የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠሩ ግጭቶች ለተጎዱና ለተጠቁ ሰዎች ማቋቋሚያ የሚውል የኹለትነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ለማሠራጨት የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ጥምረት እና (ሲሲአርዲኤ) ገንዘቡን ያሰባሰበው የሰሜን አሜሪካ የካህናት ማኅበር ማክሰኞ ጥቅምት 17/2013 በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በተካሄደ ዝግጅት ተፈራረሙ።
በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ የተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የተዋጣው ገንዘብ የአሜሪካ መንግሥት የገቢዎች ባለሥልጣን በሚጠይቀው መሠረት የኦዲት ሪፖርት አቅርቦ ገንዘቡ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ የሚችልና በግብረ ሰናይ ተግባራት ረዥም ልምድ ያለው ድርጅት ተፈልጎ ሲሲአርዲኤ እንደተመረጠ የጠቆሙት ከሰሜን አሜሪካ የመጡት የማኅበሩ ሰብሳቢ መስፍን ተገኘ (ዶ/ር) ናቸው።አያይዘውም ገንዘቡ ሲሰበሰብ ዓላማው የሽብር ተግባራትን ለመደገፍ ነው የሚል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳዩ ይኼ እንዳልሆነ በማስረዳትና የመጨረሻ ተግባሩንም በኦዲት ሪፖርት ለማስታወቅ በመስማማት ከጥምረቱ ጋር ለመሥራት መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር በየጊዜው የሚለዋወጥ እንደሆነና አሁን ለምን ያህል ሰዎች ድጋፉ እንደሚሠራጭ በግልጽ መናገር አዳጋች እንደሆነ በመግለጽ የተጎዱት ወገኖች በየበረንዳውና በየመጠለያው እንደሚገኙ መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸውና የሚለብሱትና የሚበሉት የሌላቸው እንደሆነ በጉብኝት መረጋገጡን አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ክልልና በፌዴራል መንግሥት በኩል ተጎጂዎችን ለመደገፍ የሚበረታቱ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ምንም እንኳን የገንዘብ ማሰባሰብና ተጎጂዎችን የመለየት ተግባራት ቢከናወኑም በተግባር የታየ እንደሌለ የሲሲአርዲኤ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ተወካይ በመድረኩ በመቅረብ ባደረጉት ንግግር ባንኩ ከሲሲአርዲኤ በሚሰጠው መረጃ መሠረት ገንዘቡን ለማሠራጨት የሰው ኃይልና ሌሎች ዝግጅቶችን ማድረጉን አስረድተው ባንኩም በበኩሉ አስተዋጽኦ ለማድረግም ቃል እንደገባ ተናግረዋል።
በመጀመርያ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ ኹለት ሽሕ 170 አባወራዎችን ለመደገፍ ታቅዶ እንደነበር ነገር ግን ድጋፍ እንደሚሰጥ የሰሙና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደው የነበሩ ሰዎች እየተመለሱ በመሆናቸው ‹‹ቁጥሮች በየጊዜው እየተለዋወጡ ነው›› ያሉት ንጉሡ (ዶ/ር) መረጃው እንደገና እየተጣራ እንደሆነና በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ የገንዘብ ሥርጭቱን ለማጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013



