ኢትዮ ተሌኮም የሞባይል ደንበኞቹ በተለያዩ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋበት ጊዜ ስልክ ቁጥራቸው ወዲያውኑ ባለማዘጋታቸው በሶስተኛ ወገን የቴሌኮም ማጭበርበር እየተከናወነብ ነው ሲል ለአዲስ ማለዳ በላከው ምግለጫ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ደንበኞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸው የተነሳ ወንጀለኞች የስልክ መስመሩን ለተለያዩ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች እየተጠቀሙበት ነውም ብሏል።
በዚህ ምክንያትም ኩባንያውን ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እየዳረጉ እንደሆነ አስታውቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2012 ብቻ በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የተፈጸመ ሲሆን በዚህም ኩባንያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ኪሳሬ እንደገጠመው አስታውቋል።
በመሆኑም ኩባንያው ደንበኞቹ በተለያየ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋባቸው ጊዜ ወደ ኩባንያው 994 የጥሪ ማዕከል በመደወል በ8994 አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ወይም ይፋዊ የማህበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም ወዲያውኑ መስመራቸውን እንዲያዘጉ አሳስቧል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013



