ለአዳዲስ የነዳጅ አከፋፋዮች ነዳጅ በዱቤ መስጠት ተከለከለ

0
1471

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለኩምቢ ኦይል ትሬዲንግ፣ ለድሬ ፔትሮሊክ እና አፍሪካ ለተባሉ ሦስት የነዳጅ አከፋፋዮች ነዳጅ በዱቤ መስጠት እንዳቆመ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነዳጅ በቀጥታ የገንዘብ ክፍያ ለመሸጥ የሚያፈልገውን ቅድመ ሁኔታ ሁሉ አሟልቶ ወደ የእጅ በእጅ ሽያጭ አሰራር በመግባት ላይ በመሆኑ አዳዲስ ለሆኑ የነዳጅ አከፋፋዮች በዱቤ ነዳጅ መስጠት አቁሟል። ነገርግን ነዳጅ ሙሉ በሙሉ መስጠት ከቆመ የአገር እንቅስቃሴ ስለሚቆም ለነባር ነዳጅ አከፋፋዮች እሰካሁን ነዳጅ በዱቤ እየተሰጠ እንዳለ ታደሰ አሳውቀዋል።አሠራሩ ከሚቀጥለው ዓመት 2014 መጋቢት አንድ ቀን ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል።

ከዚህ በፊት የነበረው አሠራር የነዳጅ አከፋፋይ የሆኑት የነዳጅ ማደያዎች ከኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነዳጅ ያለ ክፍያ ወስደው ከሸጡ በኋላ ገንዘቡን ይመልሳሉ ነገርግን አንዳንድ አዳዲስ የነዳጅ አቅራቢዎች ጋር በተፈጠረ የአሰራር ችግር እንዲሁም ከላይ ከተጠቀሰው ቀን መጋቢት አንድ 2014 ጀምር የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቱ አሰራሩን ስለሚቀይር አሁን አዲስ ለሆኑ የነዳጅ አቅራቢዎች ነዳጅ በዱቤ አይሰጥም።

በኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በፊት ከ10 ያልበለጡ የነዳጅ አከፋፋዮች የነበሩ ሲሆን አሁን ቁጥራቸው ከ30 መብለጡን ከዓለማሁ ፀጋየ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለማወቅ ተችሏል።ቁጥራቸው ብቻ ሳይሆን ከ 10 ዓመታት በፊት በአገሪቱ የነበሩ የነዳጅ አካፋፋዮች የውጭ አገር ባለሃብቶች የነበሩ ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተከፈቱት በአገር ውስጥ ባለሃብቶች ነው።

ከነዚህ የነዳጅ አከፋፋዮች መካካል 90 በመቶ የሚሆነው የነዳጅ ንግዱ የሚሸፈነው ቶታል፣ ኦይል ሊቪያ፣ የተባበሩት እና ኖክ ተብለው በሚጠሩት የነዳጅ ማደያዎች ነው። የነዳጅ ማደያዎቹ ከነዳጅ ሽያጭ በተጨማሪ በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከመኪና እጥበት ከካፌ አገልግሎት እና ከገበያ ማዕከላት ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ።እነዚህ የነዳጅ አከፋፋዮች ከማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስተር እና ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በተለያየ ጊዜ ስብሰባ እንደሚያደርጉ እና መሰል ችግሮቻቸውን እንደሚወያዩ ነገር ግን ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባ ጀምሮ እንዳቆሙ ለአዲስ ማለዳ አስተያታቸውን የሰጡ በአንድ የነዳጅ ማደያ ወስጥ የሚሰሩ የሰው ኃይል አስተዳደር ሰራተኛ ተናግረዋል።

ኩምቢ ኦይል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ2012 አጋማሽ ብቃቱ ተረጋግጦ ፍቃድ በማውጣት እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት አገልግሎት ለመስጠት ዋና ቢሮውን አዲስ አበባ ያደረገ በሦስት የነዳጅ ማደያዎች እና በ 10 የነዳጅ አመላላሽ ቦቲዎች ሥራ የጀመረ የነዳጅ አከፋፋይ ሲሆን በዱቤ ነዳጅ እንዳይሰጡ ከተከለከሉ ሦስት የነዳጅ አከፋፋዮች መካከል አንዱ ነው። ኩምቢን ጨምሮ ለሌሎች ሦስት የነዳጅ አቅራቢዎች ነዳጅ በዱቤ የተከለከለው ድርጅቱ አሰራሩን መቀየር ስለፈለገ እና ገንዘብ መሰብሰብ ስላለበት ነው ብለዋል ዓለማየሁ።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አዋሽ ላይ 36 ሽሕ ሜትር ኩብ አዲስ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖ አስገንብቶ ሥራ ያሥጀመረ ሲሆን ተጨማሪ 36 ሽሕ ሜትር ኩብ አዲስ የነዳጅ ማጠራቀሚያ አዋሽ ላይ በማስገንባት ላይ ይገኛል የግንባታው 80 በመቶ በዚህ የበጀት ዓመት እንደሚያልቅ እና በ2014 ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት በተጨማሪም ተመሳሳይ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዱከም ላይ ለማስገንባት እቅድ ተይዟል።

የነዳጅ ማጠራቀሚያ የሚገነቡባቸው ቦታወች የተመረጡት ለባቡር መንገድ ባላቸው ቅርበት እንደሆነ እና ነዳጅ በባቡር ጭምር ለማመላላስ እንደታሰበ ነው የገለጹት።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here