ዐይነ ስውራን ተፈታኞች ሥልጠናቸው ሳይጠናቀቅ እንዲበተኑ ተደረጉ

0
528

በ2012 አገር ዐቀፍ የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በኦንላይን ስለሚወስዱ ከወዲሁ ሥልጠና እንዲያገኙ በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ የነበሩ ዐይነ ስውራን ተፈታኖች ‹አምስተኛ ሳምንት ሳይደርስ ወደመጣንበት እንድንበተን ተደርገናል› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ የፈተና አሰጣጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን አለበት የሚል ውሳኔ ከመንግሥት ዘንድ መተላለፉን ተከትሎ በኦንላይን እንዲፈተኑ ምክረ ሐሳብ መቀመጡ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ዐይነ ስውራን ተፈታኝ ተማሪዎቹ ለአምስት ሳምንታት የሚዘልቅ መሠረታዊ የኮምፕዩተር ሥልጠና በዘንድሮው ዓመት በኦንላይን ለሚሰጠው የአገር ዐቀፍ የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ዝግጅት በማድረግ ላይ ነበሩ።

‹‹ለዚህም በቂ ዝግጅት እንድታደርጉ በሚል ሥልጠናውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎ ጊቢ ውስጥ እንድንወስድ ሲደረግ ነበር። ሆኖም ምክንያቱን ሳናውቀው አቋርጠን ከግቢው በፖሊስ እንድንወጣ ተደርገናል።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

‹‹እስከ አሁን ሥልጠናውም ሆነ ቀሪ ለእኛ ተብሎ የተደረገ ኃላፊነት የተሞላው ዝግጅት አልነበረም።›› ያሉት ተማሪዎቹ፤ ‹‹ሥልጠናውን በኹለት ፈረቃም ቢሆን ታጭቀን ነበር በሽሚያ የምንወስደው። ከዛም ባለፈ ስንገባም የኮሮና ምርምራ አልተደረገልንም። ወደ ቤተሰቦቻችን እንድንቀላቀል ስንገደድም ምንም አይነት ጥንቃቄ አልተደረገልንም።›› በማለት ተናግረዋል።

የኮቪድ 19 ምርመራ ሳይደረግልን ብሎም እንደማንኛውም መሥርያ ቤት ሙቀት ልኬት እንኳን ሳይደረግ በመግባታችን በተደጋጋሚ ጥያቄ እያነሳን የነበረ ቢሆንም አሁን ደግሞ ይባሱኑ ከሳምንት በፊት ምርምራው ሳይደረግልን እንድንበተን ተድርገናል የሚሉት ተፈታኝ ተማሪዎቹ፤ በዚህም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን ብለዋል።
በተጨማሪም ከመካከላቸው አራት ልጆች በፀና መታመማቸውን እና እንደዚህ መሆናቸው እየታወቀ ወደ ቤተሰቦቻቸው መላካቸውን አንስተዋል። በዚህም ሌሎቻችን ትልቅ ስጋት ውስጥ ወድቀናል በማለት ስጋታቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት መምህር የሆኑት አበበ የኋላወርቅ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደምም እንዲህ አይነት ሥራ መሠራት እንደሌለበት እና አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ደጋግመው መግለጻቸውን አስታውሰዋል። ከዐይነ ስውራን ማኅበር ጋርም በጋራ በመሆን ተናግረን ነበር በማለት አንስተዋል።

አክለውም ‹‹የተሠራው ሥራ ውጤት አልባ ከመሆኑም በላይ ልጆቹ በግዳጅ ሥልጠናውን እንዲወስዱ ከተደረገ በኋላ አንድ አንድ ላፕቶፕ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር። ነገር ግን ይሄንንም ትምህርት ሚኒስቴር ቃሉን አላከበረም። ከዛ ባለፈ ግን የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ለዐይነ ስውራን ተማሪዎች እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ሳለ ለእነርሱ ጥንቃቄ ማድረግ ሲገባ በቸልተኝነት ሲገቡም ሲወጡም ምርመራ አለማከናወን የሚያስወቅስ ነው።›› በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዚህ መሀል አዲስ ማለዳ ከትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ደጋግማ ስልክ ብትደውል እንዲሁም አጭር የጽሑፍ መልዕከት ብትልክም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሀረጓ ማሞን አነጋግራ በነበረበት ወቅት ሥልጠናውን በተመለከተ፤ እንዴት ተፈፃሚ ሊሆን ታሰበ እና ሥልጠናውስ ውጤታማ ሊሆን ይችላል ተብሎ ታስቦ ነው ወይ በሚለው ላይ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

በዚህም ዐይነ ስውራን ተማሪዎች ሥልጠናን በተመለከተ አምስት ሳምንታት የሚቆይ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው አስታውቀው ነበር። ‹‹ሥልጠናው ምንም አይነት ኮምፕዩተር ነክተው ለማያውቁ ዐይነ ስውራን ተማሪዎች እድል ያመቻቸ ነው። ዋና ዓላማው አቀላጥፈው እንዲችሉ ታስቦ ሳይሆን ዋና እና መሠረታዊ የኮምፕዩተር ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። ከተጀመረ አንድ ሳምንት ያስቆጠረ ቢሆንም ቀላል የማይባል ለውጥ እየታየ ነው። ሥልጠናው የሚሰጠውም ዐይነ ስውራን በሆኑ መምህራን መሆኑ ደግም በቀላሉ ልምድ ለመለዋወጥ ይረዳል።›› ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር ጉብኝት እንደሚያደርግ እና የፈተና አሰጣጡ ላይም ለሚነሳው ቅሬታ ሥልጠናው ካበቃ እና ግምገማ ከተደረገ በኋላ የሚወሰን ውሳኔ ይኖራል በማለት ጠቁመው ነበር። አሁን ግን ሥልጠናውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎችን አዲስ ማለዳ ባናገረችበት ወቅት ምንም አይነት አቅጣጫ እንዳልተሰጣቸው አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here