የኦሮሚያ ክልል የኃይል አቅርቦት በማቋረጡ ምክንያት በአዲስ አበባ የሚገኘው የቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች የውሀ አገልግሎት ካጡ ከአንድ ወር በላይ አልፏቸዋል።
የኦሮሚያ ክልል የኃይል አቅርቦቱን በክልሉ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ሙሉ በሙሉ በመስጠቱ ምከንያት ከዚህ ቀደም ውሃ ያገኝ የነበረው ቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም የውሀ አገልግሎት ካጣ ከአንድ ወር በላይ እንዳለፋቸው እና ክፍለ ከተማውን ቢጠይቁም ከአቅም በላይ ነው በማለት ምላሽ አለማግኘታቸውን ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
የቦሌን ክፍለ ከተማ በተደጋጋሚ አነጋግረናል የሚሉት ነዋሪዎቹ ሰሚትን ጨምሮ ቦሌ አራብሳ አካባቢ ያለው የውሃ አቅርቦት የሚመጣው የተቆፈሩት ጉድጓዶቹ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው፤ ስለዚህም ኦሮሚያ ውስጥ ያለው መብራት ኃይል አገልግሎት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ላሉ ፋብሪካዎች አብዛኛውን የመብራት ሀይል መስጠት በመጀመሩ ፤ ለውሃ የሚሆነውን የኃይል አቅርቦት እራሳችሁ መፍትሄ ፈልጉ በማለት ተናግረዋል ሲሉ የቦሌ ክፍለ ከተማ ውሃ ልማት ፅሕፈት ቤት እንደነገሯቸው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ከኹለተኛ ፎቅ በላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች ጭራሽ ውሃ የማግኘታቸው ነገር የማይታሰብ ነው በማለት የሚገልፁት ነዋሪዎች ከዚህ በፊት በተወሰኑ ቀናት በጀነሬተር ለሰላሳ ደቂቃ ብቻ ሲለቀቅ አንደኛ እና ኹለተኛ ፎቅ ብቻ ያሉት ጋር እንደሚደርስ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከሆነ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ታስቦ ቦሌ አራብሳ ውስጥ ለሚገኙ ለተወሰኑ አካባቢዎች በጀነሬተር ውሃ ለማዳረስ እየተሞከረ ቢሆንም ከአቅም በላይ ሆኖብናል በማለት እንደነገሯቸውም ተናግረዋል። ይሄንን ችግራቹን ምክንያት በማድረግ ከምናዳርሳቸው አካባቢዎች ጋር ተራ በማውጣት በሳምንት አንድ ጊዜ እንዲደርሳችሁ ለማድረግ እንሞክራለን ብለዋልም ሲሉ አንስተዋል።
ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖብናል የሚሉት ነዋሪዎቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ውሃ እና ፍሳሽ ሄደን መፍትሄ ስናጣ የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት እንሂድ እና እናመልክት ብለን ስንጠይቅ ከዛም ምንም አይነት ምላሽ ልታገኙ አትችሉም ከአቅም በላይ ነው ችግራችሁ እንደተባሉ ጠቁመዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ውሃ ለማግኘት እየሞከርን ያለነው ራቅ ካለ ቦታ በጋሪ ከሚያመጡ ሰዎች ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ ፤ ለአንድ 25 ሊትር ጀሪካን ከ አራተኛ ፎቅ በላይ ለማውጣት 30 ብር እየከፈሉ እንደሚገኙም አዲስ ማለዳ ታዝባለች።
በቀን እስከ መቶ ሃምሳ ብር ለውሃ የሚወጣበት ጊዜ አለ ይላሉ።ከዛም ባለፈ ኮንዶሚኒየም ላይ ካለ ውሃ ማሰብ ከባድ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ ለምን ያህል ጊዜ ደግሞ ይሄ ችግር ላይፈታ እንደሚችል ስለማይታወቅ የበለጠ ከባድ ሆኖብናል ብለዋል።
የአራብሳ ኮንዶሚኒየም አጠቃላይ በሚባል ሁኔታ ባለ ሰባት ፎቅ እንደመሆኑ አጠቃላይ ከታች ያሉት ቤቶች የንግድ መሆናቸውን አንስተዋል። በዚህም ካለ ውሃ ስራቸውን ማከናወን ስለማይችሉ ( 120 ሊትር ጀሪካን ) 120 ብር ለማውጫው ደግሞ ከ120 ብር በላይ ይጠይቃሉ። ለአንድ ታንከር 1500 ብር እየገዙ እየተጠቀሙ መሆኑን ጠቁመዋል።ስለዚህም ከውሃ እጦቱ ባለፈ ከአቅም በላይ ለሆነ ወጪ እየተዳረግን ነው በማለት ጠቁመዋል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለ ስልጣን መስርያ ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ሰርካለም ጌታቸው ለአዲስ ማላዳ እንደተናገሩት ከሆነ በኃይል ማነስ ምክንያት ችግሩ እየተፈጠረ መሆኑን እና አሁን ግን ችግሩ እንዴት ይፈታ በሚለው ላይ ከመብራት ኃይል ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራን ነው ብለዋል።
በቅርብ ቀን ቦሌ አራባሳ ኮንዶሚኒየም የሚገኙ አካባቢዎች በፈረቃ ውሃ ተደራሽ የሚሆኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013



