መስማት ለተሳናቸው መንጃ ፈቃድ መሰጠት ሊጀመር ነው

0
730

መስማት ለተሳናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ወይም መንጃ ፈቃድ መሰጠት ሊጀመር እንደሆነና ይህም በአዲስ አበባ እንደሚጀመር ተገለጸ። በአሁን ወቅት የብቃት ማረጋጫውን ለመስጠት ቅድም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቋል።
መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም፣ በቅድሚያ ግን በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሥራውን ሁኔታ ለመገምገም እና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ እንደሚተገበር በሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር አሳልፈው አሕመዲን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ ባሳለፍነው ዓመት የተጠናቀቀው፤ መስማት የተሳናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ የተዘጋጀው መመሪያ በያዘነው የ2013 በጀት ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቋል። እንዲሁም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫውን በያዝነው በጀት ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ሥልጠና ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር እንዳልካቸው ጸጋዬ ጠቁመዋል።

አንድ ሰው የጹሑፍ እና የንድፈ ሐሳቡን እንዲሁም የተግባር ፈተና ካለፈ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ እንደሚሰጠው በአዋጅ ላይ ተቀምጧል ያሉት እንዳልካቸው፣ አሁን ያለንበት ወቅት በቴክኖሎጂ የታገዙ ነገሮች የሚከወኑበት በመሆኑ የብቃት ማረጋገጫውን ማውጣት የሚችሉበት አሠራር መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር አካል ጉዳተኞች አንዳች ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሳይደርስባቸው ጥቅማቸው እንዲከበርላቸው ፈርማለች። በዚህም መስማት ለተሳናቸው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

በመመሪያው ከተካተቱ ነጥቦች መካከልም የትራፊክ ፖሊሶች የቁጥጥር ሥራቸውን በሚሠሩብት ጊዜ መስማት ከተሳናቸው ጋር መግባባት እንዲያስችላቸው የምልክት ቋንቋ መሠልጠን አለባቸው የሚለው እንደሚገኝበት እንዳልካቸው ጠቅሰዋል። የአሽከርካሪ ፈቃድ ለማግኘት ሥልጠናውን የሚሰጡት ተቋማትም ቢሆኑ በተማቋት ውስጥ የሚገኙት መምህራን የምልክት ቋንቋ መቻል ያለባቸው ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ አስተርጓሚ ማዘጋጀት እንዳለባቸው አክለው ገልጸዋል።
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ደግሞ ለሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች መመሪያውን የማውረድ ኃላፊት የተሰጠው ሲሆን፣ ተሽከርካሪዎች ላይም ከፊት እና ከኋላቸው ላይ መስማት የተሳነው አሽከርካሪ መሆኑን የሚገልጽ ምልክቶችን ያስቀምጣሉ ብለዋል።

ይህንን ሥራ በተለይም የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኃላፊነት የሚያግዝ እና የሚሠራ እንደሆነም እንዳልካቸው ጠቁመዋል።
ሥራውን በኃላፊነት ይሠራዋል የተባለው የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የትራፊክ ፖሊሶች ከመቅጣታቸው በፊት እንዴት ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸው እንጠቁማለን፤ በጤና ተቋማትም በኩል እንዴት መስተናገድ እንደሚቻሉ ድጋፍ እያደርግን ነው ብሏል።

እንደ እንዳልካቸው ገለጻ ከሆነ ደግሞ መመሪያውን ወደ ተግባር ለማስገባት በአሁን ወቅት አመቺ ሁኔታዎች አሉ። ለአብነትም ቴክኖሎጂን በመደገፍ ነገሮች የማቅለል ነገር እየተስፋፋ መምጣቱን አንስተው ‹‹እኛም ብንሆን ትራፊኮቻችንን በስፋት እያሠለጠንን ወደ ተግባር የማንገባበት ምክንያት የለም።›› ብለዋል።

የማሠልጠኛ ተቋማት ዝግጁ መሆናቸው፣ በአሁን ወቅት ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በስፋት መግባታቸውም ጨምረው ገልጸዋል።
መስማት የተሳናቸው ማኅበር ይህን የመንጃ ፈቃድ ጉዳይ በሚመለከት ጥያቄ ሲያቀርብ ከ45 ዓመታት በላይ መሆኑን የማሕበሩ ሥራ አስኪያጅ ትዕግስት ዓለሙ ገልጸዋል። በአሁን ወቅት ብዙ ሥራ ይጠበቃል ያሉት ትዕግስት፤ በተሸከርካሪዎች ላይ መስማት የተሳናቸው መሆናቸውን የሚያመለካት ምስል ከማስቀመጥ በተጨማሪ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችመኖራቸውንለኢቲቪ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here