የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች መቀዛቀዝ ትልቅ ትኩረት ይሻል!

0
763

በኢትዮጵያ ምድር የለውጥ ነፋስ መንፈስ ከጀመረበት ታኅሣሥ 2010 ጀምሮ በመንግሥት በኩል የፖለቲካ ዓውዱን ከማስፋት አንፃር የተወሰዱ በርካታ አዎንታዊ እርምጃዎች አሉ፤ ይበል የሚያሰኝ ነው። በሌላ በኩል ለውጡ እንዲመጣ የዴሞክራሲው ሥርፀት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የወጣቶችን ጥያቄ መልስ አለመስጠቱ ከዴሞክራሲ እጦት እኩል በሚባል ደረጃ አስተዋፅዖ ማድረጉ የማይታበል ሐቅ ነው። ለዚህ ጥያቄ ግን አጥጋቢ እና ተስፋ ሰጪ ምላሽ እስካሁን አልቀረበም።
አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት በሚዘወሩባት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው መርካቶ ገበያ ባደረገችው ቅኝትና ባሰባሰበችው መረጃ መሠረት የንግድ እንቀስቃሴ መቀዛቀዝ መኖሩንና ይህም ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታ እንዳለው ተረድታለች። መርካቶ ትልቁ የኢትዮጵያ የገበያ ማዕከል እንደመሆኑ መጠን በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ማሳያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። የምጣኔ ሀብቱን እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ በተመለከተ አዲስ ማለዳ በአንኳር ምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚገቡ ጉዳዮችን ለመለየትም ሞክራለች።
የመጀመሪያ ምክንያት በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን በተመለከተ ሰርክ የሚጠቀሱት እንደ ጥሬ ዕቃ እና የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች እምብዛም የተለወጡ አለመሆኑ፣ ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው ያለመረጋጋት ወይም የሰላም እጦቱ በከተሞች መካከል የሚደረገውን መናገድና በራስ መተማመን ሸርሽሮታል። ይህም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብር ላይ ጥላ ማጥላቱ አይታበልም።
በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው በውጪ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች እጥረት ለምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብር መቀዛቀዝ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ መንግሥት የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ በየጊዜው የሚወስዳቸው እርምጃዎች በጥልቅ ጥናት የታገዙ እንዲሁም መሠረታዊ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ ከመሆን ይልቅ ብዙዎች እንደሚተቹት ከ‘ማስታገሻነት’ ሲዘሉ አልታዩም። ለአብነትም የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋይ አፋሳሾችን ለመሳብ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ከወዳጅ አገሮች ብድርና ዕርዳታ በማግኝት የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ከአጭር ጊዜ ግብ አኳያ በንፅፅር ለውጥ ያመጣ ቢሆንም፥ ከመካከለኛና ረጅም ግብ አንፃር ግን ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም። ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደማሳያ የሚጠቀሰው ከወራት በፊት የዶላር ምንዛሬ በመደበኛው የባንኮች ምንዛሬ እና በትይዩ ገበያ (‘ኮንትሮባንድ’) መካከል ይሄ ነው በማይባል ልዩነት መመንዘሩ ዶላር በሕጋዊ መልኩ እንዲመነዘር ያበረታታና በንፅፅርም የኢትዮጵያ የዶላር ክምችት ላይ በጎ አስተዋፅዖ አድርጎ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤ ይሁንና ይህ በጎ ጅማሮ ሊዘልቅ ግን አልቻልም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የአንድ ዶላር ዋጋ በመደበኛው የባንክ ምንዛሬ እና በትይዩ ገበያ መካከል እስከ ዘጠኝ ብር በሚደርስ የዋጋ ልዩነት እየተመነዘረ መገኘቱ ለዶላር ክምችት እጥረት መኖር ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ሌላው ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ለመተካት እንዲሁም ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ለማበረታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ያን ያህል መሬት ጠብ ሲሉ አይታይም። በዚህም ምክንያት ተጠባቂ የምጣኔ ሀብት እመርታ ሊመዘገብ አልቻለም።
በአራተኛ ደረጃ ምጣኔ ሀብቱ እንዲህ በተቀዛቀዘበት ወቅት ዘመኑንና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ባልዋጀ መልኩ የቤቶች ኮርፖሬሽን ያልተጠና ነጋዴዎችን በንቃትና በባለቤትነት ስሜት ባላሳተፈ በሚመስል ሁኔታ ‹የተጋነነ› የንግድ ቤቶች ኪራይ ማስተካከያ ማድረጉ በተቀዛቀዘው የምጣኔ ሀብት መስተጋብር ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ከመቸለሱም ባሻገር ውዥንብር በመፍጠር ያልተረጋጋ የምጣኔ ሀብት መስተጋበር እንዲኖር በማድረግ ረገድ የማይናቅ አበርክቶ እንዳለው አዲስ ማለዳ ተረድታለች።
በመጨረሻ ደረጃ ለምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ እንደሰበብ ሊታይ የሚገባው ብላ አዲስ ማለዳ የለየችው በመንግሥት ባለቤትነት የሚካሄዱ የትልልቅ ፕሮጄክቶች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት መቋረጥ ወይም መጓተት ከፍተኛ የዕቃ ግዢዎች እንዳይኖሩ በማድረግ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዙ እንዲኖር አስተዋፅዖ ከማድረገም ባሻገር ለወጣት ኃይሉ አዳዲስ ሥራዎች በብዛት እንዳይፈጠሩ በማድረግ ረገድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ አሉታዊ አስተዋፅዖ እንዳደረጉ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በመሆኑም አዲስ ማለዳ ይህንን የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ሌላ ውስብስብ ችግሮች ይዞ ከመምጣቱ በፊት መንግሥት በአፋጣኝ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ ጊዜ እና የረጅም ጊዜ የተጠኑ እርምጃዎች መውሰድ ይገባዋል ትላለች። የብዙዎችን ቀልብ የሳቡት ፖለቲካዊ እርምጃዎች በምጣኔ ሀብቱ ሊደገሙ ይገባል። አሊያም እስካሁን የተመዘገቡትን በጎ ጅምሮች አለማስቀጠል ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የከፋ መዘዝ ይዞ ሊመጣ ይችላል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here