የዲፋክቶዎች ፍልሚያ!

0
1409

የጠሉት የደርሳል የፈሩት ይርሳል ዓይነት ክስተት ነው ግዛቸው አበበ በንስር ዓይኑ ያየውን በሕወሐት አመራሮችና በፌደራሉ መንግሥት መሀከል እተካረረ መጥቶ ሊበጠስ ትንሽ ቀረውን ፖለቲካ ሽኩቻ ወዴት ሊደርስ ይሆን ነገሩ ከሮ ከሮ ጦር ሊማዘዙ ጥቂት ቀርቷቸዋል ሲል የግል መላምቱን የስቀመጠበት የዲፋክቶዎች ፍልሚያ ያለበትን ጽሑፍ ጀባ አልናችሁ።

መቀሌ ላይ የራሱን መንግሥትነት ያወጀ እና የአዲስ አበባውን ቡድን አመራር የማይቀበል ዲፋክቶ መንግሥት ተሰይሟል። አዲሰ አበባ ላይ ደግሞ ሲያሰኘው ሕገ-መንግሥትቱ ይከበር የሚል ከተመቸው ደግሞ ሕገ-መንግሥትቱን ትቶ በራሱ ስሜት አገሪቱን እና ክልሎችን ሊገዛ የሚፈልግ፣ ከሰባት ዓመቴ ጀምሮ ራሴን እንደ ንጉሰ እየቆጠርኩ ነው የኖርኩት የሚል መሪ በዲፋክቶ ንጉስነት ነግሷል። መቀሌ ላይ የቡድን አምባገነንነትን በማራመድ ላይ ያለው ዲፋክቶው መንግሥት እና አዲስ አበባ ላይ ደግሞ የግለሰብ አምባገነንነትን እያሰፈነ ያለው ዲፋክቶው ንጉስ፣ እርስ በርሳቸው እልህ ተጋብተውና በአወቅሁሽ ናቅሁሽ አመለካከት እየተነዱ ሊፋለሙ በሚችሉበት ስሜታዊ ዓለም ውስጥ ገብተዋል። ኢትዮጵያችን በነዚህ ዲፋክቶወች ፍልሚያ ችግር ውስጥ የመግባት አደጋ ተጋርጦባታል። ችግሩ እየከፋ ሄዶ ከፍተኛ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት መጠንቀቅ ተገቢ ነው።

የበላይነቱን በማጣቱ ጥርሱን የነከሰው የመቀሌው ዲፋክቶ መንግሥት እና ነገሮችን ሁሉ እንደ ጨዋታ የሚመለከተው፣ ችግሮችን ሁሉ እያድበሰበሰና የሕዝብን እልቂት እያቃለለ በፈንጠዝያ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ላይ ጊዜውን በማሳለፍ ላይ ያለው የአዲሰ አበባው ዲፋክቶ ንጉስ በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን ለጦርነት እየተዘጋጁና ጦር እየሰበቁ መሆኑን ችላ ብሎ ማለፍ በማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

የእነ አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስን ወንበር ከነ አሻንጉሊታዊ ተግባራቱ የወረሱት ወ/ሮ ሳህለወቅር ዘውዴ ዘመኑ ፍትፍት ነው እያሉ በዲፋክቶው ንጉስ ቤተ-መንግሥት በማሳለፍ ላይ ያሉትን ቅንጡ ጊዜ ሊነግሩን ቢሞክሩም ወይዘሮዋ ዐይናቸውን መግለጥ ከቻሉ ፍትፍቱ በደም የራሰ መለኪያውም በደም የተሞላ መሆኑ ሊከሰትላቸው ይችላልና ከቡረቃው ስሜት ወጣ ብለው ሕዝብ በምን ዓይነት ችግር ውስጥ እየኖረ የመሆኑን እውነታ ያዩ ዘንድ እንጋብዛቸዋለን። በእርግጥ ይህ ዘመን ለአንዳንዶቹ ፍትፍት ዘመን መሆኑ የሚካድ አይደለም። ለውጥ ማለት በቢሮአቸው እና በየቤታቸው ሰቅለውት የነበረውን የመለስ ዜናዊን ፎቶ አውርደው የዐብይ አሕመድን ፎቶ መስቀልና በነበሩበት ሁኔታ የሚቀጥሉበት ቁማር ለሆነላቸው ጠረንገሎ ልማታዊ ካድሬወች፣ ለልማታዊ ምሁራን፣ ለልማታዊ ጋዜጠኞች፣ ለልማታዊ አርቲስቶች እና ሌሎች ልማታዊ ጓዶቻቸው ዘመኑ ፍትፍት ነው ሊባል እንደሚችል አንጠራጠርም። ከዚህ ሌላ ከሰባት ወራት በፊት ጀምሮ ወረራ እንደሚያካሂድና ከፍተኛ ውድመት ሊስከትል እንደሚችል በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ማስጠንቂያ ተነግሮበት ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም ዓይነት ጉዞውን የሚያሰናከል ወይም ድንበር አቋርጦ እንደገባ የሚያጠፋ ቅድም ዝግጅት ሳይደረግለት ቀርቶ ኢትዮጵያችን ውስጥ የቱሪስቶችን የመሰለ ሕይወት የገጠመው አንበጣም ዘመኑ ፍትፍት እንደሆነለት እንጠራጠርም።

ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ፣ በክልሌ ነው የምኖረው ቢሉም ከወላጆቻቸውና ከአያቶቻቸው የአንዱ ወይም የሁለቱ ዘር እየተመዘዘ መጤ ነህ የሚባሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች፣ ዘመኑ ስለ ፍትፍት የሚያስቡበት መሆኑ ቀርቶ በሕይወት የመኖር ዋስትናቸውን የተነፈጉበት፣ ጥረው ግረው ባፈሩት ሃብትና ንብረት የመጠቀም እና የመበልጸግ መብታቸውን ተነጥቀው የሰቆቃ ሕይወት የሚገፉበት ዘመን መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ኦሮምያ ለብዙዎች የደም መሬት ሆኖ ቀጥሏል፣ ቤኒሻንጉል ለብዙዎች የእልቂት አውድማ እየሆነ ነው። ከዓመታ በፊት እነዚህ መጤ አማሮች ደናችንን ጨፍጭፈውና መንጥረው ጨረሱብን ተብለው የተገደሉበትና የተሳደዱበት የደቡብ ኢትዮጵያው ጉራፈርዳ በመለስ ዜናዊ ፌደራላዊ ንግሥናና በሽፈራው ሽጉጤ ክልላዊ አገዛዝ ዘመን የተጀመረው የዘር ጥቃት በዐብይ አሕመድ ፌደራላዊ ንግስናና በርስቱ ይርዳ ክልላዊ የአገዛዝ ዘመን ቀጥሏል። መቀመጫቸውን መቀሌ ያደረጉ የቅማንትና የአገው ሕዝብ ወኪል ነን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በሚሰጧቸው መመሪያወችና ምክሮች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችና በአካባቢአቸው ከሚኖሩ አማራወች ጋር ሲያካሂዱት የነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት ረገብ ቢልም ውጥረት እንደነገሰ ነው። መቀሌ ገባ ወጣ የሚለው የአፋር አብዮታዊ ፓርቲ በአማራ ክልል የተከሰተውን የመሰለ ግጭት በአፋር እንዲገደም ዳር ዳር እያለ ረዘም ያለ ካስቆጠረ በኋላ አሁን በቅርቡ የትጥቅ ትግል ለማደረግ እየተገፋፋሁ ነው ሲል ተሰምቷል። በኦሮምያ ኦነግ ሸኔ እና የሕወሀት ተላላኪወች በሚባሉ ሰወች የሚፈጸሙ ግድያወች እያሰለሰሉ ከመከሰት ያላባሩ ሲሆን በተቃራኒው ኦነግ ሸኔ እና የሕወሀት ተላላኪወች እየተባሉ የሚገደሉና የሚታሰሩ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት ከፍ እያለ ነው። ከአዲሰ አበባ መቀሌ የሚያመላልሰው መንገድ በቋሚነትም፣ ከባህርዳር አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚያመላልሱት መንገዶች አልፎ አልፎ በታጠቁ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ውለው የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሕይወትና የአካል ግብር እየተከፈለባቸው ነው። የኑሮ ውድነቱና ወደ ድኅነት አዘቅት መውረዱ የሚቆም አልመስል እያለ ነው። እንግዲህ እነዚህና ሌሎችም መንግሥት የለም የሚያስብሉ አደገኛና አሳፋሪ ሁኔታወች አየታዩ ነው ዘመኑ ፍትፍት ነው የሚባለው።

ፕሬዘደንቷ ለፓርላማው ባሰሙት ንግግር ውስጥ ይህ ‘ዘመኑ ፍትፍት ነበረ’ የሚለው ሃረግ በስህተት ተጽፎ ከመታረም አምልጦ የተነበበ ወይም ሳይጻፍ በአነባብ ስህተት የተባለ ነው ብለን ተስፋ እናድርግ። ነገር ግን ይህ አባባል ታስቦበትና መባል አለበት ተብሎ፣ ዝግጅት ተደርጎበት የተባለ ከሆነ ግን ከፍተኛ አደጋ አለ ማለት ነው። አውቆ አጥፊነትና ሕዝብን የራስህ ጉዳይ ብሎ ግድ የለሽ መሆን ሰፍኗል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ለሰው ሕይወትና ለአገር ደኅንነት ግድ በሌላቸው፣ የራሳቸውን የተንደላቀቀና የተቀማጠለ ኑሮ የዕድገትና የብልጽግና መመዘኛ አድርገው በሚቆጥሩ ኮረዶችና ጎረምሶች፣ አባባወችና እማማወች እየተነዳች ነው ማለት ነው።

ይህን አስቸጋሪና እየጨመረ የሚመጣ ሰቆቃ የሞላበት ዘመን ፍትፍት የሚሉ ወገኖች ቆም ብለው ነገሮችን ማየት ከቻሉ ፍትፍቱን በተጨማሪ የደም ጎርፍ ለማረስረስና መለኪያውንም በደም ሞልቶ ለመራጨት እየተንደረደሩ መሆኑ ውል ሊልላቸው ይችላል። የአዲስ አበባና የመቀሌ ዲፋክቶወች ታጣቂ ቡድኖችን ያሰለጥናሉ እዩልኝ ከሚል መንፈስ ጋር በቀረርቶ ያስመርቃሉ። ሰበብ እየፈጠሩም ወታደራዊ ትርኢት የሚታይባቸውን ስነ-ስርዓቶች እያዘጋጁ ጉልበታቸውን ለማሳየት ይሞክራሉ። አዲስ አበባ ላይ “የማያዳግም እርምጅ እወስድብሃለሁ” የሚል ፉከራ መሰማቱን ተከትሎ ከወደ መቀሌ “ትመጣና እጅህን እቆርጥልሃለሁ” የሚል ሽለላ የተሰማው ፍትፍት በተባለው በ2012 ዓም መገባደጃ ላይ ነው።

ኢሳትን የመሳሰሉ ሚዲያዎች የኤርትራ ጦር ትግራይን እንዲወር ግልጽ ጥሪ ሲያሰሙ እነ ድምጺ ወያነ ደግሞ ቀደም ብለው የግብጽን ዛቻ አሁን ደግሞ የትራምፕን የቦምብ ይውረድ ጥሪ ከበሮ የሚያስደልቅ አጋጣሚ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው። የትራምፕን ልቅ ንግግር ተከትሎ የሕወሐት ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን፣ ሚዲያወች ላይ የተጋበዙ የመቀሌ ዩንቨርስቲ ምሁራንን በማነጋገር ላይ ያለው ነገር በአባይ ግድብ ላይ የቦምብ ዛቻ መነሰንዘሩ ወይም በግድቡ ላይ ስጋት ማጥላቱ ሳይሆን ግድቡ ከወደመ ተጣያቂው ዐብይ አሕመድ መሆኑን በመናገር የጥላቻ ፕሮፓጋንዳቸው ትርፋማ መሆኑን የማረጋገጡ ጉዳይ መሆኑ በጣሊያን ወረራ ወቅት የተፈጸመውን የኃይለስላሴ ጉግሳን ክህደት የሚስታውስ ነው። ጠላትነቱ እንዲህ ሞልቶ፣ ገደቡን ጥሶ እየፈሰሰ ነው።

የወላይታንና የሲዳማን ሕዝብ የክልል እንሁን ድምጽ ለማፈን ወታደራዊ ሃይል ልኮ በጥይት መልስ ለመስጠት ትንሽም ያላቅማማው የአዲሰ አበባው መንግሥት የመቀሌው ቡድን ተገዳዳሪ መንግሥት ከመሆን አልፎ የፌደራሉ መንግሥት እጁን ወደ ክልሉ ጉዳይ እንዳያስገባ ሲያደርገው ያላየ መስሎ ለማለፍ ተገድዷል። የአዲስ አበባው ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች አረፍት የለሽ ተኩላ ሆኖ በተደጋጋሚ ሲያጠቃ ትግራይ ላይ ግን ‘ሃይበርኔሽን’ (የወራት ጥልቅ እንቅልፍ) ውስጥ የገባ የበረዷማው የአርክቲክ ክልል ድብ ለመምሰል ተገድዷል። ኹለቱ አካሄዶች የአዲሰ አበባው ቡድን አካሄዶች ተቃራኒወች ቢሆኑም ደካማነቱንና፣ እመራበታለሁ የሚለውን ሕገ-መንግሥት አክብሮ የማስከበር ብቃት ያነሰው መሆኑን ግን በጋራ የሚያጋልጡ አጋጣሚወች ናቸው። የአዲሰ አበባው ቡድን፣ በኹለቱም አካሄዶቹ ሕጋዊ መሆኑንና ለሕግ የበላይነት የቆመ መንግሥትነቱን የማረጋገጥ ችግሮች ታይተውበታል።

ጳጉሜ 4/2012 በትግራይ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ኹለቱም ዲፋቶዎች እርስ በእርሳቸው የሚዘላለፉበትን፣ የሚሰዳደቡበትን እና አንዱ ሌላውን ከሕዝብ ለመነጠል ሴራ የሸረቡበትን ዘመቻ ከፍተዋል። የመቀሌው ቡድን ትግራይን ሙሉ በሙሉ ከአዲሰ አበባው አገዛዝ ውጭ በማድረግ የበላይነቱን እያሳየ ሲሆን የአዲስ አበባው ቡድን ደግሞ ከሕወሐት ጋር ግንኙነት ማቋረጡንና ከሕዝብ ጋር እየተገናኘ መሆኑን በማሳየት አልተሸነፉኩም የሚልበትን አስገራሚ ድራማ በመስራት ላይ ነው። ለትግራይ መድረስ ያለበትን የድጎማ በጀትና የሴፍቲ ኔት (የእርዳታ) ገንዘብ ስርጭት አስመልክቶ በሚሰራው ድራማ የአዲሰ አበባው ቡድን የበላይነቱን ለማረጋገጥ እየሞከረ ነው። ይህን የገንዘብ ድርሻ የማስተጓጎል ዘመቻ ጦርነትን እንደ መክፈት እንቆጥረዋለን ያለው የመቀሌው ቡድን በፌደራል የሚሰጠን በጀት ከእኛው የሄደ፣ በሕዝብ ስም ከውጭ የተገኘ ብድርና እርዳታ ነውና ከዚህ በኋላ ከትግራይ ወደ አዲሰ አበባ የምትላክ ሰባራ ሳንቲም አትኖርም ከማለት አልፎ ከውጭ የሚመጣውን ገንዘብ በሚመለከትም የገንዘቡ ባለቤቶች የሆኑት ፈርጆቹ እጃቸውን እንዲያስገቡ ጠይቋል።

የአዲስ አበባው ቡድን የሚወስዳቸው አንዳንድ እርምጃወች ከውጭ ቡጢ በቀመሰ ቁጥር ወደ ቤቱ ሲገባ ሚስቱን እየቀጠቀጠ ንዴቱን እንደሚያበርድ ባል እያስመሰሉት ነው። የዕርዳታው ገንዘብ መስተጓጎል ከዚህ የተለየ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። ምርታማነቱ የተሟጠጠበት መሬት እየሞነጨሩ ከዓመት ዓመት የማይዘልቅ ምርት ብቻ የሚያኙ ገበሬወች፣ ጧሪና ቀባሪ ለጆቻቸውን በጦርነት ወይም በሌላ ችግር ያጡ አዛውንቶችና ባልቴቶች፣ አካል ጉዳተኞች ወዘተ…. የሴፍቲ ኔት ተጠቃሚወች ናቸው። ታዲያ እነዚህን ሰዎች በማስራብ የሚቀጡት እነ ስዩም መስፍን ናቸው ወይስ እነ አዜብ መስፍን?

አሁን ባለው አካሄድ፣ ለትግራይ መድረሰ ያለበትን ገንዘብ በማንከላወስ ድራማ መስራቱ ሕወሐትን ብዙም እንደማይጎዳው ውል ያለለት የአዲስ አበባው ቡድን ኹለት ተጨማሪ ወታደራዊ ዕዞችን አቋቁማለሁ ሲል አንዱ ተጨማሪ ዕዝ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ነው መባሉ የሚናገረው ነገር አለ። የአዲስ አበባው ቡድን ትግራይን በገንዘብ ማዕቀብ ለመቅጣት የወጠነውን ሴራ ለማጠናከር ይህን ዕዝ ማቋቋም አስፈልጎታል ብሎ መገመት ይቻላል። ሰሜን ምዕራብ የሚባለው አካባቢ የአማራ ትግራይ ክልሎች ከሱዳን ጋር የሚያዋሰኑበት ሰፊ ቦታ ነው። ይህ ቦታ የትግራይ ክልል መንግሥት ምርቱን ወደ ውጭ የሚልክበት እና የውጭ ምርቶችንም ወደ ትግራይ የሚስገባበት ብቸኛው ቦታ ነው። ይህን ቦታ በአዲስ መልክ በተደራጀና ድንገትም ልዩ ተልዕኮ ተሸክሞ በሚሰማራው በአዲሱ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ቁጥጥር ስር ማስገባት፣ አዲሰ አበባ ላይ ሆኖ ከግብር እና ከፈረንጆች የተገኘን ገንዘብ ከማገድ ወይም ገንዘቡን ለትግራይ ወረዳወችና ቀበሌወች ነው የምሰጠው እያሉ ከመዘባነን የበለጠ አሳማሚ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም።

ሕወሐት የአዳዲሶቹን ዕዞች መመስረት በከፍተኛ ድምጽ ከመቃዎም አልፎ ትግራይ ውስጥ ከሚገኘው ከማንኛውም ሰሜን ዕዝ ሰራዊትም ሆነ የጦር መሣሪያ ተቀንሶ ወደ አዲሶቹ ዕዞች መወሰድን እንደማይፈቅድ እና እንደሚከለክል ሲናገር ለዚህ የሰጠው ምክንያት ከኤርትራ ወገን ከፍተኛ የጦርነት ስጋት አለብኝ የሚል ነው። እንዲያውም አቶ ጌታቸው ረዳ በኤርትራ በኩል ልዩ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየታየ በመሆኑ ሕወሐት ከሰሜን ዕዘ ጋር እየተነጋገረ ነው ሲሉ ተሰምተዋል።

በሌላ በኩል ግን የዐብይ አሕመድ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥነት አክትሟል የሚለው ሕወሐት ወደ መከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ከዚህ በሰፋ እና ዘለግ ባለ መንገድ እጁን ለማስገባት ፍላጎት እንዳለው እየታየ ነው። በኤርትራ በኩል ሕወሐት በትግራይ ስለሚገኘው ጦር አለመቀነስ ከመናገር አልፎ ለመላው የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ሕገ ወጥ ላለው የብልጽግና መንግሥት እንዳይታዘዝ መልዕክት አስተላልፏል። ሕወሐት ሌሎቹ ዕዞችም ለአዲሶቹ ዕዞች ሰራዊት እና የጦር መሣሪያ እንዳያዋጡ በማዘዝ ወይም በማሳሰብ ላይ ያለ ይመስላል። የአዲስ አበባው መንግሥት ከጦር ጄኔራሎቹ መካከል በሆኑት በሜጀር ጄኔራል ሹም አብደታ በኩል ሰራዊቱን ማንም እንደማያዘው፣ በማንም ላይ እርምጃ ለመውሰድ ብቃት ያለውና የሻውን እንቅስቃሴ ቢደርግ ምንም የማይገታወ መሆኑን የሚገልጽ መግለጫ ሰጥቷል። ይህ አካሄድ የዲፋክቶወች አደገኛ ጨዋታ መጀመሩን የሚያሳይ መሆኑን መጠራጠር አይገባም። የኢትዮጵያን ጦር የሚያዝዘው ማን ነው ብሎ ለመጠየቅም በር የሚከፍት ነው። ኹለቱም ዲፋክቶወች ቆም ብለው ካላሰቡና በእልህና በመናናቅ መንደርደራቸውን ካለቀቆሙ ግጭት መከሰቱ አይቀሬ ነው፣ ያልታሰበም ይሁን በአንዳቸው በኩል የታሰበበት ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል መረዳት ተገቢ ነው።

በሹክሹክታ ቢሆንም ሕወሐት በኢትዮጵያ ጦር እና በፌደራል ፖሊስ ውስጥ እጁን ለማስገባትና የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችሉት በርካታ አመች ቀዳዳወች እንዳሉ፣ እነዚህን ቀዳዳወች በመጠቀምም አልፎ አልፎ ችግሮች እንዲከሰት ማድረጉ ይሰማል። በእርግጥ የቀድሞውንና ችግሮች የሞሉበትን አሮጌ መዋቅር እንዳለ ተሸክሞ መንገታገትን ለመረጠው የብልጽግና ቡድን እነዚህን መሰል ችግሮችን መጋፈጡ የሚጠበቅ ነገር ነው። የአዲሰ አበባው ቡድን ቁንጮ ቤተ-መንግሥትቱን የሚጠብቅ ቁጥሩና አደረጃጀቱ በውል የማይታወቅ ጦር እያሰለጠነ፣ ትርኢት እያሳየ የራሱንና የቤተሰቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ ደፋ ቀና የሚለውን ያህል የአገሪቱን ኅልውና የሚጠብቀውን መከላከያን የማጥራት ስራ አለመስራቱ አስፈገራሚ ነገር ነው። የጦር ተሸከርካሪወችን በመጠቀምና እና ዶላርና ተፈላጊ ወንጀለኞችን ወደ ትግራይ በድብቅ የማሸሽ ሙከራወች እጅ ከፍንጅ ከተያዙ ወንጀል ዓይነቶች ሁለቱ ብቻ ናቸው። ያልተደረሰባቸው ወንጀሎችስ ይኖሩ የሆን? ግጭቶች በቀሰቀሱባቸው አካባቢወች በምዕራብ ጎንደር፣ በአማራ ክልል ኦሮምያ ዞን፣ በቤኒሻንጉል፣ በአፋርና ኢሳ ግጭቶች፣ በሶማሌ ክልል ወዘተ… የመከላከያ ሰራዊትን በሚመለከት ጥርጣሬወችና ሃሜቶች መስተጋባታቸው የቅርብ ጊዜ ትወስታ ነው።

የአዲሰ አበባው ቡድን ሌላም ግራ አጋቢ አካሄድ አለው። ይህ አካሄዱ ለበርካታ ችግሮች ምንጭ መሆኑ የሚታበል አይደለም። ሕወሐት በበረሀ ባረቀቀው ሕገ-መንግሥት፣ ሕወሐት ትግራይን ለመጥቀም አስቦ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎች መካከልም መጓተትን መፍጠርና ግጭትን ማጫር በሚችል መልኩ ባዋቀረው የክልሎች ካርታ፣ ሕወሐት በፌደራሊዝም እውቀት ሽፋን የኢሕአዴግ አባልና አጋር ለሚላቸው ድርጅቶቹ ውስጥ ባጎራቸው ካድሬወቹና ሹመኞቹ አእምሮ ውስጥ ያገሰው የጠበብነት ጥላቻ ወዘተ…ወዘተ… ለአዲስ አበባው ቡድን (ለብልጽግና) አስተዳደራዊ ዝርክርክነት ስንኩልነት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። የሕወሐት ተቃራኒ ነኝ የሚለው የአዲስ አበባው ቡድን በሕወሐት ኳስ እና በሕወሐት ሜዳ፣ በሕወሐታዊ አሰላለፍ እየተጫወተ በራሱ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጁ እየደነቆለ ለተቀናቃኙ ለሕወሐት ብዙ ፍጹም ቅጣት ምቶችን እያሰገኘ ነው። ከዚህም አልፎ በራሱ ግብ ላይ ብዙ ጎሎችን እያስቆጠረ ሽንፈቱንና ውርደቱን እያፋጠነ ነው። አሳዛኙ ነገር የዚህ ቡድን መሸነፍና መዋረድ በአገርና በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ ችግሮችን እሰከተለ መሆኑ ነው።

ቀደም ብሎ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አመራሮች መካከል፣ በቅርቡ ደግሞ በአማራና በቤኒሻንጉል ክልሎች አመራሮች መካከል የታየው መወዛገብና መዘላለፍ የዚህ ዓይነቱ በሕወሐት ኳስ የመጫወቱ ሞኝነት ያስከተለው ችግር ውጤት ነው። ከዘርህ ውጭ የሆነውን ኢትዮጵያዊ እንደ ወንድም አድርጎ ማየትን፣ አብሮና ተከባብሮ መኖርን፣ ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መናገርን “የአሃዳዊነት አስተሳብ ነው” እያልክ ሕወሐት መቀሌ ላይ ተቀምጦ ሌሎችን ለመዝለፍነ ራሱን ዲሚክራሲያዊ አስመስሎ ለማቅረብ የሚጠቀምበትን አነጋገር ኦሮምያን ወይም ቤኒሻንጉልን ወይም አፋርን ወይም ሲዳማን ወዘተ..እየመራሁ ነው የሚል የብልጽግና ካድሬና ሹመኛ ሲጠቀምበት ብልጽግና ከሕወሐት ሎሌነቱ ያልተላቀቀ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ይህ ችግር የዋና ዋናወቹ የብልጽግና ሰወች ችግርም መሆኑ ግልጽ ነው።

በየክልሎቹ በሕዝብ ላይ ጥቃት በተሰነዘረና ግለሰቦች በተገደሉ ቁጥር ‘የሕወሐት እጅ አለበት’ የሚለውን የብልጽግና ካድሬወችንና ሹመኞችን ክስ መስማቱ የተደጋገመና የተለመደ ነገር ነው። አገላጹ በቀጥታ ሕወሐት እና ወያኔ ወይም የቀን ጅቦች፣ ውስኪ ጨላጮች፣ ትግርኛ ሲናገሩ የሰማናቸው ወዘተ… የሚለር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከሕወሐት የቆዩ አካሄዶች በመነሳት ሕወሐት በዚህ ጊዜ የሚረብሹ ተማሪወች ስም በመጻፋ ላይ እንዳለ የክፍል አለቃ ከመሆን የዘለለ ሚና አለው ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሕወሐት ቀድሞ “ስርሂት” እያለ ያካሂዳቸው የነበሩትን የመሳሰሉ ዘመቻወችን ላካሂድ ብሎ ቢነሳ እንቅፋት የሚሆንበት አደረጃትና ብልጠት በብልጽግና በኩል አለ ለማለት አያስደፍርም። ስለዚህ በየክልሉ ለሚፈጸም ችግር የሕወሐት እጅ አለበት ከማለት ይልቅ የሕወሐት ትንሽዋ ዕጣት አለችበት ማለት ብልጽግና ራሱን እንዲፈትሽ ይረዳዋል። ለትርምሱ ምቹ መድረክ የፈጠረው ዋናው ነገር የብልጽግና ቡድን ደካማነት መሆኑን ለዚህ ድካማነትም የብልጽግና ካድሬወችና ሹማምንት ለጠባብ ዘረኛና ክልላዊ አጀንዳወቻቸው ሲሉ ቀድሞ ሕወሐት በአእምሯቸውና በልቦናቸው ያስቀመጠውን አስተሳሰብ ከማራመድ አለመቆጠባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው መገመት ይቻላል።

ከዚህ ላይ ደግሞ በየክልሉ የሚገኙ የብልጽግና ተቃዋሚወች ነን የሚሉ ቡድኖችና ግለሰቦች ሕወጥ በየክልላቸወ ያፈሰሰውን ደም እና ያካሄደውን ዝርፊያ ችላ ብለው ሕወሐትን የፌደራሊዝም ጠበቃ አድርገው በማየት ከሕወሐት ጋር ለመሞዳሞድ መንበርከካቸው፣ ለአንዳንዶችም መንበርከኩ ተሳክቶላቸው የሕወሐትን አጀንዳ ለመፈጸም ደፋ ቀና ማለታቸው ሌላው የትርምሱ ማፋፋሚያ ሰበብ መሆኑ የሚካድ አይደለም። እነዚህ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መቀሌ ሄደው ከመሰብሰብና ከመጨፈር አልፈው በጀት፣ ተልዕኮና መመሪም እየተቀበሉም ሊሆን ይችላል።

የሕወሐትና የሕዝባዊ ግንባር ግንኙነት የጌታና የሎሌ ዓይነት ነበረ፤ ሎሌውም ሕወሐት ነበረ። በተመሳሳይ የሕወሐትና የኢሕአዴግ አባልና አጋር የሚባሉት ድርጅቶች ግንኙነትም ጌታና የሎሌ እንደነበረ አይረሳም። ጌታው ሕወሐት ነበረ። በ1990 ዓም በሕወሐትና በሕዝባዊ ግንባር መካከል የነበረውና ረዥም ጊዜ ያስቆጠረው የሎሌነትና የጌታነት ግንኙነት፣ የጠላቴ ጠላት በሚለው ዘዴና አብሮ በመዝረፍ ተሸፍኖ ለከቆየ በኋላ በ1990 ዓም ሳይታሰብ በተቀሰቀሰ የእልቂት ጦርነት ተቋጭቷል።

የባድመ ጉዳይ ከሻእቢያና ከሕወሐት የበረኸኛነት ዘመን ጀምሮ ኹለቱን ቡድኖች እያነጋገረና እያወዛገበ የነበረ ነገር ነው የነበረው። ኤርትራ ስትገነጠልና በኢትዮጵያ ምርጫዎች ሲካሄዱ የባድመ ጉዳይ በለሆሳስ እየታየ ሲታለፍ የቆየ ነገር ነው። ከ1980ወቹ አጋማሽ ጀምሮ በባድመና በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የኤርትራ ታጣቂዎች ችግር እያደረሱባቸው መሆኑን ለትግራይ ክልል አስተዳዳሪወች ተደጋጋሚ እሮሮዎችን ማሰማታቸውና ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ ወደ አቶ መለስ ዜናዊ እንደደረሰ ነገር ግን አቶ መለስ ችላ ብለው እንዳለፉትም ይታወቃል። በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ችግር እየከፋና እየሰፋ፣ በመሣሪያ የታገዘው ጥቃትም እየጨመረ ቢመጣም የአቶ መለስ ችላ ባይነት አልተገታም ነበረ። እንዲያውም የባድመን ሕዝብ ወክለው ወደ አቶ መለስ ዜናዊ የቀረቡ የአካባቢው ሽማግሌወች “…. እናንተ ትምክህተኞች፣ እኛንና ሕዝባዊ ግንባርን ልታጣሉ ነው የምትሞክሩት….” የሚል ዘለፋ ተሰንዝሮባቸው አንገታቸውን ደፍተው ወደ መጡበት መመለሳቸው ይሰማል። ችግሩ እየገነነ ሲመጣ ማንኛውም ሰው ወደ አጨቃጫቂው አካባቢ ሲመጣ የጦር መሣሪያ መያዝ የለበትም የሚል ስምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የኤርትራ ሚሊሻወች ይህን ስምምነት ጥሰው በተገኙበት ጊዜ በትግራይ ሚሊሻወች መገደላቸው፣ ከዚያም እፍኝ የማይሞሉ የኤርትራ ወታደሮች ኹለት ወይም ሦስት ባለ ጎማ ታንኮች ይዘው ወደ ባድመ ሲገቡ ኹለቱ መንግሥትታት ግልጽ የጦርነት ዛቻዎችን መሰንዘር መጀመራውቸና የውስጥ ለውስጥ ድርድሮችን ማካሄዳቸው ይታወቃል።

ምንም ዓይነት ዝግጅት ሳያደርግ ቆየው የሕወሐት/ኢሕአዴግ መንግሥት ወደ ድርድሩ ቢያመዝንም የኤርትራ ጦር በባድመ የጀመረውን ድንበር ጥሶ የመግባትና ምሽግ ሰርቶ የመቀመጥ ሥራ በኦምሐጀር፣ በጾሮና፣ በዛላንበሳ፣ በባዳ ቡሬ ወዘተ…. ግንባሮች አስፋፍቶት ወደ ኹለት ዓመት የወሰደውና ከፍተኛ ደም ያፋሰሰው ጦርነት እንዲካሄድ ሰፊ በር ከፍቷል። የሕወሐትና ብልጽግና ፍጥጫስ ወዴት ያመራ ይሆን?

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here