የሥራ አጥነት ጉዳይ – ትልቁ የቤት ሥራችን

0
747

አዳጊ በሚባሉና በድህነት ውስጥ በሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሥራ አጥነት ላይ ሌላ ተጨማሪ ዕዳ መሆኑ እሙን ነው። ሥራ አጥነት ደግሞ በርካታ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን፣ አብርሐም ፀሐዬ ይህን ሐሳብ በማንሳት ዓለማቀፉ የሠራተኛ ድርጅት እነዚህን መገለጫዎች ምን ብሎ እንደሚያብራራቸው አንስተዋል። አያይዘውም በአገራችንም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ‹ሥራ አይናቅም› በሚል ‹በማይጠበቅ› የሥራ መስክ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን መልክ ከትዝብትና ትውውቃቸው ተነስተው አውስተዋል።

የዓለም ዐቀፉ የምጣኔ ሀብት ትብብርና ልማት ድርጅት ሥራ እጥነትን ሲገልጽ፣ ለአቅመ ሥራ ደርሶ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ ያልተሰማራ ሰው እንደ ሥራ አጥ ይቆጠራል ይላል። እንደውም ከ15 ዓመት በላይ የሆነና ሥራ የማይሠራ ወይም ሥራ ያጣ ሰው እንደሥራ አጥ ይታያል፤ በገለጻው።

ዓለማችን በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ዘመን የሥራ አጥነት ችግሯ ባስ ብሏል። ነገር ግን ምንም ዓይነት ችግር ባይኖር እንኳን የሥራ አጥነትን ግን ዜሮ ማድረስ እንደማይቻል ይታመናል። ከኹለት ዓመት በፊት ዓለማችን ከ170 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ሥራ አጦችን እንደያዘች ተመዝግቧል። ዛሬ ደግሞ ከዚህ ቁጥር በላይ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

በባለሙያዎች ዕይታ የሥራ አጥነት ችግር ከአራትና አምስት በመቶ በላይ ከሆነ ትልቅ ችግር ተደርጎ ቢታይም በአገራችን ኢትዮጵያ ግን እየሆነ ያለው ወደ ሠላሳ በመቶ አካባቢ ነው። ስለሆነም አንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ መረጋጋት እንዲኖራት ስትል ለዜጎቿ ሥራ የመፍጠር አቅሟ ላይ ብዙ ልትሠራ እንደሚገባ ይታመናል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት በየጊዜው እየጨመረ ከሚመጣው የሕዝብ ቁጥራቸው አንጻር ሥራ የመፍጠር አቅማቸውን በማጎልበት ቢያንስ የዜጎቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እስካልተጉ ድረስ የሚፈጠረው ቀውስ ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው።

ሥራ ሊፈጥር የሚችል ዘርፍ በመለየትና እዚያ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በማጠናከር የሥራ ምንጭ መሆን እንዲችል ማድረግ ይገባል። ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን በተለየ ማገዝም እንደዛው። ለዜጎች ሥራ መፍጠር በተለይም የወጣት ኃይል በበዛበት አገር ያለመታከት ሊታሰብበትና ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ከውዴታው በላይ ግዴታው ይበልጣል። ለአቅመ ሥራ ለደረሱ ዜጎች አዳዲስ ሥራዎችን ለመፍጠር ሲታሰብ ቀድመው በርካታ የሥራ ዕድል ፈጥረው ያሉትን ዘርፎችም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ በማጠናከር አቅማቸው እንዲጎለብት መደገፍ ተገቢ ነው።

የሥራ ማጣት ምክንያቶችንም ቀድሞ በመለየት ስጋቶችን ከወዲሁ መቅረፍ የሚቻልበትን ዕቅድ በመንደፍ እዚያ ላይ መሥራት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። ይህ የሚባልበት ምክንያት ሥራ አጥነት ማለት የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እስከማጣት የሚደርሱበት አደገኛ ችግር በመሆኑ የተነሳ የአገር ቀውስ መነሻ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው።

ሥራ የማጣት ምክንያቶች የሚባሉት የዓለምና የአገር ምጣኔ ሀብት መላሸቅ፣ የፖለቲካ ቀውስ፣ ቴክኖሎጂ ሰዎችና መሻማቱ፣ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር ከአገራት አቅም ጋር ባልተመጣጠነ መልኩ መጨመር የመሳሰሉት ናቸው። ዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት (ILO) የሥራ አጥነት ዓይነቶች ናቸው ብሎ በዘረዘራቸው ውስጥ የሚያስቀምጣቸው ማሳያዎች አሉት።

የተወሰኑትን ለማየት ያህል፦
በዓለም ወይ በአገር ውስጥ ጊዜያዊ ግን ሰፋ ያለ የምጣኔ ሀብት መላሸቅ ሲኖር ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ለመልቀቅ ሲገደዱ ሥራ አጥነት ይከሰታል። ይህ የሚሆነው ድርጅቶች ሥራቸውን ማስኬድ የማይችሉበት ተግዳሮት ወስጥ ሲወድቁ ነው። በዚህ የተነሳ የሠራተኛ ቁጥራቸውን ይቀንሳሉ። በተለይ ግዙፍ በሆኑ ኩባንያዎች ውስጥ ይህ ክስተት ይፈጠራል። የሠራተኛ ቁጥራቸውም ከፍተኛ ስለሆነ ሥራ አጥ የሚሆነውም የሰው ኃይል ቁጥሩ ከፍተኛ ሆኖ ይታያል።

መሠረታዊ በሚባል ደረጃ የሥራ አጥነትን ችግሮች የሚፈጥሩ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ ባለፉት ኻያ ዓመታት የእንግሊዝ መኪና አምራቾች የመኪና ገበያቸው እየቀነሰ መጥቷል። ይህ የሆነበትም ምክንያት ትልቁ ገበያቸው የሆነው መካከለኛው ምሥራቅ ራሱ መኪና ማምረት በመጀመሩ ነው። በዚህ የተነሳ በእንግሊዝ ያሉ አምራቾች በዚህ ዘርፍ ላሉ ሠራተኞች ሥራ ፈጥረው በብዛት የሚቀጥሩበት የተመቻቸ ሁኔታ ባለመኖሩ ያላቸውንም ሠራተኞች ለመቀነስ ተገደዋል።

አንድ ሀገር ባላት ለሥራ የደረሰ የሰው ኃይል ልክ በበቂ መልኩ ሥራ መፍጠር ካልቻለች የሥራ አጥ ዜጎቿ ቁጥር መጨመሩ ወይም መኖሩ ግድ ነው። ይህም አንዱ የሥራ አጥነት ችግር ነው።

አካባቢያዊ የሥራ አጥነት ችግሮች የሚከሰቱበት አጋጣሚም ይኖራል። በዓለም ዐቀፍም ይሁን በአገር ደረጃ በሚፈጠር የፖለቲከ፣ የምጣኔ ሀብትም ይሁን አሁን እንዳለው የወረርሽኝ ችግር የሚጎዳ አካባቢ ይኖራል። ለምሳሌ የቁም እንሰሳ ምርትን ወደ ውጪ መላክ ቢቋረጥ በአንድ አካባቢ ያሉ አርብቶ አደሮች ሊጎዱ ይችላሉ።
ከክፍያ ጋር በተያያዘ ከሚገባው በታች እየተከፈላቸው እየሠሩ ያሉ ሠራተኞችንም ከሥራ አጦች ዝርዝር ውስጥ ይመድባቸዋል።

ሠራተኞች የግልም ይሆን በቅጥር ሳሉ የነበሩበትን ሥራ በመልቀቅ ወደ ሌላ ሥራ ለመቀየር በመካከሉ የሚወስዱት የሥራ ፍለጋ ጊዜ በሥራ አጥነት እንደቆዩ ተደርጎ ይወሰዳል።

አንድ አገር በበቂ ሁኔታ የተማረ የሰው ኃይል አፍርታ ነገር ግን ያላቸው አቅም ሥራው ከሚፈልገው አንጻር የሚስማማ ወይም የሚመጥን ካልሆነ ያንን ቦታ ከውጪ በሚመጡ ባለሙያዎች ወይም በቴክኖሎጂ የማሟላት አስገዳጅ ሁኔታ ስለሚፈጠር እንደሥራ አጥነት የሚቆጠር ይሆናል።
ወቅታዊ የሥራ አጥነት የሚባሉም አሉ። በተለይም እንደ ግብርና ቱሪዝምና ግንባታ ያሉ ሥራዎች ሠራተኞቻቸውን የሚያሠሩት ሥራው ባለ ጊዜ በመሆኑ በመካከሉ የሚኖረው መቋረጥ የሥራ አጥነት ጊዜ ይባላል።

በራሳቸው ፈቃድ ሥራ የማይሠሩ ዜጎች አሉ። ማለትም የሚመጥነኝ ወይም የምፈልገው ሥራ አይደለም፣ አመቺነቱ ከክፍያና ትርፍ ከማግኘት ጋር በተያያዘ ተገቢነቱ ላይ የማያምኑና በዚህ ባለመስማማትም ወደ ሥራ የማይሰማሩ ዜጎች እንደሥራ አጥ የሚመዘገቡ ናቸው።

አገራችን ላይ ያለውን የሥራ አጥነት ቁጥር ወይም የሥራ አጥ ዜጎችን አሃዝና የዚህን መነሻ ችግር ማስረዳት ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው። በበለጸጉ አገራት ዜጎች ከፍላጎታቸው ውጪ ወይም ከተማሩት ትምህርት ጋር የማይስማማ ሥራ ላይ ከተሰማሩ እንኳን እንደሥራ አጥ ይቆጠራሉ። እኛ ጋር ምንም ተማር ምን፣ ሥራ ማግኘቱ እንደ ትልቅ ዕድል የሚቆጠር ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያችን ያለውን ገጽታ ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ካቀድኩበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ አጋጣሚዎች የቃኘሁትን አብረን እንየው።

የአገር ልጆችና ሥራ
ወደ መስተንግዶ ሥራ የሚቀላቀሉ እንስቶች በአመዛኙ ትምህርቱን አቆይተው፣ የወላጆች የኑሮ አቅም ሲደክም ወይም ከልጅነት ጋብቻ ሸሽተው የባሰባቸውም ፍቺ ፈጽመውና ጠፍተው ነው። ወንዱም የወላጆቹ የኑሮ ሸክም አስፈንጥሮት የተገኘ ነው። አልፎ አልፎ የቱንም ሥራ ሠርተው የመለወጥ ርዕይ ሰንቀው እየሠሩ ያሉ እንዳሉ ማመኔ ይታወቅልኝ።

ለማንኛውም ግን በምንገምተው አስገዳጅ ሁኔታ ወደ መስተንግዶ የገቡ ወጣቶች እንዳሉ ሆነው ከዚያ ውጪ ደሞ ወደዚህ ሥራ የመጡ ወጣቶችን ሕይወት አብረን እንቃመሰው። የማይቀየር ነገር የለምና የአስተናጋጆችም ማንነት መልኩን እየቀየረ መምጣቱን ያወኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው።

አንድ
ሬስቶራንት ውስጥ ቁጭ ብዬ የታዘዘው እስኪመጣ አንዲት የጀመርኳትን መጽሐፍ ገለጥ አድርጌ ከአንገት በላይ በሆነ ስሜት እያነበብኩ ነው። እዚያ ቤት በደንበኝነት የተነሳ ለሰላምታ የደረሰ ግብብነት ያለን፣ ምናልባትም ዕድሜዋ ከኻያ አምስት ያልበለጠች ወጣት አስተናጋጅ ጠጋ አለችኝና ‹መጽሐፉ የማነው?› አለችኝ፤ ነገርኳት።
መጽሐፉን እንዳነበበችው ከነታሪኩ ጭምር ጠቃቀሰችልኝ። ቀጠል አድርጋ ‹‹በ’ናትህ ‘ሀዲስ’ የሚባለው የበዓሉ ግርማ መጽሐፍ አለህ? ደግሜ ማንበብ እፈልጋለሁ…›› አለችኝ። ዋና ገጸ ባህሪ ሆኖ የተሳለውን የዚያ ዘመኑን ሀዲስ እንደምትወደው እንደውም ከአድማስ ባሻገር ላይ ካለውና ከዘመኑ ጋር እየተጣላ ይኖር ከነበረው አበራ ወርቁ በላይ እንደምታደንቀው አጫወተችኝ። ጭብጡን፣ መቼቱን፣ ገጸ ባህርያቱን ሁሉ ስታወራልኝ ለደቂቃዎች ገርሞኝ በአድናቆት አደመጥኳት። አለቆቿን በአንድ ዐይኗ እያየች ተረከችልኝ።

መቼ ነው ያነበብሽው? አልኳት
‹ካምፓስ እያለሁ› አለችኝ። በሲቪል ምህንድስና ከተመረቀች ኹለት ዓመቷ ነው። አዎ! አገሬ ለኢንጂነሪንጉ የረባ ቦታ የላትም፤ እናም አጅሪት ሆዬ የራሷን ቦታ ይዛለች። ይኸው እዚህ ታስተናግዳለች! እንደገረመኝ ገብቷታል። ጠጋ አለችኝና እዚያ ጥግ ላይ የቆመችውን ሌላ አስተናጋጅ ጠቆም አደረገችኝ።
‹‹እሷ በሶሲዮሎጂ ኹለተኛ ዲግሪ አላት፤ ነገር ግን እንዲህ እንደተማረች ሰው እንዲያውቅባት አትፈልግም።›› አለችኝና ሳቅ ብላ ሄደች። ያሁን ዘመን የመስተንግዶ ሰዎቻችን እንዲህ ቀለም ቀመስ ሆነውልናል እንበልና እንለፈው ይሆን?

ኹለት
ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ያው በተለምዶ ባጃጅ የምንለው ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለብቻዬ ተሳፍሬአለሁ። የባጃጁ ሹፌር ጨዋታ ይችላል። መንገዱን፣ ኑሮውንና መላቢሱን ዘመን እያማን እየተጓዝን ነው። በጨዋታችን መካከል ‹‹ፍሬኑን ላሠራ እየሄድኩ ነው ያገኘሁህ›› አለኝ።
‹‹እህ! እና ያለፍሬን ነው የምንሄደው?›› አልኩት። ‹‹አዎ! ግን የፊዚክስ ተማሪ ስለሆንኩ ችግር የለም። በመላ ነው የምነዳው።›› አለኝ እየሳቀ።
የትምህርቱ ጉዳይ ቀልዱን መስሎኝ ነበር። ነገር ግን ትንሽ ስለፊዚክስ ጽንሰ ሐሳቦችም ጨመር አድርጎ አብራራልኝና መማሩን ንግግሩ መሰከረልኝ… ሹፌሩ በ’አፕላይድ’ ፊዚክስ ተመርቋል። በሌሎቹ የባጃጅ ሹፌሮች ግን ‹የኛ ምሁር› እየባተለ እንደሚሳቅበት ነገረኝ። ‹‹እውነታቸውን ነው… የእነርሱን ሥራ እየተሻማኋቸው ነዋ!›› አለኝና በነርሱ ዘንድ መዘባበቻ መሆኑን እንደሚቀበለው ነገረኝ።

… አገሬ ፊዚክሷን ባጃጅ ላይ አኑራዋለች። አስተናጋጆቿ ኢንጂነሮች ናቸው። ያው ሥራ አይደል?! ይሁን ነው የሚባለው። ‹የሥራ ትንሽ የለውምና የትኛውም ሥራ ቢሆን መናቅ የለበትም› የሚል የቴሌቪዥን ፕሮግራም እየተቀረጸ መጽናኛ ትርክቶች ይለቀቃሉ። እንግዲህ ማታ እሱን እያዩ ጠዋት ያገኙትን መሥራት ነው። ›ምንም ማድረግ አይቻልም።› እንዳለው ነው ዲጄ ኪንግስተን።

አቶ ጁነዲን ሳዶ ይመስሉኛል፤ የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቱ ሚኒስቴር ሳሉ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሩቃን ንግግር አድርገው ነበር። ተምሮ የኮብል ድንጋይ የማንጠፍ ሥራ እስከመሠማራት የሚደርስ ሞራልና ትጋት ያስፈልገናል የሚል በአጠቃላይ ሥራ ክቡር ነው ዓይነት ይዘት ያለው ዲስኩር አድርገዋል። ያ ሁሉ ባለመነሳንስ ግን የጮኸባቸው ጩኸት ቀላል አልነበረም።

ለካ ሥራ አጥነቷን ለመሸፈን በገዢዎቻችን የማትፈጠር የሥራ መስክ የለችም። እሱ ባልከፋ፤ ከዚያ በፊት ግን ከመነሳንሱ ስር ያለው ጭንቅላት የተፈለገው የሥራ ዘርፍ ላይ እንዲሰማራ ሆኖ ነው ወይ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያለፈው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት።

ሦስት
የዛሬ ኹለት ዓመት አካባቢ ያገኘሁት ወጣት ትዝ አለኝ። በአጋጣሚ ወደሥራው የገባበትን ለሽንት ቤት የሚሆን ጉድጓድ ቁፋሮ ይሠራል። ሥራውን ሲያገኝ ራሱ እየተሳተፈ፣ እየቀጠረም ጭምር ይቆፍራል፣ ያስቆፍራል። በአጋጣሚ እየተጨዋወትን ሳለ በስታቲስቲክስ ዲግሪ እንዳለው፣ ያውም በከፍተኛ ማዕረግ እንደጨረሰ አወራልኝ። እና… ? አልኩት (እናማ ይኸው ይቆፍራላ)

ብርሃኑ ይባላል። እንደተመረቀ ሰሞን ሥራ ፍለጋ ተንከራተተ፤ ሥራው ደግሞ አልገኝ አለ። ሸሚዙም ነተበ፤ ሠርክ ጫማ ማስጠረጉም ዕዳ ሆነ። አዲስ አበባ ያስጠጉት ዘመዶቹ ደሞ ሥራ እስኪያገኝ አልታገሱትም፤ ፊት እየነሱት መጡ። ወደገጠር ተመልሶ አይገባ ነገር የማይሆን ሆነበት። ለምርቃት ድግሱ የተጣለለትን ወይፈን አይረሳውም። አገር ምድሩ ሦስት ቀን ጨፍሯል። በሰፈርና በዘመድ አዝማዱ ይቅናህ ተብሎ ተመርቋል። እንዲህ ሆኖ ‹በቃ! ከተሜ ሆነ› ተብሎ ከተሸኘ በኋላ ያለሥራ ወደዚያ መንደር መመለሱ የጎረቤት መተረቻ ያደርገዋልና ፈራ።

ባህል አንዳንዴም ክፉ ነው! የኛ አገር ነገር ደግሞ ትስስሩ ጥብቅ ስለሆነ ጎረቤቱና ሰፈርተኛው፣ ጓደኛ ወይም ባልንጀራ የሆነው ጭምር፣ ዘመድ አዝማዱ ሁሉ መጠየቅ አይተውም። ለብቻ የሚወሰን ነገር የለም። ከተመረቁ በኋላ ማን ዝም ይላል? የምርቃት ድግሱ ላይ ለእንጀራ ያብቃህ ያለ መራቂ ከወር በኋላ “እህ እንዴት ሆንክ?” ማለቱ አይቀርም። ለወግ ማዕረግ ያብቃህ፤ ወልዶ ለመሳም ያድርስህ ያለ ጎረቤት ከጊዜ በኋላ አገባህ ወይ ማለቱ አይቀርም። የኛ የኢትዮጵያውያን ኑሮ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚደረግ መፍጨርጨር ውስጥ መዳከር ነው። ትስስሩ ኃያል ነው!

ወደቆፋሪው ልመለስ። ቁፋሮውን እንዴት እንደጀመረ ሲነግረኝ የዘመዶቹ ቤት ውስጥ ለመጸዳጃ ቤት የሚሆን ጉድጓድ ሲቆፈር በነበረበት ጊዜ ከቆፋሪው ጋር ተግባባና እንደነገሩ በቁፋሮው አገዘው። በአጋጣሚ የስታቲስቲክስ ምሩቁ ሰው ጥሩ ቆፋሪ ነበር። እንደቀልድ የቁፋሮ ሕይወት ተጀመረች። ከሰለቹት ዘመዶቹ የመላቀቂያ መንገድ ሆነውና ወጥቶ ኮበለለ፤ ለጥቂት ጊዜያት ከቆፋሪው ጋር ከኖረ በኋላ አሁን ላይ ራሱን ችሏል። ይኸው በቁፋሮ መተዳደር ከጀመረ ኹለት ዓመት አለፈው። ስታቲስቲክስ አራት በኹለት ልኬት እየቀመረች የመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ትቆፍራለች!

እናም ለዚያ ነው ዩኒቨርስቲ ያሉትን ተማሪዎች ለመመረቅ እንዳይቸኩሉ ንገሯቸው የሚያስብለው። እዚያው ባሉበት ‘ከዩኒቨርሲቲ ባሻገር’ የሚል ተጨማሪ ኮርስ ያስፈልጋቸዋል። ከምርቃት ድግሳቸው በኋላ ያለውን ሁኔታ በመጠኑ ማስዳሰስና ማዘጋጀት እንደአገርም ብልህነት ነው።
አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስና የኮምዩኒኬሽን ባለሞያና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው geraramc@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here