የጤና እና ጤና ነክ ደረጃዎች ረቂቅ እየተዘጋጁ መሆኑ ተገለጸ

0
1072

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የጤና እና ጤና ነክ ደረጃዎች ረቂቅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታወቀ።
ኤጀንሲው በአሁኑ ሰዓት ከፌደራል ጤና ሚንስቴር ጋር በመተባበር ከክልሎች እና ከፌደራል ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች ረቂቅ ደረጃዎችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃ ልማት ዳይሬክተር ይልማ መንግሥቱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በረቂቅ ደረጃ እያዘጋጃቸው ያሉት ደረጃዎች በኹለት መደብ የተከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ደረጃ የጤና ተቋማት ደረጃ ሲሆን በዚህ ደረጃ ውስጥ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ክሊንኮችና መድሃኒት ቤቶች እንደሚካተቱ ተመላክቷል።
የጤና ተቋማት ደረጃው በመዘጋጀት ላይ ያለው ከዓለም ጤና ድርጅት ደረጃዎች አንጻር በኢትዮጵያ የሚነሱትን ችግሮች በማስቀረት የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ መሆኑን ዳይሬከተሩ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት የጤና ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ የግብዓት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶች፣ ሙያውን በሚገባ የተገነዘበ ባለሙያና ሌሎችም አገልግሎቱን ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በሚጠበቀው ደረጃ ልክ እንዲሟሉ የሚያስገድድ ደረጃ መሆኑ ተመላክቷል።

በዝግጅት ላይ የሚገኘው የጤና ተቋማት ረቂቅ ደረጃ ከዚህ በፊት በ2004 ጸድቆ ሥራ ላይ የነበረውን ደረጃ በማሻሻል እየተዘጋጀ ያለ ደረጃ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። ረቂቁ ያካተታቸው ማስተካከያዎች ከዚህ ቀደም በወጣው የጤና ተቋማት ደረጃ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ዘረፉን የሚመጥኑ ዝቅተኛ የባለሙያ፣ የቦታ፣ የህክምና ማሽኖችና የአገልግሎት አሰጣት ስርዓት እንደሚያሻሻልም ጠቁመዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት በ2004 በወጣው ደረጃ ላይ ፈቃድ የወሰዱ ተቋማት የሆስፒታል ደረጃ ወስደው አገልግሎት የሚሰጡበት ቦታ፣ ማሽንና የባለሙያ ብቃት ተመጣጣኝ አንዳልነበር ያስታወሱት ይልማ ችግሩን ለመቅረፍ ደረጃ ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከጤና ጋር በተያያዘ የመካከለኛ ክሊኒኮች ከሚሰጡት አገልግሎት ከባለሙያ ብቃትና ደረጃ እንዲሁም አገልግሎታቸው ምን መምሰል እንዳለበት ታሳቢ ማድረጉን እንዲሁም የቤት ለቤት ህክምና አገልግሎት ደረጃ ረቂቅ ጭምር ተገቢነት ያላቸው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ኹለተኛው ደረጃ የጤና ነክ ደረጃ ሲሆን በዚህ ደረጃ ውስጥ የሆቴል፣ የምግብ ቤቶች፣ የግሮሰሪ ፣ የወተት እና ወተት ተዋጾ፣ የአሳ መሽጫዎች እና ስጋ ቤት ተካተዋል። ይህ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ደረጃ ነው ሲሆን፣ በዚህ ደረጃ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ሰጭ የሆኑ ተቋማት በመሆናቸው በአሰራር ስርዓታቸውና በአገልግሎት አሰጣጣቸው አንዲሁም በተሰማሩበት ዘርፍ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊ ነገሮች በአግባቡ መሟላታቸወን ለማረጋገጥ መሆኑ ተመላክቷል።

ከጤና ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የዐሳ መሸጫ ሱቅ ምን መምሰል እንዳለበት እንዲሁም ጤናና ደህንነትን ከመጠበቅ አኳያ የሕዝብ መዝናኛ ማዕከላትን በተመለከተም ረቅቅ ደረጃዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ በቴክኒክ ኮሚቴ ታይቶ ለደረጃዎች ምክር ቤት ቀርበው እንደሚፀድቁ ተጠቁሟል።

በረቂቅ ደረጃ በመዘጋጀት ላይ በሚገኘው የጤና እና የጤና ነክ ደረዳዎች ጸድቆ ተግባራዊ ሲደረግ ደረጃው የተዘጋጀው በብሔራዊ ደረጃ በመሆኑ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አንድ ወጥ የሆነ በመሆነ አፈጻጸም እንደሚተገበር ተመላክቷል። ማንኛውም ተቋም በሚሰማራበት ዘርፍ የተቀመጠቀውን ዝቅተኛ መስፈርት ሳያሟላ ፈቃድ እንደማይሰጠው የገለጹት ይልማ ከዚህ ቀደም ፈቃድ ወስደው በሥራ ላይ ያሉ ተቋማት ደረጃወን ሟሟላት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የደረጃው ተፈጻሚነት በትክክል መተግነሩን በስርዓት ቁጥጥር እንሚደረግ ተጠቁሟል።

ኤጀንሲው በብሔራዊ ደረጃ ደረጃዎችን የማዘጋጀት ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ሲሆን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የምርቶችንና አገልግሎቶችን ደረጃ የማዘጋጀትና የትግበራ ስልጠናና ድጋፍ ክትትል ያደርጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here