እነልደቱ አያሌው ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገቡ

0
580

በነልደቱ አያሌው የሚመራ የቀድሞ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አባላት ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን የሕጋዊነት ጥያቄ በተመለከተ ደብዳቤ አስገባ። የፓርቲው የቀድሞ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የነበሩት አዳነ ታደሰ ታኅሣሥ 15 ለቦርዱ ያስገቡት ደብዳቤ በፓርቲው ላይ በተሠራ አሻጥር ሌሎች ወገኖች ፓርቲውን ያለአግባብ እንዲያስተዳደሩ ተደርጓል የሚል ቅሬታቸውን የሚገልጽ እና በቀድሞዋ የቦርዱ ሰብሳቢ የተጀመረውን የማጣራት ሥራ አዲስ የተሾሙት ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ እንዲቀጥሉበት የሚያሳስብ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የቀድሞው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ሐምሌ 2011 በተሰጠው መግለጫ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ፓርቲው ህልውናውን እንዲያጣ ተደርጓል ብለው የሚከራከሩት አዳነ በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከዐሥራ ሦስት በላይ አባላት በብሔራዊ ምክር ቤቱ ከተገኙ ፓርቲው ውሳኔ የማስተላለፍ መብት እንዳለው ቢደነግግም ሕጉ ግን ተግባራዊ አልሆነም ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ችግሩን በሚመለከት ውይይት ማድረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት አዳነ “ለቀድሞ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሳሚያ ዘካሪያ ችግራችንን የሚገልጽና አሰራሮች ተጣርተው ይታዩልን” በሚል የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብተናል ብለዋል። ይሁንና ከሰብሳቢዋ የሥራ ዝውውር ጋር በተያያዘ ጥያቄቸው መልስ እንዳላገኘ ጨምረው ገልጸዋል።
“ጉዳያችን ቶሎ የሚፈታልን ከሆነ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያዳግተን ነገር የለም” ያሉት አዳነ በአሁኑ ወቅት ኢዴፓን ወክሎ የሚንቀሳቀሰው ፓርቲም ሕጋዊ ማዕቀፍ የሌለው መሆኑን ገልፀዋል። “ላስገባነው ደብዳቤ ቦርዱ እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ምለሽ ካልሰጠን ወደ ሚመለከተው አካል ለማምራትም ተዘጋጅተናል” በማለትም አስጠንቅቀዋል።
በሌላ በኩል በምርጫ ቦርድ አውቅና የተሰጠው ኢዴፓ ከአርበኞች ግንቦት 7፣ ከከሰመው ሰማያዊ ፓርቲና በአንዷለም አራጌ ከሚመሩት የቀድሞ የአንድነት አመራሮች ጋር ውህድት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል። በቅርቡ የኢዴፓ ፕሬዘዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በምርጫ ቦርድ ዕውቅና እስከተሰጠን ድረስ ሥራችንን ከመሥራት የሚያቆመን የለም ማለታቸው ይታወሳል።
ላለፉት ዐሥራ ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ለሁለት በመከፈል ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ እንደገባ ይታወቃል። በእነ ልደቱ አያሌው የሚመራውና ዐሥራ ስምንት ያህል የቀድሞ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትን የያዘው ቡድን ኢዴፓ በሕግና በመርህ እየሠራ አይደለም በሚል ጫኔ ከበደ የሚመሩት ወገን ላይ ቅሬታ ማሰማታቸው ይታወሳል። ከክፍፍሉ ጋር በተያያዘ ኢዴፓ በክልል የሚገኙ አባላቱን አመኔታ ማጣቱም ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here