በብዙ ታዳጊ አገራት በተለይ በአፍሪካ ውስጥ የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነት እየተስፋፋ የመጣ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ከተሞች በተለይ በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ታዳጊ ወጣቶች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየጎዳናው ጨርቅን በጋዝና በማስቲሽ አርሰው አፍንጫቸው መሳብ የተለመደ ትዕይንት መሆኑ ዋል አደር ብሏል። የችግሩን የከፋ ደረጃ የሚያሳየው ተደብቆ የሚደረግ መሆኑ ቀርቶ በግልጽ በአደባባይ የሚደረግ መሆኑ ነው። በየትምህርት ቤቱና ዩንቨርሲቲው የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነት የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል።
ሩት ለገሰ (ስሟ ተቀይሯል) የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነው ጓደኛዋ የአደንዛዥ እፅን ያስሞከረቻት። ከዛ በኋላ ነው ሩት ከጫት በተጨማሪ ኮኬንና ሌሎች አደገኛ እፆችን መጠቀም የጀመረችው። ትምህርቷን እርግፍ አድርጋ በመተው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ኬታሚን የተባለውን መድኃኒት/ኬሚካል በመጠቀም ላይ ትገኛለች። ‹‹ስጠቀመው በጣም ደስ ይለኛል። ከዛ ውጪም ምንም ነገር የሚያስደስተኝ ነገር የለም። በየቀኑም ካልተጠቀምኩ አዝናለሁ፣ እናደዳለሁ›› ›› የምትለዋ ሩት ከ5 ዓመታት በፊት ትምህርቷን አቋርጣ ሥራ ሳትሠራ በቤተሰብ ድጋፍ እየኖረች ትገኛለች።
ጫት እና መሰል እፆችን በኢትዮጵያ በተለይ በወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ መጠቀም የተለመደ ቢሆንም ኮኬንና ኬታሚንን የመሳሰሉት ኬሚካሎችን/መድኃኒቶች መጠቀም ግን የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። ኬታሚን በሆስፒታሎችና በእንስሳት ሕክምና ማዕከላት ለማደንዘዣነት የሚያገለግል ኬሚካል ነው። አለአግባብ ይህንን መድኃኒት በሰው ላይ መጠቀም ስካር የሚመስል ሁነታን ያከትላል፣ ከዚያም ያደነዝዛል ሲበዛ ደግሞ ሞትን ሊያስከትለል ይችላል።
በአዲስ አበባ ሙሉ ከተማውን ያካተተ ጥናት ባይደረግም የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር በሺሕዎች እንደሚቆጠር ይገመታል። በኢትዮጵያ እንደነዚህ ዓይነት ማኅበራዊ ችግሮችን የማጥናት ኃላፊት የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴሩ መጤ ባሕሎችን የማጥናትና የመከታተል ኃላፊትም አለበት። የአዳዲስ ኬሚካሎች ተጠቃሚነት ከነዚህ መካከል የሚመደብ ሲሆን ከአራት ዓመታት በፊት ሚኒስቴሩ በመጤ ከሚባሉ ባሕሎች ላይ በሠራው ጥናት ከተሳተፉት 1800 ሰዎች 1692 የሆነ ዓይነት አደንዛዥ እፅ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።
የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባሕል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ግዛቸው ኪዳኔ መጤ ባሕሎችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ይመራሉ።: ‹‹በእርግጥ ትክክለኛውን ቁጥር መናገር ያስቸግራል። የገንዘብ ድጋፍ ስላጠረን ሰፊ ጥናት ማድረግ አልቻልንም። ከዚህ በፊት የተደረገው ጥናት ጥቂት ሰዎችን የሸፈነ ነበረ። ይሁንና ችግሩን እናውቀዋለን። ለመከላከልም ጥረት እያደረግን ነው›› ብለዋል።
ዓለም ዐቀፋዊ ግንኙነት መጨመር በየአገራቱ ለመጤ ባሕሎች መስፋፋት ተጽእኖ አድርጓል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሩትን የያዛት ዓይነት ሱስ ሰበብ አዳዲስ ኬሚካሎች/መድኃኒቶች በሕጋዊ እና በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር እየገቡ መሆናቸውና በቀላሉ መገኘታቸው ነው።
ኬታሚን የተባለው ኬሚካል ሕጋዊ የሕክምና መድኃኒት/ኬሚካል ቢሆንም ኮኬንን የመሳሰሉት እፆች ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ አልፈው ወደ ሌላው የዓለም ክፍል ጭምር የሚሰራጩ ናቸው። ከአፍጋኒስታን የሚመጣው ኦፒየም ወደ አውሮፓ ሳይሄድ በኬንያ ሞምባሳ ወደብ አልፎ ወደ ተለያዩ አፍሪካ አገራት ይገባል። ከዛ ሕገ ወጥ መንገድ ተደርጎ ወደ መድረሻው ይወሰዳል። በዚህ መካከል አስተላለፊ በሆኑት አፍሪካ አገራት ውስጥ ያሉ ሰዎች የሱስ ተጋላጫነታቸውን ጨምሮታል። የኬንያ ፀረ አልኮልና እፅ ብሔራዊ ንቅናቄ እ.አ.አ በ2017 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በኬንያ ውስጥ ቢያንስ 4 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች አደንዛዥ እፅን እንደሚጠቀሙ ያመለክታል።
የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነት ዓለም ዐቀፍ ችግር ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ችግሩ ኢትዮጵያ ውስጥ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ መድረሱ ይታመናል። በዮኒቨርሲቲ ደረጃ ያለውን ችግር እንደማሳያ መጥቀስም ይቻላል። ‹‹ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተማሪዎች ከመጠን በላይ በወሰዱት አደንዛዥ እፅ ምክንያት ክፍል ውስጥ ሲወድቁ አይቻለሁ። በቅርብ ወደሚገኝ ሆስፒታል ወስደንም አሳክመናቸዋል›› ብሎ አንድ የሁለተኛ ዓመት በአንድ የግል ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። በትምህርት ሕይወቱ ብዙ ጓደኞቹም በሱስ ሲጠመዱ አይቷል።
ካሌብም አስቻለው (ስሙ ተቀይሯል) ኮኬንና ኬታሚን መጠቀም የጀመረው ልክ እንደ ሩት እሱም ተማሪነት ወቅት ሲሆን ጓደኞቹ እንዳስለመዱት ይጠቅሳል። ይሁንና ካሌን እንደ ብዙዎቹ በሱስ ተዘፍቆ አልቆየም፤ እራሱን ከሱስ አላቆ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ከሱሰኝነት በሽታ ለመዳን መፍትሔ ተደርጎ በብዙ የኅብረተሰብ ክፍል ሕክምና ከመከታተል ይልቅ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መፍትሔ ላይ ትኩረት ስለሚደረግ ሕክምና መከታተልን በተመለከተ በአመለካከት ላይ ሥራ መሥራት ይገባል። በእርግጥ ሃይማኖታዊው ከሱስ የመዳን መፍትሔ አንዱ አማራጭ ሲሆን አንዳንድ ኬሚካሎች በሰውነት ውስጥ በሚፈጥሩት ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ሕክምና መከታተልን አስፈላጊ ያደርጉታል።
የእፅ ሱሰኝነትን አስከፊ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ሰዎች ያላቸውን ችግር በግልጽ መናገር አለመቻላቸው እንደሆነ ይጠቀሳል። በብዙ የዓለም ክፍሎች የአደንዛዥ እጽ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ብዙ አይነት ችግር ይደርስባቸዋል። ኬሚካሎቹ የሚያደርሱት የጤና እክል እስከሞት ከማድረሱ ባሻገር ሱሰኞች ለድኅነትና ሥራ አጥነት ይዳረጋሉ። በተጨማሪም ግድያን ጨምሮ ለተለያዩ ወንጀል ያጋልጣል። የፊሊፒንሱ ፕሬዝደንት ሮድሪጎ ዱተርቴ በብዙዎች ያስወቀሳቸውን የአደንዛዥ እፅ ፖሊሲን ሲያተዋውቁ ብዙ ሰዎች በፖሊስና በገዛ ጎረቤቶቻቸው እንደተገደሉ ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ ሰዎችን ከሱስ ከማላቀቅ ይልቅ በመግደል አገራቸው ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት እንደሚሻል ማመናቸውን በብዙ መድረክ መናገራቸውም ይታወሳል። ‹ሒውማን ራይትስ ዋች› የተባለው የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዱተርቴ ፕርዝደንት ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በአደንዛዥ እፅ ፖሊሲያቸው ምክኒያት ቢያንስ 12000 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአደንዛዥ እፅ ሱሰኝንት ዙሪያ በሰፊው ጥናት ባይካሔድም ችግሩ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ በመሄዱ ወጣቱን ከዚህ ችግር ለማላቀቅ ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት ጠቋሚ ነው። ይህም ባለመደረጉ ምክንያት ሱሰነት ለማቆም የሚደረገው ተነሳሽነት ዝቅ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል። ሩትም ከሱስ ለመላቀቅ ከማይፈልጉት ውስጥ አንደኛዋ ናት። ‹‹ለምን ብዬ ነው የማቆመው? ደስ ብሎኝ ነው የምጠቀመው፤ አላቆምም!›› ብላ ፍርጥም ብላ ተናግራለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011