በመተከል ዞን በጸጥታ ሥራ ላይ የነበሩ ሦስት ወታደሮች ተገደሉ

0
661

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን በጸጥታ ሥራ ላይ የነበሩ ሦስት ወታደሮች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች መገደላቸው ተገለጸ።
በዞኑ በንጹሀን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ግድያዎች በመፈጸማቸው እና በአካባቢው ሰላም በመጥፋቱ በመተከል ዞን ውስጥ የሚተዳደሩ አምስት ወረዳዎች ላይ የታወጀውን ኮማንድ ፖስት ለማስፈጸም የተሰማሩ ሦስት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቅምት 1 እና ጥቅምት 3/2013 መገደላቸውን የአካባቢው የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ አረጋገጡ።

የአካባቢው የአዲስ ማለዳ ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት ያሳለፍነው ሰኞ፣ ጥቅምት 1/2013 በቡለን ወረዳ ኤፓር ቀበሌ አንድ ወታደር በታጠቁ ኃይሎች በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ሲያልፍ አንድ ወታደር በጥይት ተመትቶ መቁሰሉን ገልጸዋል። በእለቱ በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ የቆሰለው ወታደር ወደ ቡለን ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገለት ነው ተብሏል።

በዚሁ ኤፓር በተባለ ቀበሌ ላይ ጥቅምት 3/2013 ምሽት ላይ ስድስት ወታደሮች ከሰፈሩበት ካምፕ አካባቢ በቀስት ተመተው ኹለቱ ወታደሮች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲልፍ አራቱ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ላይ መሆናቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ህይወታቸውን ያጡ ኹለት ወታደሮች ጥቅምት 4 /2013 በአካባቢው ማህበረሰብ የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተከውኗል ብለዋል።

ቀሪዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው አራት ወታደሮች ለህክምና ወደ ቡለን ሆስፒታል ተወስደው ሆስፒታሉ የወታደሮቹን ጉዳት ለማከም ባለመቻሉ ወታደሮቹ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ፓዌ ሆስፒታል መላካቸውን በቡለን ሆስፒታል ሀኪም የሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ ፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ አስረድተዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በአካባቢው ላይ በተደጋጋሚ በሚደርስ ግድያ የአካባቢውን ኗሪዎችን እና ከጥቃት የተረፉ የአይን እማኞችን በማነጋገር በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያለማሰለስ ስትዘግብ ቆይታለች። አሁን ላይ በአካባቢው ያለው የሰላም ሁኔታ ያለበትን ደረጃ ጥይቃ ኗሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጹ “የደህንነት ስነ ልቦናችንን አጥተናል” ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ከኤጳር ቀበሌ ድህንነታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ ወደ ቡለን ወረዳ ከተማ አቅንተው የሚኖሩ ግለስብ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ የአካባቢው ኗሪ ያሳለፍነው ሰኞ ጥቅምት 2/2013 በቡለን ወረዳ ልዩ ስሙ ችላንካ በሚባል አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በዋዜማው እሁድ ማታ ሊገደሉ መሆኑን በአንዲት ህፃን አማካኝነት መረጃ በማግኘታቸው ቀድመው በመሽሽ ወደ ቡለን ወረዳ ከተማ አቅንተው ከጥቃት መዳናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የአዲስ ማለዳ ምንጭ ሁኔታውን ሲስረዱ “እሁድ ምሽት አንድ የጉምዝ ብሔረሰብ የሆነች እና አንድ የጉምዝ ብሔረሰብ ያልሆነች ህጻን በሚጫወቱበት ጊዜ የጉምዝ ብሔረሰብ ያልሆነችው ህፃን ጭካ ስታቦካ የጉምዝ ብሔረሰብ የሆነችው ህፃን ለምንድን ነው ጭቃ የምታቦኪው የሚል ጥያቄ ስታቀርብላት ሌላኛይቱ ሕጻንም ቤት ልሰራ ብላ መልስ ትሰጣለች። በዚህም ወቅት የጉምዝ ብሔረሰብ የሆነችው ህፃን እናንተ እኮ ነገ ትገደላላችሁ ምን ይሰራልሻል ብላት የጥቃቱን እቅድ በህፃናቶቹ ጭውውት ድርሶን ወደ ከተማ ሸሽተን ዳንን።” ሲሉ አጋጣሚውን ገልጸውታል።

በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ባለፈው ሳምት የ12 ሰዎች ህይወት አልፋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመተከል ዞን ባጋጠመው የዜጎች ህይወት መጥፋት ዙሪያ ከኮማንድ ፖስት አመራር አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት የአካባቢው ነዋሪ ራሱን አደራጅቶ አስፈላጊውን ትጥቅ ታጥቆ የተጠናከረ የመከላከል አቅም መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፉት አራት ወራት በተደጋጋሚ በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች ህይወታቸውን ሲያጡ በሕይወት የተረፉት ደግሞ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው እና የስራ እንቅስቃሴቸው እስካሁንም ድረስ አንደታወከ እየገለጹ ነው።

አዲስ ማለዳ ስለ ሁኔታው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ክልሉ የኮምኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ብታደርግም ስለ ጉዳዩ ካዳመጡ በኋላ ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ገልጸው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here