ከሁሉ በፊት ሕግ ይከበር!

0
506

በአንድ አገር ውስጥ መንግስት አቋም እና አገረ መንግስት ጥንካሬ በዋናነት የሚለካው መንግስት በአገር ውስጥ ሕግ እና ስርኣትን አስከብሮ ዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ሲችል እንደሆነ በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ይህም ታዲያ ዜጎች ሰርተው ግብርን በአግባቡ ለአገር ልማት፣ ዕድገት እንዲሁም ወረድ ሲልም ለራሳቸው ደኅነት መስጠበቂያም ይከፍላሉ። ይህ ሲሆን አገርም በጠንካራ መሰረት ላይ ትገነባለች መንግስትም አገርን ለመገንባት በሚደረገው ውጣ ውረድ ላይ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ ሕዝብን እና አገርን እየመራ ወደ አገር ራዕይ ይመራል።

በኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ዕውነታ የተለየ እና በልዩ ሁኔታ የሚተገበር ሳይሆን የመንግስት ኃላፊነት ዜጎችን ሕልውና ከማስጠበቅ ባለፈ አገርን ዳር ድንበር በማስከበር የአገርን ሉዓላዊነትም አስጠብቆ የማቆየት ኃላፊነት ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከኹለት ዓመታት ወዲህ ዜጎችን ደኅንነት በሚመለከት እና በአገር ውስጥ ያለውን ሰላም እና ደኅንነት በማስጠበቅ በኩል ይህ ነው የሚባል አመርቂ ስራዎች ለመሰራታቸው በእርግጠኝነት ለመናገር ሚያስደፍር እንዳልነበር አዲስ ማለዳ በጽኑ ትገነዘባለች። በእርግጥ የለውጡ ኃይል በትረ መንግስቱን ከያዘበት ከመጋቢት 2010 ጀምሮ በርካታ አዳዲስ እና ድነቃ ድንቅ ስራዎች የተሰሩ እና አገርን አሻግረን እንድንመለከት ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች የተሰሩ እና ይበልም የሚያሰኙ ቢሆኑም በሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም በዜጎች ደኅንነት በማስጠበቅ ላይ ግን አሁም ቀሪ እና ረጅም ጉዞ መሔድ እንደሚያስፈልግ ግን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ከዜጎች ደኅንነት እና በሰላም ወጥቶ መግባት ጥበቃ ጋር በተገናኘ ዋነኛው ሳንካ በመሆን ከባድ አዙሪት ውስጥ አገሪቱን ለመክተት እየተንገታገተ ያለው ጉዳይ ደግሞ የሕግ የበላይነት በአንድም ሆነ በሌላ አለመረጋገጡ ነው።ሕግ ተከብሮ እና የሕግ በላይነት ጸንቶ በአገር ውስጥ ሲነግስ ሕገ ወጥነት እና ማን አለብኝነት ቸርሶ ሲጠፋም አገር ሕልውና ተጠናክሮ እያበበ እንደሚሄድ እሙን ነው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲተገበር እና አገርም ከስጋት ተላቃ ወደ ለውጥ ጎዳና ስትገሰግስ ለመታዘብ ግን ሩቅ የሆንን ይመስላል ስትል አዲስ ማለዳ ታስባለች። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚታየው ስርኣት አልበኝነት እና ሕገ ወጥነት መንግስት በጉዳዩ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ማንገራገሩን ወይም ዳተኝነቱን ማሳያም ነው ስትል አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። ይሁን እነጂ በመስከረም 25/2013 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስድስተኛ የስራ ዘመን መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በስራ ዘመኑ የኢፌዲሪ መንግስት አጽንኦት ሰጥቶ የሚሰራው ጉዳይ ቢኖር የሕግ የበላይነትን መስከበር እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከመንግስት ውጭ ማንም የጦር መሳሪያ የሚታጠቅ ቡድንም ሆነ ግለሰብ እንዳይኖር ማድረግ ነው።  በክብርት ፕሬዘዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አማካኝነት አጽንኦት ተሰጥቶት የተነገረው ይኸው ጉይ ታዲያ በእርግጥ ከዚህ በፊት መንግስት ስንት ጊዜ ተናግሮታል? ያልተናገረው ጊዜስ መቼ ነው እና ሲተገበርስ ለምን አላየንም መሉ ጥያቄዎችንም የሚያሰነሳ ነው።

ይበል የሚሰኙ እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ሕገ ወጥ ናቸው በተባሉ ቡድኖች ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት በይፋ መግለቻ በማውጣት ሕገ መንግስታዊ እርምጃ በመውሰድ ዓመቱን የጀመረ ቢሆንም ግን የእስካሁኑ የፈሰሱት የንጹሀን ደም እና የጠፋው ሕይወት ከዚህ በኋላ እንዳይደገም የሕግ ማስከበሩ እንቅስቃሴ እና እርምጃ ይፍጠን ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ትናንት ተሳስቦ እና ተከባብሮ የኖረውን ሕዝብ በተሳሳተ ትርክት ለፖለቲካ አጅዳ መጠቀሚያ ለማድረግ በርካቶች ተፈናቅለው ከቀያቸው ተሰደዋል። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ጀመረው አነስተኛው ግጭት እና አለመረጋጋቶች በመንግስት ቸልተኝነትም ሆነ ሆደ ሰፊነት ታልፈው አሁን በየቀኑ ዜጎች በሰቀቀን ውስጥ እንዲኖሩ እና ለወጥቶ መግባታቸው ማረጋገጫ እንዳያገኙም ሆነዋል። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ከዚህ በላይ መሔድ ስለሌለበት መንግስት በዋናነት የሕግ ማስከበሩን ሒደት በሕገ ምግስታዊ መንገድ ተጠቅሞ በፍጥነት መተግበር እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ይኖርታል ።እስከ ዛሬ ፈሰሰው ንጹሃን ደም፣ የወደመው ንብረት፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቀየ እና አድባር የተፈናቀሉ ዜጎች ተገቢውን ፍትህ ሊያገኙ እና ጩኸታቸው በመንግስት ዘንድ ሊሰማ እና ሊካሱ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በሕግ ማስከበር እና አገርን በማስተዳደር ትጉህነት የሚመዘነው የአንድ አገር መንግስት፤ በዜጎች ልብ ውስጥ ያለው ተቀባይነትም ከምንም በላይ ዋነኛው እና አስፈላጊው ጉዳይ ነውእና ይህንንም ማጣት እንደሌለበት ሊታሰብበት ይገባል። በይደር የማይቀመጥ እና ዛሬን አርፌ ነገ እሰራዋለሁ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ታዳምሮ የመንግስት ኃላፊነት በሁሉም ዘርፍ እንዳለ ሆኖ በሕግ ማስከበሩ ላይ ግን ሊፈጥን ይገባል። ሕግ በተከበረ ማግስት አገር በጤናው፣ በትምህርቱ፣ በኢንቨስትመንቱ እና በሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች እጎመራች እና እያበበች ለመሄድ የሚያስችላት እድል ሰፊ እንደሆነም ሊታሰብበሰት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ሕግ ባለመከበሩ ምክንያት ምንም እንኳን የወጪ ንግድ ተቀላጠፈ ቢሆንም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ግን በእጅጉ ለመቀዛቀዙ ማንንም ምስክር መጥራት የማያሻው ጉዳይ እንደሆነ መንግስት ራሱ የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። ይህ ግን ታዲያ በዚሁ ከቀጠለ የስራ አጥ ቁጥሩን ባለው ላይ እንዲጨምር እንደሚደርገው እና ለባሰ ጫና እና አለመረጋጋት እንደሚዳርግ መንግስት ከወዲሁ ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ልታነሳ ትወዳለች። በትምህርትም ረገድ ቢሆን ባሳለፍነው ዓመት እና ከዛ በፊት በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ታይተው የነበሩ አለመረጋጋቶች የሕግ የበላይት አለመረጋገጥ እና መንግስትም ቸልተኝነቱ የታየበት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በዚህም ምክንያት ለትምህርት የሔዱ ተማሪዎች ሞተው ቀርተዋል ልብ በሚሰብር ሁኔታም በችግር ወደ አሳደጓቸው ቤተሰቦቻቸው አስከሬናቸው ተልኮ የዘለዓለም ሰቀቀንን ፈጥሯል። ከዚህ ባሻገር ግን ትምህርት በመስተጓጎሉ ምክንያት እንደ አገር የሚባክነው ሀብት በእጅጉ የበዛ ነው። ስለሆነም ቁልፉ ሕግን ማስከበር በመሆኑ ጉዳዩን መንግስት እንዲያፈጥነው እና ነገ ዛሬ ሳይባል የሕግ የበላይነት ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ እንዲሰፍን አዲስ ማለዳ አቋሟን ትገልጻለች። ይህ ባልሆነ ሁኔታ ግን የአገር አዕማድ የምንላቸው መተሳሰብ እና መከባበር ቀስ በቀስ እየተናዱ፤ ሕዝብም በመንግስት ላይ ያለው አመኔታ እየቀነሰ ከዚህ ቀደም ብልጭ ብለው ወደ ነበረው እና በኋላም ላይ ረገብ ወዳለው ደቦ ፍርድ ማናመራበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ይህ ደግሞ አድሮ እና ውሎ አገርን ወደ ማፍረስ እንደሚያመራ ተንታኝ የማያስፈልገው ጉዳይ ነው።

ይህን ጉዳይ ግን በእንጭጩ እንኳን ባይባል ባለበት ደረጃ ላይ ደርሶ በማስቆም እና ጨርሶም በማጥፋት ከወዲሁ ሊገታ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስረግጣለች። ይህም ጉዳይ ተተግብሮ ይህ ዓመት በሚገባደድበት ወቅት የዜጎች ደኅንነት ተረጋገጠባት፣ ሰላም ተኝቶ አማን መንቃት ቅንጦት የማይሆንባት ለሁሉም ዜጋ የተመቸች ኢትዮጵያን መፍጠር እንዲቻልም መትጋት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት መንግስት ከፍተኛ ሆነ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አዲስ ማለዳ በማሳሰብ አቋሟን ታስቀምጣለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here