ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት ነው። ይህ የሚታወቀው ሰላም የታጣ ጊዜ ነው። በአገራችን ይህን እውነትና ክስተት በተደጋጋሚ ታዝበናል፤ አሁንም እማኝ እየሆንን ነው።
በጦርነት ብዙ አጥተናል። በጦርነት የተለየናቸው፣ የተለዩን አሉ። መንግሥት፣ ባለሥልጣናትና አመራሮችም የተሻለ መንገድ ፍለጋን ብለው <በእኔ መንገድ ሂዱ……አይ እኔ ባልኩት ይሻላል> ሲሟገቱ፣ ሙግታቸው እንዲህ ከፍ ብሎ ጦርን ያሳብቃል። በዚህ የማይጎዳ የለም። አንዳንዶች እንደሚሉት ምንአልባት ብቸኛው አትራፊ መወጊያውን የጦር መሣሪያ የሚሸጠው ነው።
ሰላም ማጣት፣ ግጭት እና ጦርነት አንድ ወደኋላ እንደመመለስ ነው። ግድ የሚልበት ጊዜ ቢኖር እንኳ፣ ንብረት ያወድማል፤ የሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል፤ የሥነ ልቦና ጫናም ያሳድራል።
ከዚህ በተጓዳኝ እንዲህ ባለ ወቅት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከባድ ነው። በማኅበረሰብ ውስጥም ሴቶች ካላቸው ሰፊ ድርሻ አንፃር ጉዳታቸው እና የሚያርፍባቸው ዱላም ይሰፋል። አጋጣሚውን እንዲህ ያለ ጥፉት ለመፈፀም የሚጠቀሙ እንዳሉ በተለያየ ወቅት ተመልክተናልና ነው። እናም ትኩረትና ጥንቃቄ ያሻል።
በዓለም ዙሪያ ሰላምና መረጋጋት በራቃቸው አገራትም ያየነው ይህን ነው። በስደት፣ በረሀብ፣ በችግር የሚደቆሱት እና ጉዳቱ በቁም ብዙ መከራን የሚያዩ ሴቶች ናቸው። የልጆቻቸው፣ የወንድሞቻቸው፣ የትዳር አጋራቸው ሞትና ሕመም፣ ዘልቆ ይሰማቸዋል።
ከዚህ ዓይነት አለመረጋጋት የምንወጣበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን እንመኛለን። ይህ ሰላም ለሁላችን ለእያንዳንዳችን፣ ያለብሔር፣ ያለቀለም፣ ያለፆታ ወዘተ ልዩነት የሚያስፈልገን በዋጋ የማይተመን ሀብት ነው።
በደም የተገነባ አገር በክብር ካልተጠበቀ፣ በጥንቃቄና በበጎነት ካልተያዘ፣ ግፍ ግፍን እንደሚያበዛ፣ መከራንም ሌላ መከራ ይከተለዋል። የወቀስነውን፣ ያኮነነውን፤ ደግሞ ወዲህ ከንፈር የመጠጥን ያዘንንበትን መልሰን በአዲስ ትውልድ ፊት ሲፈፀም ማየት ያሳዝናል። ሁላችን አስተዋፅኦ እንደሚኖረን ሳላነሳ አላልፍም። እንዲህ ነው፤
በዚህ ወቅት ሐሰተኛ መረጃዎች የሚያደርሱት ጥፋትና የሚፈጥሩት ውዥንብር ቀላል አይሆንም፤ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ግን ጥቂት አደናባሪዎችና ብዙ እውነትን የሚሹ ሰዎች ባሉበት ሐሰተኛ መረጃዎች እንዴትና ለምን አቅም ያገኛሉ ብለን ልንጠይቅ ይገባል።
ለጥፋት የተነሱ ሰዎች የሚያውቁትንም ሆነ የማያውቁትን ለማጋራት ይሉኝታን አያውቁም። እንደሚባለው ባላቸው ድብቅ ዓላማ ሊሆንም ይችላል። በዛም አለ በዚህ ግን በሬ ወለደ የሚል ያልተፈጠረ ጉዳይ ሊያወሩ ይችላሉ።
ኹለት አካላት ተከታዩን ጥፋት ያጠፋሉ፤ በአንድ ጎን ይህን መረጃ የሚያጋሩ፣ በሌላ በኩል እውነቱ እንዳልሆነ እያወቁ ዝም የሚሉ።
ያልተረጋገጠ መረጃን ማጋራት ከመረጃው አመንጪ ያልተናነሰ ጥፋት መሆኑ ግልፅ ነው። መከላከል አለመቻል፣ አለመቃወምና እውነትን አለመናገር ደግሞ ከሕሊና አንፃር ከቀደሙት የሚብስ ይመስለኛል። በዚህ ዙሪያ እንደ ማኅበረሰብ ኃላፊነቱ የሁሉም ነው።
መድኃኒት ለታመመ እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ ሰላምም ከመቼውም በላይ ሊዘመርለትና ሊጠራ የሚገባው አሁን ነው። በአፍ ሳይሆን በተግባር። ከዚህ አሁን እየሆነ ካለው ነገር ሁሉ ተምረን፣ ታርመን ነገ የትላንት ሥራችን ከሚያስረክበን ውጤት ተነስተን የተሻልን የማንሆን ከሆነ፣ እየከሰርን፣ ፊደል እየሆንን መቀጠላችን ነው። እናም እንደ አገር…ስለ አገር፤ ልብ እንበል።
ሊድያ ተስፋዬ
ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013


