ተስፋዬ ኡርጌ “የክስ መሞከሪያ ላብራቶሪ ሆኛለሁ” አሉ

0
679

በሰኔ 16ቱ ጥቃት፣ በሰብኣዊ መብት ጥሰት እና ሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ቢሮ የጸረ-ሽብር ኃላፊ ተስፋዬ ኡርጌ ለፍርድ በቀረቡበት ወቅት የክስ መሞከሪያ ላብራቶሪም ሆኛለሁ ሲሉ አማረሩ። ባሳለፍነው ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 በቀረቡበት በልደታ ምድብ ችሎት፣ 10ኛ ወንጀል ችሎት “ልቦለዳዊና ሐሳባዊ የሆነ መረጃ ላይ በመመስረት ላለፉት ስድስት ወራት ያለውጤት ነው ፍርድ ቤት እየተመላለሰኩ የምገኘው” በሚል ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤቱ ያሰሙት ተስፋዬ እንደማሳያም ፖሊስ እስካሁን እያቀረበብኝ ያለው ክስ ተመሳሳይ ነው ብለዋል።
ፖሊስ በበኩሉ የምርመራውን አስቸጋሪነት በመጥቀስ ወንጀሉ ክልል አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኦሮሚያና አማራ ክልል ከተሞች የተደረገ በመሆኑ ተጎጂዎች ፈልጎ ለማግኘት አስፈላጊውን ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል። በዚህም ምክንያት ተከሳሽ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮችን የማስፈራራትና የመደበቅ ተግባር ሊያከናውኑ ስለሚችሉ የዋስ መብት እንዳይሰጣቸው ጠይቀዋል። የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው እስካሁን በማስረጋጃ መልክ ከመርማሪ ፖሊስ የሚቀረበው ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ክስ በመሆኑ የዋስ መብታቸው ተከብሮ ተከሳሽ ከእስር እንዲፈቱ ለችሎት አቅርበዋል።
በተጨማሪም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ቢሮ ውስጥ ተገኘ ስለሚባለው መርዝ የማወቀው ነገር የለም ያሉት ተስፋዬ በጊዜ ቀጠሮ ብዛት ወንጀሉን እንዳምን እየተገደድኩ ነው ብለዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ መርዙ የተገኘው በግለሰብ መኖሪያ ቤት ሳይሆን በአንድ ትልቅ ተቋም ውስጥ እስከሆነ ድረስ ይህን የማወቅ ኃላፊነት ይኖርባችዋል ሲል ምላሽ ሰጥቷል። የተከሳሽ ጠበቃ በበኩሉ ደንበኛዬ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደ መሆኑ በዋስ ቢፈታ ሊሰወርብት የሚችልበት ቦታ የለውም ብለዋል። በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች መሬት ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ ለተለያዩ ሰዎች ሰጥቷል በሚልም መርማሪ ፖሊስ መረጃ እንዳለውም ለችሎቱ አስረድቷል።ችሎቱም በቀጣይ መርማሪ ፖሊስ የቀረውን የምርመራ ሥራዎች አጠናቆ እንዲቀርብ የዐሥር ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here