የመስቀል በዓል አከባበር – በዘመናት መካከል

0
2740

በኢትዮጵያ በባህል፣ በሀይማኖት ወይንም በሕግ ተደንግገው፤ የሚታወሱበት ቀን እና ጊዜ ተሰጥቷቸው የሚከበሩ የአደባባይ የአንድነት በዓላት ይገኛሉ። ከእነዚህ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ የአንድነት የአደባባይ በዓላት መካከል ደግሞ በወርሃ መስከረም የእንቁጣጣሽ በዓልን ተከትሎ በመስከረም 17 ተከብሮ የሚውለው የመስቀል በዓል አንዱ ነው። በመላው ኢትዮጵያም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምዕመናን በሚገኙበት ሁሉ በታላቅ ድምቀት፤ ሃይማኖታዊ ስርዓትን ጠብቆ ይከበራል።

ይህ ሀይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ አልፎም ለማኅበራዊ ትስስር ፋይዳ ያለው በዓል ለአገራችንም በቱሪስት መስህብነት ዘርፍ ከፍተኛ እውቅናን ማግኘቱም የሚታወስ ነው። በ2006 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስ መዝገብ ሰፍሯል።

የመስቀል በዓል ታሪካዊ ዳራ
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሚከበርበት ስነስርዓት ሁልጊዜ ተመሳሳይ ቢሆንም ነገር ግን የአከባበር ድምቀቱ እንደቦታና ወቅቱ የተለያየ ይዘት ይኖረዋል። በመስቀል በዓል እና የአከባበር ስነስርዓት ዙሪያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የመገናኛ ብዙኀን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መምህራን ፋንታሁን ሙጬ፣ አከባበሩ ኹለት መነሻ ሐሳብ እንዳለው አንስተዋል።

በዚህም መሠረት አንደኛው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንግሥት እሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ለማውጣት ያደረገችውን ጥረት እና በመጨረሻም መስቀሉ መገኘቱን በማስታወስ ነው። ኹለተኛው ደግሞ በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ክርስቶሰ የተሰቀለበትን ቀኝ ግማደ መስቀል እና የተለያዩ ነዋየ ቅዱሳት ከግብፅ አሌክሳንድሪያ ወደ ኢትዮጵያ በአፄ ዳዊት አማካኝነት መግባቱን በማስመልከት ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

‹‹ንግሥት እሌኒ የክርስቶስን መስቀል ለማግኘት ደመራ ደምራ ስለነበርና ጭሱም ወደታች ወርዶ መስቀሉ ያለበትን ስፍራ (የተቀበረበትን ተራራ) በማመልከቱ ያንን ቱባውንና የመጀመሪያውን ባህሪ መሰረት በማድረግ የመስቀል በዓል እለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በየዓመቱ ደመራ ትደምራለች። በተጨማሪም በአፄ ዳዊት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ቀኝ ግማደ መስቀሉን ለማስቀመጥ ልዩ ልዩ ጥረቶች ቢያደርጉም በመጨረሻም ‹መስቀሌን በመስቀልያ ስፍራ አስቀምጠው› የሚል መለኮታዊ ምሪትን በመስማታቸው ወደ ግሸን ማርያም ተወስዶ በዛ እንዲቀመጥ ተደርጓል። ስለዚህም በግሸን መስቀሉ በመቀመጡ መስከረም 21 ቀን ግሸን ማርያም ላይ ይከበራል።›› በማለት የመስቀል በዓል አከባበር ታሪካዊ ዳራ ያስረዳሉ።

በዓለም ላይ መስቀልን የሚያከብሩ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም በኢትዮጵያ ባለው ስርዓት ወይም ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ፈልጋ ባገኘችበት መንገድ የሚያከብር የለም። ይህንንም የጠቀሱት ሊቀመምህራን ፋንታሁን፣ ይሄ አከባበር በተለያዩ መንግሥታትና ነገሥታት ስር ፈተናዎች እየገጠሙትም ቢሆን እስካሁን ድረስ ወግና ስርዓቱን ጠብቆ ሲከበር መቆየቱን ይገልፃሉ።

የመስቀል ደመራ አበራር ስነስርዓቱ በአብዛኛው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በወሩ 17ኛ ቀን ወይንም የበዓሉ እለት የሚከናወን ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በ16 ደመራው ይበራል። በዓሉ ሲከበር ሀይማኖታዊውን ይዘት ጠብቆ እንዲሁም ከክረምት ጨለማ መገፈፍ እና ደፍርሶ ከነበረው ከውሀው መጥራት ጋር የመልካም ዘመን ተምሳሌትነት በማያያዝም ነው።

በመስቀል ደመራ እለት የሚከወኑ ሀይማኖታዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎችን ሊቀመምህራን ፋንታሁን ሲያስረዱ፣ ‹‹ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ የሠራቸው የተለያዩ ዜማዎች አሉ። ዜማዎቹ በካህናት አማካኝነት በተለያየ ሁኔታ ይቀርባሉ። በዓሉን የሚያስመለክተው ወረብ ይወረባል። የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ሊቃውንቱን ተከትለው እንደዚሁ ለእለቱ የሚገባውን ያሬዳዊ ዜማ ያቀርባሉ።›› ብለዋል።

አክለውም በተለይ በአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የማህበረ ቅዱሳን መዘምራን፣ መስማት የተሳናቸው በምልክት ቋንቋ እንዲሁም የፖሊስ ማርሽ ባንድ ዝማሬና ዜማዎችን እንደሚያቀርቡ ጠቅሰዋል። አባት አርበኞች በትርዒት ይሳተፋሉ። በመጨረሻም በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን አማካኝነት ንግሥት እሌኒ እንዴት አድርጋ መስቀሉን እንዳገኘችው የሚያሳይ ልዩ ትርዒት ያቀርባሉ።

የመስቀል በዓል አከባበር በየዘመንና መንግሥታቱ
የመስቀል ደመራ በዓል በአገራችን በድምቀት የአደባባይ በዓል ሆኖ መከበር የጀመረው በ1898 በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ነው። የበዓል ስነ ስርዓቱም በጃንሜዳ ከዛም ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን በስተደቡብ ወረድ ብሎ በሚገኘው ቦታ ላይ ይከናወን እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ።
ከዛም በማስከተል በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለመስቀል ደመራ ማክበሪያ ይሆን ዘንድ ከግል ርስታቸው በመክፈል አሁን መስቀል አደባባይ በመባል የሚጠራውን ስፍራ ሰጡ። በዛም ምክንያት ደመራው የሚበራበት አደባባይ ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ መስቀል አደባባይ ተዛወረ። በዚህም ስፍራ ላይ የጃንሆይ መንግሥት ውድቀት ድረስ ማለትም እስከ 1967 በዓሉ ይከበር ነበር።

‹‹የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ ቅርፁ የሚለወጥ አይደለም።›› የሚሉት ሊቀ መምህራን ፋንታሁን፣ ምንም የተለየ አመለካከት እና የተለየ እምነት ያለው መንግሥት ቢመጣ ሀይማኖታዊ ስርዓቱ የሚቀየር አለመሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹የሚለወጠው ምንድን ነው! ለምሳሌ በድሮ ዘመን ነገሥታቱ በበዓሉ ላይ ይገኙ ነበረ። በበዓሉ ላይ የሚቀር ንጉሥ አልነበረም። በተለየ ሁኔታ ነገሥታቱ ሲመጡ ክብሩም እጅግ የተለየ ነውና በዓሉም በተለየ ስሜት ይከበር ነበር። ነገሥታቱ ደግሞ ከበዓሉ በኋላ በማግስቱ ግብር ያገቡና ሕዝቡን ያበሉ ነበረ።›› ሲሉም የዘመናት እና በመንግሥታት መካከል ስለነበረው የበዓል አከባበር ስነስርዓት ያወሳሉ።

‹‹እኔ የማስታውሰው ልጅ ሆኜ ያሳለፍኩትና እስከ 1964 ወይ 1965 ድረስ ያለውን የመስቀል ደመራ አከባበር ነው። የዛን ጊዜ በዓሉ በከፍተኛ ድምቀት ይከበር ነበር።›› የሚለው ደግሞ ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ ነው። ዘነበ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ በመስቀል ደመራ አከባበር ስርአት ዙሪያ ያለውን ትውስታ እንዲህ ያጋራናል።

‹‹አዲስ አበባ አሁን መስቀል አደባባይ የሚባለው ያኔ እራስ ብሩ ሜዳ ነበር የሚባለው። እዛ ላይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ይመጡና ጀርባቸውን ለራስ ብሩ ቤት ሰጥተው ይቀመጣሉ። ሜዳው ላይ ደመራው ይደመራል። ደመራውም ተደምሮ ከመለኮሱ በፊት የሰልፍ ትርኢት ይታይ ነበር። ክቡር ዘበኛ፣ ፖሊስ ሰራዊት፣ የባህር ኃይል እንዲሁም የአየር ኃይል ሰልፈኞች ያልፋሉ። ሰዉ የዛን እለት ነጭ በነጭ የሆነ የበዓል ልብሱን ለብሶ በጣም ልዩ የሆነ ስነ ስርዓትን ለማክበር ነው የሚመጣው።
እኔ ያኔ ከአባቴ ጋር ነበር በዓሉን ለመታደም የምገኘው። አባቴን እንኮኮ አድርገኝ እለዋለሁ፤ እንደውም አባቴ እንኮኮ ያደረገኝን ጊዜ የማስታውሰው እዛ ጋር ነው። እንኮኮ ያደርገኛል። ከርቀት የማይታዩኝ ትዕይንቶች ምን ምን እንደሆኑም ይነግረኛል።›› በማለት በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረውን የመስቀል በዓል አከባበር ስነ ስርዓት ያስታውሳል።

‹‹ጃንሆይ ወደ ደመራ ማብሪያው ስፍራ ሲመጡ በጭብጨባ እና በእልልታ ምድር ነው የምትርደው…›› የሚለው ዘነበ፣ በበዓሉ እለት እንስሳት ሁሉ ለልዩ ትርኢት ይወጡ እንደነበር ያወሳል። ‹‹ጃንሆይ መኩሪያ የሚባል አንበሳ ነበራቸው። መኩሪያም እዚሁ የሰልፍ ትዕይንት ላይ በአንድ ግልፅ መኪና ላይ ሆኖ እንግዲህ ወይ ሰውየው ጎሸም አድርጎት ይሁን ወይንም ጃንሆይን አውቋቸው እንደሆነ ባላውቅም ግን ያጓራል። በዚህ መልኩ ሰልፉ በእሳቸው ፊት ካለፈ በኋላ ደመራው በቤተ ክህነት አባቶች ይባረክና የጸሎት ስነስርዕት ከተካሄደ በኋላ ይለኮሳል።

በዓሉም በእንዲህ አይነት መልኩ ደምቆ በአደባባዩ የተገኘውም ማኅበረሰብ አንዳች ረብሻና ችግረ ሳይፈጥር በስነ ስርዓት አክብሮ ወደ ቤቱ ይገባል። ይሄ 1965 አካባቢ የነበረ የበዓል አከባበር ነው። በኋላ ደግሞ የነበረው ችግር ይታወቃል። አብዮት ፈነዳ ብዙ መመሰቃቀል ተፈጠረ። እኔም ጎረመስኩና ከነጭራሹ መስቀል አደባባይ መሄድ አቆምኩኝ።›› ሲል የልጅነት ትውስታውን ያጋራል።

በ1967 ደርግ ወደ ሥልጣን ሲወጣ በጃንሆይ ዘመነ መንግሥት በዓሉ ይከናወንበት የነበረውን የመስቀል አደባባይ ሥያሜ ወደ አብዮት አደባባይነት ተቀየረ። የደመራው ሥርዓትም ከአደባባዩ ተነጥሎ ቀድሞ ይከበርበት ወደነበረው ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን እንዲመለስ ሆነ።

‹‹ከደርግ በኋላ ደመራ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ነበረ የሚከበረው።›› የሚለው ዘነበ፣ ‹‹በዛን ወቅት ጥቂት የቤተክርስትያን ከፍተኛ ኃላፊዎች በደመራው ስነ ስርዓት ላይ በመገኘት ደመራውን ይለኩሳሉ። ከዛ ጊዜ በኋላም ነው እንግዲህ ያ መስቀል አደባባይ በመባል የሚታወቀው ስፍራ አብዮት አደባባይ የሚል ሥያሜ የተሰጠው። ይህም ሕጋዊ ወይንም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣለት ሥም ሳይሆን ህብረተሰቡ አንዳንድ ድርጊት ሲካሄድበት በመመልከቱ አብዮት አደባባይ አለው።
በኋላ የደርግ ስርዓት ፈርሶ ኢሕአዲግ ሲመጣ እንደገና የቤተክርስትያን ሰዎች ደመራዉን ወደዚህ አመጡት። በደርግ ጊዜ የዳመራው ስነ ስርዓት ወደ ጊዮርጊስ ተዘዋውሮ ለአስራ ስድስት ወይንም አስራ ሰባት ዓመታት ከተከበረ በኋላ እንደገና ወደዚህ እንዲመለስ ተደረገ።›› በማለት በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረውን የመስቀል ደመራ አከባበር ሁኔታ ያስታውሳል።

ሊቀመምህራን ፋንታሁን በዚህ ላይ ሐሳብ አክለዋል። እንዲህም አሉ፤ ‹‹በተለየ ሁኔታ የኮሚኒዝም (ደርግ) ስርዓት ውስጥ ኮሚኒዝም በራሱ ፈጣሪን የመካድ እሳቤን ስለሚያራምድ፤ አይደለም በመሪ ደረጃ ሕዝቡም እራሱ ወደ አደባባይ መሄድ እንደ ነውር የሚቆጠር እና በመሥሪያ ቤትም እድገት የማያስገኝ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።››
‹‹ነገር ግን…›› ይላሉ ሊቀመምህራን፣ ‹‹ነገር ግን ሕዝቡ ከሌላው ጊዜ በበለጠ እንደውም ወደ መስቀል በዓልም ይሁን ወደ ቤተክርስትያን በተለየ ሁኔታ ይመጣ ነበር።›› በማለት እንደምሳሌ መርካቶ የሚገኘውና በተለምዶው አዲሱ ሚካኤል ተብሎ የሚጠራው የሚካኤል ካቴድራል ቤተክርስትያን የተሠራው በዛ ስርአት እና ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ያነሳሉ።

‹‹ሕዝቡ የበለጠ ወደ ሀይማኖቱ የመጣበት ወቅት ነበር። ነገር ግን በተነፃፃሪነት ሲታይ [የመስቀል ደመራ በዓል] እንደቀደመው ጊዜ በቤተመንግሥት ሰዎች የሚከበር አልነበረም። ከደርግ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ግን ሌላ አገራዊ አጀንዳን ካልያዙ በስተቀር ከንቲባዎች በተለይ አዲስ አበባ ላይ ይገኛሉ።›› ብለዋልም።
ታዲያ የመስቀል ደመራ በዓል እንዲህ እንዲህ እያለ በየዘመን እና መንግሥታቱ መከበሩን ቀጥሎ በግንቦት ወር 1983 ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር በዓሉ በጥንታዊ ይዞታው በመመለስ በአሁኑ መስቀል አደባባይ ተከብሯል። እስከ አሁንም በዚሁ ቦታ ላይ እየተከበረ ይገኛል።

‹‹አሁን አሁን በመስቀል ደመራ አከባበር ስነ ስርዓት ላይ ያለውን ተግዳሮት ከአዲስ አበባ ወጣ ብለን ስናየው፣ በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘቱን የማስለቀቅ ነው።›› የሚሉት ሊቀ መምህራን ፋንታሁን፣ የመስቀል በዓል በዩኔስኮ የተመዘገበው በባህላዊ ይዘቱ ሳይሆን በሀይማኖታዊ ይዘቱ ይልቁንም ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በአደባባይ ደመራ ለኩሶ እየዘመረ በማክበሩ መሆኑን ይገልፃሉ።

‹‹በኢትዮጵያ አብዛኞቹ በዓላት ከድግስ ጋር ተያይዘው የሚከበሩ ናቸው። ታዲያ ከድግስ ጋር ተያይዘው ተከበሩ ማለት ግን ሀይማኖታዊ ይዘታቸው ጠፍቶ ባህላዊ ይዘታቸው ጎልቶ ይታዩ ማለት አይደለም። መስቀል ሀይማኖታዊ ይዘት ነው ያለው፤ የክርስቶስ መስቀል በቁፋሮ ስለተገኘ እርሱን ለማመመልከት የሚከበር በዓል ነው።›› ሲሉም አሁን አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የበዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘት እየጠፋ ወደ ባህላዊ ይዘት ማዘንበሉን ያነሳሉ።

የመስቀል ደመራና ማኅበራዊ እሴቱ
‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እናት ናት። የሌለችበት ብሔር የለም። አጉልታም ሆነ አሳንሳ የምታሳየው ብሔር የለም። ሁሉም ልጆችዋ ናቸው።›› የሚሉት ሊቀመምህራን አያይዘውም ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘውና ወደ መስቀል አደባባይ የሚሄደውም ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ነው። በበዓል አከባበሩ ስነስርዓቱ ላይ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማሪያን ሲዘምሩ የተለያዩ ቋንቋዎችን አብረው ይዘምራሉ። ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጣው ሰው አንድ አይነት አላማ ይዞ ነው የሚመጣው፤ እሱም መስቀሉ ያስገኘልንን ሰላም ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ› በመስቀሉ ሰላምን አደረገ ነው ያለው። ስለዚህ ተጣልተው እና ተኮራርፈው የነበሩ አንድ የሚሆኑበት እርቅ የሚፈጥሩበት ነው።›› ብለዋል።

ምክንያቱ ደግሞ በመስቀሉ ነፍስና ስጋ፣ ሰው እና እግዚአብሔር፣ ሰው እና መልአክትም ታርቀዋልና ነው። እናም ክርስትና ‹ከእኔ በላይ ማንም የለም› ሳይሆን ለሌላው የሚኖር ኑሮ ነው ሲሉ አጽንዖት ይሰጣሉ። ‹‹ይህም ነው በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ ያለው።›› ሲሉ የበዓሉ መከበር ለሰዎች ሰላምና ፍቅር እንዲሁም ማኅበረሰባዊ ትስስር ያለውን ፋይዳ ይገልፃሉ።

በዓሉ ለማኅበራዊ ትስስር ትልቅ ፋዳ አለው የሚለው ዘነበ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ብዙ የኢትዮጵያዊ ነገሮች አስጠብቆ በማስቀጠል ተወዳዳሪ የሌላት መሆኗን ይገልፃል። ‹‹መጽሐፍቶቻችንን፣ ፊደላትን፣ ጥንታዊ ቅርሶችን ጠብቃልናለች። ኅብረተሰባችን የተጠቀማቸውን እቃዎች ሁሉ ጠብቃ በማቆየትም ሆነ የኢትዮጵያን አንድነት በመገንባት ትልቅ ሚና ነው ያላት።›› ብሏልም።

የመስቀል በዓልን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በጋራ የሚደሰቱባቸውን፣ ሰላምን የሚመኙባቸውን፣ ሩቅ መመልከት የሚያስችሉ ትልቅ በዓላትን የመሠረተችው ቤተክርስትያኒቱ መሆነኗን የሚጠቀሰው ዘነበ፣ ‹‹ይሄ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ብትችል እንደውም ወደፊት ደግሞ ቤተክርስቲያኒቷ በዘመናዊ መማር ማስተማር ውስጥ ተሳትፋ ልጆች ግብረገብን እንዲያውቁ እያደረገች ሳይንስና ቴክኖሎጂን ደግሞ ባህላቸው እንዲያደርጉ ብታደርግ ትልቅ አገር የመፍጠር እድል ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።›› ሲልም ሐሳቡን ይገልፃል።

የ2013 የመስቀል በዓል
የ2013 የመስቀል ደመራ በዓል በአገራችን ብሎም በዓለም የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ሲባል የታዳሚውን መጠን እንዲቀንስ ግድ ሆኗል። ይህንንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትሪያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤትና የውጪ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው። ይህም ቀድሞ የነበረውን የበዓል አከባበር ድምቀት እንደሚቀንሰው መገመት አያዳግትም።

ዘነበ በበኩሉ ‹‹እኛ በአንድነት ነው የምንበላው፣ በኅብረት ነው የምናስበው። ብንጣላና ብንኮራረፍ እንኳን የራስ ሰው ጋር ነው ሄደን አቤት የምንለው። ከአንድነት ውጪ ምንም መድኃኒት የለንም። አንድነቱ ምን ያህል እንደሚያስፈልገንና ኮሮና ደግሞ እንዴት እያፈረሰን እንደሆነ ግልፅ ነው።›› ብሏል።
ኮሮና የኢትዮጵያውያንን ማኅበራዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለምን ማኅበራዊ መስተጋብር እንደመታም ዘነበ ያነሳል። ስለዚህ በዓለም ላይ የመጣ ችግር እስከሆነ ድረስ ደግሞ መቀበል ግድ ይላልና፤ በየቤት ሆኖ የበዓል ስነ ስርዓቱን በቴሌቭዥን የመከታተል እድል ስላለ እሱን መጠቀም ጥሩ ነው ሲል ዘነበ ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል።

‹‹ሰው ለሰው ይኖራል። ቤተክርስቲንም ለልጆችዋ ነው የምትኖረው።›› የሚሉት ሊቀ መምህራን ፋንታሁን ናቸው። አክለውም እንዲህ አሉ፤
‹‹የዘንድሮውን የመስቀል በዓል ስናከብር ኹለት ነገሮች አሉ። አንደኛው የዓለም ስጋት የሆነው የኮቪድ 19 ችግር ነው። እኛ ልጆቻችን በበሽታ እንዲያዙብን፣ እንዲሞቱ አንፈልግም። የኮቪድ አስቸጋሪው ነገር አንተ ብቻ ታመህ የምትቀርበት አይደለም። አንተ ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝተህ የሕመሙ ተጠቂ ስትሆን ምንም የማያውቁ ሕጻናት ልጆችህ ወዳሉበት ቤት ነው ይዘህ የምትሄደው። ስለዚህ ለጠቢባንም ጥበብ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው።

ለጊዜው መድኃኒቱ ባይገኝም ችግሩ እንዲቀል ሕዝብ ተፋፍጎ መገኘት የለበትም። በሽታው እንዳይዘን ተራርቀን አፋችን ላይም ማድረግ ያለብንን መሸፈኛ አድርገን በዓላችንን ማክበር አለብን። ይህንን የምናደርገው ለራሳችን ብቻ አስበን ሳይሆን ለሌላውም ስለምናስብ ነው። ይሄንን ምዕመኑ አይምሮው ውስጥ ሊያስገባው ይገባል።›› ሲሉ አሳስበዋል።

በዚህም ላይ በመስቀል አደባባይ ያለውን የግንባታና ልማት ሥራ አንስተዋል። ይህንንም በሚመለከት ያሉት እንዲህ ነው፤ ‹‹…አሁን በመስቀል አደባባይ ላይ ያለው አደባባዩን የማሳመር የኮንስትራክሽን ሥራ ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት እጅግ ባማረ መልኩ እንድናከብረው የሚያስችል ሥራ ይሆናል። በመሆኑም ልክ የዛሬ ዓመት ባከበርነው ልክ አሳምረን እንድናከብረው የሚያስችል አይደለም። ይሄንንም ታሳቢ በማድረግ ያስፈልጋል።

ይሄንን በዓል የሚያከብሩ አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የቤተክርስትያን አባቶችን ድምፅ መስማት ያስፈልጋል። በተጓዳኝ አዲስ አበባ ላይ እንደሚታወቀው በየመንደሩ ደግሞ በዓሉን ደመራውን ደምረው የሚያከብሩ ወጣቶች አሉ። እነሱም ቢሆኑ እራሳቸውን ከእንደዚህ አይነት ነገር ቆጥበው ማክበር ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም ወደ ክፍለ አገር የሚወጡና ቤተሰቦቻቸው ጋር በመሄድ የሚያከብሩ ኦርቶዶክሳዊያንም በዓል ዘንድሮ ብቻ አይደለም የሚከበረው፤ ፈጣሪ ይሄንንም በሽታ ከአገራችንና ከምድራችን ያጠፋልናል የሚል ፍፁም እምነት አለን። እናም በሚቀጥለው ዓመት ካደረሰን የዘንድሮውን ደርበን ልናከብረው እንችላለን። ስለዚህ ሁሉም በያለበት ሆኖ እንዲከብረው።›› ሲሉ መልዕክታቸውን በተማጽኖ አስተላፈዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here