የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ከብሄራዊ ባንክ ወጥቶ ለብቻው እንዲቋቋም ተጠየቀ

0
655

የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ከብሄራዊ ባንክ ወጥቶ ለብቻው እንዲቋቋም በብሄራዊ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ከፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በቅርቡ በተደረገ ውይይት ላይ ተጠየቀ።

ከብሄራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ጋር በጷግሜ 4/ 2012 በተደረገው ውይይት ላይ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ከብሄራዊ ባንክ ወጥቶ ለብቻው እንዲቋቋም ጥያቄን ያቀረቡት በአገራችን የኢንሹራንስ ዘርፍ ላይ የረጅም አመታትን ልምድ ያካበቱና በአሁኑ ወቅት የህብረት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የህብረት ኢንሹራንስ የቴክኒክና ግንኙነት አማካሪ የሆኑት እየሱስወርቅ ዛፉ ናቸው።

በውይይቱ ላይም ለባንክ ተቋማት እየተሰጠ ያለውን ትኩረት ያህል ለኢንሹራንስ ተቋማት እየተሰጠ አይደለም ያሉት እየሱስወርቅ ይህም ለኢንሹራንስ ዘርፉ እድገት መቀጨጭ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል። የኢንሹራንስ ተቋማቱ እንዲስፋፉና እራሣቸውን ችለው እንዲቆሙም ከተፈለገ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ከብሄራዊ ባንክ ወጥቶ ለብቻው እንዲቋቋም ይገባል ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል።

በአለም ደረጃ ካለው የሌሎች አገሮች ውጤታማ ልምድ በማንሳት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት እየሱስወርቅ ዛፉ በጣም ጥቂት በሆኑ አገራት ብቻ ኢንሹራንስ በማእከላዊ ባንክ ሱፕርቫይዝ እንደሚደረግ አንስተው በአብዛኛው አለም ኢንሹራንስ ራሱን የቻለ ሱፐርቪዥን እንደሚቋቋምለትም ገልፀዋል። ብዙ ጊዜ ኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ኮሚሽን፣ ኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ኤጀንሲ ወይንም ደግሞ ኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ባለስልጣን ተብሎ እንዲቋቋም ይደረጋል። በእኛም አገር ተመሳሳይ ገለልተኛ ተቋም ተቋቁሞ ብሄራዊ ባንክ ግን የቦርዱ ሰብሳቢ ሊሆን ይችላል። ተቋሙን የሚያስተዳድረው ቦርድ ከኢንሹራንስ ማህበሩ ያሉ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች የሚወከሉበት ሊሆን ይችላል ነገር ግን ተቋሙ እራሱን ችሎ የሚቋቋምና የሚሰራ ነው መሆን የሚገባው ሲሉም እየሱስወርቅ አስረድተዋል።

የብሄራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴም ጥያቄው በተነሳበት መድረክ ላይ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ከብሄራዊ ባንክ ወጥቶ ለብቻው ይቋቋም አይቋቋም የሚለው በጥናት መታየት አለበት ያሉ ሲሆን ይህም ለብሄራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ማህበራት በተደጋጋሚ ለሚያነሱት ለዚህ ጥያቄ የተሰጠ የመጀመሪያው አዎንታዊ መልስ ነው።
ይናገር እንዳሉትም ጥናቱ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ የቀጨጨው በብሄራዊ ባንክ ቁጥጥር ስር በመሆኑ ነው ወይንስ በሌላ ምክንያት የሚለውን መመለስ አለበት ብለዋል። ዋናው የትኛውን መንገድ ብንጠቀም ለዘርፉና ለአገራችን ይጠቅማል የሚለውን ማየት ነው ስለዚህም በጥናት ከተለየ ምክክር ልናደርግ እንችላለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተውበታል።

ባንክና ኢንሹራንስ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ናቸው የሚሉት እየሱስወርቅ ብሔራዊ ባንክ ስለ ባንኮች ብዙ ያውቃል ስለኢንሹራንስ ግን ምንም አያውቅም። ስለዚህም ልምድ እና እውቀቱ በሌለው ዘርፍ ላይ ዝም ብሎ አለቃ መሆን አይጠቅምም ሲሉ ይናገራሉ። ኢንሹራንስ ማደግ በሚገባው ደረጃ እያደገ አይደለም እጅግ የጫጨና አቅመ ቢስ የሆነ ተቋም ነው አሁን ያለን፤ ይህ ግን ሊሆን አይገባውም በማለትም ይገልፃሉ።

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማህበር ብሄራዊ ባንክ በማያውቀው ነገር ውስጥ ነው ያለውና እባካችሁ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ለብቻው አቋቁሙልን እያለ ሲጠይቅ ረጅም አመታት አስቆጥሯል። ይሄ ስራ ከብሄራዊ ባንክ ውጪ በሆነ ተቋም እንዲካሄድ በፅሁፍም ጠይቀዋል በተጨማሪም ከውጪ አገር አጥኚዎችም በተደጋጋሚ መጥተው አጥንተው ይሄንኑ አመላክተዋል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ አልተፈፀመም። አሁን ግን ጊዜው ደርሷል መፈፀም አለበት በማለት የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አጥብቆ እየጠየቀ ነው ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መድህን ሰጪዎች ማህበር ይሄን ጥያቄ ለብሄራዊ ባንክ በይፋ አቅርቧል ታይቶ ቀና ምላሽ ይሰጠናል ብለን እየጠበቅን ነው ያለነው የሚሉት ደግሞ የኒያላ ኢሹራንስ ዋና ስራ አስፈፃሚና የኢትዮጵያ መድህን ሰጪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ያሬድ ሞላ ናቸው። ያሬድ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከብሄራዊ ባንክ የመውጣት ያለመውጣት ጉዳይ ሳይሆን የኢንሹራንስ ኮሚሽን እራሱን የቻለ ተቋም ነው መሆን የሚገባው።

ኢንሹራንስ ብዙ ጉዳዮች ያሉት ዘርፍ ነው፤ አንደኛ ሌሎች አገራት የደረሱበት እና ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ የኢንሹራንስ አይነቶችን ቀርፆ በየጊዜው በስራ ላይ ማዋል እንዲሁም በሰው ኃይል በእውቀት የተሻለና የሌላው አለም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚያስችሉ የአቅም ማጎልበት ስራዎች ይሰራሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

ያሬድ አክለውም በሌሎች አገሮች ኢንሹራንስ እንዴት አደገ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ፤ የራሱ የሆነ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ኮሚሽን በማቋቋማቸው ነው። ይሄን የሚያቋቋመው መንግስት ነው መንግስት ቦርድ አቋቋሞ ቦርዱን ሊመራው ይችላል ግን ኮሚሽን ውስጥ በጣም ብቃት ያላቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ናቸው የሚቀጠሩት እዛ ውስጥ ኢንሹራንስ ከሚሰጡት ኩባንያዎች ብቃት የእነሱ በጣም የላቀ ነው። ያስተምሯቸዋል፣ ያሰለጥኗቸዋል አዳዲስ የኢንሹራንስ አይነቶችን እንዲያመጡ ያግዟቸዋል።

ብዙም ሳንርቅ የእነ ኬንያ፣ ታንዛንያ ኡጋንዳ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገራት በኢንሹራንስ ኮሚሽን በጣም ውጤታማ ለውጥን አምጥተዋል ሲሉ ያሬድ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here