ፍትህን ስንሻ!

0
418

‹ሌባ አለ፣ ኪሳችሁን እየጠበቃችሁ!› የሚል አዘውትሬ ትራንስፖርት ጥበቃ ከምቆምበት ታክሲ ተራ የምመለከተው ተራ አስከባሪ ወጣት አለ። ሁሌም የሚገርመኝ ታድያ ሌባውን እያወቀው ለምን አይነግረንም የሚለው ጉዳይ ነው። በአካባቢው ሁሌም የማይጠፉ ተራ በማስከበር ያሉ ወጣቶች በታክሲ ግርግር መካከል ያሉትንና ኪስ እየበረበሩ የሚሰርቁትን በደንብ ያውቋቸዋል። ግን ያስጠነቅቃሉ እንጂ ‹እነዚህ ሌቦች ናቸው› ብለው አይናገሩም።

ብዙ ሰው በዛ ታክሲ ተራ ተሰርቋል። ‹ተጠንቀቁ እያልን አትሰሙም!› ብለው አስቀድመው የሚቆጡትና ‹የራሳችሁ ጉዳይ!› የሚሉት ራሳቸው ተራ አስከባሪዎቹ ናቸው። ግን ‹ሌባው ማን እንደሆነ እያወቃችሁ ብትነግሩን ምን አለ!?› የሚለው ወቀሳ ከጆሯቸውም አይደርስ። ሌባውን ከመያዝና ከማስያዝ፣ ከማጋለጥም ‹ተጠንቀቁ!› ማለቱን አስበልጠው ነው። የሌቦቹን የመስረቅ ‹መብት› ሳይነኩ፣ እኛን ሊጠብቁ ነው። ፍትህ ወይም እውነት ማለት ይህ ነው?

ላነሳ የወደድኩት ጉዳይ ወዲህ ነው። ሁሌም የሴቶች ጥቃት ሲነሳ ወደ አእምሮዬ ደርሰው የሚመጡ ወጣትና ሕጻናት ሴቶች አሉ። በመኪና የተጠለፉ፣ አሲድ የተደፋባቸው፣ በስለት የተወጉ፣ በብዙ ወንዶች የተደፈሩ ብዙ ብዙ፣ ምስላቸውም አብሮ ወደ ዐይነ ሕሊናዬ ይመጣል። ለምን ቢባል መገናኛ ብዙኀን፣ ማኅበራዊ መገናኛ ገጾች የእነዚህን ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በሐዘኔታና ‹ይበቃል!› በሚል መንፈስ አጋርተዉታል።

ጥቃት አድራሾችስ? ምን ዓይነት የፍትህ አሠራር እንደሆነ ግልጽ ሆኖ ባያውቅም እንዲደበቁ፣ እንዳይታዩና እንዲሸሸጉ ይደረጋል። ይህ ምን ያህል ትክክል ነው? በእርግጥ ተጠርጣሪ ተብሎ የተያዘና ወንጀሉ ያልተረጋገጠን ሰው መደበቅ ተገቢ ሊሆን ይችላል፣ ግን የተበዳይ ያለመታወቅ መብት ተጥሶ በደል ማድረሱ የተረጋገጠ ወንጀለኛ ለምን ይሸሸጋል?

ኋላቀር ያስብል እንደሆነ አላውቅም፣ ግን የድሮን ጊዜ በዚህ አደንቃለሁ። እንዲህ ያለ አስነዋሪ ጥፋት ያጠፋ ሰው በአደባባይ እንዲዞርና ሕዝብ እንዲያየው ይደረግ ነበር። የሰረቀም ቢሆን በአደባባይ ወጥቶ እንዲታይ ይሆናል። ምን አልባት የሚበዛና ከልክ ያለፈ ቅጣት የነበረ ሊመስለን ይችላል፣ ሆኖም የሌላን ሰው የመኖር መብት የነፈገ፣ በሥነልቦና የማይሽር ጠባሳ ያኖረ ሰው ተገቢ ቅጣት እንደሚገባው እንስማማለን።

ጥፋት ያጠፋ ሰው አለመደበቁም በአንድ በኩል ማኅበረሰቡ እንዲጠነቀቅ ሲያደርግ፣ በአንዲት ሴት መስዋዕትነት ሌላዋ ሴት እንድትጠነቀቅ እንደሚባለው ሁሉ፣ በዚህ ሰው መገለጥ ሌላው ሰውም ወደ ጥፋት እንዳይገባ ይጠነቀቃል።

የዚህ ጉዳይ ጥያቄ ለፍትህ አካላት ቀርቧል፣ ጥቃት ማድረሱ የተረጋገጠ ሰው ተገልጦ እንዲታይ፣ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦች እንዲታዩና ማኅበረሰቡ እንዲያውቃቸው። ተፈትተው ሲወጡ መገለል እንዲያደርስባቸው ሳይሆን፣ ቢያንስ እንዲጠነቀቃቸው ያስችላል። እንጂ ከላይ እንዳነሳነው ተራ አስከባሪ፣ ‹ተጠንቀቁ አስገድዶ ሊድፍር፣ ሊጠልፍ የሚችል ሰው ተፈትቷል› ማለት ተገቢም በቂም አይደለም።

በዚህ ብቻ አይደለም። መንገድ ላይ አንዲት ሴት መቀመጫዋን ሲመቷት ወይም ምቾት የሚነሳ ንግግር ሲናገሯት፣ ሰዉ የሚመለከተው እርሷን እንጂ አጥፊውን አይደለም። ለወንዱ የበዛ መብት የሰጠ ማኅበረሰብ በመሆኑ፣ መንገድ ላይ አላስኬድ ያላት ሰው ሲኖር እንኳ፣ ‹ማን በየመንገዱ ሳቂ አለሽ? ማን ይህንና ያንን ልበሺ አለሽ? ለምን መንገድ አትቀይሪም?› ይላታል። ይህም ለአጥፊው የልብ ልብ ይሰጣል።

ፍትህን ስንሻ ይህ እንዲቀር ድምጽ ማሰማት ያስፈልጋል። ከዛ ደግሞ ተጽእኖ መፍጠር፣ ቸል አለማለትና የሚፈለገው መልስ እስኪገኝ መታገል ያስፈልጋል። ፍትህን ስንሻ የእውነት እንጂ የአንድ ሰው አጀንዳ ለማድረግ መሆን የለበትም።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here