ከመቶ ሳምንታት – ለትውስታ

0
1234

አዲስ ማለዳ ላለፉት 100 ሳምንታት ያለማቋረጥ በየሳምንቱ ቅዳሜ ማልዳ ለአንባቢያን ስትቀርብ ቆይታለች፤ እነሆ ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2013 100ኛ እትሟ ሆነ። አሐዱ ብላ ስትጀምር በገባችው ቃል መሠረትም ሙያዊ ሥነ ምግባር ሳይጎድልባት፣ የተለያዩ ሐሳቦችን እያስተናገደች፣ ቃሏን ጠብቃ እዚህ ደርሳለች። ዛሬ ካደረሳት መንገድ ይልቅ የሚቀራት ብዙ መሆኑ እሙን ነው። አሁን ግን መቶኛ ሳምንቷን፣ መቶኛ እትሟን ምክንያት በማድረግ አረፍ ብላ በትውስታ የቀደመውን ልታስቃኛችሁ ወድዳለች።

በዚህ በአንደበት አምድ የፖለቲካ ሰዎችን ጨምሮ ምሁራንና መምህራን፣ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ በጎ አድጊዎች፣ አሸናፊዎችና ብርቱዎች፣ ከአንጋፎች እስከ ወጣኒ ወጣቶች ድረስ በእንግድነት በየሳምንቱ ቀርበዋል። ከእነዚህ መካከል በዚህ እትም የተወሰኑትን በማንሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ ካነሱት ሐሳብ መካከል የተወሰነውን በመምረጥ የአዲስ ማለዳው ዳዊት አስታጥቄ ተከታዩን አሰናድቷል

‹‹በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ታግሎ የሚያውቅ ድርጅት ኖሮ አያውቅም››

ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር)

ፖለቲከኛና የ‹ምሁሩ› መጽሐፍ አዘጋጅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካቶች የኢትዮጵያ ትልቁ ተግዳሮት የዘውግ ብሔርተኝነት እንደሆነ በስፋት ሲናገሩ ይሰማል። መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?

ዐቢይ አሕመድ ማለት የኦዴፓና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ናቸው። እርሳቸው ራሳቸው ዛሬ ትልቁ ተግዳሮታችን ብሔርተኛነት ነው ብለው ነው የሚያስተምሩን። ልብ አድርግ! ራሳቸው የአንድ ብሔርተኛ ፓርቲ ሊቀ መንበር መሆናቸውን።

በመጀመሪያ እርምጃ ነገዳዊ ብሔርተኝነት ወይም በአጠቃላይ ብሔርተኝነት ከታሪክ የተፈጠረ ክስተት እንጂ እንደው ከሰማይ ዱብ ያለ መጥፎ ነገር አይደለም። የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለያየ እምነት የሚያራምዱ፣ የተለያየ ሐሳብ፣ የተለያየ ማኅበረ ሥነ ልቦና ያላቸው ሕዝቦች ከመኖራቸው ጋር የተያያዘ ነው።

ነገድ በጣም ለስላሳ አስተሳሰብ ነው። ያንን ለስላሳ ሐሳብ ወስደው ተበድያለሁ ማለት ሲጀመርና የፖለቲካ ልሂቁ ሲገባበት ወደ ርዕዮት ይቀየራል። ስለዚህ የመጀመሪያ ነገር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትልቁ ተግዳሮት ብሔርተኝነት መሆኑን መቀበል ነው። በትምክህተኝነትም በጠባብነት በሚሉት ማለት ነው።

ችግሩ መፈታት አለበት። ለመፍታት ደግሞ ምን መደረግ አለበት የሚለው ቀጣይ ጥያቄ ነው የሚሆነው። መልሱ ደግሞ ከዓለም ታሪክ መማር ነው። በመጽሐፌ ውስጥ ኢትዮጵያ ልትማር የምትችልባቸውን ስምንት አገራት ጠቅሻለሁ። ብሔርተኝነትን በመፍታት ረገድ ሊብራል ዴሞክራሲ ነው የሚያዋጣው። ሶሻሊዝም ብሔርተኝነትን አልፈታም፤ እንዲያውም የበለጠ ወደ ከረረ ሁኔታ ውስጥ ነው የከተተው። መሰመር ያለበት ብሔርተኝነት የሕዝቡ ርዕዮት አይደለም፤ የልሂቁ እንጂ።

ታኅሳስ 9 ቀን 2011

‹‹በብሔራዊ መግባባት እነዚህን ለብዙ ዘመናት ተከማችተው የመጡ ችግሮች ሁሉ በአንዴ እንፍታ ማለት አይቻልም።››

መረራ ጉዲና (/)

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር

የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ መሠረታዊ የምንላቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?

ኢትዮጵያ ወዴት ትሂድ፣ አንድ አገረ አለን የለንም የሚለው ላይ መስማማት ያስፈልጋል። እየታገልን ያለነው የተለያዩ አገሮችን ለመፍጠር ነው ወይስ የተሻለ አንድ አገርን ለመገንባት ነው? የአገሪቱ አንድነት ላይ አቅጣጫ ማስያዝ የግድ ያስፈልጋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ላይ መስማማት አለብን። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሁንታን ያገኘው ፓርቲ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን የሚወጣበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝብ ይሁንታን ያላገኘው የሚወርድበትና ትግሉን የሕዝብ ይሁንታ እስኪያገኝ የሚቀጥልበት ሥርዓት ማለት ነው።

ከዚህ ውጪ ያሉ ጉዳዮችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ፖሊሲያቸው ቢያደርጉት ጥሩ ነው። ለምሳሌ የቋንቋ ጥያቄን፣ ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም እንከተል የሚለውን፣ የግለሰብ መብቶችንና የማኅበረሰብ መብቶችን እና የመሬት ጥያቄን የመሳሰሉትን ማለቴ ነው። የኢትዮጵያ ችግር ኢሕአዴግ 27 ዓመታት የከፋፍለህ ግዛ ሴራ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም አላመጣም። የመድረክ አቋም ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም እስከተገነባ ድረስ የግለሰብ መብትና የቡድን መብቶች አንድ ላይ መስተናገድ ይችላሉ የሚል ነው።

በብሔራዊ መግባባት እነዚህን ለብዙ ዘመናት ተከማችተው የመጡ ችግሮች ሁሉ በአንዴ እንፍታ ማለት አይቻልም። ችግሮች መፈታት ያለባቸው ደረጃ በደረጃ ነው። አለበለዚያ ችግሩ ተቃዋሚውን በመከፋፈልና አገሪቱን ሌላ ዙር ቀውስ ውስጥ ይከታታል።

እንዴት አብረን እንኑር፣ ምን ዓይነት የመንግሥት ቅርጽ ይኑረን፣ ሁላችንንም በእኩልንት የሚያስተዳድር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት እንፍጠር በሚሉት ዙሪያ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተነጋገሩና እየተደራደሩ መፍታት ላይ መድረስ ይሻላል።

ኅዳር 10፣2011

‹‹እዚህ አገር መንግሥት በጣም ተዳክሟል፤ እንደኔ ያሉ ሰዎች ከገፋነው ፍርክስክሱ ሊወጣ ይችላል።››

ጃዋር መሐመድ

የኦፌኮ አማራር አባል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ከውጪ ለመጡት ፖለቲከኞችና ተሟጋቾ የሰጡትን ትኩረት ያክል ላንተ አልሰጡም ይባላል። በዚህ ምክንያት የጃዋር የፖለቲካ ተሳትፎና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ እየቀነሰ ነው የሚል ዕይታ አለ። እዚህ ላይ ምን ትላለህ?

አልስማማም! እዛ [አሜሪካ] ሲመጡ ተወያይተናል፤ እዚህም ስመጣ በተደጋጋሚ ተወያይተናል። መንግሥትን ሆነ ተቃዋሚውን የመቀላቀል ፍላጎት የለኝም፤ በመብት ተሟጋችነቴ ነው መቀጠል የምፈልገው። እንደተሟጋች ከመንግሥት በመጠነኛ ርቀት መራቅ አለብህ። ምክንያቱም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ነህ ብሎ ካሰበ ላንተ የሚኖረው ቀረቤታ የዛኑ ያክል ይሆናል። መንግሥትንም በጣም ከቀረብክና ትችት የምትሰጣቸው ከሆነ ‹እንዴት ጉያዬ ሥር ሆኖ ይተቸኛል› የሚል ነገር ይመጣል። ስለዚህ ተከባብረህ በመጠነኛ ርቀት ላይ መገኘቱ አስፈላጊ ነው።

ተፅዕኖና ተሳትፎን በተመለከተም ቀንሷል። ለምን?

ምክንያቱም በጣም ተፅዕኖ ሲፈጠር የነበረው የአንባገነን ሥርዓት ስለነበረ ነው። አሁን ለውጡን እየመሩት ወደ ዴሞክራሲ እያሸጋገሩን ነው የሚል እምነት አለኝ።

ኹለተኛ እዚህ አገር መንግሥት በጣም ተዳክሟል፤ እንደኔ ያሉ ሰዎች ከገፋነው ፍርክስክሱ ሊወጣ ይችላል። ስለዚህ መጠንቀቅ አለብን። ተቃዋሚቹም የሚንቀሳቀሱት በጣም በጥንቃቄ ነው። እኛም ቢሆን መንግሥትን የመደገፍ ሥራ ነው እየሠራን ያለነው። ይሁንና ‹እንደዚሁ እንቀጥላለን ወይ› ለሚለው መልሴ እንደሁኔታው የሚል ነው። እነዐቢይ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር የሚሔዱ ከሆነ ድጋፋችንን እንቀጥላለን፤ ወደ መቀልበስ ከሔዱ ተፅዕኗችን እየጨመረ ይሔዳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

 ‹‹አገሪቷ ውስጥ ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ያካተተ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ችግሮች መፍታት አይቻልም።››

ከአንዳርጋቸው ጽጌ

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ችግር ለማቃለል አንዳንዶች የሽግግር መንግሥት ወይም የሽግግር ምክር ቤት መቋቋም አለበት በሚል ይሞግታሉ። በዚህስ ላይ የእናንተ አቋም ምንድን ነው?

አገሪቷ ውስጥ ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ያካተተ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ችግሮች መፍታት አይቻልም።

አሁን ዐቢይ እየሠራ ያለው ተቋማትን ነፃ ማድረግ፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ሽብርተኛ የተባሉ ድርጅቶችን በሙሉ በአገር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ የሽግግር መንግሥት ከሚሠራው በላይ በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ ነው ብዬ አስባለሁ። የሽግግር መንግሥት ቢመጣ በአገሪቷ ውስጥ የበለጠ ቀውስ ይፈጥራል።

መጀመሪያም ቢሆን ከ80 በላይ ፓርቲዎች ባሉበት አገር የሽግግር መንግሥት ማድረግ የሚታሰብ አይደለም። ወሳኝ በመሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት እና የሕግ ጉዳዮች ላይ መምከር ይገባል። እሱም ላይ ቢሆን ከፓርቲዎች ብዛት አንጻር መንግሥት የሆነ ነገር ማድረግ አለበት።

በፌዴራል መንግሥቱና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?

በመጀመሪያ ፌደራላዊ ስርዓቱ ሲዋቀር እያንዳንዱ ክልል ራሱን የቻለ ማዕከላዊ መንግሥት መገዳደር የሚችል ጉልበት በሚኖረው ደረጃ ሠራዊትና ሌላ ነገር እንዲያቋቁሙ የተደረገበት መንገድ ውሎ አድሮ አሁን ያለው ሊፈጠር እንደሚችል ተነጋግረን ነበር።

በ1985 ባቀረብኩት ክርክር የብሔር መብት ማስከበር ቋንቋን፣ ባሕልን ማሳደግ፣ መጠቀምና ማስጠበቅ ጥሩ ሆኖ ሳለ ዞሮ ዞሮ ዘር ወደሚወልደው የብሔር አደረጃጀት መግባት አደገኛ መሆኑን አመላክቻለሁ። እያንዳንዱን አካባቢ ሥም እየጠራሁ ድርጅት መኖር የለበትም እስከማለት ድረስ ሔጃለ። አሁን የምናየው ፌደራሊዝሙ የተደራጀበት ውጤት ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

 ‹‹ሕወሓት ያለው አንድ አማራጭ ሥልጣን ለሕዝብ አስረክቦ ተቃዋሚ ሆኖ መቀጠል ነው››

አብረሃ ደስታ

የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዓረና) ሊቀመንበር

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ክልል መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ግልጽ የሆነ የአቋም ልዩነቶች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። አሁን ባለው አካሔድ የሕወሓት ዕጣ ፈንታ ምንድነው?

ሕወሓት አሁን ካለው የፌደራል መንግሥት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ጥረት ማድረግ የሚችል ይመስለኛል። ቢሆንም ሕወሓት በጣም የተጠላ ድርጅት ነው። በጣም ብዙ ችግር፣ ግፍ ሲፈጽም ነበረ። ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቀበለውም፤ የትግራይ ሕዝብም አይቀበለውም። በመሆኑም በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ይቀበሉታል ብለን አናስብም። በዚህ ሁኔታ ሕወሓት ያለው አንድ አማራጭ ሥልጣን ለሕዝብ አስረክቦ ተቃዋሚ ሆኖ መቀጠል ነው። በትግራይ ክልል ከተመረጠ ግን ሊያስተዳደር ይችላል። ስለዚህ የግድ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስላልተስማማ ይጠፋል ማለት አይደለም።

ለውጡ በሕወሓት ብዙም ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም ይባላል። በሕዝቡና በእናንተ በኩል ያለውን እውነት ቢገልጹልን?

እኛ ለውጥ መደረግ እንዳለበት እናምናለን፤ ለውጡንም እንደግፋለን። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የለውጡ ሒደት በትክክል እየተመራ አይደለም ብለን እናምናለን፤ ምክንያቱም መጀመሪያ ትኩረት ማግኘት ያለበት የፀጥታ፣ ሠላም እና መረጋጋት መኖር ላይ ነው። መንግሥት በእያንዳንዱ አካባቢ ቁጥጥር ሊኖረው ይገባል።

[ሁኔታዎች] ወዳልተፈለገ [መንገድ] እንዳያመሩ፣ ሕዝቡ እንዳይጋጭ ሕግ መከበር አለበት፣ ስርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል። በድምሩ የለውጡ ሒደት በትክክል እየተካሔደ ነው ብለን አናስብም። ስለዚህ ወደ ዴሞክራሲ የምናደርገው ሽግግር የተሳካ እንዲሆን መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ ብለን እናምናለን።

በነገራችን ላይ የትግራይ ሕዝብ እውነታውን ያውቀዋል። ነገር ግን ሕወሓት አሁን እየተካሔደ ያለውን ለውጥ ‹‹ፀረ ትግራይ የሆነ፣ የትግራይን ሕዝብ ለመምታት የተቃጣ እንጂ የትግራይን ሕዝብ ለመጥቀም አይደለም›› በሚል ነው እየሰበከ ያለው። የትግራይ ሕዝብም ‹‹ለውጡ ሕዝብን ለማጥቃት ወይስ ሕዝብን ለመጥቀም ነው እየተደረገ ያለው›› በሚል ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

 ‹‹አምባገነን ሥርዓትን ለማፍረስ የተጠቀምክበትን ሥልት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመገንባት ልትጠቀምበት አትችልም››

አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር)

በዩናይትድ ኪንግደም ኪል ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር

የትርክት ልዩነቶች ጫፍ ደርሰው ለአገር ሕልውና አደጋ ሊሆኑ አይችሉም?

ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የማንነት ፖለቲካ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ባገኘበት አገር ይህ የማንነት ፖለቲካ በጣም ጫፍ ደርሶ የጋራ ርዕይ በሌለበት፣  ሁሉም ወደ ሥልጣን ሊያደርሰኝ የሚችለው ይሄ ነው ብሎ የረጅም ጊዜ ግብ ሳይያዝ ጉዞ የሚደረግ ከሆነ ትልቅ ስጋት ሊሆን ይችላል።

አንድ ዓይነት የትግል ዘዴን የተወሰነ የትግል ምዕራፍን ለማለፍ ከተጠቀምክ ያንን ምዕራፍ ደግሞ አገር ለመገንባት የሚያስፈልገው ስትራቴጂ እንድንጠቀም ማተኮር ይኖርብናል። ከዛሬ 10 ወራት በፊት የመታገያ ዘዴዎች ዛሬም የምንጠቀምባቸው ከሆነ ትግል ላይ አይደለንም፤ በግብታዊነት እየተንቀሳቀስን ነው ማለት ነው።

ኅብረተሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ የተለያዩ የትግል ደረጃዎችና ስልቶችን መጠቀም ያስፈልጋል።አምባገነን ሥርዓትን ለማፍረስ የተጠቀምክበትን ስልት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመገንባት ልትጠቀምበት አትችልም። አሁን ትርክቶች ገንቢ መሆን መቻል አለባቸው። ተዋስኦው መልሶ ገንቢ መሆን መቻል አለበት። ዝም ብሎ አፍራሽ መሆን አይደለም። እንደ ግለሰብም እንደተቋምም መለወጥ ያስፈልጋል። አተያያችን ከድሮው አቅጣጫ ትንሽ ዞር ማለት አለበት።

አሁን ትልቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ከዚህ በፊት ተጎዳሁ የሚለው አካል ያስብ የነበረው ስለጉዳቱ ስለነበረ፣ ከዛ አመለካከት መውጣት አልቻለም። አሁን ቅርብ ጊዜም ሥልጣን አጣሁ የሚለው አካል ደግሞ ተመልሶ እዛው ተጎዳሁ የሚለው አመለካከት ውስጥ ገብቷል። በሄድክበት አቅጣጫ ሁሉ የምታገኘው የተጎዳ ሕዝብን ነው። ሁሉም ተጎጂ ነኝ በሚልበት ወቅት አጓጊ፣ ቆራጥ የሆነ መጪውን አመልካች የሆነ ርዕይ ለማየት ያስቸግራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

 ‹‹የምርጫ ሥራ አስቸጋሪ ነው። የፈለግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብሆን እንኳን ነገ ጠዋት ተነስቼ እንደ አዲስ ቀን እቀጥላለሁ።››

ብርቱካን ሚዴቅሳ

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

የምርጫ ቦርድ ሥራ ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። ቢሮውን ከመያዞት በፊት የነበረዎት ግምትና ቢሮውን ተረክበው በተግባር ያገኙት ሲነጻጸር ምን ይመስላል?

የዚህ ቤት [ምርጫ ቦርድ] የረጅም ጊዜ ደንበኛ ነኝ። በተለያየ መልኩ አንዱ ምርጫ አልፎ ሌላው ሲመጣ እንደተወዳዳሪ፣ የፓርቲ ጠበቃ፣ ከምርጫ መዛባት ጋር በተያያዘ፣ እንደ ፓርቲ መሪ ወዘተ ስለዚህ ችግሮቹን በደንብ አውቃቸዋለሁ።

በእርግጥ አሁን ቦርዱ ውስጥ ገብቼ ሳየው እንደጠበቅኩት ነው ያገኘሁት። ከግምቴ በጣም የራቀ፣ አስደነገጠኝ የምለው ነገር የለም። [ችግሮቹም] አዲስ ሆኖብኛል ለማለት አልችልም። ምክንያቱም የለመድኳቸውም የማውቃቸውም ስለሆኑ ነው።

አሁን አዳዲስ የፖለቲካ ተዋናዮች አሉ፤ የመገናኛ ብዙኀን በጣም ሊያግዙ ይችላሉ። ለውጡን የሚመጥን ሥራ ካልሠራን አስቸጋሪ እንደሚሆን በደንብ እረዳለሁ። ሥራው ከባድ ነው፤ ከገመትኩት በላይ ግን ከባድ ነው ብዬ እስካሁን አንገቴን አልደፋሁም።

ስለዚህ በብቃት እወጣዋለሁ ብለው ያምናሉ?

እንደሱ ለማድረግ እምነት ባይኖረኝ እዚህ ለምን እቀመጣለው? እንደአገርም እንደግለሰብም ዕድሉ በጣም ዋጋ የሚሰጠው ነው ብዬ አምናለሁ። ያን ዕድል በጣም ወደ ተሻለ ውጤት ለማምጣት የምችለውን በሙሉ አደርጋለሁ። ‹ይሆናል አይሆንም› ብዬ ብዙም አላመነታም፤ እንዲሆን መሥራት ነው ያለብኝ። አዕምሮዬ ውስጥም ያለው ይኸው ነው።

በተለይ ውጪ አገር ቆይቶ ለመጣ ሰው ተስፋ የሚያስቆርጡ ብዙ ነገሮች አሉ። ፍጥነት እና ነገሮች ቀልጠፍጠፍ ብለው እንዲሠሩ ትፈልጋለህ፤ የቴክኖሌጂውም፣ የሰው ኃይል አቅሙም በምትፈልገው መንገድ አይሔድልህም። የፈለገ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብሆን እንኳን ነገ ጠዋት ተነስቼ እንደ አዲስ ቀን እቀጥላለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

‹‹ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር የነዐቢይ ብቻ ኀላፊነት ሳይሆን የእኛም ጭምር መሆኑን እንዲረዱም፣ እንዲያምኑም እንፈልጋለን።››

ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላችሁ ብዙ ጊዜ ይወራል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ አጋጣሚ በሕዝብ በቀጥታ የሚመረጥ መሪ እንዲኖር እንደሚፈልጉ የተናገሩበት አጋጣሚም አለ። በዚህ ዓይነት አብሮ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የመሥራት አጋጣሚው ይኖረናል ብለው ያስባሉ?

የእኛ ፍላጎት ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊ አገር እንዲኖር ነው። ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አገር በአንድ ፓርቲ ላይ ተመስርቶ አይሆንም። ኹለት ሦስት ጠንካራ፣ መወዳደር የሚችሉ፣ የተለያየ አመለካከት ያላቸው፣ አማራጭ ማቅረብ የሚችሉ ፓርቲዎች መኖር አለባቸው ብለን እናምናለን። ጠንካራ የተቃዋቀሚ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ።

ከነዐቢይ ጋር ለዘለቄታው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ አብረን እንሰራለን። ምክንያቱም የጋራ አገር ነው ያለን፣ አገር በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ከተበጠበጠ ሁላችንም ነው የሚጎድልብን። ይህንን የለውጥ ሒደት ትክክለኛው ቦታ ላይ አድርሶ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር ካልቻልን አማራጩ ሌላ አንባገነን ማምጣት ሳይሆን የአገር መፍረስ ሊያጋጥም ይችላል፤ ጉዳዩ ቀላል አይደለም።

እኛ የምናየው በረጅም ጊዜ ጠንካራ መደላድል ላይ የሚቆም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዴት እንፍጠር የሚለውን ነው። ይሄን ከሚያስቡ ኃይሎች ጋር በመመካከር የጋራ ስርዓት የማቆም ኀላፊነት አለብን።

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር የነዐቢይ ብቻ ኀላፊነት ሳይሆን የእኛም ጭምር መሆኑን እንዲረዱም፣ እንዲያምኑም እንፈልጋለን።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

‹‹አፋር ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ ማንነት የለውም።››

/ ኮንቴ ሞሳ

የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ ሊቀመንበር

የብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ አፋር እምብዛም አይታይም።ዚህ መሠረቱ ምንድን ነው?

አፋር “ግብዝ” ነው። ያለእኛ ኢትዮጵያ የለችም፤ እኛም ያለኢትዮጵያ የለንም ይላል። ስለዚህም እኛ ጋር የሚኖረው ሕዝብ ወገናችን ነው ብሎ ያምናል። በአፋር ባሕል ውስጥ እሴቶች አሉ። ለምሳሌ በአፋር ነፍሰ ገዳይ አይገደልም፣ እስር ቤትም የለም። ምክንያቱም “ነፍስ ከሁሉ በላይ ክቡር ናት፤ ከፈጣሪ በቀር ነፍስ የማጥፋት መብት ያለው ሰው የለም” ብለው ያምናሉ። ይህ ለአፋር ሕዝብ መሠረታዊ ፍልስፍና ነው። አብሮ የመኖሩ ነገር ለየት ያለው ከዚህ የተነሳ ነው።

በተጨማሪም የአፋር ሕዝብ አብሮ እንጂ እንደ ግለሰብ መኖር የሚችል አይደለም። አካባቢው አደገኛ ነው፤ በረሃ ነው፤ ሀብትንም መጋራት አለ። ሕዝቡ እንጂ ክልሉ ለየት ያለ ስርዓትና አስተዳደር ኖሮት አይደለም።

በሙዚቃችንም “አገር ብርሃን የላትም፤ ምድር ብርሃን የላትም፤ ብርሃኗ ሕዝቧ ነው” የሚባል ነገር አለ። ይህ ከትውልድ ትውልድ ሕጻናት ሲዘምሩት የሚያድጉት ነው።

ሌላው ለኢትዮጵያ ብዙ የተከፈለ መስዋዕትነት አለ። ቱርክ፣ ግብጽን፣ ፖርቱጋልና አረቦችንም ከመመለስ ታሪክ አንጻር ብዙ ያልተዘመረላቸው ናቸው። ለእኛ ኢትጵያዊነትን የሚሰጥ ሰው የለም ይላሉ። አንድ ግመል እየነዳ የሚሔድ ሰው የኢትዮጵያን ባንዲራ አድርጎ በረሃ ሲያቋርጥ፤ አንዳንድ ሰዎች እንዴት ክብር ያለውን ባንዲራ አንገቱ ላይ እንደጨርቅ አንጠልጥሎ ይሔዳል ይሉታል። አፋሮች የሚሉት “አገራችን እኛን መስላ የምትኖር ናት” ነው። እኛ ተንቀሳቃሽ ነን፤ አንድ ቦታ የሚኖር ሰው ይኖራል፤ እኛ ግን ስለምንሔድና ተጓዥ ስለሆንን በሔድንበት አብራን ታድራለች የሚል እሴት አላቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

 ‹‹በማዕከላዊ ጥፊ፣ ድብደባና ማስፈራራት ይካሔድብኝ ነበር።››

ኦኬሎ አኳይ ኦቻላ

የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር

በማዕከላዊ ያለፉበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር፤ የክስ ሂደቱስ?

በማዕከላዊ ጥፊ፣ ድብደባና ማስፈራራት ይካሔድብኝ ነበር። በመጀመሪያ በአገር ክህደት ሊከሱኝ አስበው ነበር በኋላ ላይ ግን ሽብርተኛ ብለውኝ ቂሊንጦ እስር ቤት ወረወሩኝ። መቀመጫዬ ላይ በርግጫ የተመታሁት ለበሸታ (Perianal Festula) ዳርጎኛል። ኖርዌይ ከተመለስኩ በኋላ ዶክትር ለማግኘት አንድ ዓመት ፈጅቶብኝ ኹለት ጊዜ ኦፕራሲዮን አድርጌያለሁ።

ቂሊንጦ ክስ የተመሠረተብኝ በሽብርተኝነት ነው። ራሳቸው የሠሩት ሥራ እና የፈጸሙትን ግድያ ነው ወደ እኔ ያስተላለፉት። ብዙ ክስ ነበረብኝ። የሽብር ክሱ ከግንቦት 7 ሊቀ መንበር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ከኦነጉ ሊቀመንበር ከዳዉድ ኢብሳ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ሊቀ መንበር በሬ አግድ እና የጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋዴን) ሊቀመንበር አፒ ኡጁሉ ጋር አሲረሃል በሚል ነው። በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን መሪ ዴቪድ ያውያው ጋርም ግንኙነት በመፍጠር መንግሥት ለመገልበጥ በማቀድ ተከስሻለሁ።

በክስ ሒደቱ ጠበቃ አልፈልግም አልኩኝ፤ መንግሥት የሾመው ጠበቃ መከሰስ የለባቸውም አለ። ደቡብ ሱዳን ነው የተያዙትና ወደዚያው መልሷቸው አለ። ይህን በማለቱም ጠበቃው ከሥራው ተባረረ።

ከዛ በኋላ አምሃ መኮንን ጠበቃ ሆነልኝ፤ ኖርዌይ ኤምባሲ እየሔደ ሥራው ተጀመረ።

ከኹለት ዓመት ክርክር በኋላ በ2008 የሽብር ክሱ ውድቅ ተደረገ። ከዛ ደግሞ ጋምቤላን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አሲረሃል በሚል በወንጀለኛ አዋጅ ቁጥር 241 መሰረት ዘጠኝ ዓመት ተፈረደብኝ፤ ወደ ቃሊቲ ገባሁ።

የእስር ቆይታዬ በድምሩ ሦስት ዓመት ከ11 ወር ነው።[ጠቅላይ ሚኒስትር] ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሥልጣናቸው በፈቃዳቸው ከመልቀቃቸው አንድ ቀን በፊት ተፈታሁ። ፓስፖርቴ እስር ቤት ስለጠፋ ጊዜያዊ ፓስፖርት የኖርዌ ኤምባሲ ሰጥቶኝ ወዲያውኑ ወደ ኖርዌይ መልሶኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

 ‹‹ፖለቲከኛው ሊያብድ ይችላል፤ ሕዝብ ግን ሕዝብ ነው።››

አባ ዱላ ገመዳ

በአብዛኛው ባለሥልጣናት የትምህርት ሚኒስትር ሆነውም፣ ልጆቻቸው አገር ውስጥ ከሚያስተምሩት የማያስተምሩት ይበልጣል ይባላል፤ እርስዎ እንዴት አገር ውስጥ ለማስተማር ወስኑ?

ልጆች ወደ ውጭ ሲሔዱ ኹለት ነገር ይጎድላቸዋል ብዬ አምናለሁ። ይሄን ሌላው ላያምንበት ይችላል። ልጆችን ልጅ የሚያደርገው የቤተሰብ ፍቅር ነው። ማንነታቸውን የሚገልጸው ቤተሰባቸው ነው። ማንም ሰው ለትምህርት በሔደበት አገር በሙያ የሚጨምረው ትንሽ ነው፤ ይዞት የሚያድገው ዋናው ባህሪ ቤተሰቡ ጋር የፈጠረው ነው።

ስለዚህ ከአገር በተለዩ ቁጥር ከቤተሰብ ፍቅራቸውና ከቤተሰብ ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ ከሰውም ጋር ያላቸው አጠቃላይ ነገር ይዘበራረቃል። ይሄን በጽኑ አምንበታለው። ብዙ ዕድል ነበር፣ ትንሽ ደግሞ በራሴ አይቻለሁ። የመጀመሪያ ልጄን ልኬ አይቼዋለሁ፤ መልሼዋለሁ። በትንሹ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገር ውስጥ መጨረስ አለባቸው።

ኹለተኛው አገርን ይረሳሉ። የኔ ልጆች አገርን ዕወቅ ፕሮግራም ነበራቸው። አሁን ትንሽ የጸጥታ ችግር ስለሆነ ነው ያቆሙት። አንድ ክረምት ጎጃም፣ ጎንደር ሔደዋል፤ አይተዋል። ማንም የሚቀበላቸው የለም። እናታቸው ናት ይዛቸው የምትሔደው። በራሳቸው ሆቴል ይይዛሉ፣ ታክሲ ይዘው ይንቀሳቀሳሉ፤ ይመጣሉ፣ ይሔዳሉ፣ ያያሉ። ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢም ብዙ አይተዋል፤ ሐዋሳም ሌሎችንም። ለመዝናኛ አይደለም፤ ማወቅ ስላለባቸው ነው። ትግራይ ሔደዋል፤ በደንብም አይተውታል። አሁን መጨረሻ ጅግጅጋ ሊሔዱ ሲሉ ነው የጸጥታ ችግር የተፈጠረው።

ይሄ ለምንድነው፤ አገር ውስጥ ስለኖርሽ ብቻ አገርን አታውቂም። እዚህ ሆኖ ሰዉ በጣም ያወቀው ስለአሜሪካ ነው። ይሄ ጥሩ ነው፤ ስለአሜሪካም ስለጃፓንም ማወቅ አለብን። ከሁሉ በፊት ግን አገራችንን ማወቅ አለብን። እኔ ደግሞ በጣም አምንበታለሁ። መጽሐፌን አይተሸ ከሆነ ስለእኔ ከሚገልጸው በላይ ስለ አገሪቱ ይገልጻል። ስለዚህ አገርን ሕዝብን እንደማወቅ ትልቅ ነገር የለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

 ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ በጣም አስደምመውኝ ነበር። እጅግ የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር ህልም አላቸው።

ፈራንሲስ ፉኩያማ (ፕሮፌሰር) በሃርቫርድ ዩኒቨሪቲ ፖለቲካል ሳይንስ መምህር

አስቀድሞ የማንነት ፖለቲካን ሲያነሱ፤ በጣም መከፋፈል ባለባቸው አገራት የሚታዩ የመፍረስ ምልክቶችን ለይተው ነበር። ከዛ አንጻር አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?

ኢትዮጵያ በርግጥም አደጋ ውስጥ ናት፣ አደጋው ምናልባትም የመፈራረስ ሊሆን ይችላል። ይህም የሆነው የብሔራዊ አንድነት ስሜት ያልተሰማቸውና በኢትዮጵያ ውስጥ ራሳቸውን ማየት ያልቻሉ ብዙ የብሔር ቡድኖች ስላሉ ነው። ይህ በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው። ሶርያ፣ ኢራቅና ሶማሊያን አይተናል። ሁሉን የሚያስማማ አንድ ብሔራዊ ማንነት መፍጠር ባለመቻላቸው የመፈራረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል በቅርቡም የፈረሱ አገራትን ተመልክተናል። ኢትዮጵያ በዚህ መንገድና አቅጣጫ ልትሔድ አይገባም።

ችግሩን እዛ ደረጃ ሳይደርስ ለመፍታት ምን ቢደረግ ይላሉ?

መፍትሔው የሚመሰረተው እንዳልኩት ብሔራዊ አንድነትን በመፍጠር ላይ ነው። ይህም በተለይም በአገር መሪዎች ላይ የሚጣል ኀላፊነት ነው። ሰዎች ከብሔር ማንነት ጋር ሚዛናዊ የሆነ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብን ሊፈጥሩ ይገባል። ለምሳሌ ሶሪያን ብትወስጂ ሁሉም ስለራሱ ሃይማኖት እና ጎሳ ላይ ያተኩራል እንጂ ስለ ሶሪያ የሚያስብ አልነበረም። ይህም በመጨረሻ ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርቷል።

ከዚህ ቀደም በነበሮት ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይን የማግኘት ዕድል ነበረዎት። በእሳቸው እና በመንግሥታቸው ላይ ያሎት አሰተያየትስ ምንድን ነው?

ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ በጣም አስደምመውኝ ነበር። እጅግ የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር ህልም አላቸው። የአገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ የሚችል ፕሮጀክት ይዘው መጥተዋል ብዬ አምናለሁ።

(ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here