የምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት አሃዞች ሲፈተሹ

0
732

እንግዲህ የ2013 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባ በሳምንቱ መጀመሪያ ተካሂዷል።ስድስተኛ የሆነ የፓርላማ ዓመት ስብሰባ ሲካሄድ ያሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ማለትም በዘመነ ኢሃዴግ ከዛም ብልፅግና ሀገሪቱ መተዳደር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ።ከመደበኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ውጪ በጠ/ሚ ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተደረገም የመጀመሪያ ዓመት ስብሰባ ነው።በዚህ ስብሰባም ጠ/ሚሩ እይታ ውስጥ የሚከታቸውን ሙሉ ልብስ ለብሰው ነው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተገኙት።

ባሳለፍነው መስከረም 25/2013 የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሁለቱን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን በከፈቱበት ወቅት እንደ አጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ሊከናወኑ የታሰቡተንና እየተደረጉ ያሉትን ተግባራት መጥቀሳቸው ይታወሳል።እናም ይህንኑ ንግግር በመመስረት የምክር ቤቱ አባላት ያላቸውን ጥያቄ እንዲያሰሙ በማስቀደም ነበር ስብሰባው የተጀመረው።ጠቅላይ ሚንስትሩም በመጀመሪያ ዙር የቀረበላቸውን ጥያቄዎች በዝርዘር ከመመለሳቸው በፊት በሳለፍነው ዓመት ውስጥ የተከናወነውን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ተግባር በአሐዛዊ መንገድ ተንትነው ለማቅረብ ሞክረዋል። የዚህ ትንታኔ ዐብይ ትኩረትም እነዚህን አሐዛዊ ሪፖርቶችን መሰረት በማድረግ በኢኮኖሚ ባለሙያዎችና በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እየተነሱ ያሉ ሀሳቦችን መሰረት ያደረገ ነው።

አብይ አህመድ(ዶ/ር) በቁጥር አስደግፈው ከገለፁኣቸው ነገሮች አንዱ ባሳለፍነው አመትና በያዝነው ሩብ ዓመት በኢኮኖሚው ላይ ታየ የተባለው እድገት ነው።ጠቅላይ ሚነስትሩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ የስድስት ነጥብ አንድ በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት መመዝገቡን አስታውቀው ይህ ቁጥር በአለም ላይ ብዙሃን ሀገሮች ካስመዘገቡት ከዜሮ በታች የአራት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት እጅግ የተሻለና ጥቂት ሀገራት ብቻ ያሳኩት ነው ብለዋል አብይ።መንግስት ከዕቅዱ የ2 ነጥብ 9 በመቶ ቀናሽ የሆነ ዕድገት ቢያስመዘግብም የተገኘው ዕድገት ግን አበረታች መሆኑን አመላክተዋል።”ኢትዮጵያ ብዙ ኮሮናዎች ያሉባት ሀገር ናት” የታሰበውን ያህል ባይሆንም ከወቅታዊው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አንፃር በበጀት ዓመቱ ተስፋ ሰጪ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል።ከኮሮና ወረርሺኝ ጋር ተያይዞ በመንግስት የተወሰዱ ዕርምጃዎች ማለትም እንደ አየር መንገድና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሙሉ በሙሉ አለመዘጋቱ ለዕድገቱ አይነተኛ ሚና ነበራቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ።

በመንግስት መረጃ መሰረት የሀገሪቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) በስድስት ነጥብ አንድ ከመቶ ሲያድግ ጠቅላላ ሀብት መጠኑ 107 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወይም 3 ነጥብ 375 ትርሊየን ብር ደርሷል። በዚህ ስሌት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ ከ1000 ዶላር በላይ በዓመት እንደሚያገኝ ያሳያል ይላሉ ቁጥሩን የፈተሹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ።በቀላል ቋንቋ የሀገሪቷ ጠቅላላ ሀብት ቢከፋፈል ዜጎች በወር 3000 ብር ያገኛሉ እንደ ማለት ነው።

መንግስት ከግብርና፤ከኢንዱስትሪና ከአገልግሎት ዘርፎች በተሻለ በማዕድን ዘርፉ 91 በመቶ የሆነና ከሌሎች ዘርፎች የተሻለ ዕድገት ማስመዘገቡን ገልጿል ለዚህም የተደረጉ የፖሊሲ መሻሻያዎችና የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ መከሰትን ተከትሎ ድንበሮች መዘጋታቸው ትልቁን አስተዋፅኦ እንዳደረገ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለቀረቡት የፓርላማ አባላት ጥያቄዎች የሰጡትን ግብረ መልስን ተከትሎ በተለይ ተመዘገበ ከተባለው ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ይገኛሉ።በዜጎች የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ አንጻራዊ ለውጥ ያላመጣና ከዕለት ወደ ዕለት እየናረ የመጣውን የፍጆተና የመገልገያ እቃዎች ዋጋ ንረት ያልቀረፈ እድገት ለመንግስት ሪፖርት ማድመቂያ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ ቢስ ነው ብለው የሚከራከሩ ግለሰቦች ሲኖሩ በአንፃሩ ከከተሞች ይልቅ በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል እየተደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ የግብርና እንቅስቃሴ ከአመት አመት እየተሻለ ያለና በሂደትም በከተሞች የሚሰተዋለውን የዋጋ ግሽበት የሚያረጋጋ ነው የሚሉ ወገኖችም አልጠፉም።

በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ዕይታ GDP የግብርና፤ የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፍ ድምር ውጤት ተወስዶ ነው የሚሰላው ስለዚህ በ2012 የግብርናው ዘርፍ በአራት ነጥብ ሶስት በመቶ ፤ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በዘጠኝ በመቶ እና የአገልግሎት ዘርፉ በአምስት ነጥብ ሶስት በመቶ ከሆነ ያደጉት ጠቅላላ ሀገራዊ ምርታችን በ ስድስት ነጥብ ሁለት በመቶ ነው አደገ መባል ያለበት ሚል ሀሳብን ሲሰነዝሩ ይታያል። ሆኖም ግን ቀደም ብሎ በነበረው ሳምንት የፋይናንስ ሚንስትሩ እድገቱ ሰባት ከመቶ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

በተያያዘም የኢትዮጵያውያን አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአንድ ሺህ ዶላር በላይ ደርሷል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በአመቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ለመመደብ የነበረን ጥረት ፍሬ ያፈራበት ነው ብለዋል።

እውን እንደቀረበው የበጀት አመት ሪፖርት መሬት ላይ ያለው የዜጎች ህይወት እድገቶች የተመላከቱበት ነው ወይ? አሁን ላይ ካለው ሰው ሰራሽና ተፈጥሮኣዊ ችግሮች አንፃር ተገኘ የተባለው እድገት ቀጣይነት ሊኖረው የሚችለው አይነት ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን በዚህ ትንታኔ ማንሳት ተገቢነት ያለው ጉዳይ ነው።
ዋሲሁን በላይ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ባለሙያና ተንታኝ ሲሆኑ በየጊዜውም ሀገራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና የዋጋ ግሽበት ንረት ላይ የተለያዩ ፅሁፎችን በመፃፍ ይታወቃሉ።በፓርላመው የቀረበው አሀዝ ጥቅልና ሀገሪቱ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቿ በአሐዛዊ መረጃዎቸ መሻሻሏን ለማሳየት የቀረበ ነው ብለው ያስባሉ።

ለአብነትም መንግስት የሀገራችን GDP 107 ነጠብ 4 ቢሊየን ዶላር ደረሰ ሲል ምን ማለት ነው ይላሉ? እንደ እሳቸው እምነት ከሆነ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ያስመዘገበው ጠቅላላ ሃገራዊ ምርት ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ አይበልጥም ባይ ናቸው ።ከመቶም ፈቅ ብሏል ከተባለ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች አሉ።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ የስድስት ነጥብ አንድ በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት መመዝገቡን ሲገልጹ የጠቅላላ የዜጎች የሸመታ አቅም አሳድገን ነው?ጠቅላላ ሀገራዊ ምርቱስ የመንግስትን የወጪ መጠን፤ ወደ ውጪ ኤክስፖርት አድርገን ያገኘነው እና ከውጪ ለማስገባት ባወጣነው ወጪ መካከል ባለ ልዩነት፤ የውጪ ብድር እና እርዳታ መጠን፤ በዜጎች የመሸመት እና ኢንቨስት የማድረግ አቅም ላይ ተመርኩዘን መሆን አለበት ባይ ናቸው ባለሙያው።

እንደ ኢኮኖሚስቱ አስተያየት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት እየተከተለው ያለው መርህ ፍላጎትን እንጂ አቅርቦትን የሚያበረታታ አይደለም በዚህም የዋጋ ንረት በሀገሪቱ ከ24 በመቶ በላይ እያለፈ ነው።ለሦስት ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል ሲባል በየትኞቹ ክልልሎች ምን ያህል የስራ እድል እንደተፈጠረ፤ ክልሎች ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በምን ያህል በመቶ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ መቀመጥ አለበት።የስራ እደል ፈጠራ ከሚታይባቸው ዘርፎች የአምራቹ ዘርፍ አንዱ ሲሆን ዜጎች በዚህ ዘርፍ ሲሰሩ የፍላጎት ዘርፍ ላይ የተንጠለጠሉ ነው የሚሆኑት።የቤት ኪራይ፤ትራንስፖርት የእለት ፍጆት ግዢዎችን ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው ስለዚህ መንግስት የፍላጎት ኢንደስትሪን እያበረታታ ነው ማለት ነው። ከአቅርቦት ይልቅ ለፍላጎት ያደላ ኢኮኖሚያዊ አካሄድ በተከተልን ቁጥር ዓለም ከዜሮ በታች እያደገ እኛ ከዜሮ በላይም አድገን ለውጡ ከዋጋ ንረት እና ስራ አጥነት ጋር አብሮ እንዲመጣ ያደርገዋል። አሁንም የሆነው ይሄ ነው ይላሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው።

የኢትጵያ የዋጋ ንረት ከመቼ ጀምሮ ነው እዚ ደረጃ የደረሰው ተብሎ ከተወሰደ ሀገሪቱ ሚሊኒየሟን ካከረበችበት አንስቶ ባለፉት አመታቶች የዋጋ ንረት በሀገሪቱ ከ15 በመቶ የሆነ ጭማሪ አሳይቷል።ለጭማሪው ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም አንደኛው ምክንያት ግን የምንከተለው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ነው።የምንከተለው ስትራቴጂ በባህሪው ፍላጎትን እንጂ አቅርቦትን የሚያበረታታ አይደለም።መንገዶች ተሰርተው ለGDP አስተዋፅኦ የማይኖራቸው ከሆነ፤ፕሮጀከቶች ተጀምረው የሚቋረጡ ከሆነ የፍላጎት መንገድን የሚከፍቱ ነው የሚሆኑት።ግብርናው ላይ ለሌሎች ዘርፎች እየተመደበ ካለው ድጋፍ የበለጠ ተሻሽሎ የሚቀርብበት ሁኔታ ካለ የአቅርቦት ጥያቄን በመመለስ ከፍላጎት ጋር ያለውን ሚዛን የሚያመጣጥነው ይሆናል እንደ ተንታኙ ሀሳብ።

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ከምግብ የሚነሳ እንደ መሆኑ መጠን የምግብ ዋጋን ማረጋጋት የመንግስት ተቀዳሚ ሚና ሊሆን ይገባል።መንግስት ምርትና ምርታማነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ከሆነ ነገሮች የተሻለ ይሆናሉና።

እርግጥ ነው በሀገሪቱ ቀጣይ የአኮኖሚ እድገት ዙሪያ ኹለት ኹነኛ አመላካቾች ይታያሉ እነዚህም በሀገሪቱ የተጀመሩ ያሉ እንደ የግድብና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ በተለይም በያዝነው ዓመት ተስፋ ሰጪ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።ሌላው ደግሞ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሌላ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ፕሮጀክት ነው።በአመቱ አጋማሽ ኹለቱ ተርባይኖች ተከፍተው ሀይል ማመንጨት የሚችሉ ከሆነ ትልቅ እድል ነው ምክንያቱም ሀይል ኢኮኖሚን ለማሳደግ የሚያበረክትው አስተዋፅኦ የሚታወቅ ነውና።

አሁን እየተሰሩ ያሉ የቱሪዘም መሰረተ ልማቶችም እንደ ጥሩ እድል ልንጠቀምባቸው እንችላለን በዚህ ሁኔታ ፕሮጀክቶቹ በሀገር ውስጥ ዜጎች በስፋት የመታየት እድል እያገኙ ያሉ ሲሆን በቀጣይም የኮሮና ቫይረስ (Covid-19) ስርጭት እየቀነሰ የሚመጣ ከሆነ የውጪ ቱሪስቶች በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ስለሚኖር ለሴክተሩም ለሀገርም የሚኖራቸው አበርክቶት ከፍተኛ ነው የሚሆነው እንደ ዋሲሁን አስተያየት።

የገንዘብ ለውጡ የቀጣይ የኢኮኖሚው መሻሻል አንዱ ገፊ ምክንያት ነው።ምክንያቱም የብር ኖት ለውጡን ተከትሎ ብዙ ገንዘቦች ወደ ባንኮች ተቀማጭ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል።እነዚህን ተቀማጭ ብሮች በጥንቃቄ ለስራ የሚውሉ ከሆነ ማለትም ለኢንቨስትመንት ተግባር በተለይ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።ምክንያቱም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ እቃን ወደ ውጪ በመላክ የተመሰረቱ በመሆናቸው ከዛም በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የሰው ሃይል የሚይዙ እንደመሆናቸው አንፃር እነዚህን ኢንቨስትመንቶች እየለዩ ብደርን ማቅረብ ጉልህ ሚና አለው።ከዛ በሻገር የግሉ ሴክተርም ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ የሚመቻች ከሆነ በሀገሪቱ ላይ አንድም የምርት ዕድገት ይኖራል በሌላ በኩል የዋጋ መረጋጋትም እንዲኖር ያስችላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ አንበጣ፣ ከፍተኛ የሆነ ጎርፍና ሌሎች ሰው ሰራሽ ክስተቶች ደግሞ ኢኮኖሚው ላይ ስጋት እየደቀኑ ያሉ ችግሮች ናቸው።አንበጣው ከ400 ሺ ሄክታር እያወደመ እንደሚገኝ እየሰማን ብዙሃኑንም እየመከትን ያለበት ሁኔታ ባህላዊ ከመሆኑ አንፃር ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ላይ የተደቀነ ስጋት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ይላሉ ዋሲሁን።

የህዝብ ቁጥር እድገት ላይም ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም በርካታ ናቸው፡፤የህዝብ እድገት መጠኑ ሁለት ነጥብ ስምንት ከመቶ ነው የሚለው ቁጥርም ብዙም አሳማኝ አይደለም።የቤተሰብ ምጣኔ መከላከያ አማራጭን እየፈለገ ዛሬም ድረስ አገልግሎቱን ያላገኘው ህዝብ 60 በመቶ ይደርሳል።ምክንያቱም ሀገሪቱ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አቅርቦቷ 40 በመቶ ስለሆነ።

የንግድ ስርኣታችንም ምንም አይነት እሴትን መጨመር በማይችሉ አካላት ጣልቃ ገብነት የተበተበ በመሆኑ በመሆኑ በምርት አቅራቢውና በሸማቹ መካከል ያለው ሰንሰለት በጣም ረዝሞ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት እንዲፈጥር ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ባለሙያው እነዚህ ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ስራ መሰራት አለበት ይላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here