የዋስትና መብት መነፈግ በህግ ባለሙያዎች እይታ

0
1670

የሰሞነኛው የአገራችን የፍርድ ቤት ውሎን በተመለከተ በተደጋጋሚ ከምንሰማቸው እንግዳ መሳይ ክስተቶች መካከል ዳኞች ግራ ቀኙን ተመልክተው  ተከሳሽ ተጠርጥሮ የተያዘበትን ጉዳይ ካመዛዘኑ ፍርድ ቤት የሚሰጧቸው የዋስትና መብቶች ተፈፃሚነት በፖሊስ መደነቃቀፉ ነው፡፡

ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጣቸውን የዋስትና መብት ተጠቅመው የተጠየቁትን የዋስትና ማስያዣ ቢያሟሉም ፖሊስ ግን የፍርድ ቤትን ትእዛዝ መፈጸም አለመቻሉ የፍርድ ቤትን ነጻነትን፣ የህግ የበላይነትን እና ልዕልናን አደጋ ውስጥ ጥሏል፡፡

ለዚህ ማሳያ ከሆኑት የፍርድ ቤት ውሎዎች መካከል  የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያው ፓርቲ (ኢዴፓ)አባል የሆኑት  ልደቱ አያሌው ዋነኛው ናቸው፡፡ልደቱ  መስከረም 12 2013  ላይ ቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ተመልክቶ የክስ ሂደታቸውን በውጪ ሆነው መከታተል ይችላሉ ሲል የ100 ሺህ ብር ዋስትና ተጠይቆባቸው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር ፡፡

በትዕዛዙም መሰረትም ልደቱ አያሌው የተጠየቁትን የ100 ሺህ ብር የዋስትና ትዕዛዝ ቢያሟሉም ፖሊስ ሊፈታቸው ፍቃደኛ ካለመሆኑ በላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ ዋስትናቸው እንዲታገድ አድርጓል፡፡ ይህምበ ለሁለት ጊዜ ችሎትከመሆኑም በላይ ህጉን የተከተለ ነው? ወይንስ አይደለም  በሚል ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ አና የሃሳብ ምልልስ እየተደረገበት ይገኛል፡፡

ከዚህ በፊትም በአራት አስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ላይ ከሀጫሉ ግድያ በኋላ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ንብረት እንዲወድም፣ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለቱ አራዳ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት መዝገብ እንደከፈተባቸው ይታወቃል።

በቀረበባቸው ክስም ፍርድ ቤቱ በዋስትና ከእስር  እንዲለቀቁ ቢወስንም በላይ ማናዬ፣ ሙሉጌታ አንበርብርና ምስጋናው ከፈለኝ ሲቪል በለበሱ ግለሰቦች ተይዘው እንደነበር የአስራት ቴሌቪዥን ዘግቦ ነበር።

ታዲያ በፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው የተረጋጋጠላቸው ተከሳሾችን ፖሊስ አለቅም ማለቱ በህግ ባለሙያዎች እና በዘርፉ በርካታ አመታትን በዘርፉ ከሰሩ ምሁራንን ዘንድ ምን አንድምታ አለው በማለት አዲስ ማለዳ አነጋግራለች፡፡

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ብዙሃኑ የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ አሁን እየሆነ ያለው እና በፍርድ ቤቶች ውሎ ተደጋግሞ የሚሰማው አካሄድ በፍፁም ትክክል ያልሆን እና የህግ ስርዓቱ  ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚሳድር ፤ ከእዛም ሲከፋ የሰዎችን ህገ -መንግስታዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብትን የሚጋፋ  ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡

በየነ ይርጉ ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ የህግ ባለሙያ እንደተናገሩት ከሆነ ‹‹አቃቤ ህግ ይግባኝ ለመጠየቅ የህግ መሰረት እንደሌለው እና እንዲያውም ጉዳዩ የህገ መንግስት ጉዳይ ብቻም ሳይሆን የሰብዓዊ መብትም ጨምር እንደሆነ አንስተዋል፡፡ የዋስትን ጉዳይ ከምንም ምክንያት በጣም ጥበቃ ከሚደረግላቸው መብቶች መካከል ዋስትና መብት አንዱ መሆኑን አንስተዋል ፡፡

ስለዚህም  ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው  ያ መብት ግን በሌላ ኃይል ሲገደብ  ሰብዓዊ መብታቸው ፤ ወይንም ነፃነታቸው እንደተገደበ ስለሚቆጠር ትልቅ ስህተት መሆኑን ያነሳሉ፡፡ በእርግጥ የዋስትና መብት የሚከለከልባቸው ልዩ ጉዳዮች መኖራቸው እና ይኸውም አንዱ የወንጀሉ ክብደት መሆኑ ሌላኛው ደግሞ በህዝብ እና በግለሰብ ላይ የደረሰው ወንጀል ታይቶ፣ በዋስ እንዲወጡ ቢደረግ በሕዝብ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ታይቶ (ተገምቶ) የዋስትና መብት ሊከለከል እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡

አሁን  ያለው ግን ፍርድ ቤት ከግራ እና ከቀኝ ያለውን ጉዳይ አመዛዝኖ የዋስትና መብት ከፈቀደልህ በኋላ አቃቤ ህግ ይግባኝ ማለት ይችላል ወይ ነው ጥያቄው ? እንደ ባለሙያው ከሆነ ተጠርጣሪው ያን የዋስትና መብት ተከልክሎ ቢሆን ይግባኝ ማለት እንደሚችል ጠቅሰው ይህም የተፈቀደበት ምክንያት ዋስትና ለተከለከለው ተጠርጣሪ የነፃነት መብቱን በመሆኑ ሁለተኛ እድል እንዲሰጠው ማድረግ ስለተፈለገ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

መንግስት ግን  ፍርድ ቤት ላይ ባለው እምነት የተነሳ ሁኔታዎችን አመዛዝኖ የዋስትና መብት ከፈቀደ አቃቤ ህግ የተሰጠው የዋስትና መብት ላይ ይግባኝ  እንዲጠይቁ የሚያደርግ መብት በግልፅ አለመኖሩ፣ ሁለት አይነት አተረጓጎም እንዲይዝ እንዳደረገው የሚያነሱት ባለሙያው እንደሚያነሱት በግልፅ ካለተፈቀደ እንደ ተከለከለ ይቆጠራል የሚሉ ባለያዎች አሉ፡፡ ስለዚህም እንደዚህ አይነት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ላይ መብትን ለመገደብ በግልፅ የተቀመጠ ስልጣን ሊኖር እንደሚገባም ያነሳሉ፡፡

በሂደቱም ፍርድ ቤቱ ሊያይ የሚገባው  ይግባኝ ማለት የሚችል መብት ባለው ላይ ነው እንጂ በግልፅ ያልተቀመጠ ስልጣን አለኝ በሚለው ላይ አለመሆኑ ይጨምራሉ፡፡ በተጨማሪ እንደ ማጠቃለያ የህግ ባለሙያው የተናገሩት ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ቀድሞውንም ሲፈቅድ ካመዛዘነ በኋላ ስለሚሆን እስክ ጭራሹም ከዛ ሂደት በኋላ የዋስትና መብት ለምን ተፈቀደ ብሎ አቃቤ ህግ ይግባኝ የሚጠይቅበት የህግ አግባብ የለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ሃሳብ የሰጡ የህግ ባለሙያዎች እንዳሉን ደግሞ  እንደዚህ ሊያስደርግ የሚያስችል ምንም አይነት ህጋዊ ምክንያት አለመኖሩን ተናግረዋል ይህም ፍርድ ቤት የዋስትና መብት የሰጠው ሰው ከእስር ቤት የመውጣት ጉዳይ እድል ሳይሆን መብት መሆኑን ጨምረው አንስተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹እኔም እንደዚህ አይነት ችግር አጋጥሞኝ ነበር› የሚሉት የህግ ባለሙያው ይሄ ህገወጥ ድርጊት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ህገ ወጥነቱም  በፖሊስ እና በአቃቤ ህግ መካከል የሚደረግ ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን እና የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አክብሮ ተጠርጣሪን ለቆ አቃቢ ህግ ይግባኝ ከጠየቀበት ግን በይግባኙ መሰረት የተፈቀደው ዋስትና መብት አክብሮ፣ ትክክል አይደለም ከተባለ ግን ተጠርጣሪን ዳግም መያዝ ይችላል እንጂ ፤ እጁ ላይ አቆይቶ መጠየቅ አይችልም ብለዋል ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፖሊስ በበኩሉ የአቃቤ ህግ ይግባኝ ማለት አለማለት አይመለከተውም ይልቁንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ማክበር  ብቻ ከፖሊስ  እንደሚጠበቅ ያስረዳሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱ እንዲከበር የመታወቂያ ዋስም ይሁን  የገንዘብ ዋስ እነዚያን አሟልቶ ሲገኝ ፖሊስ መልቀቅ ብቻ እንደሚጠበቅበት አንስተዋል ፡፡ ይህንንም ጥያቄ ቢሆን ተጠርጣሪው የሚያቀርበው ለፖሊስም እናለአቃቤ ህግ ሳይሆን  ለፍርድ ቤቱ መሆኑን ገልጸዋል ከዚያም ፍርድ ቤቱ  በተራው ትዕዛዝ ሊሰጣል እንደሚችል ያነሳሉ፡፡  ይህንን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተቀበለ ማንኛውም የሕግ አካል በእጁ  ላይ የሚገኝን የትኛውም ተጠርጣሪ የመልቀቅ ግዴታ አለበት ይላሉ፡፡

ይሄ ሊሆን የማይችልበት ሁኔታ ግን ሊኖር እንደሚችል በመደበኛው ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ውስጥ መኖሩን እና አቃቤ ህግ ይግባኝ መጠየቅ እንዲችል የሚፈቅድለት  ዋስትናውን ሊያስከለክል የሚችል አዲስ ነገር ያገኘ ከሆነ የዋስትናው መብት እንዲሻሻል መጠየቅ እንደሚችል ሌላናው የህግ ባለሙያ  ለአዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ አብራርተዋል፡፡

ይህን ክፍተት በማየት እየተዘጋጀ ያለው ረቂቅ ህግ ሊያየው እንደሚችል ይገመታል፡፡ለ60 ዓመታት ገደማ በሥራ ላይ የቆየው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እንዲሻሻል ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ የሚንስትሮች ምክር ቤት መስከረም 16/2013 ባካሄደው ስብሰባ መወሰኑ ይታወሳል። በዚህም ምናልባትም ክፍተቱን ሊሞላ እንደሚችል ከሰሞኑ ሕጉን በማርቀቅ ሂደት ለረጅም ጊዜ የተሳተፉት ሙሉወርቅ ሚደቅሳ  እንስተዋል፡፡

“በአጠቃለይ ረቂቅ ሕጉ ሲተገበር አብዛኛውን ሥራ ለፖሊስ እና ለዐቃቤ ሕግ በመስጠት ፍርድ ቤት ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ ተጠርጣሪዎች እና ተከሳሾች ረዥም ጊዜ ፍትሕ ሳያገኙ የሚቆዩበትን ጊዜ ያስጥራል፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን አስሮ ከመመርመር ይልቅ ምርመራ አከናውኖ ወደ መያዝ እንደሚገባው ስለሚያደርግ ትልቅ እፎይታ ሊሰጥ እንደሚችል ያነሳሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል የዋስትና መብት፣ የጊዜ ቀጠሮ እና የቅጣት አፈጻጸሞች ላይ ለውጦች እንደሚኖር ጠቁመዋል።

  • የዋስትና መብት

ብዙ ጊዜ ጠበቆች ደንበኛዬ ተጠርጥሮ የታሰረበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያስከለክል አይለደም’ ሲሉ ዐቃቤ ሕግ በተቃራኒው ‘የዋስትና መብት መሰጠት የለበትም’ የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ መስማት የተለመደ ነገር ነው።

የሕግ ባለሙያው  ሙሉወርቅ ሚደቅሳም የዋስትና መብት ብዙ አጨቃጫቂ ነገሮች እንደሉት ይናገራሉ። ይህ ረቂቅ አዋጅም አጨቃጫቂ የሚባሉ የዋስትና መብት ጉዳዮችን ግልጽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይጠቅሳሉ።

በኢትዮጵያ እስካሁን የተለመደው የገንዘብ ዋትስና መሆኑን በማስታወስም፤ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተጠርጣሪው በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ ወደ መንግሥት ተቋም እየቀረበ ሪፖርት እያደረገ ከዚያ ውጪ ሥራውን እንዲሰራ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ይናገራሉ።

  • የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ

መርማሪ ፖሊስ በያዘው ተጠርጣሪ ላይ ምርመራ ለማድረግ ፍርድ ቤትን በተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ ይስተዋላል።

ነባሩ የሥነ ሥርዓት ሕግ መደበኛው በሚባለው ወንጀል የ14 ቀን በጸረ-ሽብር ደግሞ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድ እንሚችል ያስቀምጣል። ይሁን እንጂ ነባሩ ሕግ፣ ገደብ አያስቀምጥም። “ለምን ያክል ጊዜ ነው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የሚያስቀምጠው የሚለው ላይ ገደብ የለም” ይላሉ።

አዲሱ ሕግ ግን ለወንጀሎቹ ዝቅተኛ ወንጀል፣ መካከለኛ ወንጀል እና ከፍተኛ ወንጀል የሚል ደረጃ በማውጣት የምርመራ ቀን ብዛት እና ገደብ ላይ ጣራ ማውጣቱን ይናገራሉ ሙሉወርቅ ይናገራሉ።

“ይሄ ከተከሳሾች መብት አንጻር ጠቃሚ ድንጋጌ ነው። ለምሳሌ መካከለኛ ለሚባሉ ወንጀሎች መርማሪ ፖሊስ ከሁለት ጊዜ በላይ የምረመራ ጊዜ መጠየቅ አይችልም።”

በተቻለ መጠን አንድ ተጠርጣሪ ከመያዙ በፊት ፖሊስ ማስረጃ እንዲሰበሰብ ጥረት የሚያደርግ ሕግ ነው ይላሉ ሙሉወርቅ።

“ተጠርጣሪው ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ አውቆ እራሱን ለመሰወር እና ማስረጃ ለማጥፋት የሚሞክርበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ ፖሊስ የምረመራ ስራውን ጨርሶ  መያዝ እንዳለበት ያስቀምጣል። ተጠርጣሪን ይዞ ማስረጃ የመፈለግ ሂደት መቀየር እንዳለበትም ያስቀምጣል፡፡

  • የቅጣት አፈጻጸም

ነባሩ የሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ የቅጣት አፈጻጸም ዝርዝር ነገሮች የሉትም። ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ተፈጻሚ ባይሆንም የሞት ቅጣትን ፍርድ ቤቶች እንደሚያስተላልፉ የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።

ይህ የሞት ቅጣት በምን መንገድ ነው መፈጸም ያለበት? የሞት ቅጣት የተበየነበት ሰው የሞት ፍርዱ ወደ የእድሜ ልክ እስራት ሳይቀየርለት ወይም የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ ሳይሆንበት ለምን ያህለ ጊዜ ይቆያል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ አዲሱ ሕግ ዝርዝር የአፈጻጸም ድንጋጌዎች ይዟል።

ከሞት ቅጣት በተጨማሪ ዝርዝር የሆነ የገንዘብ ቅጣት እና የእስራት ቅጣት ላይ ዝርዝር የአፈጻጸም ድንጋጌዎችን መያዙን  ሙሉወርቅ  ከቢቢሲ ጋር ከነበራችው ቆይታ አንስተዋል።

 

 

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here