ሕክምና ባለሙያዎች ‹‹ሀይ›› ሊባሉ ይገባል!!

0
343

ከረጅም ዓመት የፈረንጅ አገር ቆይታው ወደ አገር ቤት የተመለሰውን የልጅነት ጓደኛየን አግኝቼ የባጥ ቆጡን ስንጨዋወት ነበር። ታዲያ ቀድሞም በነጭ ወዳድነቱ የምናውቀው ወዳጄ አሁን ደግሞ ይባሱኑ ብሶበት ነበር የመጣው። ረጅም ዘመናትን በኖረበት አገር ታዲያ እንዴት የተመቻቸ ኑሮ፣ ሁሉ በሁሉ የሆነ ከባቢ፣ የሰውን መብት ላለመንካት የሚጠነቀቁ ማኅበረሰብ መሀል መኖሩን በተመስጦ ለረጅም ሰዓታት አጠመቀኝ ብል ይቀለኛል። ታዲያ በዚህ ወቅር እንድ ነገር ሰነዘርኩ እንዲያው ዝምታየን ለመስበር ያህል።

በኖረበት አገር ያለውን የሙያ ስነ ምግባር እና ባለሙያዎች ያላቸውን ተጠያቂነት እንደ ቀልድ ነበር የሰነዘርኩት። ይሁን እንጂ ያገኘሁት ምላሽ ግን ከጠበኩት በጣም የተለየ ነበር። ‹‹ምን ነካህ እያንዳንዱ ሙያተኛ እኮ በሙያው የሚፈጽመውን ስህተት በሕግ እንደሚጠየቅበት ስለሚያውቅ በጥንቃቄ ነው የሚከውነው›› ሲል መለሰልኝ። እንደ ቀላል የመለሰው ጉዳይ ግን እኔን አርቆ የአገሬን ችግር እንድመለከት አድርጎኛል።

በእርግጥ በኢትዮጵያ ከቀን ወደ ቀን የሙያ ላይ ስህተቶች በተለይም ደግሞ በመሐንዲሶች እና በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ መታየቱ ብቻም ሳይሆን እየተበራከተ መምጣቱ ትልቅ ራስ ምታት መሆን ከጀመረ ሰነባብቷ። በተለይም ደግሞ በሕክምና ተቋማት ላይ የሚታየው ሕክምና ስህተቶች እና ስህተቶችንም ተከትሎ ተጠያቂ አለመኖር እጅግ ከባድ ጉዳይ ሆኗል። በሕክምና ተቋማት ስህተት እጅግ በጣም ለበዛው ከከፍተኛ ወጪ መዳረግ እስከ የአካል መጉደል እና የክቡር ሕይወት መጥፋት ተገልጋዮች ሲዳረጉ ማየት እጅግ የተለመደ ሆኗል።

አዲስ ማለዳ ከወራት በፊት በአንድ የመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ተገኝታ ትርፍ አንጀት በሽታን በቀዶ ጥገና ለመገላገል የገባችው የስድስት ኣመት ታዳጊ በደረሰባት የሕክምና ስህተት ለሰባት ወራት ራሷን መቆጣጠር የማትችልበት ደረጃ ላይ ሰውነቶቿ የማይታዘዙላት ሆና ለመመልከትም ችላ ነበር።

በዚህ ወቅት ታዲያ መንግሥትም ሆነ በየደረጃው ያለው የሆስፒታሉ የስራ ኃላፊዎች ምንም አይነት እርምጃም ሆነ የቀዶ ጥገናውን በሰራው ባለሙያ ላይ አለማድረጋቸው በእጅጉ ከሰብዓዊነት እና ከሙያ ስነ ምግባር አንጻር ተገቢ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። አንድን ሆስፒታል ብቻ አነሳን እንጂ በርካታ በተለይም ደግሞ የመንግሥት ሆስፒታሎች ዕጅግ የበዛ ጉድለቶችን እና ሙያዊ ስህተቶችን በአልጠየቅም ባይነት እና ግዴለሽነት ሲከውኑት መመልከት በእጅጉ አስፈሪ ጉዳይ ነው።
በሕክምና ስህተት ምክንያት ብዙዎች ቤት ቀዝቅዟል፤ ሕጻናት በልጅነታቸው መቦረቂያ ጊዜያቸውን አጥተዋል፤ አረጋዊያን ያለ ጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል። ይህ ዐብይ ጉዳይ ግን አሁንም በመንግስት የተሰጠው ትኩረት በእጅጉ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ እና ጥፋተኛ ተብሎ ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደበት የጤና ባለሙያ ባለመኖሩ የተነሳ ለግድ የለሽነቱ መባባስም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንዳለው አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተደጋጋሚ በሚደረጉ እና በአደባባይም ወጥተው እና ሕዝብ ይፍረደኝ የሚሉ የተጎጂዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበም ይገኛል።

በቅርቡ በአንድ ድምጻዊ ልጅ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ሕልፈትም በርካቶችን ልብ ያደማ እና በተለይም ደግሞ በወሊድ ምክንያት ለሕልፈት መብቃቷ እና ወላጆች እና ከቤተሰቦቿም ሀሳብ መረዳት እንደሚቻለው በሕክምና ተቋሙ ውስጥ ነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ያሳዩ የነበረው መዘናጋት እና ግድ የለሽት ለሕልፈት እንደዳረጋት ይናገራሉ። ይህ ግን አሁንም በሕግ አውጪው አካል የሚታየው መዘዘናጋት እና ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይህ በእጅጉ ቀላሉ ጉዳይ ቢሆንም ሕክምና ስህተት መፈጠሩን እንኳን ሪፖርት የሚደረግበት አካል አለመኖሩ ደግሞ ተጎጂዎች ከእነ ጉዳታቸው በቤታቸው ውስጥ ተቀምጠው ኑሯቸውን እንዲገፉ አድርጓል።

በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ስህተቶች በእርግጥም የሚጠበቁ ቢሆኑም፤ ነገር ግን በሕክምናው ዘርፍ ስህተቶች ቢቻሉ እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ማድረጉ በእጅጉ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ቢደርሱ እንኳን ተጠያቂ የሚሆን አካል ሊኖር ግድ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ክቡር በሆነው የሰው ሕይወት እና ለማይተካው የአካል ጉዳት መዳረግ በአገር እና በሕዝብ ላይ ሊያጋጥም የሚችለው የምጣኔ ሀብት ጫናም ቀላል አይደለም። በርካታ የመንግሥት ሆስፒታሎች እና አሁን አሁን ደግሞ የግል ሕክምና ተቋማት ላይ እየተበራከተ የመጣው የሕክምና ላይ ስህተት ‹‹ሀይ›› ባይ ያጣ ይመስላል።

በሌሎች ተግባራት መጠመድ እና በተለይም ደግሞ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሌሎች ሕክምና ተያያዥ ጉዳዮች ተዘንግተዋል። ነገር ግን አሁንም አልረፈደም እና በሕክምና ዙሪያ ላይ ያለው መዘናጋት ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትል እና ስር ሳይሰድ ከወዲሁ ሊታረም እና ሕግም ሊበጅለት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

አምራቹን ኃይል በቤት ውስጥ እያስዋለ ያለው የሕክምና ስህተት፤ በቋፍ ላይ ላለው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ጭራሹኑ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል። በአንዲት ዕድሜያቸው ለገፋ ሴት ላይ የሕክምና ስህተቱ እንዲህ ነበር የተፈጠረው። ትንሽ የሕመም ስሜት ተሰምቷቸው ወደ አቅራቢያቸው ሕክምና ተቋም አምርተው ምርመራ ከተደረጋለቸው በኋላ መድኃኒት ገዝተው እንዲወስዱ ይታዘዝላቸዋል። የተባሉትን መድኃኒት ገዝተው በወሰዱበት ወቅት ግን ያጋጠማቸው ከፈውስ ይልቅ ሰውነታቸው በሙሉ ከመጠን በላይ ማበጥን ነበር።

በአስቸኳይ መጀመሪያ ወደ ታዩበት የሕክምና ተቋም ያመሩት እኚህ አሩግ ከዶክተሩ ያገኙት ምላሽ ግን ‹‹ውይ ተሳስቼ እኮ ትክክለኛውን መድኃኒት አልሰጠሁዎትም›› የሚል ነበር። እንዲህ በማን አለብኝነት ምላሽ የሚሰጠው እና ስህተቱን የሚናገረው ሕክምና ባለሙያ ምንም የሚመጣበት ሕጋዊ እርምጃ ባለመኖሩ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ይህን እንደማሳያ አቀረብን እንጂ በየሥፍራው እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ዕልፍ እንደሆኑ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። ይህን ጉዳይ ታዲያ መንግስት በአስቸኳይ ሊያየው እና ሕጋዊ ማስተካከያዎችም ሆነ ማረቂያዎችን ሊያሳርፍበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

በመንግሥት ሆስፒታሎች ላይ የታየው የሕክምና ላይ ስህተት እና በመንግሥት በኩል የታየው ለዘብተኝነት ጉዳዩን ወደ ግል የሕክምና ተቋማት እንዲዛመት እንዳደረገው አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። በዚህም ምክንያት በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸው እና ወደ ፊትም እልፎች እንደሚደርስባቸው ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። መንግሥት በዚህ በኩል ያለውን ዝምታ ሰብሮ በአስቸኳይ እንዲያስተካክል አዲስ ማለዳ አቋሟን ትገልጻለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here