በሳውዲ አረቢያ እስር ቤት ሦስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን አምነስቲ ይፋ አደረገ

0
745

በሳውዲ አረቢያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ስደተኞች አያያዝ በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባካሄደው ምርመራ አዳዲስና አሰቃቂ ዝርዝር መረጃ ማግኘቱን ይፋ አደረገ።

ድርጅቱ እንዳለው በዚህም ሳቢያ የስደተኞቹ ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን አመልክቶ ሦስት ኢትዮጵያዊያን መሞታቸውን በእስር ቤቶቹ ካሉ ስደተኞች ማረጋገጡን ስለሁኔታው ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል  ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አምነስቲ ጨምሮም የሳዑዲ መንግሥት ስደተኞቹ ያሉበት አደገኛ ሁኔታ እንዲያሻሽል እንዲሁም ነጻ እንዲወጡ ተይቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የስደተኞቹ አያያዝ እንዲስተካከል ግፊት እንዲያደርግና ፈቃደኛ የሆኑትም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚደረግበትን መንገድ እንዲፈልግም ጠይቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት  ጽዮን ተክሉ በበኩላቸው  የኢትዮጵያ መንግሥት በስደተኛ ማቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ጉዳይ ሪፖርቶች ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ ጀምሮ እየተከታተለ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ የሚገልጹ ሪፖርቶች በሚወጡ ጊዜም ጉዳዩን ለሳዑዲ ባለስልጣናት በማሳወቅ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ከመጠየቅ ተቆጥበው እንደማያውቁም ተናግረዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የየመን አማጺያን በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊን ስደተኞችን፣ ከየመን አስወጥተው በማባረራቸው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገብተው ለሕይወት አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቋል።

አምነስቲ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን እንደተናገሩት ለሁለት ሆነው በሰንሰለት መታሰር፣ በታሰሩበት ክፍል ውስጥ እንዲጸዳዱ መደረግ፣ ለ24 ሰዓታት በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ ማድረግን ጨምሮ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ የመከራ ሕይወትን እየመሩ ነው ብለዋል።

አምነስቲ  ከተለያዩ ታሳሪዎች ያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ እንዳመለከተው በእስር ቤቱ ውስጥ የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል።

በተጨማሪም በገለልተኛ ሁኔታ ለማረጋገጥ አልቻልኩም ያላቸው ቢያንስ የአራት ኢትዮጵያውያንን ሞት መስማቱን አመልክቷል።

በእስር ቤቱ ውስጥ ባለ በሽታ፣ የምግብና ውሃ ችግር እንዲሁም የህክምና አገልግሎት አለመኖር ለሞት የሚዳረጉትን ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ሪፖርቱ ጠቅሷል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here