‹‹በእድሳት ምክንያት ከቤታችን ብንወጣም ችግር ውስጥ ነን›› የአልፋ መንደር ነዋሪዎች

0
504

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ልዩ ሥሙ ጃፓን ኤምባሲ ወይም በተለምዶ አልፋ መንደር በመባል በሚታወቀው አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ‹ቤታችሁ እድሳት ተደርጎለት ለአዲስ ዓመት ትገባላችሁ ተብሎ በከተማ አስተዳደሩ በኩል የተነገረን ቢሆንም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት እድሳት አለመጀመሩ አሳስቦናል› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቁጥራቸው 44 የሚጠጉ የወረዳው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታችሁ በአጭር ጊዜ ታድሶ ለአዲስ ዓመት ትረከባላችሁ የተባሉ ቢሆንም፣ እስካሁን በወረዳ 02 በሚገኘው ወጣት ማዕከል ምቹ ባልሆን ሁኔታ መቀመጣቸውን ጨምረው ተናግረዋል። የነዋሪዎቹ ቤት የፈረሰበት ቦታ ድርስ በመሄድ ምልከታ ያደረገችው አዲስ ማለዳም፣ ለአዲስ ዓመት ተጠናቅቆ ትረከባላችሁ የተባለው ቦታ ላይ ምንም አይነት ግንባታ አለመጀመሩን፣ ነገር ግን መኖሪያ ቤቶቹ ፈርሰው መሬቱን የማረስ ሥራ እየተከናወን መሆኑን ታዝባለች።

ከመኖርያ ቤታቸው ከወጡ አንድ ወር ያለፋቸው ነዋሪዎች እስከሁን ግልፅ የሆነ ነገር እንዳልተቀመጠላቸውም ነው የጠቀሱት። መጀመሪያ አካባቢ መዘናጋቱን ሲመለከቱ ‹እድሳቱ ይቅር እና በነበረው ቤት እንኑር› በማለት ጥያቄ አቅርበው እንደነበረና በወረዳው አስተዳደር በኩል ግን ‹ይታደሳል፤ ሲጠናቀቅ ትገባላችሁ› መባላቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የመኖሪያ ቤቶቹ እድሳት ውጥን የሰባት ሰዎችን ቤት ለማደስ በመጣ አንድ ባለሀብት የተጀመር ሲሆን፣ ለአዲስ ዓመት ሊያድስላቸው ቃል ገብቶ እንደነበር አውስተዋል። ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቦታው ተገኝተው ከታዘቡ በኋላ ሁሉም መኖርያ ቤቶች መታደስ አለባቸው ብለው መወሰናቸውን አስታውሰዋል።

በቦታው ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ አለመጀመሩ እና ቦታውን ሊሸጡት ነው በሚል አልፎ አልፎ እየተሰማ ባለው ወሬ እየተረበሹ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ‹‹ቅድሚያ የነበረው እና የተነገረን ቤቱ በነበረው ካሬ ልክ እዚያው ላይ ታድሶ እንደሚሰጠን ነበር። አሁን ግን ለነበሩት ለ44ቱም ነዋሪዎች ባለ 25 ካሬ ቤት ብቻ እንደሚሰጠን ነግረውናል።›› ብለዋል።

በተያያዘም አሁን በወረዳው በሚገኝ ወጣት ማእከል ውስጥ እንዳሉ አዲስ ማለዳ ታዝባለች። ‹‹ንብረታችን እየወደመ ነው። ይዘነው የመጣነው ንብረት ማደሪያችን ቤት ውስጥ ማስቀመጪያ በማጠሩ ምክንያት፤ ዝናብ እና ፀሐይ እየተፈራረቀበት ነው። ምን ይዘን ወደ መኖርያ ቤታችን እንደምንገባ አናውቅም።›› በማለትም ለአዲስ ማለዳ የሆነውን አሰምተዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ነሐሴ 14 ቀን 2012፤ ‹‹አቅም የሌላቸውን ቤተሰቦቻችንን ለመደገፍ እና ለመርዳት የቤቶችን እድሳትና ደረጃ የማሳደግ ሥራዎች በቦሌ ሩዋንዳ ልዩ ሥሙ ጃፖን አልፋ መንደር የሚገኙ 44 ቤቶች እድሳት እና ደረጃ የማሳደግ ሥራዎችን አስጀምረናል። በእድሳቱም ውሃ፣ መብራት እንዲሁም መጸዳጃ ቤት እንደ አዲስ የሚሠራ ይሆናል። ከዚህ ውስጥ ሰባቱን የአካባቢው ባለሀብት ዮናታን አንቶኒዮ (Taurus investment group) በበጎ ፍቃዳቸው የሚያሠሯቸው ይሆናሉ።›› በማለት መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ አልፊያ ዩሱፍ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ የቤት እድሳቱ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ የሚከናወን ነው። ስለዚህም በአስራ አምስት ቀን ወይንም በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ማለት አይቻልም።

ከዚህ በተጨማሪ የቤቱ ሥራ አልተቋረጠም ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን ተቋርጦ ከሆነ እና በቅልጥፍና እየተሠራ ካልሆነ ከክፍለ ከተማው ጋር በመነጋገር ይፈታል በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም ቤቱ እንዲፈረስ ከተደረገ እና ከዛ በኋላ ባለፉት ቀናት ማንም ዞር ብሎ አላየንም የሚል ቅሬታ ከነዋሪዎቹ ዘንድ ከተነሳ፣ ከቦሌ ከፍለ ከተማ ጋር በመነጋገር እንፈታዋለን ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here