በኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ መካከል መካካል እርቀ ሰላም ተካሄደ

0
1366

ቀሲስ በላይ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንደሚያቋቁሙ መግለጻቸውን ተከትሎ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።ቤተ ክርስቲያኒቱ ባለፉት ጥቂት ቀናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ስታደርግ ከተነሱ ነጥቦች አንዱ በቀሲስ በላይና በሲኖዶሱ መካከል ዕርቀ ሰላም ማውረድ እንደሆነ መዘገባችንም አይዘነጋም።

የእርቅ ሂደቱን ሲመሩ የነበሩ አባቶች ዛሬ ጥቅምት19/2013 በሰጡት መግለጫ “በመጀመሪያ ቋሚ ሲኖዶስ በመቀጠልም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ባጸደቀው መሠረት የዕርቅ ሂደቱ ተጠናቋል” ተብሏል።

በመግለጫው ኦሮሚያ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መዳከም ያሳሰባቸው ወገኖች ችግሩን ለመፍታት በሚል የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ማቋቋማቸውን በማስታወስ “የተነሱት ችግሮች እንዳሉ በአባቶች ሊቃውንት እና ምእመናን ቢታመንም መፍትሔው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት መቋቋም ነው? የሚለው በአባቶች እና በምዕመናን ዘንድ መከፋፈል ፈጥሯል” ይላል።

በኦሮሚያ አለ የሚባለውን የአገልግሎት መዳከም በቋንቋው የሚያስተምሩ በቂ አገልጋዮች አለመኖር እና ሌሎችም የአስተዳደር ችግሮች እንዴት ይፈቱ? የሚለው ላይ ልዩነቶች እንደነበሩ ተገልጿል።

ስለዚህም ችግሩን በውይይት ለመፍታት የተቋቋመው የሽማግሌዎች ቡድን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አመራሮችን፣ ቋሚ ሲኖዶሱን እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን እንዳነጋገረ በመግለጫው ተመልክቷል።

“በኦሮሚያ ያጋጠመው የአገልግሎት መዳከም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር በሚቋቋም ጠንካራ አካል በኩል በአንድነት መፍታት የተሻለ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ታምኖበታል” ሲልም መግለጫው ያትታል።

በኦሮሚያ ያጋጠመው የአገልግሎት መዳከም የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ተደርጎ እንደሚወሰድ በመግለጽ “ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት በኦሮምኛ ቋንቋ የሚሰጠው አገልግሎት እጅግ በተጠናከረ መልኩ ለማካሄድ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች አንድ ሆነው እንዲነሱ አደራ እንላለን” ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here