በአዲስ አባባ በሦስት ዓመታት ውስጥ 15 የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች እና ዋሻዎች ይገነባሉ

0
552

በአዲስ አበባ ከተማ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ 15 የእግረኛ መሸጋገሪያ ድልድዮች እና አምስት የእግረኛ ዋሻዎችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል።

በቀለበት መንገዶች ላይ ይገነባሉ የተባሉት 9 ድልድዮች እና የእግረኛ መሻጋሪያ ዋሻዎች በአንድ ዓመት ከ9 ወር(21 ወር) ውስጥ ተገንብተው የሚጠናቀቁ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኃላፊ ኢንጅነር ጂረኛ ሂርፓ አስታውቀዋል።ኃላፊው አክለውም በቀላል ባቡር መስመር ላይ የሚገነቡት 5 ድልድይ እና 5 የመስመር መሻገሪያ ዋሻዎች በኹለት ዓመት ከአንድ ወር (25 ወራት) ጊዜ እንደሚፈጁ እቅድ ተይዟል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከተያዘው 2013 አስከ 2015 ድረስ ተግባራዊ የሚሆን “የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂክ የመተግበሪያ ዕቅድ” ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ አድርጓል።የድልድይ እና የእግረኛ መሻገሪያ ዋሻዎች ግንባታ ስራዎችም የዚሁ እቅድ አካል ናቸው ተብሏል።
አዲስ አበባ ትራንስፖርት ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከእግረኛ ድልድይ ግንባታዎች በተጨማሪ በቀጣይ ሶስት ዓመታት በተለዩ 210 ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ የእግረኛ መንገዶችን መሻሻልና 350 ኪሎ ሜትር የተሰሩ መንገዶችን ማሻሻያ እንደሚሰራ ተመላክቷል።

እንዲሁም በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ደህንነትን ማሻሻል አንዱ የሦስት ዓመት እቅድ ነው ተብሏል።በዚህም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት እና ማስተካካያ ስራዎችን መስራትና መንገዶችን ለሁሉም ጠቃሚ አንዲሆኑ መልሶ መስራት ሲሆኑ መንገዶች ለሁሉም አገልግሎት አንዲሰጡ ለማድረግ መልሶ ይሰራል ተብሏል። ከታሰቡት ማሻሻያዎች ውስጥ በለገሀር ቸርችል መንገድ ፒያሳ የጎዳና ላይ መከለያዎችን (streetscaping) ግንባታ ፕሮጀክት እና በፑሽኪን ፣ሜክሲኮ አደባባይ፣ ብሔራዊ ትያትር፣ ካሳንችስ፣ ኡራኤል መንገድ ዝርዝር ዲዛይን እና ግንባታ ይጀመራል የተባለ ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት እስከ ኹለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ በእቅዱ ተመላክቷል።

ኤጀንሲው ይፋ ያደረገው የሦስተ ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ለእግረኞች ምቹ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባለፈ የትራፊክ ህግ ተላልፈው የተገኙ እግረኞችን በቅጣት ለማረም ቅጣት መመሪያ እንደሚዘጋጅና ተግባራዊ አንደሚደረግ የኤጀንሲው ኃላፊ አመላክተዋል።የእግረኞች ቅጣት መመሪያ ለማዘጋጀትና ተግባራዊ ለማድረግ ኹለት ዓመት ከግማሽ እንደሚፈጅ ተገልጿል።

በተጨማሪም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የትራፊክ ደንብ ማሻሻያ ይደረጋል ተብሏል።በዚሁ መሰረት በደንብ 395/2009 ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና በማሻሻል ተፅዕኖ ፈጣሪ ቅጣት እንዲጸድቅ እና ሌሎች የህግ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

በከተማዋ በሦስት ዓመት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይፋ በተደረገው የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ደህንነት ስትራቴጂ ይፋ በተደረገበት ባሳለፍነው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አስተዳደሩ ለእቅዱ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት 17 ሺህ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል።ከእነዚህም ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ የተከሰተ አደጋ መሆኑን ኢንጅነር ጂረኛ አስታውሰዋል።በአዲስ አበባ በአማከኝ በቀን የአንድ ሰው ህይወት በትራፊክ አደጋ እንደሚያልፍ እና በቀን ሰባት የአካል ጉዳት አንደሚደርስ ኢንጅነሩ ጠቁመዋል።በኢትዮጵያ ባለፈው 2012 በጀት ዓመት 4 ሺ 133 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሞተዋል።አብዛኛዎቹ የሞቱት በአዲስ አበባ ነው።የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ በሰጠው መረጃ መሰረት በየዓመቱ የትራፊክ አደጋን በስድስት በመቶ እንዲቀንስ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ እና አፈጻጸሙም አመርቂ እንደሆነ መናገሩ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here