ከኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንክ 12 ቢሊዮን ብር ከትርፍ ድርሻ ክፍያ ተገኘ

0
1088

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በ2012 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከተገኘው 300 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ውስጥ ከትርፍ ድርሻ ክፍያ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘቱን የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በየነ ገብረመስቀል በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።

በ2012 ለኤጀንሲው ተጠሪ ከሆኑት እና የትርፍ ድርሻ ክፍያ መፈጸም ከሚጠበቅባቸው ድርጅቶች ከተገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ከትርፍ ድርሻ ክፍያ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን በዚህም 12 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ ማስገባት መቻሉም ተገልጿል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከሚያስተዳድራቸው 21 የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከተገኘውም የ12 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ከትርፍ ድርሻ ክፍያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚይዘው ንግድ ባንክ ሲሆን ከ8 ቢሊዮን ብር ገቢ የትርፍ ድርሻ ክፍያ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማስገባቱን በየነ አስታውቀዋል።

የስነ ምጣኔ ባለሙያው አለማየሁ ገዳ ስለ ስለትርፍ ድርሻ ክፍያ ስርአትና የአከፋፈል ሂደት ሲያስረዱ የመንግስት የልማት ድርጅቶቹ በመንግስት ባለቤትነት ስር ስለሚተዳደሩ የትርፍ ድርሻ ክፍያ የሚከፍሉት ለመንግስት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ይገልፃሉ።

ባለሙያው እንደሚሉት ድርጅቶቹ ከሚያገኙት አጠቃላይ ገቢ ላይ ከወጪያቸው ላይ በመቀነስ እና ከታክስ ክፍያ በኋላ የሚቀረውን የተጣራ ገቢ ወይንም ትርፍ ድጋሚ ወደስራ እናውለው ወይስ ለባለቤቱ በትርፍ ድርሻ ክፍያ መልክ ይሰጥ በሚለው ጉዳይ ላይ የድርጅቶቹ ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔ ያስተላልፋል በማለትም አስረድተዋል።

ነገር ግን አንዳንዴ የመንግስትም ድርጅት ሆኖ የተለያዩ ሌሎች የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶች ከድርጅቱ ላይ ድርሻ ሊኖራቸው ይችላል የሚሉት አለማየሁ በዚህን ጊዜ ድርጅቶቹ ከአጠቃላይ ወጪው እና ከታክስ ክፍያው በኋላ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው አካላቶች እንደ መሆናቸው እንደ ድርሻቸው መሰረት ከትርፍ ድርሻ ክፍያ እንደሚያገኙ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ባሳለፍነው የ2012 በጀት አመት በኤጀንሲው ስር ካሉት የልማት ድርጅቶች ከ338 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ ያገኛል ተብሎ ተጠብቆ እንደነበር የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ከታቀደው ገቢ 89 በመቶ በማሳካት 300.5 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ተናግረዋል።

ከዚህም ገቢ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ122 ቢሊዮን ብር ማስገኘቱ የተገለፀ ሲሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ከ47.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱና ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡም ተገልጿል።

ኤጀንሲው በስሩ ከሚገኙ የልማት ድርጅቶች እንቅስቃሴ ይጠበቅ የነበረው የትርፍ መጠን ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ቢሆንም፣ ከታቀደው የትርፍ መጠን 79 በመቶው በማሳካት 56 ቢሊዮን ብር ያህል የትርፍ መጠን መመዝገቡም ተገልጿል።

በሌላ በኩል ምርትና አገልግሎታቸውን በውጭ ምንዛሬ ከሚሸጡ ድርጅቶች 8.67 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱንም የተናገሩት በየነ የኢትዮጲያ አየር መንገድ ግሩፕ ከዚህ ውስጥ 3.74 ቢሊዮን ዶላር በማስገባት በአንደኝነት ደረጃ ላይ ሲገኝ የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ደግሞ 3.43 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ በማስገኘት እንደሚከተልም አስታውቀዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት በሥሩ ከሚያስተዳድራቸው 21 ድርጅቶች፣ በ2012 ዓ.ም በጀት አመት 20ዎቹም አትራፊ ሆነው ዓመቱን ያጠናቀቁ ሲሆን ስኳር ኮርፖሬሽን ብቻ ለኪሳራ የተዳረገ ድርጅት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ነገር ግን የትርፍ ክፍያ ያስገኙት ድርጅቶች ሁለት ብቻ የሆኑበት ምክንያት የሌሎቹ ድርጅቶች ሂሳብ ገና ተሰርቶ ያላለቀ በመሆኑ እንደሆነ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወንዳፍራሽ አሰፋ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተያዘው በጀት አመትም ኤጀንሲው 376.6 ቢሊዮን ብር ገቢን በስሩ ከሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች ለማግኘት ማቀዱን ያስታወቁት በየነ ይህም በ2012 ዓ.ም ከተገኘው ገቢ የ22 በመቶ ጭማሪ የተደረገበት መሆኑን አስታውቀዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here