ትጥቅን የማስፈታት እና ሕግን የማስከበር ዕቅድ

0
1252

ታሪካዊ ኹነት ነው! ቆይተው አስተካከሉት እና ስንተኛ ዓመት ስራ ዘመን እንደነበርም አስቀሩት እንጂ ወደ አዳራሽ በገባንበት ወቅት 5ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ነበር የሚለው።

በወቅቱም የኤፌዲሪ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጋራ ምክር ቤቶችን በይፋ ከፈቱ ሲሆን በወቅቱም የኢትዮጵያን የ2012 በጀት ዓመት ‹‹ምርቅ እና ፍትፍት ›› ሲሉ ገልጸውት ነበር። እነሆ ታዲያ መጻኢውን ኢትዮጵያን ሁኔታም በሚመለከት በ2013 መንግስት በሕግ ማስከበር እና በትጥቅ ማስፈታት ሒደት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥጦ ሚሰራው ጉዳይ እንደሆነም አበክረው የገለጹበት ኹነት ነበር።

ከለውጡ የመጀመሪ ቀናት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሲነገሩ ከከረሙት ጉዳዮች ውስጥ ሕን ማስከበር አንዱ እና ዋነኛው ጉዳይ ለመሆኑ ሕያዋን እንመሰክራለን።  ዓመት ሄዶ አመት በመጣ ቁጥርም ይህ ጉዳይ ሳይነሳ ቀረበት አጋጣሚ የለም ቢባም ማጋነን አይሆንም። ‹‹በዚህ አገር ውስጥ ያለው አንድ መንግስት ነው እሱም እኔ የምመራው መንግስት ነው›› ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በዛው አገር ላይ ‹‹በዚህ አገር ኹለት መንግስት ነው ያለው›› በሚል ደግሞ ተቀናቃኝም ተነሳበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትውስታም ናቸው። በሕግ ማስከበር እና ትጥቅ ማስፈታት ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት በ2013 ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ጉዳይ ለመሆኑ በኹለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መናገራቸውም ይታወሳል። ይህንንም ጉዳይ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና በትጥቅ ማስፈታት ዙሪያ ተጻፉ ጥናታዊ ጽሑፎችን አገላብጦ የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።ባለፉት ዓመታት ምናልባትም በኢትዮጵያ ለውጥ ንፋስ እየነፈሰ ነው ከሚባልበት ከሚያዚያ 2010 ወዲህ በርካታ ጉዳዮች በዋናነት እየተነሱ ሲጣሉ ከራርመዋል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅም እንዲሁ አለመረጋጋቶች ያልተከሰቱበት እና ንጹሀን ሕይወታቸው ያልተፋበት እና ደማቸው ያልፈሰሰበት ኢትዮጵያ ጓዳ ጎድጓዳ ይኖራል ማለት አይቻልም።

ለረጅም ዓመታት በፖለቲካ ልዩነታቸው በውጭ እና በጎረቤት አገራት ተጠልለው የትጥቅ ትግል ሲያካሒዱ የነበሩ እና መቀመቻቸውን በቅንጡ አገራት አድርገው ደግሞ በአገር ውስጥም ያለውን እንቅስቃሴ በሀሳብም ሆነ በሌሎቸች ነገሮች ሲረዱ የነበሩ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ውጣ ውረዶችም በዚሁ ጋር ተያይዞ ተከስቷል። ወደ አገር ውስጥ ከገባው እና በትጥቅ ትግል ውስጥ ነበር ከሚባለው አንደኛው የሆነው ኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) አንዱ ነበር። በርካታ ታጣቂ የነበሩት ፖለቲካ ድርጅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ አስመራ አቅንቶ ነበረው በለማ መገርሳ እና በወቅቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ድርድር ተደርጎ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ግን በትጥቅ መፍታት እና ብረት ማውረድ ዙሪያ ከባድ የሆነ ውዝግብ ተከስቶ እንደነበርም ወቅቱ መወያያ ርዕስ ሆኖ አልፏል። በ2012 የመጀመሪያ ወራት ከባድ የሚባል ውጊያም በፌደራል መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ተዋጊ ከሚባል ቡድን ጋር እንደተካሄም የሚታወቅ ነው። በዚህ ወቀት ታዲያ ፌደራል መንግስት አላግባብ ኃይል ተጠቅሟል፣ ሔሊኮፕተሮችንም አንቀሳቅሷል ሚል ወቀሳ ተነስቶበት ነበረ ሲሆን ይህንንም ከመከላከያ ሚኒስቴር በኩል ሔሊኮፕተሮች ውሃ እና ለወታደሮች የስንቅ አገልግሎት ለማቅረብ እንጂ ለውጊያ አለመዋሉም ተነግሮ ነበር።

ይሁን እንጂ ከዛመም አስቀድሞ በኢትዮጵያ ታይቶ በማይወቅ ሁኔታ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀል እና አሁንም ድረስ ይህ ጉዳይ አለመፈታቱ ደግሞ ጉዳዮን አሳሳቢ ያደርገዋል። አዲስ ማለዳ በከፍተኛ ሁኔታ ሰዎች ተፈናቅለውበታል እና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው ተብሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሲናፈስ በነበረበት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የጌዴኦ ዞን ውስጥ በአካል ተገኝታ ለመታዘብ እና ዜጎችንም ለማነጋገር የቻለችበት አጋጣሚም ነበር ። በወቅቱ ታዲያ ታጣቂዎች እንዳፈናቀሏቸው እናበዚህም ጉዳይ የተነሳ በርካታ አካባቢዎች ሰው አልባ ቀበሌዎች መሆናቸውንም ለማየት ተችሎ ነበር። ይህ ታዲያ በ2011 መጨረሻ አካባቢ ቢሆንም 2012 እዲህ አይነት ነገር እንደማይደገም እና ሕግን ለማስከበር መንግስት ከባድ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሕዝብ ሲያደርስም ቆይቶ ሕዝብም ተስፋ ሰንቆ ነበር  ወደ 2012 የተሻገረው ይሁን እንጂ የተገባው ተስፋ በተለይም ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጭራሹኑ የሚታወስም እስከማይመስል ድረስ ትላልቅ አንገት አስደፊ ጉዳዮችም ሲከሰቱ ነበር 2012 የተገባደደው።

ከዓመት ወደ ዓመት አሁንም የዜጎችን መፈናቀል፣ መገደል፣ በስጋት ውስጥ መኖርን እየተመለከትን እና እሰማን እንዲሁም በል ሲልም ጉዳታቸውን በግንባር ሔደን እየተመለከትን ነገር ግን ዜናዎች እና መረጃዎች መደጋገም በሰሚው ዘንድ ወደ መልመድም ከፍ እያለ እና ትኩረት ማጣት አዝማሚያም መከሰት እየዳዳው ይመስላል። ይህ ዜጎች መፈናቀል እና ሕግን ካለማስከበር የሚመነጨው እንዲሁም በሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ባለፈም በመታጠቅ አገርን ለማሸበር የሚደረገው ሙከራም እየተባባሰ ለመቀጠሉ ከቀን ወደ ቀን ሚፈተሩት ድርጊቶች አመላካች ናቸው። በቅርቡ ወደ ደቡብ ምእራብ የተጓዘችው አዲስ ማለዳ በሦስት ቀበሌዎች ላይ ሕያዋን አለመኖራቸውን ታዝባለች። በስፍራው ከሰባት ወራት በፊት ግጭቶች ተከስተው ከባድ ጥፋት ተፈጽሞ ማለፉን እና ይህም በስፍራው ለሚገኙ ሰዎች መፈናቀል ምክነያት እንደሆነው አካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በዋናነት የተደራጁ ቡድኖች በቀስት እና በጠመንጃ ጉዳት ሲያደርሱ እንደነበር እና የክልሉ ልዩ ኃይል ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ስፍራውን ለማረጋጋት እየሞከሩ እንደሆነ እና አሁንም አልፎ አልፎ ጥቃት አድራሾች ሙከራ እንደሚያደርጉ እና የጦር መሳሪያ እና ትጥቃቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እንደሚመጣም ጠቁመዋል። ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት በስፍራው በሰላም እና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየደረጉ የሚገኙ የፌደራል ፖሊስ አባላት ይናገራሉ።ይሁን እንጂ አስከ አሁን የአጥፊዎች ትጥቅ ከመንግስት የጸጥታ አካላት ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ቢሆንም ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ስጋት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ በስፍራው በመገኘት የሰበሰበችው መረጃ እንደሚያመለክተው ከመፈናቀል የተረፉት ሰዎች አሁንም ስጋት እንዳለባቸው እና አዲስ ማለዳም በስፍራው ስትገኝ ለማስተዋል እንደተሞከረው እጅግ የበዛ በመከላከያ እና ፌደራል እንዲሁም ልዩ ኃይል አባላት ከፍተኛ ቁጥጥር አድርገውልንም ነበር። እንደ አካባቢው ሰዎች ገለጻም በስፍራው በየዕለቱ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰሙ እና የፌደራል የጸጥታ ኃይላት ከመጡ በኋላ ግን ዕረፍት ማግኘታቸውን አልሸሸጉም።

ይህ እንደማሳያ ያስቀመጥነው ጉዳይ በዚህ ኣባቢ ብቻ ሳይሆን ሕግ በላይትን እንዲሁም ሕገ ወጥ ታጣቂዎችም ከዚህም ከዛም እየተበራከቱ መምጣታቸው የወደፊቷን ኢትዮጵያ አሻግሮ ለማየት አሳሳቢ የሚያደርገው ነው ሚሆነው። በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚችል ደረጃ ሕገ ወጥ መሳሪያዎችን በድብቅ በማዘዋወር እና ለገበያ በማቅረብ በርካታ ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ገዝተው እንዲታጠቁ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ምስክር መሆን ትችላለች። በሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ እና አካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ መሳሪያ ዝውውሩ መጧጧፉንም ምንጮች ከስፍራው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የእርሻ ጥማድ በሬዎች እየተሸጡ ለመሳሪያ መግዣ ሲውልም የዓይን እማኞች መታዘባቸውንም ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ ከስፍራው እንዳገነችው መረጃ መሰረት ከሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውሩ እና በሕገ ወጥ መንገሰድ ከመታጠቅ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በሰላማዊን ይሞካሽ የነበረው ደምቢያ ወረዳ እና በቅርቡ ገበታ ለአገር በተሰነው መርሃ ግብር ውስጥ የተካተተችው ጎርጎራ ከተማ አንዳንድ ሕገ ወጦች እየተስተዋሉባትም እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በተወሰነ ስፍራ ተገነው መረጃ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ተመሳሳይ ጉዳይ እንዳለ እና ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በክልሉ መረጋጋቶች ታይተውበት እንደማያውቁ እና ክልሉ ከጎረቤት አገራት ጋር እንደመዋሰኑም በሕገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያዎች ስለሚገቡ እና ለሽያጭም ስለሚውሉ በስፍራው በርካታ ታጣቂዎች ለመፈጠራቸው ምክንያት እንደሆነም ይነገራል።

በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወረውን ሕገ ወጥ መሳሪያ መንግስት ለመቆጠጠርም ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም እና በዚህም ረገድ በርካታ የሕገ ወጥ መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ እና ገብተውም በሕገ ወጥ መንገድ ሲሸጡ በቁጥጥር ስር በማዋል ስራ ላይ እንደሚገኝም የሚታወቅ ሀቅ ነው። ይሁን እንጂ አገባብ ታክቲካቸውን ቀየሩ እና በቁጥር ላቅ ያሉ ዜጎችን የጦር መሳሪያ ባለቤትነት ያረጋገቱ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውሮች ግን አሁንም ተጠናክረው ለመቀጠላቸው አዲስ ማለዳ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች ያሰበሰበቻቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ደግሞ በእጅጉ በነዋሪዎች ዘንድ ስጋትን የሚፈጥር እና ዜጎች በነጻነት ወጥተው ሰርተው የመግባት መብታቸውን በእጅጉ የሚነፍግ እንደሆነ እየተጠቀሰ ያለ ጉዳይ መሆኑንም በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች አዲስ ማለዳ ለመታዘብ የቻለችው ጉዳይ ነው። ይህ ሕግን የማስከበር ጉዳይ እና ሕገ ወጥን መሳሪያዎችን ዝውውር እንዲሁም ሽያጭ ከማካሔድ አኳያ የተለያዩ ጠበቅ ያሉ ሕጎችን እና አዋጆችን መንግስት ቢያወጣም በዚሁ በተጓዳኝ ግን የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ መሳ ለመሳ እየተጧጧፈ መሆኑን ለማወቅ ይቻላል። ከ2010 መጋቢት ወር ጀምሮ ወደ ፊት በመምጣት አገር የማስተዳደር ዕድሉን ያገኘው የለውጡ ኃይል በጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት እንዲሁም በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ፈቃድ የሌለው የጦር መሳሪያን ይዞ በመገኘት ረገድ ጠንከር ያለ አዋጅ ካወጣባቸው ጉዳዮች ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። በዚህም መሰረት የጦር መሳሪያን ማዘዋወር እና ፈቃድ አልባ የቶር መሳሪያን ይዞ መገኘት አስከ አስር ዓመት እስር እና 100 ሽ ብር መቀጮ እንደሚኖረው በአዋጁ ላይ መቀመጡም የሚታወስ ነው። ይህ ታዲያ አሁንም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር አቅም ያገኘ አይመስልም። በዚህ ብቻ ሳይገታ ከዓመት በፊት በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሚገቡ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ መነሻቸው የት አገር እንደሆነ በመደረሱ ከመነሻ አገራት ጋር በመነጋገር ከመነሻው ለማድረቅ የተደረገ ሙከራ መኖሩንም በወቅቱ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብርሀኑ ጸጋዬ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር። በእርግጥ ይህ ድርድር እና ውይይት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ አዲስ ማለዳ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ

በታሪክ የመጀመሪያው የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛ የስራ ዘመን መስከረም 25/2013 በይፋ ተጀምሯል። የኹለቱን ምክር ቤቶች ስራ ዘመን በይፋ ያስጀመሩት ደግሞ የኢፌዲሪ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ነበሩ። በዚህም ወቅት ታዲያ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን 2012 ዓመትን የአጠቃላይ እና ዋና ዋና ኹነቶችን ደስታ እና መከራዎችን በአገር ላይ ተጋርጦ የነበሩትን ‹‹ምርቅ እና ፍትፍት›› ነበር ሲሉም ነበር የገለጹት። ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም እና የተያውን በጀት ዓመት 2013 ዐቅድ እና ቢጋር በመናገርም የምክር ቤቶችን የስራ ዘመን በመልካም ምኞች አስጅምረዋል።

በዚህም መሰረት አጽንኦት ከሰጡበት እና በተያዘው ዓመት ትጥቅ የማስፈታት እና ሕግን የማስከበር ጉዳይ መንግስት በእጅጉ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት እንደሆነም አስረግጠው ተናግረዋል። በዚህም ረገድ ተጥቅ የማስፈታቱን ሂደትም በርካቶች በተስፋ የሚጠብቁት ጉዳይም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።  ፖለቲከኛ እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ ሆኑት ሙሳ አደም ስለ ጉዳዩ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ ‹‹በእርግጥ ሕግን ማስከበር የጸጥታ አካሉ እና መንግስት በአጠቃላይ ድርሻ ሲሆን ሕዝብም ሕግን የማክበር ግዴታ አለበት ይላሉ›› ይሁን እንጂ በትጥቅ ማስፈታት ረገድ ግን ውስብስብ እና ጠንካራ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት የሚያወጣውን ስትቴጂ እና መመሪያ መከተል እና ማየት እንደሚሻል በመግለጽ ከተጨማሪ ማብራሪያ ተቆጥበዋል።

በሕወሓት የትጥቅ ትግል ወቅት ላዕላይ አመራር ነበሩት እና በኋላም በከፍተኛ ኃላፊነት ስፍራ ላይ ያገለገሉ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት ሙሉጌታ በርሄ (ዶ/ር) ‹‹ከጦርነት ወደ ሰላም ሽግግር፤ የኢትዮጵያ ትጥቅ የማስፈታት፣ ከትጥቅ ወይም ከመከላከያ ሰራዊት መበተን እና መልሶ ወደ ሕብረተሰቡ የመቀላቀል በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ ሰፊ ትንታኔ አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እና ከ1983 እስከ 1989 ባለው ጊዜ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ እና በአፍሪካ ተወዳዳሪ አይገኝለትም ስለተባለው የደርግ ዘመነ  መንግስት አገር መከላከያ ሰራዊት ጉዳይ እንዲህ ያስቀምጣሉ።  በወቅቱ የደርግ መንግስት ተገርስሶ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት በርካታ ቁስለኛ ቀድሞው ጦር በደብረዘይት እና በታጠቅ ጦር ሰፈር ከትመው እንደነበር የሚጠቅሰው ጽሑፋቸው ኢትዮጵያ በወቅቱ ከጦርነት ወደ ሰላም ምታደርገውን ሽግግር ለማቀላተፍ የበዛ ቁጥር ያላቸውን የቀድሞው ጦር አባላትን ችግር አሰቀድሞ ሳይፈታ ማይታሰብ እንደሆነም ይገልጻል።

የሙሉጌታ ገብረሕይወትን ጽሑፍ እና ሐሳብ የሚጋሩት እና ተመሳሳይ ሀሳብ ያላቸው ደግሞ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ‹‹ መንግስት ለረጅም ዓመታት በትጥቅ ትግለ ውስጥ ነበሩ ሰዎችን ትጥቅ አስፈትቶ ያውም በአንድ ጊዜ ከዛ በኋላ ችግራቸውን እንዴት ሊፈታው እንደሚሞክር ሳያስብ ነው ትጥቅ ፍቱ የሚለው ። ይህ ደግሞ መጀመሪያ ሊታሰብበት የሚገባ እና ቅድሚያ ሊሰጠው ሚገባ ጉዳይ ነው›› ሲሉም ይናገራሉ።

ከጊዜያት በፊት አዲስ ማለዳ ለንባብ ባበቃችው ዕትም ላይ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ እና በትትጥቅ ትግል ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ ቡድኖች ጋረ በተያያዘ ይህን ዘግባ ነበር። ‹‹ ከወራት በፊት የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ አምስት ለሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ይደረግ ዘንድ የለቀቀው 10 ሚሊዮን ዩሮ እንዳልተሰጣቸው እና እስከ አሁንም በመንግስት እጅ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ለወታደሮቹ ገንዘቡ ድጋፍ እንዲደረግ የተሰጠው በመንግስት ደረጃ በፌደራል አደጋ መከላከል እና ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል እንደሚሆን እንደተገለፀላቸው የተጠቆመ ሲሆን አስካሁ ግን አምስት የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ከተቀረፁ በኋላ የትኛው ወደ ትግበራ ይገባ በሚለው ላይ ውይይት እየተደረገ ነው በማለት እንዳዘገዩት እንደተገለፀላቸው የኢትዮጲያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (የኢዜማ) ዋና ፀሃፊ የሆኑት አበበ አካሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አበበ እንደሚሉ በትጥቅ ትግል ውስጥ ቆይተው በኢትዮጵያ በተፈጠረው የለውጥ ሒደት በተደረገላቸው ጥሪ ወደ አገር ወስጥ የገቡት እና በአገር ውስጥ ትግል ሲያደርጉ የቆዩትን ጨምሮ አምስት ለሚሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ድጋፉ መታሰቡን ማለትም የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ( ኦነግ) ፣ (ደምህት) ዲሞክራሲ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ ፣የአማራ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ንቅናቄ (አዴህን) ፣ ኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም እስካሁን ባለው የዕርዳታ አሰጣጡ በተመለከተ ከፌደራል አደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ተገቢውን እርዳታ እንዲያደርግላቸው እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አበበ ። ከምግባቸው እና ከሚያርፉበት መኝታ ውጪ በየወሩ 3000 ሺህ ብር እየተደጎሙ እንደነበር እና መልሶ ማቋቋሙ እስኪሳካ ድረስ በዚሁ መልክ ነው መቆየታቸውን እየተከታተልን ያለነው ብለዋል ።

አበበ እንዳነሱት በመጀመርያው ዙር እርዳታው ( መልሶ መቋቋሙ) ይደረጋል የተባለው 3950 ለሚደርሱ ከሁሉም ትጥቅ ትግል ውስጥ ከነበሩ አባላት ዝርዝር ተወስዶ የሚደረግ መሆኑን ከአደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ዋና ፅህፈት ቤት እንደተነገራቸው ጠቅሰው፤ በቀጣዩ ዙር ግን ምን ያህል ወታደሮች ይሳተፋሉ ሚለው እንዳልተነገራቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል››።

ይህ ጉዳይ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት አሁንም ድረስ አለመፈታቱ እና ከላይ ከመረራ ጉዲና (ፕ/ር) እና በሙሉጌታ ገብረሕይወት (ዶ/ር) ሐሳብ ጋር የሚጣጣም እና አገርን ሰላም እንዲሁም ወደ ሰላም የሚደረግን ጉዞ በትጥቅ ማስፈታቱ መንገድ ላይ መንግስት ሊወስዳቸው የሚገቡ ጉዳዮች እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ እርምጃዎችን የሚያሰቀምጥ እንዲሁም በእጁ ላይ ያለውን ጉዳይም ቶሎ ለታሰብ ዓላማ እንዲያውልም ምክረ ሀሳብ የሚያስቀምጥ ነው።

ሙሉጌታ ገብረሕይወት በጽሑፋቸው በወቅቱ ተሰናባች ወታደሮችን በማሰናበት ረገድ እና ወደ ትጥቅ ፈተው ወደ ሕዝብም የሚቀላቀለሉበትን የተዘጋጀውን መመሪያ አካተዋል። በዚህም መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ ለተሰናባች ወታደሮች ራሳቸውን ለሰላማዊ እና ከሕብረተሰቡ ጋር አብሮ ለመኖር የሚያስችል ስነ ልቦና እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው። ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን በቀጣይም መልሰው የሕዝብ ሆነው የሚቀላቀሉበትን መስመር እና አፈጻጸሙን ሁኔታም ግልጽ ተደርጎ በመመሪያው ላይ ተካቶ እንደነበር ያወሳል። በመልሶ መቃለቀሉ ሂደት ላይ ሊደግፍ የሚችል አገራዊ ገቢ ምንጮችንም በተገቢው ሁኔታ የማሰስ እና የመገምገም ስራም ተከናውኗል። በመጨረሻም እንደተሰናባች ወታደሮች እና እንደሚገባቸው መጠን የሚደርሳቸውን መልሶ የማቀላቀል ስራውን በገቢዎች መደገፍ ስራም ተሰርቷል ሲል በጽሑፉ ተካቷል።

ቀድሞውን ጦር ከሁሉም አስቀድሞ ግን ትጥቅ በማስፈታት፣ በመበተን እና ተመልሶ ወደ ሕብረተሰቡ መቀላቀል ሒደትን በመገናኛ ብዙኃን በመጥራት እና በኢትዮጵያ ተለያዩ ጥግ ላይ ተበታትኖ የነበረውን ጦር ወደ አንድ ማዕከል እንዲገባ በማድረግ መንግስታዊ ጥሪ መደረጉ እንደነበር ሙሉጌታ ገብረሕይወት በጽሑፋቸው ይገልጻሉ።

በዚህ ሒደት ላይ ታዲያ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጡት መረራ ‹‹መንግስት በኃይል ትጥቅን ለማስፈታት የሞክራል ይህ ደግሞ ከባድ ነው የሚሆነው›› ሲሉ ገለጹ ሲሆን ሙሉጌታ ገብረሕይወትም ለፈውን የቀድሞውን ቶር ትጥቅ በማስፈታት እና በመበተን ረገድ ተሰራውን ስራ በጽሑፋቸው በገለጹበት ወቅት ትጥቅ በማስፈታት ረገድ ሁሉን አቀፍ እና አካታች ውይይቶች እና ሂደቶች መኖር እንዳለባቸው እና ይህም ሳይነ ከቀረ ውጤታማነታቸው እንደሚያጠራጥር አስቀምጠዋል።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ባሉት ክልሎች በተለየ ሁኔታ በሱማሌ ክልል የትጥቅ ማስፈታት እና ታጣቂዎችን ወደ ሕብረተሰቡ የማቀላቀል ብሎም ሰላማዊ ኑሮን መምራት ሚችሉበትን አግባብ በመፍተር ረገድ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ታውቋል። በዚህም ረገድ ቀድም ሲል በክልሉ ውስጥ አልፎ አልፎ በጎሳዎች መካከል የሚፈጠረውን ግጭት እና አለመረጋጋት እንደ ምክንያት ሚጠቀሰው በክልሉ ውስጥ ያለው ነፍጥ ያነገቡ ቡድኖች እና ግለሰቦች መሆናቸውን ነው። ይህንንም ተከትሎ ብረት የማስወረድ ስራ እና ክልሉን ፍጹም ሰላማዊ መድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ክልሉ የጸጥታ እና ደኅንነት አማካሪ መሐመድ ሙሳ ከአሀዱ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ባደረጉ ጊዜ ተናግረዋል። በክልሉ አንድ ስፍራ ላይ ሽማግሌዎችን እስከ መግደል ደረሱ ሽፍታዎች እንደነበሩ እና አሁን ግን በሰላማዊ መንገድ ሕዝብንም በማሳመን ትጥቅ የማስፈታት ሂደት እየተሰራ እንደሆነ ተጨምሮ ተገልጿል። በክል በአሁኑ ሰኣት ያለው የልዩ ኃይል በስነ ምግባር የታነጸ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ማስፈታቱ ሂደት እየተከናወነ ሲሆን ከሁሉ አስቀድሞ ግን በሕብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር ሂደቱ ውጤታማ እንደነበርም አዲስ ማለዳ ከክልሉ መንግስት እና ከአሃዱ ቴሌቪዥን ያገነችው መረጃ ያመላክታል።

ሕግን ማስከበር

የኢፌዲሪ ፕሬዘዳንት የ2013 የመንግስትን ዕቅድ ባስታወቁበት የኹለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ከመንግስት ውጪ በአገር ውስጥ ታጠቀ ኃይል እንዳይኖር ካሉ በኋላ ሕግን የማስከበር ጉዳይም ተቀዳሚው አጀንዳ እንደሚሆንም አስረግተው ተናግረዋል። ይህን በሚመለከትም መረራ ጉዲና ለአዲስ ማለዳ ሲነገሩ ‹‹ሲጀመር ኹለት ነገሮችን በአንድ አገር ውስጥ ማስኬድ አይቻልም። ትጥቅ ትግልን የሚያደርጉ እና መንግስት አንድ ላይ ሊሆን የማይችል ጉዳይ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ። በአንድ አገር ውስጥ የሚገኘው መንግስት ስርዓትን የማስከበር ግዴታም እንዳለበት ያስረዳሉ።

ከዚሁ በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) መንግስት ሕግ ማስከበር እንዳለበት እና በተለይም ደግሞ በቅርቡ ‹‹ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም›› በሚል አገር ለማተራመስ የሚተጉ ኃይላትን እንዲያስታግስ እና ሕግን እንዲያስከብር ባወጣው መግለጫ በሚገባ አስረግጧል። በተመሳሳይም ደግሞ በትግራይ ክልል የተካሔደውን እና ከፌደራል መንግስት ዕውቅና ውጪ የተከናወነውን ክልላዊ ምርጫ ተከትሎም የፌደሬሽን ምክር ቤት አዲሱ የትግራይ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደማይኖረው እና ይህም ሕጋዊም እንዳልሆነ አስታውቋል። ይህንን አስከትሎም የፌደራል መንግስት እጅግ ለትግራይ መንግስት ምንም አይነት ድጎማ በጀት እንደማያደርግ እና በቀጥታም ግንኙነቱ ከወረዳ ቀበሌ እና ከተማ መስተዳደር ጋር እንደሚገናኝም አስታውቋል። በተጨማሪም የፌደራል መንግስቱ ሕግን ከማስከበር ጋር ባለው ጉዳይ መሰረትም የፌደራል መንግስት ተቋማት ከክልሉ ጋር ደብዳቤ መላላክም ሆነ የተለያዩ ኹነቶች ላይ ማሳተፍ እንደማይገባም አስታውቋል። በወቅቱ የነበረውን የፌደሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔም ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንዲህ አስነብቦ ነበር ‹‹ የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚው አካል/ካቢኔ/ ህገመንግስታዊ ቅቡልነት ስለሌላቸው ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ምንም ዓይነት ህጋዊ ግንኙነት ማድረግ እንደማይችሉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባሄ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

ይህም በመሆኑም ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ከፍተኛ አስፈፃሚ አካላት ጋር እንደህጋዊ አካላት በመቁጠር ደብዳቤ መፃፃፍ፣ መረጃ መላላክ፣ የፌዴራል ተቋማት ለክልል ተቋማት የሚሰጧቸውን ድጋፎች መስጠት፣ በፌዴራል ደረጃ የሚካሄዱ መድረኮች ላይ ማሳተፍ የመሳሰሉ ጉዳዮችን ማድረግ አይቻልም ብለዋል፡፡

በአንጻሩ የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ የልማትና የአገልግሎት ተጠቃሚነቱ እንዳይስተጓጎል እንደ ቀበሌ ፣ወረዳ ፣ ከተማ ካሉ ህጋዊ የክልሉ መዋቅር ጋር ብቻ ግንኙነቱ እንደሚደረግና ይህም በሚዋቀር ኮሚቴ ክትትል እንደሚደረግ አቶ አደም ፋራህ በተለይ ለኢቲቪ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ውሳኔ ሊደረስ የቻለው የትግራይ ክልል መንግስትና ገዥው ፓርቲ ህውሃት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ባከበረ መልኩ የስራ ዘመኑ በምክር ቤቱ ውሳኔ የተራዘመውን የክልሉን ምክር ቤት የህግ አስፈፃሚ አካል ወደ ቦታው መመለስ ስላልቻሉ ነው ብለዋል አፈ ጉባኤው፡፡

ውሳኔው የትግራይ ህዝብ ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ እየተከተለ ባለ ቡድን ምክንያት ከሰላም፣ልማትና መሰረታዊ አገልግሎት አንፃር እንዳይጎዳና የትግራይ ህዝብ እንደሌሎች የአገራችን ህዝቦች መሰረታዊ የልማትና የደህንነት አገልግሎቶች እንዲያገኙ ታስቦ መተላለፉንም አመልክተዋል፡፡

‹‹ይሄ ሊሆን የቻለው ለትግራይ ህዝብ ካለን ክብር ነው›› ያሉት አፈ-ጉባሄው፤‹‹ ህዝብም እንደ ሌሎች የአገራችን ህዝቦች ሊያገኘው የሚገባውን ጥቅም ሊከበርለት ይገባል ከሚል ጽኑ እምነት የመነጨ ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የውሳኔ አፈፃፀምም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥናት ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ይሆናል ተብሏል፡፡

በህገወጥ መንገድ የተቋቋመው የትግራይ ምክር ቤትና ካቢኔ ህጋዊ ሰውነት ስለሌለው የፌዴራል መንግስት የበጀት ድጎማ እንደማያደርግለትም ተመልክቷል፡፡

በቀጣይ በክልሉ ካሉ የከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በተለይ ህዝቡ ማግኘት የሚገባውን መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኝ በጥናት ተመስርቶ ተፈፃሚ ይደረጋልም ተብሏል፡፡›› ይህን በሚመለከትም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የፓርቲ አባላት ውሳኔው ተገቢ መሆኑን አምነው ነገር ግን  አሁንም በቀጣይ መደረግ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አልደበቁም።

መደምደሚያ

ትጥቅ በማስፈታት ረገድ መንግስት በርካታ አካሔዶችን መከተል እንደሚኖርበት የታመነ ነው። በዚህም ረገድ ሙሉጌታ ገብረሕይወት በጽሑፋቸውበወቅቱ የነበረው ትጥቅ የማስፈታት እና ብተና ሒደት የተሳካ ነበረው የኣለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብነት አለመኖር እና በዛው በአገሩ መንግስት ሙሉ በሙሉ መተግበሩ እንደሆነ ያወሳሉ። ይህም ታዲያ ለዚህ ዘመንም የትጥቅ አፈታት ስርኣት ተግባራዊ እንደሚደረግም ሚታመን ሲሆን በተለይም ደግሞ በሱማሌ ክልል የተካሔደው እና እየተካሔደ ያለው ጉዳይም ለዚህ ማሳያ እንደሚሆን እሙን ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here