የአዲስ ማለዳ የአንድ መቶ ሳምንታት ጉዞ!

0
700

የዛሬዋ አዲስ ማለዳ ለአንድ መቶኛ ዕትም መድረስ ያን ያክል ባያኩራራም ያስደስታል! ደስታው ለምን ቢሉ ያለማቋረጥ እዚህ ላይ መድረስ በቀላሉ አይቻልምና የሚል ምላሽ አለው። በሌላ በኩል ደግሞ አብረዋት፣ ወይም ቀደም ብለው አሊያም ዘግየት ብለው የጀመሩ ጋዜጦች በሚያሳዝን መልኩ መንገድ ላይ መቅረታቸውም ተጠቃሽ ነው። ላለመኩራራት ደግሞ በአገራችን በግል ዘርፍ ከኹለት ዐሥርታት በላይ የቆዩ ጋዜጦች በመኖራቸው ነው።

የሆነው ሆኖ አዲስ ማለዳ ከየት ወዴት የሚለውን በዚህ ርዕሰ አንቀጽ ላይ ለመጻፍ መነሳታችን የኋላ ከሌለ የለም የፊቱ የሚለው መርኅ መሰረት አደርገን ጋዜጣዋ የመጣችበትን መንገድ ዓይታ የጎደላትን ለመሙላት ይረዳታል ከሚል እሳቤ መሆኑ ይሰመርበት።

ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባት መሰረት ነው። የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ደግሞ ይህንን ዕሴት ዕውን ለማድረግ እና ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚጠብቃቸውን የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ አማራጭ መድረክ ናቸው። በመረጃ ያልበለጸገ ማኅበረሰብ መንግሥትን ተጠያቂ የማድረቅ አቅሙ ውስን ነው። የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ሊዳብር የሚችለውም የሐሳብ ሙግትና ምክንያታዊነት እየጎለበተና ባህል እየሆነ ሲመጣ ነው። እነዚህን ዐቢይ ተልዕኮዎች ለማሳካት ከግለሰብ፣ ከቡድንና መንግሥት ተጽዕኖ የተላቀቁና በስርዓት የተደራጁ የብዙኀን መገናኛ ተቋማት ያስፈልጋል።

የመገናኛ ብዙኀን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። አንዳንዶች እንዲያውም ዘርፉ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከጀርባ አጥትነት ሚና ጋር ያመሳስሉታል።

አዲስ ማለዳ ዜጎች ማወቅ የሚገባቸውን ወቅታዊ መረጃዎች ታደርሳለች፤ ትምህርት አዘል ሥልጡን የውይይት መድረክ በመፍጠር የሠለጠነ ማኅበረ-ለፖለቲካዊ ተዋስዖ ከነውስንነቱ እንዲዳብር የበኩሏን ተወጥታለች፤ እየተወጣችም ትገኛለች። በተጨማሪም የምርመራ ጋዜጠኝነትን በመተግበር የአገር ሀብት እንዳይባክን፣ የተደራጀ ወንጀል እንዳይስፋፋና በሥልጣን መባለግና ያለአግባብ መጠቀምን በማጋለጥ ዴሞክራሲያዊነት እንዲያብብ፣ የመብት ተጠያቂነት እንዲጎለብት ብሎም ኀላፊነትና ተጠያቂነት በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በመንግሥት ደረጃ እንዲዳብር በመጠኑም ቢሆን የበኩሏን ሚና እየተወጣች ትገኛለች። አዲስ ማለዳ በዚህ ረገድ ከሠራቻቸው ጥቂት ማሳያ አብነቶችን ወረድ ብለን እንጠቅሳለን።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ገለልተኛና ነፃ መድረክ ነች። ታማኝነታችን እና ወገንተኝነታችን ለሙያችን፣ ለእሴቶችን እና ለዲሞክራሲያዊ መርሆቻችን መሆኑን በተግባር እስካሁን አስመስክረናል ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።

በርዕይዋ በኢትዮጵያ የአራተኛነት መንግሥት ሚናዋና ለመውጣት እና ዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል ነጻ፣ ገለልጸኛና ተዓማኒ መገናኛ ብዙኀን መሆንን የሰነቀችው አዲስ ማለዳ፣ በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑንን ዓላማ አድርጋ እየሠራች ብትገኝም የምኞቷን ያክል አሳክታለች የሚል ቅዠት ግን የላትም፤ ገና ብዙ ይቀራታልና።

አዲስ ማለዳ ዕሴቶቼ ናቸው ብላ ያነገበቻቸውን ሐቀኝነት፣ ምክንያታዊነት፣ ብዝኀነት፣ ስልጡንነት፣ ጨዋነት እና ሙያተኝነት ጋር የማይፃረሩ ሐሳቦችን እና አስተያየቶችን ሁሉ እያስተናገደች ከርማለች፤ ወደፊትም ታስተናግዳለች። ከዚህ ባሻገር ዝርዝር ዓላማዬ ብላ የለየቻቸው ለተደራሲያን ወቅታዊ መረጃዎችን ማቅረብ፣ ትምህርት አዘል ሥልጡን ውይይት ማስተናገድ፤ ዴሞክራሲያዊነት እንዲያብብ፣ የመብት ጠያቂነት እንዲጎለብት እንዲሁም ዜጎች፣ በተለይም ደግሞ ድምጽ አልባ ለሆኑት ልሳን መሆንን ያካትታል። እነዚህን ዓላማዎችን እያሳካች መሆን አለመሆኑን መፍረድ የተደራሲያንም ቢሆን፣ ለማታወስ ያክል አንዳንዶቹን በመጠቃቀስ ለአንባብያን እናስታውሳል።

በአንድ መቶ ሳምንታት ቀይታዋ፥ አዲስ ማለዳ ብዙ ዘገባዎችን ያስተናገደች ሲሆን አንዳንዶቹ ዘገባዎች ወይም ጽሑፎች ተደራሲያኖቿን እንዲሁም የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ትኩረት እንዲሁም ሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙኀንን የሳቡ፣ ያወያዩ ጉዳዮች ሆነው አልፈዋል። ይህም አዲስ ማለዳን ለማስተወወቅ የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ በተለይ በብዙዎች ዘንድ የምትታወቀው በየትኛውም መገናኛ ብዙኀን ያልተሰሙ ዘገባዎችን መሥራቷ ነው፤ በባልደረቦቿ አጠራር ‘ፕሮጀክት ዜና’ ይባላል። አልፎ አልፎም በጥቆማ የምታገኛቸውን አንዳንዶች ‘ጮማ’ የሚሉት ቀልብ ሳቢ ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ ተሠርተው ሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙኀን በፍጥነት የተቀባሏቸው፤ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይም የናኙ ወይም በከፍተኛ ደረጃ የተሰራጩ ዘገባዎች ለመሥራትም ታድላለች።

ከበርካታዎቹ ኹለቱን ለአብነት መጥቀስ ደራሲዎቿን እናስታውስ፤ አንደኛው መስከረም 17/2012 በፊት ገጽ ላይ ያስነበበችው “የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ በሚል ሥያሜ ኢሕአዴግ ውሕድ ፓርቲ ሊሆን ነው” የሚለው አልቦ ዜናዋ በዚህ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ሰበር ዜናዋ ነበር። የዜናውን ፍንጭ ረቡዕ አግኝታ፣ ኀሙስና አርብን ለማረጋገጥ ላይ ታች ስትል ቆይታ ዓርብ ምሽቱን ተጽፎና ተዘጋጅቶ ወደ ኅትመት ገብቶ እስኪወጣ ድረስ በመደበኛ ብዙኀንም ይሁን በማኅበራዊ ገፆች ምንም ሳይባል ነው ዜናውን ለአንባብያን ያደረሰችው። ይህ አጋጣሚ ለአዲስ ማለዳ መታወቅ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ አደርጓል።

በሌላ ቀን ደግሞ ፓስፖርት ለማደስም ይሁን አዲስ ለማውጣት ዜጎች በተቸገሩበት ወቅት፥ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ሠራተኞች ይህንን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚውን በመጠቀም ከጉዞ ወኪል ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር የሙስና አሠራር ሰንሰለቶችን በመዘርጋት ዜጎችን ሲያጉላሉ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፋ የምርመራ ዘገባ ማቅረቧን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን የሚያጣራና ለችግሩ መፍትሔ የሚሰጥ ግብረ ኀይል ወዲያውኑ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱና በአጭር ጊዜ ውስጥ ላጋጠመው ችግር መፍትሔ ለመስጠት መሞከሩ አዲስ ማለዳን ካኮሯት ሥራዎቿ ተርታ ይመደባል።

አሁን አሁን በአገራችን መገናኛ ብዙኀን እምብዛም የማይሠራውን የምርመራ ዘገባ እና ትንታኔ አዲስ ማለዳ አቅም በፈቀደ መጠን ለመሥራት ታትራለች። በዚህም ከፍተኛ ትኩረትን መሳብ ከመቻሏም ባሻገር አበረታች የሞራል ድጋፍን አትርፋበታለች። ከእነዚህ የምርመራ ዘገባዎች እና ሰፊ ትንታኔዎች መካከል ስለ አንዳንድ የፕሮቴስታንት አጭበርባሪ የሃይማኖት አስተማሪዎች፣ በአዲስ አበባ በዘመነ ኮሮና የከተማዋ ከበርቴዎች የራቁት እና የግብረሰዶም ምሽት ቤቶች ክራሞት እንዲሁም የአደንዛዥ ዝውውርና ተጠቃሚነት ዙሪያ የተሠሩት የሚገኙባቸው ሲሆን የብዙዎችን ቀልብም ስበዋል፤ በአስተማሪነታቸውም ተወድሰዋል። በተጨማሪም በወንጀል መከላከል ላይ ለተሠማሩ የመንግሥት አካላትም መነሻ ፍንጭ ሰጥቷቸዋል የሚል እምንት አዲስ ማለዳ አላት።

ይሁንና እነዚህ የምርመራ ዘገባዎች በሚሠሩበት ወቅት እንዲሁም ከተሠሩም በኋላ ከፍተኛ ጫና ከተለያዩ ወገኖች የነበሩ ቢሆንም ከማስፈራሪና ዛቻነት ግን የዘለሉ አልነበሩም።

የአዲስ ማለዳ የአንድ መቶ ሳምንታት ጉዞዋ አልጋ በአልጋ ነበር ማለት አይቻልም። ሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙኀን  በተለይ የኅትመቶቹ የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ሁሉ አዲስ ማለዳም ተጋፍጣለች። የኅትመትት ዋጋ በዋናነት በየጊዜው ማሻቀብ፣ መረጃ በተፈለገው ጊዜና መጠን ልክ ለማግኘት ወይም ማረጋገጥ አለመቻል፣ የዘጋቢዎች የሙያ ብቃት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ ተቋማዊ የአቅም ውስንነት እንዲሁም የሠራተኞች በሥራ ገበታ ላይ እምብዛም ሳይቆዩ መልቀቅ ተጠቃሽ ተግዳሮቶች ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ማለዳ በሥርጭት በኩል ያጋጠሟትን ተግዳሮት እስካሁን ድረስ የተከተላት ዘልቋል።  በተጨማሪም በቅርቡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና (የኦቪድ 19) ወረርሺኝ ምክንያት በከፍተኛ ችግር ቢያጋጥማትም ችግሩን በመቋቋም ለአንድም ቀን ኅትመቱ ሳይቋረጥ ማስቀጠል መቻሏ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ነው።

አዲስ ማለዳ በተጓዘችባቸው አንድ መቶ ሳምንታት ብዙም ባይባልመ የዘገባ ዝንፈቶች ፈጽማ ታውቃለች፤ ወዲያውኑ የማስተካከያ እርምጃዎችን ብትወስድም።  የአቅም ማነስ፣ የሰው ሐሳብን በትክክል ዕውቅና ሳይሰጡና ምንጭ ሳይጠቅሱ መሥራት፤ ባስ ሲልም እንደራስ አድርጎ ማቅረብ ሲሆኑ እነዚህን ግድፈቶች ባጋጠሙ ጊዜ ወዲያውኑ ማስተካከያዎች እንዲደረጉና ተመጣጣኝ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ እንዲታረሙ አድርጋለች። በተጨማሪም የተደራሽነት ችግር በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ መወሰኗ የጋዜጣዋ ተጠቃሽ ድክመት ነው።

የአዲስ ማለዳ ከኅትመት ጎን ለጎን ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲጅታል አማራጭ መድረኮችን በደንብ መጠቀም ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እየሠራች ትገኛለች። በተለይ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ያላትን አማራጭ ተዓማኒ የዜና ምንጭነቷን በመጠቀም እየሠራች ትገኛለች። በፌስቡክ፣ በቲውተር፣ በቴሌራም፣ በዩቲዩብ እንዲሁም በይፋዊ ድረገጿ ተደራሽነቷን እያሰፋች ትገኛለች፤ በተጠናከረ መንገድ ለመውጣት ብዙ ጥረቶችን እንዲሁም መሬት የወረዱ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ትገኛለች።

በዚህ አጋጣሚ ሳይጠቀስ የሚያልፈው ጉዳይ፥ አዲስ ማለዳ በአንድ መቶ ሳምንታት ቆይታዋ በአዲሱ ዓመት 2013 መጀመሪያ ላይ ራሱን የቻለ ወርሃዊ “አዲስ ማለዳ መጽሔትን” በገጸ በረከትነት ማቅረብ መቻሏ ነው። አዲስ ማለዳ መጽሔት ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሠራ ዓላማ የሰነቀ ሲሆን በቤተሰብ ላይ ልዩ ትኩረት ያደርጋል። ባህልና ማኅበረሰብ፣ ትምህርት፣ ታሪክ፣ ሥነ ፆታ፣ አካባቢና ተፈጥሮ እና ሌሎች አምዶች ያሉት ሲሆን በመልካም አርዓያነት የሚጠቀሱ ግለሰቦች ትውልዱን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ይሠራል፤ የማይታወቁ ነገር ግን በኅብረተሰብ ላይ ለውጥ በማምጣት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ተቋማትንም ያስተዋውቃል። እዚህ ላይ በአንክሮ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ፥ መጽሔቱ ያለምንም የዕድሜ ገደብ፣ የፆታ ልዩነት፣ የዕውቀት ደረጃ እና የሕይወት ተመክሮ የሚነበብ መሆኑ ነው።

በመጨረሻም መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው አዲስ ማለዳ በእስካሁን ጉዞዋ የምትኩራራ ሳይሆን ከድክመቷ እየተማረች፣ ጥንካሬዋን ይበልጥ እያጎለበተች የምትቀጥል እንዲሁም እስካሁን ለሄደችበትም ሆነ ለምትቀጥለው ጉዞ የአንባቢዎቿ ድጋፍ፣ አስተያየትና ትችት አሁንም ይቀጥል ስትል ላለፈው ምስጋና ለወደፊቱ ደግሞ ጥሪዋን ታቀርባለች።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here