ማየትና መመልከት!

0
632

ሴቶችን የምናይበት መነጽር ምን ይመስላል? የምንመለከትበትስ? ማየትና መመልከት ምንም እንኳ ተመሳሳይ ነጥቦች ቢሆኑም፣ ቀጥሎ ለምናነሳው ጉዳይ ግን በልዩነት እንድንመለከታቸው እጠይቃለሁ።

አንዳንዴ እንዲህ ያጋጥማል፣ በእጃችን የያዝነውን ዕቃ እንፈልጋለን። ተንቀሳቃሽ ስልካችንን እያወራንበት ወይም ፊት ለፊት እያየነው የጠፋ መስሎን ፍለጋ እንኳትናለን። ጤናማ ባይመስልም እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል። በተጓዳኝ ባለሞያዎች ሲናገሩ ይህ ማየት እንጂ መመልከት ባለመቻል፣ ልብ ባለማለትና ትኩረት ባለመስጠት የሚመጣ ነው ይላሉ።

እንደዛው ሁሉ ሴቶችን የምናይበትና የምንመለከትበት ዐይን ምን ይመስላል የሚለውን መቃኘት ያስፈልጋል። ይህም እንደ ሰብኣዊ ፍጡር ሳይሆን ማኅበራዊ ሥሪታችንን ተከትሎ የሚመጣ ነው። ታድያ በዚህ መሠረት ሴቶችን እንዴት እናያለን፣ እንዴትስ እንመለከታለን?

ብዙዎች በሚያዩት ይፈርዳሉ ወይም ‹ያ እንዲህ ነው፣ ይህ እንዲህ ነው› ይላሉ እንጂ፣ ለመመልከትና ለመረዳት ጊዜ አይሰጡም። ለዛም ነው የሴቶች ነገር ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ሚዛን ከመልክ፣ ውበትና ቁመና ጋር እንዲያያዝ የሆነው። እንደምናውቀው በቆየው የተመለደ አካሄድ፣ ቆንጆ ሴት ለዝምድናም ትመረጣለች። ‹ሙያ ከጎረቤት!› የሚለውን ብሂል ስንመለከትም፣ ዋናው መልክና ውበት ከተገኘ ሌላው ችሎታና ሙያ ከሰው መማር ይቻላል የሚል ነው።

መጽሐፍት፣ ፊልሞች፣ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች፣ ድራማና የተለያዩ የመድረክ ዝግጅቶች ሴቶችን የሚያነሱ ከሆነ ስለውበታቸው ይዘምራሉ። ይህም ከመደጋገሙ የተነሳ የሰዎች አካላዊ ዐይንና መመልከቻ ልቦናቸው አንድ የሆነ ያህል ይተሳሰራል። አንዱን ያለሌላው መመልከት ያቆማሉ።

ይህን በሚመለከት አንድ በተደጋጋሚ ሲነሳ የምሰማው ሐሳብ አለ። እንዲህ ነው፤ ብዙ የዓለማችንን ታሪክ በወረቀት ላይ ያሰፈሩት ወንዶች ናቸው። እነርሱም ታድያ ሲጽፉ የራሳቸውንና የወንዶችን ጀግንነትና ጀብዱ ያብራራሉ። በአንጻሩ ደግሞ ሴቶችን የጠቀሱ እንደሆነ ውበትን ወይም ሙያን አንጻር ያደርጋሉ። ይህ በአንድ ጎን ሴቶች የሚታዩበትን መነጽር ሲበይን፣ በሌላ በኩል ወንዶች ከጀግንነት አንጻር እንዲታዩና ውበት የተነሳ እንደሆነ ዳር ተመልካች እንዲሆኑ አድርጓል።

በአገራችን ወንድ ‹ሞዴል› የሚባል ነገር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተለመደ መምጣቱ እንጂ፣ ለወንድ ‹ውበት ምን ይሠራለታል፣ አንበሳ ገዳይ ከሆነ ይበቃል!› እንደሚባል የታወቀ ነው። ይህ ታድያ ለምን ለሴቶችስ ሊሠራ አልቻለም? ለምን ሴቶችን በመልክ፣ በቁመና፣ በሰውነት ቅርጽና መሰል አካላዊ ሁኔታዎች እንበይናለን? ለምን ከምናየው ተሻግረን መመልከት አንችልም? ነው ጥያቄው።

በዚህ ብዙዎቻችን ራሳችንን መታዘብ እንችላለን። ለምሳሌ በቴሌቭዥን መስኮቶቻችን ብቅ የሚሉ ሴቶችን ስናይ ‹ውይ! ምነው እንዲህ ሜክአፕ አበዛች! ፀጉሯ የራሷ ነው? ቅንድቧ ምን ሆኖ ነው?› ወዘተ እያልን ለዐይናችን የገባውን እንገመግማለን። በአንጻሩ ግን ያቺ ሴት የምትለውን፣ የምትናገረውን ምልከታና ዕይታዋን ለመመልከት ጊዜ አናገኝም።

በእርግጥ ሴቶችም ጋር ለዚህ ቅርብ የሚያደርጉ ጉዳዮች ያጋጥማሉ። በተለይም በብዛት የሚያስወቅሰው የውበት ማድመቂያ ቁሳቁስና ኬሚካሎችን አጠቃቀም በሚመለከት እርማት የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ ግልጽ ነው። ያም ቢሆን ግን ሰዎች በሚያዩት ሊበይኑ አይገባም። መመልከት እንዲችሉ ግን ጆሮ መስጠትና ማዳመጥ፣ ማስተዋልም ይጠየቅባቸዋል።

ያ ካልሆነ ሴቶች ወደ አደባባይ ወጡ፣ መድረክ ላይ ተናገሩ፣ ሐሳባቸውን አካፈሉ፣ ይጠቅማል ያሉትን ዕይታቸውን አጋሩ፣ ግን ጠብ የሚል ነገር አይኖርም። ምክንያቱም እኛ እየተመለከትን፣ እያዳመጥን ሳይሆን፣ እያየንና እየሰማን ብቻ ነው። ግምገማችን ሽፋኑ ላይ ብቻ ሆኖ በዛ ጊዜ እያጠፋን፣ በጥልቀት ለመረዳትና ለመግባባት ጊዜ አይተርፈንም። እናም የምናይበትና የምንመለከትበትን መንገድ ልብ እንበለው!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here