በአማራ ክልል ለጤና ጎጂ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች እንዳሉ ታወቀ

0
758

በአማራ ክልል በሁሉም ወረዳዎች መወገድ ያለባቸው ጊዜያቸው ያለፈባቸው በተለያዩ ጊዜያት ለፀረ ሰብል ተባይ ማጥፊያ ለወባ ማጥፊያ ለትምህርትና ምርምር ተብለው የገቡ ኬሚካሎች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ተቀምጠው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግሥት የአካባቢና ደንና የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በላይነህ አየለ (ዶ/ር) እንዳሉት መወገድ ያለባቸው ኬሚካሎች እንዳሉ እና እነዚህ ኬሚካሎች ለጤና ጠንቅ እንደሆኑ ተናግረዋል ።

የኬሚካሎቹ ዓይነትም በሦስት ምድብ የሚከፈሉ ሲሆኑ የመጀመሪያው የፀረ ሠብል ተባይ መከላከያ ኬሚካሎች እንደ ማላታይን አልድሪን ዲአልድሪን ዚንክ ፎስፌት እና ሌሎችም ሲሆኑ ኹለተኛው ደግሞ ወባን ለመከላከል የገባው ዲዲቲ( ማላታይን) እንዲሁም ሦስተኛው ደግሞ ለተለያዩ የትምህርትና የምርምር ሥራዎች ተብለው የገቡ የኬሚካል ዓይነቶች እንደሆኑ ጠቁመውናል።

እነዚህ ኬሚካሎች መወገድ ያለበቻው እንደሆነ በተለይም ዲዲቲ የተሰኘው ኬሚካል ውስጡ የማምክን(ዘርን የማቋረጥ)የሰው ልጅን ጎጂ ንጥረነገር እንዳለው ገልፀው በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠቀም እንደተከለከለም ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለወባ ሲባል ጥጠቅም ይሰጥ እንደነበር እና ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን መጠቀም እንደቆመ የተናገሩት በላይነህ (ዶ/ር) ነገር ግን እስከ አሁን ድርስ በክልላቸው እንዳሉና እንዳልተወገዱ ተናግረዋል።

ዲዲቲ ወባን ለማጥፋት ተብሎ 27¸500 ኪሎ ግራም ዲዲቲ በክልሉ 105 በሚሆኑ ወረዳዎች የጤና ጣቢያ ማዕከላት መጋዘን ተቀምጦ እንዳለ ነግረውናል። ዲዲቲን እነደ ክልል ማስወገድ እንደማይቻል እና በአገር ደረጃም ቢሆን ዲዲደቲን ለማስወገድ የሚሆን መሰረተ ልማት እንደሌለ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ዲዲቲ ቶሎ መወገድ እንዳለበት ያሳወቁት ኃላፊው በአንዳንድ ወረዳዎች ላይ ነቀዝን ያጠፋልናል በሚል በአሁኑ ጊዜ ዲዲቲን እየተሰረቁ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ማኅበረሰቡን ትልቅ ችግር ውስጥ ይከታልም ብለዋል።

የፀረ ሰብል ተባይ ኬሚካሎች እና ለጥናትና ምርምር ለትምህርት ተብለው የገቡት ኬሚካሎችን በተመለከተ ጊዜያቸው ያለፈባቸው በሁሉም ክልሉ ላይ ባሉ ወረዳዎች አሉ ያሉት ኃላፊው ለአብነትም በባህር ዳር ጣና ሀይቅ ትምህርት ቤት ላይ 140 የሚሆኑ የተለያዩ ኬሚካሎች አሉ በተለይም ማላታይን በሁሉም ወረዳዎች 6182 ኪሎ ግራም የሚሆን እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመነጋገር ኬሚካሎቹን ለማስወገድ እንዲያስችል በሁሉም ወረዳዎች ላይ የኬሚካል ቆጠራዎቹ እንደተከናወኑ እነዚህን ኬሚካሎች ለማስወገድም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ተናግረው በተደጋጋሚ ጥናቶች ተጠንተው እንዲወገድልን ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ እንደቀረቡና መልስ በመጠባበቅይ ላይ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

እነዚህ ኬሚካሎች እስኪወገዱ ድረስ በቀዝቃዛ አካባቢ መቀመጥ እንዳለባቸው ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በሙቀት ምክንያት እየፈነዱ ያሉ ኬሚካሎች እንዳሉ እና ይህም ደግሞ ማኅበረሰቡን የበለጠ ለአደጋ ያጋልጠዋል ብለዋል።

አክለውም ማኅበረሰቡ እነዚህ ኬሚካሎች ለጤና ከፍተኛ ጉዳት እንዳላቸው ተገንዝቦ መንግሥት እስኪያስወግደው ድረስ በትዕግስት መጠበቅ እንዳለባቸውም የሚሰርቁ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገራቸው የአካባቢ ቴክኖሎጂ ባለሙያ የአለምሰው አደላ እንዳሉት ከጤና አኳያ እነዚህ ኬሚካሎች በሰው ላይ የዘረመል መዛባት (ጄኔቲክ ዲስ ኦርደር) በተለይም የነርቭ ጉዳቶችን አላቸው ብለዋል።

በተለይም ዲዲቲ የተባለው ኬሚካል በጣም ጉዳት አለው ያሉት የአለምሰው ዲዲቲ በባህሪው ቅባት ይወዳል በዚህም ምክንያት ሰዎች ውስጥ ለመግባት ይችላል ነው ያሉት።ይህ ዲዲቲ የተባለው ኬሚካል ወደ አገር ሲገባ በዋነኝነት ለወባ ማጥፊያ እንዲውል እንደሆነ አሳውቀዋል።

ለወባ ማጥፊያ ተብለው አንድ ቦታ ላይ የሚረጨው ዲዲቲ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በአፈር እና በውሀ ላይ በሰው ልጆች ፀጉር ውስጥ በእናት ጡት ወተት ውስጥ መገኘት በመጀመሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ1970 እንደ አውሮፕያን አቆጣጠር ዲዲቲ በሰው ልጆች ላይ ከጂን ጋር በተያያዘ ጄኔቲክ ዲስ ዖርደር(የዘረመል መዛባት) እንደሚያደርስ ስላወቁ በውጪ አገራት መጠቀም ማቆማቸውን ነገር ግን አፍሪካ ላይ ብሎም በአገራችን ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እየተጠቀምነው እንደነበርም አስታውሰዋል።

ሌሎች ኬሚካሎችን በተመለከተ ደግሞ ቶሎ ጊዜያቸው የሚያልፍበት ምክንያት በብዛት ከተለያዩ አውሮፓ አገራት በእርዳታ መልክ የምናገኛቸው ኬሚካሎች የአገልግሎት ጊዜያቸው ሊያበቃ ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው ምናልባትም ስድስት ወር ሲቀራቸው እንደሆነ በዚህም ምክንያት ወደብ ላይ ቆይቶ እኛ ጋር እስኪደርስ ጊዜ እንደሚፈጅ እና አገር ውስጥ ሲገባ ሳንጠቀምባቸው የአገልግሎት ጊዜያቸው እንደሚያበቃ ተናግረዋል።

እነዚህን ኬሚካሎች ለማስወገድ በአገር ደረጃ ስለማንችል ወደ ውጪ አገር ተወስደው እንደሚወገዱ አስታውሰው ይህን ለማድረግ ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት እንደሚጠይቅ የተናገሩት ባለሙያው በሰዎች ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የማስወገድ ሂደቱ አፋጣኝ በሆነ መልኩ መፍትሄ ቢገኝለት ምናልባትም በራሳችን አገር ላይ የማስወገጃ ቦታን መገንባት ብንችል እንደውም ገንዘብ ማግኛ መንገድም ይሆነን ነበር ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማላዳ ያነጋገረቻቸው የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ግርማ ገመቹ ኬሚካል ማስወገድን በተመለከተ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አና አማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ከተሞች ብዛት ያላቸው ኬሚካሎች መኖራቸውን አሳውቀውናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here