በሞያሌ ሰዓት እላፊ ታወጀ

0
527

ተደጋጋሚ ግጭት ባጋጠማት ሞያሌ የሰዐት እላፊ ማወጁን በፌደራል መንግሥት የተዋቀረው የሞያሌ ከተማ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
ሰዐት እላፊው መሠረት በሞያሌ ከምሽቱ 3፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 ድረስ ከፌደራል ጸጥታ አስከባሪ ኃይል አባላት ውጭ ማንም መንቀሳቀስ አይችለም፤ ሲንቀሳቀስ ከተገኘ ‹‹እንደተጠርጣሪ ተቆጥሮ በሕግ ይጠየቃል፤ እርምጃም ወሰድበታል›› ተብሏል።
ከላይ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአምቡላንስ ውጭ የትኛው ተሸርካሪ መንቀሳቀስ እንደማይችልም ታውጇል። እላፊ በታወጀበት ሰዐት የንግድ ሱቆችንና መጠጥ ቤቶችን ጨምሮ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ በከተማዋ መከወን እንደማይችልም አሳስቧል።
ሞያሌ ከተማን የሚዋሰኑት የሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች እያጋጠመ ያለው የፀጥታ ችግር ከአቅማቸው በላይ መሆኑን በመጥቀስ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸው ተመልክቷል። ይህን ተከትሎም ኃላፊነቱ ለፌደራል መከላከያ ሠራዊት፣ ለፌደራል ፖሊስና ለጸረ ሽብር ኃይል መሰጠቱ ታውቋል። በዚህ መሠረት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የአካባቢውን ሰላምና የሕዝቡን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲል ላልተወሰነ ጊዜ በማታውና ሌሊቱ መርሀ ግብር የሠዓት እላፊ ማወጁን ይፋ አድርጓል።
በሞያሌ ተደጋጋሚ ግጭቶች እየተነሱ ለበርካታ የሰው ሕይወት ኅልፈት፣ ንብረት መውደምና ዜጎች መፈናቀል ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ ዋነኛ የግጭት መነሻውም በሞያሌ አካባቢ በሚኖሩ የኦሮሚያና የሱማሌ ጎሳዎች የመሬት ይገባኛል ጥያቄ መሆኑም ይነሳል፡፡
አዲስ ማለዳ በታኅሣሥ 20/2011 ዕትሟ ሰፊ ቃለ ምልልስ ያደረገችላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የሥነ ሰብዕ (‹አንትሮፖሎጂ›) መምህርና ተማራማሪው ጌታቸው ካሳ (ዶ/ር) በሞያሌ አካባቢ ለሚፈጠረው ተደጋጋሚ ግጭት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ደረጃ በሱማሌ ገሪ እና በኦሮሚያ ቦረና ጎሳ መካከል ይዘራ የነበረው ትርክት ስህተት መሆኑ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ሕዝቦች በጋራ የሚኖሩና ብዙ ነገሮችንም የሚጋሩ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን የመሩ የተለያዩ መንግሥታት አንዱን ጎሳ የኢትጵያዊነት ጠባቂ ሌላው ደግሞ በተቃራኒው አገር አፍራሽ አድርጎ መሳልና በሥልጣንም ሆን ተብሎ ጫና እንዲያሳድሩ ማድረግ እንደነበር የሚያነሱት ተመራማሪው ዛሬ ላይ ለሚፈጠሩት ግጭቶች ዋነኘ መንስዔዎች መሆናቸውንም አክለዋል።
አዲስ ማለዳ ሞያሌ ወደሚገኙት የኦሮሚያና ሱማሌ ክልል የዞን አስተዳዳሪዎች የእጅ ስልክ ተደጋጋሚ የጥሪ ሙከራን ብታደርግም ስልካቸው ሊሰራ ባለመቻሉ በቦታው ስላለው ሁኔታ መረጃን ማካተት አልቻለችም፡፡ በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች ግን ሰዓት እላፊው ተግባራዊ ስለመደረጉ ተናግረዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here