የ አገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት መሻሻሉን ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ

0
1222

የብሄራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የብሄራዊ ባንክን የሶስት ወራት የስራ አፈፃፀም ባቀረቡበት መግለጫቸው ብሄራዊ ባንክ የዋጋ ንረትንና የውጪ ምንዛሬን ከመረጋጋት አንፃር፤የፋይናንስ ዘርፍን ጤናማነት ከመጠበቅ አኳያ እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ ግኝት ቁጠባ ኢንቨስትመንትን ከማበረታት አንፃር የተለያዩ ተግበራትን ማከናወቸውን አስታውቀዋል ።

በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ሀገሪቱ ከሸቀጦች ወጪ ንግድ 832 ሚሊየን ዶላር ማግኘቷን አስታውቀው ይህም ግኝት ከፍተኛ የሆነና ከአምናው ሩብ አመት እንቅስቃሴ ጋር ሲነፃፃር የ15 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው ተብሏል።በሸቀጦች ወጪ ንግድ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ዝቅተኛ የሆነ አሃዝ አስመዝግባ ነበር ያሉት ይናገር የሩብ ዓመቱ ግኝት አበረታች ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት በሸቀጦች የወጪ ንግድና ገቢ ንግድ መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ጉድለት (trade deficit) አምና ከነበረበት 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዘንድሮ ወደ 2.6 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ሊጠብ ችሏል ያሉት የባንኩ ገዢ ለዚህም የቁጥር መቀነስ ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸው ሸቀጦች ጭማሪ አይነተኛ ሚና ተጫውቷል ተብሏል።

የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ድርሻ አምና በሶስት ወራት ወቅት ከነበረበት 12.2 በመቶ በያዝነው የበጀት ዓመት ሁለት ወራት ብቻ ወደ 11 በመቶ ቀንሷል ብለዋል የባንኩ ገዢ።

በሌላ በኩል ባለፉት ሶስት ወራት ብሄራዊ ባንክ በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ወሳኝ አምራቾች ስራ እንዳይስተጓጎል በተለየ ሁኔታ ጣልቃ በመግባት ከፍተኛ ስራ እንደተሰራ የተገለፀ ሲሆን በተለይም ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የውጪ ምንዛሬ ከመመደብ አልፎ እንደ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እና የዘይት አምራቾች ላሉት ሁሉ የውጪ ምንዛሪ በመመደብ ኢኮኖሚውን የማረጋጋት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፖሊሲ አጥኚዎች የተለያዩ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ሲያቀርቡ እንደቆዩ የሚታወቅ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የወጪ ንግድ ምርቶችን በመጠንና በዓይነት አብዝቶ በማምረት፣ በጥራት ለዓለም ገበያ አቅርቦ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ ተገድቦ በመቆየት ሊከሰት የሚችለውን የተጋላጭነት አደጋ መቀነስ የሚቻልበትን አካሄድ በስፋት ሲገልፁ ቆይተዋል። የወጪ ንግድን ከማበረታታቱ ጎን ለጎን፣ የገቢ ምርቶችንም የመተካት ሥራዎችን በስፋት መሥራት ወሳኝ መሆኑን በስፋት ሲገለፅ የቆየ ጉዳይ ነው።
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት የምታስገባቸው ምርቶች ከፍተኛ በመሆናቸው ምክንያት ሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ እንዳታገኝ ሲያደርጋት መቆየቱን አንስተው ባለሀብቶች ፋብሪካን ገንብተው ከማምረት ይልቅ ከውጪ የተመረተ ምርት አምጥቶ በመሸጥ ሲተጉ ነበር ብለዋል።ከዚህ ባሻገርም ሀገሪቱ ላይ በሚከሰቱ የተለያዩ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ምክንያት የወጪ ንግድ በመቀነሱ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከዚህ በፊት ከፍተኛ እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

ብርሃኑ ጌታቸው በጅማ የኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የፋይናሺያል ኢኮኖሚከስ የፒኤችዲ ተማሪ ሲሆኑ በግሎባላይዜሽን ዘመን የሰው ልጅ አኗኗር ተመሳሳይ ነው በመሆኑም የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት ሰፊ ከመሆኑ አነፃር ከዚም በላይ በሀገራችን ቁጥሩ ለያሻቅብ የሚችል ፍላጎት ቢኖርም በሶስት ወራቱ የተገለፀው ሪፖርት ግን ይበል የሚያሰኝ ነው ይላሉ።

እስካሁን የኛ ኢኮኖሚ ተመሳሳይ ባህሪ አልነበረውም በዚህም ምክንያት ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት ባለሙያው ሆኖም ባህሪውን እየተረዳነው በመጣን ቁጥር የራሱ ዘዴ እንዳለው በመረዳት ከዚህ በላይ ሊቀነስ የሚችልበትን መንገድ መቀየስ እንደሚቻል እና ለዚህም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጥሩ ምሳሌ እንደሆነ ያስቀምጣሉ።

እንደ ዜጋ ህብረተሰቡ የሚያረካም ባይሆን የሚያባብል የሆነውን በሀገር ውስጥ የሚመረት ምርት የመጠቀም ልምዱን ማዳበር ከቻለ የተሻለ ነገሮች አንደሚኖሩ ባለሙያው ጠቁመዋል።

ወቅታዊው የአንበጣና የኮቪድ -19 በቀጣይ ቁጥሩን ለመቆጣጠርና ለመቀነስ ስጋት አይሆንም የሚል ጥያቄ ከአዲስ ማለዳ የቀረበላቸው የኢኮኖሚክስ መምህሩ ሲመልሱ በያዝነው የበጀት ዓመት ለግብርናው ዘርፍ ከተሰጠው ድጋፍ አኳያ አሁንም ሀገራዊ ምርት በተሻለ ሁኔታ የሚመረት ይሆናል ያሉ ሲሆን የምርት ፍላጎት መጨመሩም በዛው የሚሸፈን ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት አስቀምጠዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here