‹Mulan/ሙላን›ን እንዳየሁት…

0
383

ሙላን ‹Mulan› በድርጊት የተሞላ ወይም አክሽን ዘውግ ያለው ፊልም ነው። የፊልሙ መጠሪያም በፊልሙ የምትታየው ዋና ገጸ ባህሪ ሥም ነው። ፊልሙ በዲዝኒ ዋና አዘጋጅነት ለዕይታ የቀረበ ነው፣ የታሪኩ ምንጭ እና የፊልሙ መቼት ደግሞ ቻይና።

የአገሬው የፊልም ባለሞያዎች በተለይም የፊልሙ መነሻ የሆነውን ታሪክ የሚያውቁቱ ፊልሙን በሙያዊ ዕይታ ሲተቹ፣ ከታሪክና ከመቼት አንጻር መፋለሶች አሉት ብለው ተሟግተዋል። ያም ሆነ ይህ፣ ቻይናን በታሪክና በአካል በቅርብ የሚያውቋትና በንባብም የተረዷት ካልሆኑ በቀር፣ ለብዙኀኑ ተመልካች ጎልተው ላይታዩ ይችላሉ። እናም ጉዳያችንም ከፊልሙ መቼትና ታሪካዊ ይዘት አንጻር ሳይሆን፣ ስለፊልሙ ጭብጥና ራሳችንን እንድንመለከት ስለሚጋብዘን ሐሳብ ነው።

የፊልሙ ባለታሪክ ‹ቦታሽ ትዳር መስርቶ ለባል ረዳት፣ ለቤተሰብም ክብርን ማምጣት ነው› ተብላ ያደገችው ሙላን፣ ከልጅነት ጀምሮ በምታደርጋቸውና በባህሉ በሴት አልተለመዱም በሚባሉ እንቅስቃሴዎቿ በአካባቢው ነዋሪ ትኩረትን አግኝታለች፤ ትነቀፋለችም። አቅሟን የሚያውቁ አባቷ እንኳ ችሎታዋን እንድትደብቅ ግድ ይሏት ነበር። ቤተሰቧን ልታስከብር የምትችልበት ብቸኛው መንገድ ጋብቻም እንደሆነ ደጋግመው ያሳስቧታል።

በአንድ ወቅት ታድያ መኖሪያ አገራቸው በጠላት ሊወረር መሆኑ ተሰምቶ፣ ንጉሡ ሁሉም ቤተሰብ አንድ ወንድ ልጁን እንዲሰጥ ያዝዛል። በሙላን ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ወንድ ልጅ የለም። እናም አስቀድሞ ጦረኛ የነበሩትና በሕመምና በእድሜ ጭነት ጉዳት ያለባቸው አባቷ በቤተሰቡ ተወክለው ለጦርነት እንደሚዘምቱና ለሥልጠና በተባለው ቦታ እንደሚገኙ አስታወቁ።

ሙላን አባቷ ጦር ሜዳ ቢሄዱ በሕይወት እንደማይመለሱ ታውቃለች። እናም በእኩለ ሌሊት የአባቷን የጦር መሣሪያ ይዛ፣ ወንድ መስላና ሴትነቷን ደብቃ ወደ ጦር ሜዳ ትዘምታለች። ታሪኩ የዚህች ሴት ትግል፣ በጦርነት የምታሳልፈውን ጊዜ ያስቃኛል። በመጨረሻም ድል አድራጊ ሆና ወደ ቤተሰቧ ትመለሳለች። በፊልሙ የሚሆነውን ግን አንባብያን እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ።

ይህ ታሪክ በቻይና ከ1500 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው። ታሪኩም በአፈ ታሪክነት ከመዘዋወሩ የተነሳ መነሻውን ትቶ በተለያየ መንገድ ሲተረክ ቆይቷል። መነሻ ታሪኩን በሚገባ የሚያውቁ ባለሞያዎች ሲናሩም፣ የሙላን የትውልድ ስፍራ፣ ወደ ውጊያ ስትሄድ ልትዘምትለት የሄደችው ወገን ወዘተ በተለያየ መንገድ ሲነገር ቆይቷል ይላሉ።

በ2020 በዲዝኒ ተሠርቶ ለዕይታ ከመቅረቡ በፊትም በ1998 በካርቱን ፊልም ተሰናድቶ ታይቷል። ይኸው ታሪክ በፊልም መልክ በ1939፣ በ1964 እንዲሁም በ2009 ተሠርቶ ለዕይታ ቀርቧል። በእርግጥ የፊልም ሃያስያን በፊልሙ በውስጠ ወይራ የተላለፉ ያሏቸውን ለምሳሌ ሙላን ወንድ መስላ በጦርነት መሳተፏን ጠቅሰው ያ ተገቢ እንዳልሆነ ያነሳሉ። በአንጻሩ ከ2020ው ሙላን ፊልም ይልቅ ሴቶችን በማጉላት ረገድ የተሻለ የገለጹ ፊልሞች አሉ ብለው ይሞግታሉ።

ያም ሆነ ይህ፣ ይህን ፊልም ስመለከት የእኛዋ ውርድወት (የቃቄ ውርድወት) ትዝ አለችኝ። እርሷ ብቻ አይደለችም፣ አንዴ በፖለቲካ ንትርክ፣ አንዴ በእምነትና ሃይማኖት ወዲያ በየምዕራፉ ከተን ቸል ያልናቸውን ሴቶች ታሪክ አሰብኩ። ከ1500 ዓመት በፊት የነበረችው ሙላን፣ አነሰም በዛ፣ የሆሊውድን ትኩረት ያገኘችው በቅድሚያ ቻይና ራሷ ለጀግናዋ እውቅና እና ትኩረት በመስጠቷ ነው።

እናም በኢትዮጵያችን ስንት የሆሊውድን መንደር የሚያስደነግጡ፣ አዲስ ዕይታና ጭብጥ የሚያቀርቡ፣ ያልተሰሙ እውነቶችና ኹነቶችን የሚነግሩ የፊልም ታሪኮች ተቀብረው እንዳሉ አስቡ! ‹የሴት ዳሌ በማሳየት› እና ‹ሴቶች ለገንዘብ ሟች ናቸው!› ብሎ ለመሳቅና ለመሳለቅ የዋሉ ፊልሞችን በመሥራት ያባከንነው ሀብት፣ ጊዜና ጉልበትስ አይቆጭም?

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here