በቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ላይ በትብብር የሚሰራ የቅንጅት መድረክ ተመሰረተ

0
947

ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ዋና የቱሪዝም መዳረሻ አገር ለማድረግ ዓላማው ያደረገ በቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ላይ በትብብር የሚሰራ የቅንጅት መድረክ ተመሰረተ።

የቅንጅት መድረኩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ዲፕሎማሲና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ፂዮን ተክሉ ሰብሳቢነት የሚመራ ሲሆን የቱሪዝም ዘርፍ የቅንጅት መድረክ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ ተዋንያን የሆኑ ዘርፎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም መሰረት በቅንጅት መድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የሆቴሎች፣ የቱር ኦፕሬተሮች፣ አስጎብኚ ድርጀቶች፣ የሼፎች እና የቱሪዝም ማርኬቲንግ ማህበራት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በአባልነት እንዲካተቱ ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ስራውን ለማሳለጥ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት እንዲሁም የአገራችን የቱሪዝም መስህቦችን በተቀናጀ መንገድ ለማስተዋወቅ የሚረዳ ተጨማሪ የስቲሪንግና የቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሟል።

የቅንጅት ኮሚቴው የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራትና የስራ ድርሻ ላይ በመወያየት የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ስራውን ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት መስራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል።

በዚህም በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊያ እና ትውልድ ኢትዮጵያዊ የአገራችንን የቱሪስት መስህቦች በማስተዋወቅም ሆነ እራሱም አገሩን መጥቶ እንዲጎበኝ በዲያስፖራ ኤጀንሲ በኩል አስፈላጊው ስራ አንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በተጨማሪም በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ተዋንያን የሆኑ ዘርፎች የዓለም ጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ላይ እና 2013 የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ስትራቴጂ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በኮቪድ 19 ምክንያት በከፊል የተዘጋውን የአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ በመጪው ጥቅምት መጀመሪያ አካባቢ ለውጭ ቱሪስቶች ለመክፈት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሚዲያን ተጠቅመው የማስተዋወቅ ስራ ከወዲሁ መስራት እንደሚገባቸው ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅና መረጃ በማጠናቀር ተገቢው ስራ እንዲሰራ በቱሪዝም ኢትዮጵያ አስተባባሪነትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here