መንግሥት ሕግን ያክብር ከአዙሪት እንውጣ!!

0
564

በአንድ አገር ውስጥ ሕግን አክብሮ የሚኖር ሕዝብ ሕግን በሚያስከብር መንግስት ተከብሮ እንደሚኖር እና ሕግም ለአገረ መንግስት መዝለቅ እና መቃናት ዘብ ሆኖ ይቆማል። በአንድ አገርም ሕግን ከማክበር እና ከማስከበር አኳያ እከሌ እና እከሌ ተብሎ የማይለይ እና ሁሉም በሚኖርበት አገር ሕግ ተገዝቶ እና ተስማምቶ ሊኖር ራሱ የአገር መተበቂያ ዘቡ ሕግ ያዛል ይደነግጋልም።

ይህ ታዲያ እንደ አገር ኢትዮጵያንም ብዙኃኑ ከተስማማበት እውነታ እና ገሀዳዊ ሐቅ የሚለያት አይደለም እና በኢትዮጵያም ይህ እንዳይሆን የሚደርግ ክስተት ወይም ልዩ ገጠመኝ አይኖርም። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መንግስት በሕግ ማስከበሩ ረገድ የታዩበትን ክፍተቶች ነቅሳ በማውጣት እንዲህ መሆን የለበትም፤ መንግስት ሕግን ለማስከበር መስነፍ የለበትም እና የሕግ የበላይነት መከበር ከሁሉም በፊል ሊቀድም ግድ እንደሆነ አስረግጣለች። የታዩ ክፍተቶች የመደፈናቸውን ያህል ግን ታዲያ መንግስትም ራሱኑ ያወጣውን ሕግ ጥሶ ሕግ ማለት ወደ ግለሰቦች ደረጃ በመውረድ እንደተፈለገው ሌላውን መጉጃ እና ማሳቀቂያ ሲሆን ደግሞ መመልከት ተጀምሯል። ‹‹ባለቤት ያቀለለውን ባለዕዳ አይሸከመውም ›› ነው እና ተረቱ ራሱ መንግስት አገርን እያስተዳደረ የሚገነውን ሕግ በራሱ አውጥቶ እና አጽድቆ ነገር ግን ራሱ ሲጥሰው እና ሌላው እንዲያከብረው መጠበቅ የዋህነት ነው።

ከሰሞኑ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ሕግን የሚጻረር እና ጋዜጠኝነትን ሙያ ለማሸማቀቅ በእውቅ የተሰራ እንደሆነ ማሳያዎችም መጥቀስ ይቻላል። ግለሰቡ በሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት በሚል በፖሊሶች ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ከመወሰዱ አስቀድሞ በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላይ ጻፈ የተባለው ጉዳይ መነሾ እንደነበር በቁጥጥር ስር ከመዋሉ ጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ የወጡ የመንግስት እና ፓርቲ መረጃዎች ማሳያ ናቸው።

የ2020 የ Pen2Pen አሸናፊው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በእርግጥም በሰራው ስራ ስህተት ሰርቶ ቢሆን እና ስሜ ጠፍቷል ወይም ደግሞ ሐሰተኛ መረጃ ነው ሚል አካል ካለ በመጀመሪያ ደረጃ ትክክለኛውን መረጃ በማቅረብ ለዝግጅት ክፍሉ በማስረዳት ዕርማት ማውጣት አካሄድ እንዲሄድ የማድረግ ስራ ማሰራት እንደሚቻል የሚጠፋ ጉዳይ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በዚህ በተቀመጠው የመጀመሪያ እርምጃ ታዲያ ዝግጅት ክፍሉ አሻፈረኝ ብሎ ዕርማት ለማውጣት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ወደ ሕግ በመሔድ ክስ መመስረት ሚቻልበት አግባብ እንዳለ አሁንም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በቁጥጥር ስር ያዋለው አካል ሳይረዳ ይቀራል ማለት አይቻልም። ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መጥሪ የያዙ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሚችሉ ሕጉም ያዛል ያውም በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት በቀጠሮ ቀን ያልቀረበን አካል ነው እንደዛ ማድረግ የሚቻለው።

የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000ም ሆነ አሁን ጸድቆ በነጋሪት ጋዜጣ በመታተም ላይ ያለው የፕሬስ አዋጅ አንድ ጋዜጠኛ በጻፈው ጽሑፍ ክስ ሳይመሰረትበት ለተጨማሪ ምርመራ መታሰር እንደሌለበት ይገልጻል። ይሁን እንጂ መንግስት ራሱ ያወጣውን እና ያጸደቀውን ሕግ ተገዢ ሳይሆን ቀርቶ በድንገት ወደ ጋዜጠኛው የስራ ቦታ በመሄድ ለመያዝ መሞከር እና በኋላም የመጽሔቱን ዋና አዘጋጅ እና ማኔጂንግ ኤዲተርን በቁጥጥር ስር አውለው አንድ ቀን ካሳደሯቸው በኋላ ስንፈልጋችሁ ትመጣላችሁ በሚል አሰናብቷቸዋል።

ምንም እንኳን በቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያት ግልጽነት ጎደለው እና ሕጋዊነትን የተከተለ እንዳልሆነ ቢታወቅም በውል ለማይታወቀው የመለቀቃቸው ምክንያትም እንዲሁ ግራ የሚጋባ እና ሕግን በመንግስት እንደተጣሰ ማሳያ ነው።

ለዓመታት እንዲህ አይነት እሽክርክሪት ውስጥ ለኖረችው ኢትዮጵያ ይህ እንግዳ ነገር ባይሆንም ለውጥ መጥቷል አዲስ ነገርም ተግባራዊ እየሆነ ነው ሚዲያ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ነጻነት ለማረጋገጥ አስራለሁ ከሚለው አዲሱ ለውጥ መንግስት ደግሞ ይህን አይነት ግድፈት መታዘብ በእርግጥም ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ እንዳለን ሚጠቁም ነው ስትል አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። በቅርብ ጊዜያት በርከት ያሉ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ውለው ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ለወራት የታሰሩበት አጋጣሚ እና በኋላም በነጻ የተሰናበቱ እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል። ይህ ታዲያ ለአገር እንደ አራተኛ መንግስት ሆኖ የሚያገለግለውን ሚዲያ ኢንዱስትሪውን ካለው የቀነጨረ ዕድገት ላይ በባሰ ሁኔታ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን አያጠራጥርም።

በተስፋ እና በከፍተኛ ጉጉት የመጣውን ለውጥ ለማጣጣም በሚጓጉ ዜጎች ላይ ይህን አይነት ሳንካ መደቀን ከባዱን እና ያለፈውን ጊዜ ለማስታወስ እምብዛም ቀስቃሽ የማያስፈልገው ሕዝብ ነው እና ያለው በመንግስት ላይ ሚኖረው አመኔታ እጅጉን ይሸረሸራል። አሁንም ቢሆን ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ እና ከቀናት በኋላ የተለቀቀውን ጋዜጠኛ ጌጥዬን ብናነሳም በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የፍትህ መጽሔት ዋና አዘጋጅ አንተ ነህ ወይ ? የሚል ጥያቄ ቀርቦለት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። በመጀመሪያ ደረጃ ጋዜጠኛው የፍትህ መጽሔት ዋና አጋጅ ሳይን የባልደራስ ፓርቲ ልሳን ጋዜጣ ላይ ነው የሚሰራው። ይሁን እንጂ የፍትህ መጽሔት ላይ የሚሰራም ቢሆን የሚያሳስረው ጉዳይ በግልጽ የለም እና ጉዳዩ ከመንግስት ወገን ሕግን በመጣስ ወደ ተለመደው አዙሪት ውስጥ ለማስገባት ሚሞክር አይጠፋም እና መንግስት ሕግን ያክብር ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ግለሰብ ስሜ ጠፍቷል ወይም ደግሞ እኔን መሰረት ያደረገ ሐሰተኛ መረጃ ተሰራጭቷል የሚል ቅሬታ ሲገጥመው እንደ ግለሰብ ክስ መመስረት ሒደቶች እንዳሉ ቢታወቅም መንግስት መዋቅር በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት እርምጃ ለመውሰድ መሞከር አዲስ ማለዳ ተገቢ ነው ብላ አታምንም። ዛሬ በዚህ የተጀመረው አካሔድ ወደ ምርጫ እተንደረደረደረች ላላች አገር ሚዲያው እንዴት አይነት ነጻነት እና በነጻነት ስራን የመከወን ማስተማመኛ እንደማያገኝ ከወዲሁ እንዲሰማው የሚደርግ ጉዳይም ነው።

ምክንያቱ ደግሞ በአንዳች ነገር ላይ በስጋት ጋዜጠኝነት አይሰራም እና ሕግን በተከተለ መልኩ ያጠፉ የትኛውም አካላት ሊጠየቁ የሚገባ ሲሆን ደስ ያለው አካል እያሳሰረ የመናገር እና መጻፍ ነጻነትን በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን የሚገፍፍ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

አንድ ጋዜጠኛ በሙያው ወደ ሕዝብ ሚያደርሰው መረጃ ፍጹም ታአማኒነት ተሞላ እና ሚዛናዊ መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን። ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ስህተቶች ሲያጋጥሙ በአስቸኳይ ወደ እስር ቤት መውሰድ ግን ዘርፉን ከመጉዳት ባሻገር ሚጠቅመው ነገር አይኖርም። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከላይ ተፈጠረ እንደተባለው ጉዳይ ሲፈጸም ደግሞ ዲሞክራሲን በርቀት መሰናበት ግድ ሊሆን እንደሚችል አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here