‹‹ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቃቸውን በማስፈታት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ይደረጋል›› የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

0
661

ለኹለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው 11ኛው የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ ጥቅምት 06/2013 ተጠናቋል።
ጉባኤውን አስመልክቶም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ከውሳኔ የተደረሱ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ላይም ‹‹ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቃቸውን በማስፈታት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ይደረጋል›› ያሉት ኮሚሽነሩ ‹‹በዚህ አገር ላይ ኹለት ታጣቂ ኃይል መኖር አይችልም›› ብለዋል።

በኢትዮጵያ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚንቀሳቀስ አደረጃጀት እንዳይኖር ኀብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ለማከናወን መወሰኑንም ተናግረዋል።
የኢ- መደበኛ አደረጃጀትን የማክሰም ስራ ለማከናወን ከስምምነት ላይ መደረሱን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የግጭት መነሻዎችን ማጥናት እና በጥናት የተደገፈ የቅድመ መከላከል ስራዎች ማካሄድ ሌላው ጉዳይ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
አክለውም ሕብረተሰቡን ያማከለ የወንጀል መከላከል ስኬታማ እንዲሆን የማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ማስፋትና ከህዝቡ ጋር ያለውን ቅንጅት በትኩረት እንደሚሰራበትም ገልጸዋል።

ከፌዴራልና ከክልል ፖሊስ ስምሪት ባሻገር ያልተሸፈኑ ቦታዎች ካሉም ሚሊሻዎችን በአግባቡ በማደራጀት የተናበበ ስራ በመስራት ችግሮችን መፍታት የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የሰራዊቱ ደሞዝ ስኬል ተጠንቶ መጠናቀቁን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው፤ የህክምና፣ የቀለብ፣ የሙያ አበል እንዲሁም የትምህርት እድል እንዲያገኙ ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here