ርክክብና ክፍያ ለማይፈጽሙ መስሪያ ቤቶች አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣልባቸው ሃሳብ ቀርቧል
የፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፤ከግዢና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የነበረውን አዋጅ 649/2011 እያሻሻለ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
አዋጁን ለማሻሻልም ያስፈለገበት ምክንይት ከዚህ ቀደም የነበው አዋጅ ስለ ኮንትራት አስተዳደር በግልጽ የተብራሩ ነገሮች አለመኖራቸው አዋጁን ለማሻሻል አንዱና ዋነኛው ተጠቃሽ ምክንይት እንደሆነም አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ ‹‹የኮንትራት አስተዳደር›› ብሎ ርዕስ እንኳን የለም ያሉት በመንግስት የግዥና የንብረት ማስወገድ አገልግሎት የኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት ሰለሞን ፋንታሁን ፤ አሁን ግን እየተሻሻለ ባለው አዋጅ ውስጥ የኮንትራት አስተዳደር ብሎ ከማካተት ውጪም ቢዚህ ጉደይ ላይ ዝርዝር ጉዳዮች መካተታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሌላው ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ላይ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ግዢ ከፈጸሙ በኋላ በአምስት ቀናት ውስጥ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ቢሆንም ካልከፈሉ ግን ምን ዓይነት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የሚገልጸው ነገር ባለመኖሩ አዋጁን ለማሻሻ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አሁን እየተሻሻለ ባለው አዋጅ ውስጥም ግዢ ከፈጸሙ በኋላ ክፍያ በማይፈጽሙ መንግስታዊ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል ብለዋል -ሰለሞን።
የግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ክፍያ ብቻ ሳይሆን የንብረት ርክክብ ላይም የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ርክክቡ በምን ያህል ቀናት ውስጥ መከናወን አለበት የሚለውም በሚሻሻለው አዋጅ ውሰጥ እንደተካተተም ለማወቅ ተችሏል።
በአጠቃላይ ግን አዋጁ ሥራ ላይ በዋለባቸው ዓመታት በአፈጻጸም ወቅት ለታዩ ችግሮች መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ እንዲሁም አዋጁን ዘመናዊ እና ግልጽ ለማድረግ በመንግስት ግዢ አስተዳደርና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚከሰት የሕግ ጥሰት ታሳቢ በማድረግ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያካተተ ለማድረግ ታስቦ አዋጁን ለማዘጋጀት እንዳስፈለገም ተብራርቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከልም፤ ‹‹የመንግሥት የግዥ እና የንብረት ተቆጣጣሪ ባለስላጣን ከዚህ በኋላ ባለስልጣኑ እየተባለ የሚጠራ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ በዚህ አዋጅ እንደገና መቋቋሙንና ባለስልጣኑ ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ይሆናል›› ሲልም ተካቷል።
ባለስልጣኑም በመንግስትና የግዥ ንብረት አስተዳደር ፖሊሲዎች መርሆችና አፈጻጸም ላይ የፌደራል መንግስትን ማማከር፤ ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳደሮች የቴክኒክ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር በመንግስት መሥሪያ ቤቶች በጋራ ለሚፈለጉ ንብረቶች ደረጃ ማውጣትና የወጡትን ደረጃዎች ወጥነት ባለው መንገድ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ ከተሰጠው ኃላፊነት መካከል ተጠቃሽ ሲሆን ይህም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተካቷል።
የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ አዋጅ በአሁን ወቅት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን እና አዋጁ ይጽደቅ አይጽደቅ በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔያቸውን እየተጠባበቁ እንደሆነ ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የግዥና ንብረት አስተዳደር የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት በግዢ ከሚያቀርብላቸው ግብዓቶች መካከል የቴክሎኖሎጂ እቃዎች፣የስቴሽነሪ እቃዎች፣የንጽኅና ዕቃዎች እና የቢሮ እቃዎች ይገኙበታል።
ግብዓቶችንን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ውል በመግባት ግዢዎችን እንደሚፈጽም ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአሁን ወቅት ቁጥራቸው እስከ 20 የሚደርሱ የተለያዩ ተቋማት ግዢ ከፈጸሙ በኋላ በአምስት ቀናት ውስጥ ክፍያዎች መፈጸም ቢኖርባቸውም ነገር ግን ክፍያ ለመፈጸም ገና በሂደት ላይ መሆናቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይሁን እንጂ ተቋማቱ እነማን እንደሆኑና ምን ያህል ብር እንዳልከፈሉ ለመግለጽ ሰለሞን ከመናገር ተቆጥበዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013


