዳት ሲጥሩ ነበር። ሕወሐቶች ደግሞ የኮቪድ-19 ወረራ በምድራቸው ባለበት ወቅት ምርጫ ያካሄዱ መንግሥታትንና አገራትን ብቻ በመጥቀስ፣ ምርጫ ያስረዘሙና የሰረዙ መኖራቸውን በመካድ የያዙት አቋም ትክክለኛ መሆኑን በመተረክ አካሄዳቸው እንከን አልባ ሆነው ለመታየት ሞክረዋል።

ሌላው አስገራሚ ነገር ብልጽግናዎችም ሆኑ ሕወሐቶች ሕዝብ እንደመረጣቸውና ሕዝብ የሰጣቸውን ሥልጣን ለሕዝብ መልሰው በመስጠት፣ ሕዝብ እንደገና ሥልጣኑን ለመረጠው እንዲሰጥ አበክረው እየሠሩ መስለው ለመታየት ድራማ እየሠሩ መሆናቸው ነው። ግንቦት 2007 ሕዝብ መቶ በመቶ መረጠን ብለው ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሞክረው ከ2008 የመጀመሪያ ወራት ጀምሮ በተቀጣጠለው አመጽ ሕዝብ እንዳልመረጣቸው ማረጋገጫ የተገኘባቸው መሆኑን ረስተው፣ ሕዝብ የመረጣው ለመምሰል መሞከራቸው ፖለቲካዊ አቅልን መሳት ውስጥ መግባታቸውን የሚያሳይ ነው።

ኹለቱም ቡድኖች ሕዝባዊ አመጹ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓትን ቢንደውም ጠንካራና ሥልጣን ለመያዝ በሚያስችል ደረጃ የተደራጀ ተቃዋሚ ባለመኖሩ፣ ሥልጣኑን በሕወሐትና በብልጽግና ሥም ለመቀራመት ዕድል የፈጠረላቸው መሆኑን ዘንግተውታል። የተቃዋሚዎች አለመተባበርና በዓላማ መራራቅ የፈጠረው ክፍተት እነሱ አዲስ አበባና መቀሌ ላይ በገዥነት ለመቀጠል አጋጣሚውን እንዳመቻቸላቸው የዘነጉ መስለዋል።

ይህን ምርጫውን ተንተርሶ የተነሳው ውዝግብና መፋጠጥ ቁልጭ አድርጎ ያሳየው አንድ መራር ሃቅ አለ። አዲስ አበባ ላይ ግለሰባዊ አምባገነንነት እየሰፈነ ሲሆን መቀሌ ላይ የተለመደው ቡድናዊ አምባገነንነት ይበልጥ አይሎ እየቀጠለ ነው። ይህን ፈጽሞ መካድ አይቻልም።

ብልጽግናዎች ምርጫ ሕዝብን በማሰባሰብ የሚካሄድ ሥራ በመሆኑ ለኮቪድ-19 መሰራጨትና መስፋፋት ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል ብለው ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምና ሥልጣኑም ከእጃቸው ሳይወጣ እንዲቆይ ቢያደርጉም፣ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የተጀመሩ ሥልጠናዎች፣ ሰልፎች፣ የንቅናቄ ግርግሮች ወዘተ… ባሉበት ቀጥለው ታይተዋል። ሕወሐቶችም ኮቪድ-19 ምን ዓይነት አደጋ ያስከትላል ብለው ከመጨነቅ ይልቅ ከባላንጣቸው ጋር በተጋቡት እልሀወ የበላይነቱን ስፍራ ለመውሰድና ደጋፊና ተከታይ ለማብዛት በማሰብ ሕዝባዊ ግርግሮችን፣ ወታደራዊ ትርኢቶችንና ምርጫውንም ጭምር እንደ መሣሪያ ተጠቅመውበታል።

ሕወሐት ይህን ምርጫ መቃወምን በትግራይና በሕዝቧ ላይ ክህደት እንደመፈጸም፣ የተሰዉትን ታጋዮች እንደ መናቅ፣ አሃዳዊነትን ለመመለስ እንደ መሞከር፣ እንደ ጸረ-ፌዴራሊስትነት፣ እንደ ባርነት ናፋቂነት ወዘተ…አድርጎ እየገለጸው ነው የምርጫ ዝግጅት ያካሄደው። የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን አባላትና ተቃዋሚወች ነን ብለው ወደ ምርጫው የገቡት ቡድኖች ይህንኑ አስተሳሳብ በተደጋጋሚ አስተጋብተውታል።

‹‹ምርጫ የራስን እድል በራሰ የመወሰን እንዱ መገለጫ ነው!›› በሚል መርህና ‹ትግራይ ትመርጣለች!› በሚል መሪ መፈክር ስር የተካሄደው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ በሕወሐት ሰዎችም ሆነ በተቃዋሚ ተወዳዳሪዎች በኩል እንደ ሪፈረንደም ተቆጥሮ ነው የተካሄደው። የምርጫው መካሄድ በትግራይ የፌዴራሊዝም ስርዓት መንገሡ፣ በምርጫው መካፈል የፌዴራሊስትነት ማረጋገጫ፣ እንዲሁም ምርጫው እንዲካሄድ ከብልጽግና ጋር የተፋጠጠው ሕወሐት የፌዴራሊዝም አባትና ጠበቃ የመሆኑ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ እየተሰበከም ጭምር ነው ምርጫው የተካሄደው።

ይህ አመለካከት በሕወሐትና በትግራይ በሚንቀሳቀሱ የሕወሐት አጋር ወይም ተለጣፊ የመሆን አዝማሚያ በሚታይባቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብሔረሰቦችን እንወክላለን በሚሉ ብሔርተኛ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ጭምር ሲቀነቀን የነበረ ነው። በተለይ ደግሞ በውጭ አገራት የሚኖሩ ብሔርተኛ የኦሮሞ ልሂቃንና የሚዲያ ሰዎች በሰፊው ሲራገብ የሰነበተ ጉዳይ ነው።

እነዚህ የኦሮሞ ልሂቃንና አክቲቪስቶች ሕወሐት ለ27 ዓመታት አሰፈንኩት ያለውን ፌዴራሊዝም ረስተው፣ ሕወሐትና በሚቃወመው የኦሮሞ ወጣት ላይ የወረደውን መከራ ረስተው ዛሬ ሕወሐትን የፌዴራሊዝም ጠበቃ አድርገው በነጋ በጠባ በትግራይ ሚዲያዎች ላይም ጭምር ምስክር መሆናቸው አስደንጋጭና አሳፋሪ ነገር ነበር። የትግራይ ነጻነት ድርጅት (ውድብ ናጽነት ትግራይ- ው.ና.ት.) የተባለው ቡድን ደግሞ ምርጫውን በተለየ መንገድ በማየት ትግራይን ለመገንጠል የሚካሄደው የትልቅ ሪፈረንደም የመጀመሪያ እርምጃ አድርጎ ገልጾታል። ው.ና.ት. ይህን ሲል በዚህ ምርጫ ካሸነፈ ሕዝቡ በው.ና.ት. አማካኝነት ሪፈረንደም ተካሂዶ ትግራይ ከኢትዮጵያ እንድትለይ እንደሚፈልግ የሚያሳይ ትልቅ ማረጋገጫ ነው ማለቱ ነው።

በትግራዩ ክልላዊ ምርጫ ዋዜማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጨረቃ ምርጫ፣ በድሮ የሞተ ሐሳብ የሚራመድ፣ ጭንቅላቱ የደረቀ እና ገንዘቡ ሲደርቅ የሚቆም በሚሉ ቁጭትና ብስጭት የወለዳቸው የሚመስሉ አባባሎችን እየወረወሩ ሕወሐት ገንዘብ ስላለው ምርጫውን እንደሚያካሄድ ሲናገሩ ተሰምቷል። ምክትል ፕሬዝደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ደግሞ ለጠቅላዩ መልስ ሰጡ ብሎ ለመናገር በሚያስደፍር አኳኋን ‹ማውራት ይችላል፤ እጁን ማስገባት ግን አይችልም። ማቆም አይችልም።› ሲሉ ተደምጠዋል። ምክትል ፕሬዘደንቱ ይህን ያሉት ጋዜጠኞች የጠቅላዩን ንግግር ጠቅሰው ጥያቄ ካቀረቡላቸው በኋላ ነበር። ከዚያም ምርጫው ጳጉሜ 4/2012 ተካሂዷል። ሕወሐት ለዚህ ምርጫ ወደ 200 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጉም ተነግሯል።

የትግራይ ምርጫ
በምርጫው ሕወሐትና ሦስቱ ክልል ዐቀፍ ተቃዋሚ ቡድኖች ማለትም ብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (የታላቋ ትግራይ ሸንጎ)፣ ሳ.ወ.ት. (ሳልሳይ ወያነ ትግራይ)፣ ው.ና.ት. (ውድብ ናጽነት ትግራይ) በመላ ትግራይ ሲወዳደሩ አካባቢያዊ ፓርቲ የሆነው ዓ.ዴ.ፓ. (ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ) ደግሞ በኢሮብ ወረዳና በዙሪያው ነው ለምርጫ የቀረበው።

ተቃዋሚወቹ ራሳቸው ሕወሐት በምርጫው እንደሚያሸንፍና እነሱ ለዴሞክራሲ ልምምድ ወደ ምርጫው እንደገቡ ሲናገሩ የነበሩ ቢሆንም፣ ዓ.ዴ.ፓ. በኢሮብ፣ ባይቶና ደግሞ በምሥራቃዊ ትግራይ በተለይም በዓዲግራትና አካባቢው በርከት ያሉ ተወዳዳሪዎቻቸውን ሊያስመርጡ እንደሚችሉ ተስፋ ተሰንቆ ነበር። ውናት ደግሞ የተበታተነ የዲጂታል ወያኔዎችን ድምጽ እዚህና እዚያ በሰፊው አግኝቶ ትይዩ፣ ተመጣጣኝ ውክልና በሚለው አሰራር ከተመደቡት 38 ወንበሮች ጥቂቶቹን እንደሚያገኝ በሰፊው ተናግሮና አስነግሮ ነበረ።

በትግራይ ምርጫ 2 ሚሊዮን 789 ሺሕ 254 ሕዝብ ለመመረጥ ተመዝገቧል። ይህን ቁጥር መጠራጠር አይገባም። ትግራይ ውስጥ ምርጫ በመጣ ቁጥር ከቤት እመቤቶች ጀምሮ እስከ መሥሪያ ቤቶች ለምርጫ ተመዝገቡ የሚል ውትወታ ዕለት በዕለት መደረጉ፣ የተመዘገበና ያልተመዘገበ እየተለየ ግምገማ መደረጉ፣ በጠርናፊዎች በሚደረግ ክትትልና ማጣራት ያልተመዘገቡ ሰዎች እረፍት እንዲያጡ ከተቻለም ሥጋት እንዲያድርባቸው በማድረግና የመሳሰሉት የቁጥጥር አካሄዶች የተለመዱ ናቸው።

ድምጽ በመስጠቱ መሳተፍና አለመሳተፍም በዚህ ሂደት የሚቃኝ ነውና የተባለውን ያህል ሕዝብ ድምጽ መስጠቱም ተነግሯል። የተለያዩ ሰልፎች በሕወሐት ወይም በትግራይ መንግሥት ሲጠሩም በተዋረድ በተዘረጋው ጥርናፌ (አደረጃጀት) አንድ ሰው በስሩ ያሉትን ሰዎች የማንቀሳቀስና የመቆጣጠር ሥራ እየሠራ ነው፤ ሕዝብ ወዶም ሆነ ሳይወድ አደባባዮችንና ጎዳናዎችን የሚያጥለቀልቀው።

ለምርጫው እያንዳንዱ ክልላዊ ፓርቲ 152፣ ዓዴፓ 13 ተመራጮችን ያቀረቡ ሲሆን በግል የተወዳሩ ደግሞ አራት ነበሩ። በግል ለመወዳር የተመዘገቡት 11 ሲሆኑ፣ ራሳቸውን ለሕዝብ ለማስተዋወቅና ለቅስቀሳ የተመቻቸው መድረክ የለም በሚል ቅሬታ ሰባቱ ራሳቸውን አግልለዋል። መጀመሪያውኑ በግል ለመወዳደር የቀረቡት 11 ሰዎች ብቻ መሆናቸው ከትግራይ ሕዝብ ብዙው ወይም ጥቂቱ ምርጫን እንዴት እንደሚያየው የሚያሳይ ነው።

በትግራይ ምርጫ ሲካሄድ ሕወሐትን መገዳደር እንደ ወንጀል ብቻ ሳይሆን እንደ ኃጢአትም ተደርጎ እየተነገረ የኖረ ጉዳይ ነው። ምርጫ በመጣ ቁጥር በትግራይ ምድር ሕወሐትን ለመቀናቀን የሚወዳደሩ አገር ዐቀፍም ሆኑ የክልሉ ተቃዋሚ ቡድኖች ባንዳዎች፣ የነፍጠኞች ወይም የትምክህተኞች ተላላኪዎች፣ ትርፍራፊ የደርግ-ኢሰፓ ወኪሎች ወዘተ… መሆናቸው በካድሬዎች ብቻ ሳይሆን በክልሉ ውስጥ በሚገኙ መገናኛ ብዙኀንም ጭምር እየተነገረ ነው፤ ሕወሐት ብቻውን እየተመረጠ የኖረው።
በትግራይ ምድር በግል ተነሳስቶ ወደ ምርጫ ውድድር መግባትም በጠላትነት ከመፈረጅ አያድንም። በአንድ ወቅት በ1997 ምርጫ መቀሌ ላይ በግል ለወዳደር ቀርበው የነበሩት ወይዘሮ አበባ ገብረሥላሴ ያጋጠማቸውን ችግር በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ በጥቂቱ ለንባብ በቅቶ ነበረ። በቅርቡ ደግሞ ወይዘሮ አበባ ገብረሥላሴ ቢቢሲ ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በወቅቱ ያጋጠማቸውን ችግሮች በጥቂቱ አስደምጠዋል።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በየካቲት 14 ቀን 2012 እትሟ “ኦሮምያ እንደ ትግራይ- ጅማም እንደ ዓድዋ?!” በሚል አርእስት ስር ምርጫው ሳንካ ሊገጥመው እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውን የሚመለከት ጽሑፍ አስተናግዳ ነበረ።

በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሕወሐት/ኢሕአዴግ ምርጫዎች በግልጽ በሚታወቁ ሕገ-ወጥና ጸረ-ዴሞክራሲ አሠራሮች የተሞሉ ሆነው የሚካሄዱ መሆናቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም። ‹… አስፈላጊ ከሆነ ማን ለማን ድምጽ እንደሰጠ ወረቀቱ ላይ ያረፈውን አሻራ መርምረን ጠላትና ወዳጃችንን እንለያለን› የሚለው ማስፈራሪያ የተለመደ አስበርጋጊ አሰራር ነው። አንድ ለአምስት እየተጠረነፉ ‘በመመካከር’ ተመሳሳይ ድምጽ መስጠትና፣ ከዚህ ጥርናፌ ያፈነገጠን ሰው ማሸማቀቅና ጥምድ አድርጎ በመያዝ በሌላ ምርጫ ‘እንዲስተካከል’ ማድረግም በሰፊው የሚሠራበት ዘዴ ነው።

በምርጫ ወቅት መራጮች ሕወሐት/ኢሕአዴግን እንዲመርጡ በግልጽ መወትወት፣ በምስጢር ድምጽ መስጫ ክፍል ውስጥ ተቀምጠው ‘ምልክት እዚህ ላይ አድርግ’ ብለው ትዕዛዝ በሚሰጡ ካድሬዎች ሰዎችን መጠምዘዝ ወዘተ…. የማይረሱ የምርጫ ወቅት ገጠመኞች ናቸው። ኮርኒስ ውስጥ ወይም በምስጢር ድምጽ የሚሰጥበትን ክፍል ለማየት በሚያስችል ክፍል ውስጥ ሆነው አጮልቀው እያዩ፣ ማን ማንን እንደመረጠ እየመዘገቡ ከሕወሐት/ኢሕአዴግ ለተለየ ተወዳዳሪ ድምጽ የሰጡትን በማጥቃትና በማሳደድም ተሳዳጆቹ ለቀጣዩ ምርጫ ‘እንዲታረሙ’ ማድረግ ይኸኛውን ምርጫ ደግሞ በኮረጆ ግልበጣ ‘ማስተካከልም’ በሰፊው የተሠራበት ዘዴ ነው።
ሌሎችም ብዙ አሳፋሪ ዘዴዎች ነበሩ። በምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎችን ጸጥ የማሰኘት፣ የመደለል ካልሆነም ታዛቢዎችን ከምርጫ ጣቢያዎች አጥረግርጎ የማባረር ሥራ መሠራቱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ስለዚህ የትግራዩ ምርጫ በአንዴ ነጻና ዴሞክራሲዊ ሆኖ ይካሄዳል ተብሎ አይጠበቅም። በእርግጥ ትግራይ ውስጥ በብዙ አካባቢዎች ሕወሐትን መቃወም እንደ ኃጢአት የሚቆጠረው በምርጫ ቅስቀሳና በድምጽ መስጫ ዕለት ብቻ ሳይሆን በጠላ ቤትና በሻይ ቤት በሚደረጉ ተራ ጭውውቶች ላይ ጭምር ነው። ለአንዳንዶች ሕወሐት ልጆቻቸውን ወይም ወላጆቻቸውን የሰዉላት ብቸኛ አለኝታቸው ናት። ለሌሎች ደግሞ ትግራይ ውስጥ ተቀምጦ ሕወሐትን መቃወም በእሳት እንደ መጫወት የሚቆጠር ነው።

ከዚህ ሌላ ከወይን ጋዜጣና ከድምጽ ወያነ ሬዲዮ ውጭ ምንም ዓይነት የወሬ ምንጭ የማያገኘው ወይም መከታተል የማይፈልገው ሕዝብ ጥቂት አይደለም።
ጳጉሜ 4/2012 በተካሄደው የትግራይ ምርጫ ሕወሐት ብቻውን ለውድድር የቀረበበት ዓይነት ምርጫ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ሕወሐት በመንግሥታዊ ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆን የግል ንብረቱ በሆነው በድምጺ ወያነ ሬዲዮና ቴሌቪዝን፣ በወይን ጋዜጣና መጽሔት እንደ ልቡ ሲቀሰቅስ ከርሟል። ሌሎች ተወዳዳሪ ቡድኖች ግን ይህን የመሰለ ዕድል አልነበራቸውም። ብዙው የትግራይ ሕዝብ የሕወሐትን ተቀናቃኞች ለስድስት ጊዜያት ያህል በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ካካሄዱትን ክርክር ውጭ እነሱን ለማወቅ መድረክና አጋጣሚ አግኝቷል ማለት አይቻልም።

በኮቪድ-19 ምክንያት መሰባሰብና እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው ራሳቸውን ማስተዋወቅ ላልቻሉት ተቃዋሚዎች መንግሥታዊው የትግራይ መገናኛ ብዙኀን የምርጫ ቅስቀሳው እስኪጀመር የፈቀዱላቸው ነገር ነበር ማለት አይቻልም። በሳተላይት የሚተላለፈው ትግራይ ሚዲያ ሃውስ ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ እያወያየና በተናጠልም ቃለ ምልልሰ እያደረገ ከሕዝብ ጋር ሊስተዋውቃቸው ሙከራ አድርጓል። ስንቱ የትግራይ ሕዝብ ይህን የሳተላይት ሚዲያ ሊከታተለው ይችል ይሆን? ይህን መሰሉ የመድረክ ድርቀት በምርጫ ተፎካካሪ መሆን ብቻ እንደ ጠላት የመፈረጅ የረዥም ጊዜ ልምድ በዳበረበት የትግራይ ምርጫ በእቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ መሆኑ አይቀሬ ነው።

ከዚህ ሌላ ከሕወሐት ውጭ ያሉት ክልላዊ ፓርቲዎች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ዝቅዝቅ ማድረጋቸው ለብዙው የትግራይ ሕዝብ ምን ትርጉም እንዳለው የተገነዘቡ አይመስሉም። ኢትዮጵያን ለመበታተን እሠራለሁ የሚለው ውናት፣ ኢትዮጵያዊነት ኮንትራት ነው ስንፈልግ ኮንትራቱን እናራዝማለን ካልፈለግንም ኮንትራቱን እናቋርጣለን የሚለው ባይቶና፣ ከሕወሐት የበለጥኩ ወያኔ ነኝ የሚለው ሣልሳይ ወያነ የትግራይን ሕዝብ በዚህ መንገድ መተዋወቃቸው ጥሩ ዘዴ የሆነ አይመስልም።

በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት ሕወሐት ለፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ጠበቃ ሆኖ መቆሙና ሌሎቹ ክልላዊ ፓርቲዎች ሕወሐትን የሚገባውን ያህል ብሔርተኛ አይደለም፣ ለኢትዮጵያ ሲል ትግራይንና ትግራዋይነቱን የረሳ ነው እያሉ መሞገታቸው ከጎልማሳና በዕድሜ ከገፉ ተጋሩ ጋር ሳያቃቅራቸው አልቀረም። በዚህና በሌሎችን ምክንያቶች የምርጫውን ውጤት ለመገምገም ሕወሐት ብቻውን ተወዳደረ ወይስ አጭበረበረ በሚሉት ኹለት ጉዳዮች ዙሪያ ነገሮችን ማጤን ተገቢ ነው።

የምርጫው ውጤት
የምርጫው የመጀመሪያው ውጤት መስከረም 1/2013 ይፋ ሆነ። በርካታ የመገናኛ ብዙኀን ሰዎች፣ የምርጫ ኮሚሽኑ አባላትና የተጋበዙ እንግዶች በተገኙት ቦታ ውጤቱ የቀረበው በአንዲት ወይዘሮ አንባቢነት ነው። ወይዘሮዋ መረጋጋት ርቋቸውና ተደነጋግረው ነበረ። ንባባቸውም የተወለካከፈና የተቆራረጠ ነበር።
ወይዘሮዋ ሕወሐት ድምጽ ከሰጡት ከ2.6 ሚሊዮን መራጮች ውስጥ 98.2% ወይም 2,590,620 ድምጽ አግኝቶ በምርጫ (በአብላጫ ድምጽ የሚገኘውን) 152 ወንበር በሙሉ ማሸነፉን ሲናገሩ፣ የጥቂት ሰዎች እጅ የፈጠረው የተንጠባጠበ ጅምር ጭብጨባ ተሰማና ጸጥታ ሰፈነ። የፌዴራሊስቱ ሕወሐት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲህ ይሆናል ብሎ ማን ይጠብቃል!

ወይዘሮዋ እየተርበተበቱ የምርጫ ውጤት የተባለውን ማንበባቸውን ቀጥለዋል። ባይቶና- ኣባይ ትግራይ 0.8% ወይም 20,839.5፣ ው.ና.ት. 0.71% ወይም 18,479፣ ሳልሳይ ወያነ 0.275% ወይም 7,136.75፣ ዓዴፓ 0.01.% ወይም 774 ማግኘታቸው ተነበበ። ስለዚህ 152 በአብላጫ ድምጽ የሚገኙ ወንበሮችን ሙሉ በሙሉ የወሰደው ሕወሐት ለተመጣጣኝ ውክልና ከተዘጋጁት 38 ወንበሮች 37ቱን መቆጣጠሩና ቀሪውን አንድ ወንበር በባይቶና መወሰዱ በወይዘሮዋ ንባብ ተገለጸ። በጠቅላላ ከትግራይ ክልል ምክር ቤት 190 ወንበሮች ሕወሐት 189 ወረሰ ማለት ነው።

በዚህ የምርጫ መግለጫ ወቅት የጀመረው ጸጥታ ለቀናት ቀጠለ። በእርግጥ በሕወሐት፣ በተቃዋሚዎቹና በእረፍት የለሾቹ በዲጂታል ወያኔወች ሰፈር የሰፈነው ጸጥታ ከባድ ነበር። የማሕበራዊ ሚዲያ አርበኞቹ ዲጂታል ወያኔዎች ስለምርጫው ትንፍሽ የሚሉት በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በምርጫው ውጤት የሚያሾፍ ሰዎች ሲገኙ ብቻ ነው። ትግራይ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ፣ ድምጺ ወያነ ቴሌቪዥንና ራዲዮ፣ ትግራይ ሚዲያ ሃውስ፣ ኢትዮ-ፎረም፣ አውሎ ሚዲያ፣ አውራ አምባ ታይምስ፣ ሰሜን ሚዲያ፣ ራራ ሚዲያና እና ሌሎችም የሕወሐት ቃል አቀባይ ወይም የሕወሐት ደጋፊ ወይም የሕወሐት ተደጓሚ ሚዲያዎችም ውጤቱን ከማወጅ አልፈው ዝምታቸውን መስበር ሳይችሉ ቀናትን አሳልፈዋል።

መስከረም 5/2013 አውሎ ሚዲያ ሣልሳይ ወያነ ቅሬታ ማሰማቱን ተከትሎ ከፓርቲው መሪ ጋር ቃለ ምልልስ ከማድረጉና ትግራይ ሚዲያ ሃውስ በትግራይ የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎችን ተመርኩዞ መስከረም 6/2013 ምርጫው ምን ይናገራል የሚል የጋዜጠኞች ውይይት አካሂዷል። ከዚህ ውጭ ውጤቱን በሚመለከት ትንተና ለመሥራት ወይም ሰፊ አስተያየት ለመስጠት የሞከረ ወይም ይህን የሚያደርግ እንግዳ የጋበዘ ሚዲያ የለም። አክቲቪስቶች፣ ችኩሎቹ የመቀሌ ዩንቨርሲቲ ምሁራን፣ የፌዴራሊዝም ተንታኞች ወዘተ… ካደፈጡበት ሳይወጡ ቀናት ተቆጠሩ።

ቆየት ብሎ ደግሞ ትግራይ ሚድያ ሃውስ ድምጹን አሰምቷል። ተደርጎ በማያውቅ መልኩም ሚድያው ምርጫው አሳፋሪና ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲ እንደሌለ ማሳያ ነው ሲል በግልጽ ኮንኗል። ይህንን ችግር የፈጠረውም ከላይ እስከ ታች የተጠረነፈ አደረጃጀት ነው ያለ ሲሆን፣ ይህ አካሄድ ለወደፊትም የዴሞክራሲ ጸር ስለሆነ የክልሉ መንግሥት ይህን ካላስተካከለ እስከመቼውም በክልሉ ዴሞክራሲ አያብብም ሲል ሚድያው ስጋቱንም በግልጽ አስቀምጧል። እንደውም ይህ ውጤት በአማራ ወይም በኦሮሞያ ቢከሰት አገር ይደባለቅና ብዙዎችም ይቃወሙ እንደነበር በማንሳት፣ በትግራይ ክልል ግን ሕዝቡ በጥርናፍ በመያዙ ያ ሳይሆን ቀርቷል ብሏል።

ከዚህ ባለፈ ከተቃዋሚዎች መካከል ከምርጫው በኋላ መስከረም 2/2013 በማሕበራዊ ሚዲያው ላይ መልዕክት ያስቀመጠው ባይቶና ብቻ ነው። መልዕክቱም የኖርዘርን ስታር ሆቴል ባለቤት የአንድ ሚሊዮን ብር፣ ነጋዴዎች ደግሞ የባይቶና ዓርማ ምስል ያረፈበት የሰዓት ስጦታ ስላበረከቱለት ምስጋና ያቀረበበት ነው። ስጦታው የዴሞክራሲን ማቆጥቆጥ ያሳያል ብሏል፤ ባይቶና። የሰዓት ሽልማቱም ሆነ የባለሃብቱ የአንድ ሚሊዮን ብር የገንዘብ ስጦታ ሕወሐትን ጨምሮ በምርጫው ለተወዳደሩ ክልላዊ ፓርቲዎች ሁሉ የደረሰ ሲሆን፣ አካባቢያዊ ፓርቲ ለሆነው ለዓዴፓ ወደ ሩብ ሚሊዮን ብር መስጠታቸው ተነግሯል።

መልሶም በሳምንቱ ማጠናቀቂያ ሐሙስ እለት መስከረም 7/2013 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያገኘውን አንድ ወንበር ሊረከብበት የሚያስችል የሕገ አግባብ አለመኖሩ ገልጿል። ከዛ ውጭም በምርጫው ሂደት በርካታ ሕገ-ወጥ ተግባራት መፈፀማቸውን ጠቅሶ እንዳወገዘ የጀርመን ድምጽ ራድዮን ጣቢያ ዘግቧል።
ወደኋላ መለስ ስንል፤ የምርጫው ማግስት አርብ እንቁጣጣሽ መሆኑ፣ ቀጣዩ ቀን ቅዳሜ ለበዓሉ የታሰበው ዝግጅት ሁሉ የሚተገበርበትና የእንቁጣጣሽን ድባብ የተሸከመ እርድ የሚካሄድበት ዕለት ስለነበረ ለዝምታቸው ሽፋን ሆኖላቸዋል። ከዚያ በኋላ ያሉት ቀናት ግን ማፈራቸው የተጋለጠባቸው ቀናት ሆነዋል። በብዙዎች ዘንድ ሕወሐት ጥቂት ወንበሮችን ለተቃዋሚወች እንደሚሰጥ ወይም ተቃዋሚወች ጥቂት ወንበሮችን እንደሚይዙ ምንም ጥርጣሬ አልነበረም። ይህ አለመሆኑ አስደንጋጭ ነበረ።

ይህ የዴሞክራሲ ልምምድን ሳይሆን ቀድሞ ‹ስዩመ እንግዚአብሔር ናቸው› ለሚባሉት ነገሥታት ‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ› የሚለው አመለካከት በትግራይ ለሕወሐት ይሠራ ዘንድ በሰፊው መሠራቱን የሚያሳይ ነው። ሕወሐት ከትግራይ ሕዝብ ጋር ያለው ቁርኝት ኦሕዴድ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር፣ ብአዴን ከአማራ ሕዝብ ጋር እንዳላቸው ዓይነት አለመሆኑን ግልጽ ቢሆንም፣ ሕወሐት ይህን ግንኙነት ዴሞክራሲያዊ አመለካከትን በሕዝቡ ዘንድ ለማበልጸግ ከመሥራት ይልቅ በተቃራኒው ወደ ዘላለማዊ የአምላኪና ተመላኪ ዝምድና መውሰዱ ምርጫዎችን የተለመዱ የይስሙላ ጨዋታዎች አድጓቸዋል።

ምርጫው ከተካሄደ በአራተኛው ቀን ሣልሳይ ወያነ መገናኛ ብዙኀን ጠርቶ ቅሬታውን አሰምቷል። የተለመዱት በምርጫ ቅስቀሳ ቀናትና በምርጫ ዕለት የሚከሰቱ ችግሮች በትግራዩ ክልላዊ ምርጫም መደገማቸውን አሳውቆ ቅሬታውን የገለጸ ሲሆን፣ ስህተቱ ለወደፊት መታረም አለበት ብሏል። ሣልሳይ ወያነ ሕወሐት በምርጫው እንዳሻው አድርጓል ብሏል። ተመሳሳይ ቅሬታ በው.ና.ት. በኩል በጓዳ ተሰምቷል። በጠቅላላው ግን ለምርጫው ፈጥረውት ከነበረው ግርግር አንጻር ከሣልሳይ ወያነ ውጭ ያሉት ቡድኖች የዝምታ ጾማቸውን አልፈቱም።

ምክትል ፕሬዘደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ‹‹በምርጫው እናሸንፋለን ብለን አልገመትንም ነበር።›› ሲሉ መሰማታቸው ብዙዎችን አስገርሟል። ይህ የምክትል ፕሬዘደንቱ ስጋት ወይም ስሜት በብዙዎቹ የሕወሐት ካድሬዎች ልብ ሲብላላ የቆየ ከሆነ ከከተሞች እስከ ወረዳዎች፣ ከቀበሌዎች እስከ ገበሬ መንደሮች ውስጥ በሚርመሰመሱት ልማደኛ የሕወሐት ካድሬዎች ምን ተሠርቶ ይሆን ብሎ ለመጠየቅ በር የሚከፍት ነው።

በትግራይ ዝምታ ውስጥ የሕወሐት ካድሬዎች ሥራቸውን ቀጥለዋል። ምርጫውን ተከትሎ በኩሃና በአንዳንድ ትንንሽ ከተሞች የጀመረው ከዚያም በበርካታ የትግራይ ከተሞች የቀጠለው የድጋፍ ሰልፍ መስከረም 6/2013 በመቀሌ በተካሄደው ትልቅ ሰልፍ ተደምድሟል። ኮቪድ-19 ከምድር ገጽ የጠፋ ይመስል የጥንቃቄ እርምጃዎች ሁሉ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ተዘንግተው፣ ጭፈራና ፉከራ ሞልቶባቸው የተካሄዱት ሰልፎቹ ሕወሐት በሕዝብ መመረጡን የመሰከሩ አጋጣሚዎች ናቸው እየተባሉ ነው።
የሰልፎቹ ዓላማ ሕወሐት መመረጡን መደገፍና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን መቃወም ነው። በሰልፎቹ ላይ የምርጫው ውጤት ትግራይ በባንዳዎች ለመገዛት የማትፈልግ መሆኗን ያሳየ ነው የሚል መፈክር ተስተጋብቷል። በመቀሌው ሰልፍ ላይ የተገኙት ምክትል ፕሬዘደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ‹‹ምርጫው የትግራይ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱን ለዓለም ያስመሰከረበት ታሪካዊ ምርጫ ነው።›› ካሉ በኋላ፣ ለሰፊና አሳታፊ አገር አቀፍ ውይይት ጥሪ አድርገው ጣታቸውን በትግራይ ላይ የሚቀስሩ ላሏቸው የጦርነት የመሰለ ማስጠንቀቂያ ሰንዝረዋል።

ይህ የምርጫ ውጤት ሕወሐትን የዴሞክራሲና የፌዴራሊዝም ጠበቃ አድርገው ለሚመለከቱ ወገኖች ሁሉ ሊያስተላልፈው የሚገባ መልዕክት አለ። ከውጭ አገራት ይሁን ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እየተነሱ፣ በአካልም ሆነ በመንፈስ ወደ መቀሌ እየተጓዙ፣ ስለ ፌዴራሊዝምና ስለ ዴሞክራሲ የሕወሐትን ሌክቸር የሚጋቱ፣ ዴሞክራሲንና ፌዴራሊዝም ለማራመድ በሚል ሽፋን ይሁን በሚል እምነት ከሕወሐት የቤት ሥራ እየተቀበሉ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመወሰድ የሚሞክሩ ወገኖች ሕዝብን እና አገርን ወደተለመደው አፈናና አምባገነናዊ አካሄድ ለመመለስ አጫፋሪዎች እየሆኑ መሆኑን የዚህ ምርጫ ውጤት ሊነግራቸው ይገባል።

ላለፉት 27 የሕወሐት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ችግሮችን ረስተውና ሕወሐትን ከደሙ ንጹሕ አስመስለው የሚሯሯጡ ቡድኖችና ግለሰቦች በጳጉሜ 4/2013 የታየውን ዓይነት ዴሞክራሲንና ፌዴራሊዝምን ለሕዝባቸው ለማሸከም የሚጥሩ ናቸውና ራሳቸውን ሊመረምሩ የሚገባበት ጊዜ አሁን ነው። ለሕወሐት ዴሞክራሲ ማለት በየአምስት ዓመቱ መቶ-በመቶ እየደፈኑ የምርጫ ሂሳብን መዝጋት ነው። ለሕወሐት ፌደራሊዝም ማለት በክልል ደረጃ አሃዳዊና አምባገነናዊ ስርዓትን መትከል ማለት ነው።

ብልጽግናዎች አፈናና አምባገነንነትን በአዲሰ መልክ ለማስፈን ከመውተርተር አልፈው ስኬታማ እመቃዎችን እያደረጉ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ ለየትኛውም ሕዝብ ከአዲሱ የብልጽግናዎች አምባገነንነት ከለመድነው የሕወሐቶች አምባገነንነት የቱ ይሻላል የሚል አማራጭ ሊቀርብለት አይገባም። ተገቢው ወደ ዴሞክራሲ መሄጃ መንገድ ለሕወሐት/ኢሕአዴግ የተካሄደው ሰላማዊና ሕዝባዊ ፍልሚያ በብልጽግና ላይም መድገም ነው።

የጳጉሜ 4/2012 ምርጫ ለትግራይ ሕዝብ ስለ ሕወሐት ሃቁንና ቁርጡን ነግሮታል። ቀጣዩና በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የሚካሄድ ምርጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ብልጽግና ተመሳሳዩን መልዕክት የሚያሳውቅ እንዳይሆን መሥራት ይገባል።

ግዛቸው አበበ በሙያቸው መምህር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ላይ ሊገኙ ይችላሉ፤

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here