አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከምስረታው ጀምሮ ይጠቀምበት የ`ነበረውን ዋና መሥሪያ ቤት በከተማ አስተዳደሩ ትዕዛዝ ለመልቀቅ መገደዱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 በተለምዶ አንበሳ ጋራዥ በመባል የሚታወቀውን የድርጅቱን ዋና መስሪያ ቤት ለመልቀቅ የተገደደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦታው ለግንባታ ይፈለጋል ማለቱን ተከትሎ እንደሆነ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ስምሪት ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት መሪ የሆኑት መላኩ ካሳ ደስታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ ለ75 ዓመታት ሲሰራበት የነበረውን ዋና መስርያ ቤቱን እንዲለቅ በከተማ አስተዳደሩ ትዕዛዝ ከተሰጠው 7 ወራት ያለፉት ሲሆን ከሁለት ወር አስቀድሞ ቢሮውን በመቀየር በኪራይ በተለምዶው ኮከብ ህንፃ አዳራሽ በመባል የሚታወቀው ህንፃ ላይ መግባቱን መላኩ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
እርሳቸው ጨምረው እንዳነሱት ከሆነ ለዋናው መሥሪያ ቤት የኪራይ ወጪ ለሁለት አመታት ጊዜ እስከ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ተከፍሎላችኃል ከመባሉ ውጪ ስለ ዝርዝር በከተማ አስተዳደሩ እንዳልተገለፀላቸው አንስተዋል።
አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ለግንባታ ይፈለጋል ተብሎ የተወሰደበት ቦታ 97 ሺኅካሬ ሲሆን የከታማ አስተዳደሩም በዚህ ልክ የሚሆን ልዋጭ ቦታ አማካኝ የከተማው አካባቢ ፈልጎ እንደሚሰጣቸው ቃል መግባቱን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ቃል በተገባው መሰረት አስካሁን መልስ አልተሰጠንም ፤ድርጀቱም ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ቦታ እየተፈለገ ነው ከማለት ውጪ ተጨባጭ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን መላኩ ካሳ ደስታ የአንበሳ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ስምሪት ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት መሪ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ዋና መሥሪያ ቤቱን የለቀቅን ቢሆንም አውቶብሶቻችንን ግን አሁንም እያሳደርንባቸው ነው በማለት ጨምረው ተናግረዋል።
በተጨማሪ የስምሪት ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት መሪው እንዳነሱት አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ገርጂ ከሚገኘው ከዋናው መስሪያ ቤት ውጪ በሶስት ቦታዎች ላይ የስምሪት ቦታዎች እንዳሉት ገለፀው ፤ቃሊቲ ፣ሸጎሌ ፣እና መካኒሳ ( ዴፖ) መስሪያ ቤቶች ግን የስምሪት ቦታዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደሩን ለማነጋገር የመሬት አስተዳደር ዋና ሃላፊዋ ጋር ደውላ አዲስ ማለዳ ከምን ደረሰ ለማለት ብትሞክርም የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደሩን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊን አናግሩ ብለው ቢጠቁሙንም እርሳቸውም ፍቃደኛ አልሆኑም።
አንበሳ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ድርጅት አገልግሎቱን የጀመረው 1945 ሲሆን በአሁኑ ወቅት 4500 የሚጠጉ ሰራተኞችን በስሩ አያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን በአጠቃላይ 725 የሚጠጉ የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች ያሉት መሆናቸውን ገልፀዋል።ከእነዚህም ውስጥ ጥገና የሚያስፈልጋቸው 52 አውቶብሶች በብልሽት ምክንያት የቆሙ መሆኑን አንስተዋል።
ከእነዛ መሃል 22 የሚሆኑት ውጫዊ አካል (የቦዲ ) መስተካከል የሚያስፈልጋቸው ሲሆን የተቀሩት 30 ዎቹ ደግሞ የሞተር (መካኒካል) ጥገና እና መለዋወጫ የሚፈልጉ ናቸው ሲሉ መላኩ ካሳ ደስታ የአንበሳ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ስምሪት ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት መሪ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013



