100 ሳምንታት

0
857

አዲስ ማለዳ እስከ መቶኛ እትም ስትጓዝ ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ቀደማ ለኢትዮጵያውያን ካስነበበቻቸው እና ምርመራ በማድረግ ካቀረበቻቸው  አቦል ዜናዎች መኸል ደግሞ ለትውስታ እንዲሆን ከበርካታዎቹ መኸል የሚከተሉትን አቀርበንላችኋል፡፡

 ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ”ሚል ስያሜ  ውሕድ ፓርቲ ሊሆን ነው

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በትጥቅ ትግል ላይ እያሉ በትግራይ በረሃ በ1981 የመሰረቱት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ (ኢብፓ)/ Ethiopian Prosperity Party (EPP) ሊባል እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮች ሰማች።

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ፍልስፍና ሲመራ የቆየው ኢሕአዴግ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የሶማሌና የሐረሪ ክልል ገዢ ፓርቲዎችን በማቀፍ አንድ ወጥ ፓርቲ ሆነው ለመውጣት የፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብና ለኢትዮጵያ ብልጽግናን ያመጣሉ ተብለው ተስፋ የሚጣልባቸውን የፓርቲውን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በወጣት ምሁራን በማስረቀቅ ሒደት ላይ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ያረጋግጣሉ።

ከመስከረም 8 ጀምሮ ለአምስት ቀናት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን በጉባዔው አብዮታዊ ዴሞክራሲን በመተካት የአዲሱ ፓርቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ይሆናል በተባለው የመደመር የፖለቲካ ቀመር ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች። የመደመር ፍልስፍና ላይ በባህር ዳር፣ በአዳማ እና ሐዋሳ ከተሞች ላይ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ወጣቶችንና ምሁራንን ያሳተፈ ዝግ ስብሳባ እየተደረገ ይገኛል።(ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012)

 

 ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ቸርችል ጎዳና አካባቢ በሚገኙ ባለቤታቸው በውል የማይታወቁ ሁለት ሕንፃዎች በካሬ ከ300 እስከ 400 ብር እየከፈለ ለዐሥር ዓመታት መከራየቱ ታወቀ።

አዲስ ማለዳ ሕንፃዎቹ በሚገኙበት አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በአካል በመገኘት ሁለቱ ባለ አራትና ስምንት ፎቅ ሕንፃዎች በአንድ ግለሰብ ባለቤትነት ሥር እንደሆኑና ባለቤቱም በውል እንደማይታወቁ አረጋግጣለች።

ኢትዮ ቴሌኮም ባለ አራት ፎቁን ሕንፃ ከዛሬ ዐሥር ዓመት በፊት በጊዜው ለነበረው “ትርንስፎርሜሽን ፕሮግራም ኦፊስ” እንዲሁም ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃውን ደግሞ ከአምስት ዓመት በፊት ለጥሪ ማዕከልነት እንደተከራየው ለማወቅ ተችሏል።

የሕንፃዎቹን ባለቤት ኃይለሥላሴ እንደሚባሉ እና ከሥማቸው ውጭ በፎቶም ሆነ በአካል አይተዋቸው እንደማያውቁ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሕንፃዎቹን ኢትዮ ቴሌኮም ከተከራያቸው ረጅም ጊዜ ስለሆነው እና ሕንፃዎቹንም የሚያስተዳድረው ኢትዮ ቴሌኮም ስለሆነ ኢትዩ ቴሌኮም ገዝቷቸዋል እስከማለትም ደርሰው እንደነበር አክለዋል።(1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011)

በ10 ዓመታት ውስጥ 261 ጋዜጣና መጽሔቶች ከኅትመት ውጭ ሆነዋል

ከየካቲት ወር 2001 እስከ ኅዳር 2011 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ 288 ጋዜጣና መጽሔቶች ፍቃድ ቢወስዱም 27 ብቻ ኅትመት ላይ እንዳሉ ታወቀ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ከ2001 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ውስጥ 87 ጋዜጦች እና 174 መጽሔቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከኅትመት ውጭ ሆነዋል።

የባለሥልጣኑ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ገብረ ጊዮርጊስ አብርሃ የኅዳር ወር መረጃን መሠረት በማድረግ ‹‹ቁጥራቸው በየወሩ ልዩነት ቢያሳይም በኅዳር ወር 27 የተለያየ ይዘት ያላቸው የኅትመት ሚዲያዎች ብቻ ናቸው ገበያ ላይ የዋሉት›› ብለዋል።

አያይዘውም የተጠቀሰው አኀዝ የሚያመለክተው የብሮድካስት ባለሥልጣን ቁጥጥር በሚያደርግባቸው አዲስ አበባ እና ክልሎች ላይ የስርጭት አድማስ ያላቸውን የኅትመት ሚዲያዎች እንጂ ክልላዊ ጋዜጦችና መጽሔቶን አይጨምርም ብለዋል።

ለኅትመት መገናኛዎቹ መክሰም በባለሥልጣኑ እንደ ምክንያት የተዘረዘሩት የኅትመት ዋጋ መጨመር፣ የመረጃ እጥረት፣ የቤት ኪራይ መጨመር እና ማስታወቂያዎች በጥቂት የመገናኛ ኅትመቶች ቁጥጥር ሥር መውደቅ ናቸው።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል በተደጋጋሚ ቁጥራቸው የበረከቱ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን እና ግብይቶችን በመረጃ አስደግፌ ለሚመለከተው አካል ባቀርብም እርምጃ አልተወሰደልንም ሲል ወቀሰ።

ማዕከሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በሥልጣን ላይ እያሉ በተደጋጋሚ ‹‹የሕገ ወጥ ዝውውሩን እና ግብይቱን ምንጮች በተጨባጭ መረጃ አስደግፌ ሪፖርት ባደርግም ምላሽ ሳይሰጠኝ ቀርቷል›› ብሏል። በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ሕገ ወጥ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገራት ገንዘቦች ዝውውር አስቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር ሲሉ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኪዳነማሪያም ገብረፃዲቅ መግለፃቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተስፋየ ዳባ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። አሁንም ቢሆን የተደራጁ መረጃዎችን ወደ እርምጃ የመቀየር ክፍተት መኖሩን ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴው አሳውቀዋል።(ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

የአዲስ አበባ አስተዳደር በሰንዳፋው ቆሻሻ ማስወገጃ ላይ ፍላጎት የለውም ተባለ

ከአዲስ አበባ አስተዳደር በ37 ኪሎ ሜትር ርቀት ሰንዳፋ ላይ ተገንቶ የነበረውና በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ገጥሞት ሥራ ያቆመው ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ላይ ብዙም ፍላጎት እንደሌለው ታወቀ፡፡

አዲስ ማለዳ ከአንድ የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ እንደሰማችው አስተዳደሩ በተቃውሞ የተቋረጠውን ማስወገጃ ወደ አገልግሎት የመመለስ ፍላጎት የለውም፡፡

የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንዳሉት አንድ የአሜሪካ ኩባንያ በስፍራው ጥናት እያደረገ ይገኛል። በጥናቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴርም እየተሳተፈ ስለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ጥናቱም ከዚህ ቀደም የተደፋው ቆሻሻ በአካባቢው ላይ ተፅዕኖ ይሩረው፣ አይሩረው ለማወቅ እና መፍትሔውስ ምንድን ነው የሚሉትን ለመለየት የሚካሄድ ነው ተብሏል፡፡

አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የወጣበት ‹‹የሰንዳፋ ዘመናዊ የቆሻሻ ላንድ ፊል›› ከፈረንሳይ መንግሥት  በተገኘ ገንዘብ የተገነባ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡ ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

በወለጋ የንግድ ባንክ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ቅጣት ተጥሎባቸው የነበሩ ግለሰብ ሹመት ተሰጣቸው

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታኅሣሥ 18/2011 በጊምቢ ቅርንጫፍ ከተፈጸመው የ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ያልተገባ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ተብሎ ቅጣት ተጥሎባቸው የነበሩትን ካሳሁን ሽፈራው የኦፕሬቲቭ ሪሌሺንሺፕ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አድርጎ መሾሙ ጥያቄ አስነሳ።

በተለይም ያለ ባንኩ ዋና መስሪያ ቤት እውቅና እንዲሁም ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ዘረፋው በተፈፀመበት ዕለት ጠዋት ላይ የጊምቢ ቅርንጫፍ እንደ ʻኢሹʼ ቅርንጫፍ – ማለትም በአካባቢው ከሚገኙ ቅርንጫፎች ብር ለማሳደር – እንዲያገለግል ትዕዛዝ መስጠታቸው ተረጋግጦ እያለ ሹመት መሰጠቱ ውዝግብን ፈጥሯል።

በተጨማሪ በታጣቂዎች ገንዘቡ በተዘረፈበት ቀን 9 ሰዓት ከ45 ላይ ያለበቂ አጀብ ገንዘቡን አልሰጥም ያሉትን የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ደሳለኝ ረጋሳን በስልክ ገንዘቡን ለዳሌ ቅርንጫፍ እንዲሰጡ ማዘዛቸውን ካሳሁን አምነው ቢቀጡም ተጨማሪ ሹመት መሰጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ ከባንኩ የሰው ሀብት ክፍል ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ገልፀዋል።(ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

በጋምቤላ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በ13 በመቶ ቀነሰ

በጋምቤላ ክልል ባለፉት ኹለት ዓመታት ሲከሰቱ በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የጤና አገልግሎቶችን ባግባቡ ተደራሽ ለማድረግ ባላመቻሉ ከኹለት ዓመት በፊት 33 በመቶ ደርሶ የነበረው የወሊድ መቆጣጠሪያ ሽፋን በ13 በመቶ በማሽቆልቆል 20 በመቶ ደረሰ።

በፀጥታ መደፍረስ አማካኝነት በከተሞች እና በወረዳዎች መሠራት የነበረባቸው የሥነ ተዋልዶ ሥራዎችን እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለማከናወን አለመቻሉ መሰረታዊ ምክንያት ይሁን እንጂ፣ የተለያዩ ችግሮች ለሽፋኑ መቀነስ ምክንያት እንደሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ካን ጋልዋክ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።(ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here