በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለዉን ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝዉዉር እና ባለቤትነትን በተመለከተ እስከ 10 ዓመት እስር ያስቀጣል የተባለዉ ሕግ በቅርቡ እንደሚጸድቅ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ። ሕጉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከተ የመጣውን ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝዉዉር ለማዳከም ብሎም ለመግታት በአዘዋዋሪዎች ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሪፖርቱ እንደገለጸዉ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ዝዉዉሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ እንደመጣ ገልጾ ይህም ለኢትዮጵያ ሰላም አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ጠቁሟል። በተያያዘ ዜና ለሕገ ወጥ ዝዉዉሩ መስፋፋት እንደ ምክንያት የተቀመጠዉ ደግሞ እስካሁን በዚህ ተግባር ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች ላይ ይወሰድ የነበረዉ እርምጃ ጠንካራ ስላልነበር ነዉ ተብሏል። የእርምጃው ጠንካራ አለመሆን ደግሞ በርካታ ግለሰቦች ወደ ሕገ ወጥ ዝዉዉሩ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗቸዋል*
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የ5 ወራት አፈፃጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ባቀረበበት ወቅት ብርሃኑ ጸጋዬ እንደገለጹት የሕገ ወጥ መሳሪያ ገበያዉ በአሁኑ ጊዜ ፈጣን እድገት እያሳየ እንደሆነ ገልጸዉ በጊዜ መፍትሄ የማይበጅለት ከሆነ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚደረስ ጠቁመዋል። ይህ ደግሞ ይላሉ ብርሃኑ ጸጋዬ ኢትዮጵያ የተያያዘችዉን የለውጥ ጎዳና አቅጣጫ የሚያስት እና ብዙዎች የሚናፍቁትን ሰላም የሚያሳጣ ነዉ። እስካሁን ድረስም ከፌደራል ፖሊስ እና ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በቅንጅት በመስራት በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ሊዉሉ እንደቻሉ በብርሃኑ ጸጋዬ ተጠቅሷል። ስለዚህ አዲሱ ሕግ በቶሎ እንዲጸድቅ መስሪያ ቤቱ እየሰራ እንደሆነ ይገልፃሉ። ከሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝዉዉር ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ወደ 500 የሚጠጉ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች በባህር ዳር ከተማ በአንድ ግለሰብ ቤት ዉስጥ መያዛቸዉ የሚታወስ ነዉ።
ከሕገ ወጥ የገንዘብ ዝዉዉር ጋር በተያያዘም ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የተገኘዉ መረጃ እንደሚያመለክተዉ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩና አሁንም ሥልጣን ላይ ባይኖሩም በፓርቲ አመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች ተሳታፊ እንደሆኑ ለማዎቅ ተችሏል። በዚህ የወንጀል ተግባር ላይ ከባለስልጣናትም በተጨማሪ ሌሎች ግለሰቦችም እጃቸዉ እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን የማጣራት ስራ እየተሰራም እንደሆነ ታዉቋል። እስካሁንም በተገኘዉ መረጃ በተለያዩ መንገዶች ከሀገር በርካታ ገንዘብ እንደሸሸ እና በግለሰቦች ስም ዓለም አቀፍ ባንኮች ውስጥ እንዳለ የተደረሰበት ሲሆን አሁን ላይ ገንዘቦች በሚመለሱበት ሁኔታ ከየሀገራቱ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል። አያይዘዉም በርሃኑ ጸጋዬ እንደገለጹት የሕዝብን ሀብት ዘርፈዉ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ገንዘቡን ለመንግስት በመመለሳቸዉ የተለቀቁ ግለሰቦች እንዳሉ ጠቁመዋል። ከዚህም በተጨማሪ እዚሁ ሀገር ዉስጥ በግለሰብ ደረጃ የባንክን ስራ ተክተዉ የሚሰሩ የዉጭ ሀገራት ገንዘቦችን መመንዘርን ጨምሮ ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ ግለሰቦች እንዳሉ የተደረሰበት ሲሆን መረጃ በመሰብሰብ ወደ ሕግ የማቅረብ ስራ እየተሠራ እንደሆነ ተገልጿል። ተያይዞም እንደተገለጸዉ በኅብረተሰቡ ጥቆማ እና ከሕግ አካላት ጋር በተደረገ ርብርብ በመላ ኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወርና ከሀገር ሊወጣ የነበረ በርካታ የዉጭ ሀገራት ገንዘብ ለመያዝ ተችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ዝዉዉር በተጨማሪ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እጃቸዉ አለበት በተባሉ የመንግሥት ሥልጣን ላይ በነበሩ ግለሰቦች ላይ ዐቃቤ ሕጉ ከተናገሩት ለመረዳት እንደተቻለዉ በሁሉም ክልሎች የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ወንጀለኞችን የመደበቅ ሁኔታ እየታየ ሲሆን በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑትንም እንደሚደብቁ ታዉቋል። በዚህ ጉዳይ ከክልሎች ጋር ዉይይት ቢደረግም እስካሁን የታየ ለዉጥ የለም ነገር ግን በቅርቡ ዉጤት ላይ ይደረሳል ብለዋል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ የቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት ኃላፊ ስለነበሩት ጌታቸዉ አሰፋ ጉዳይ በተመለከተ “ዐቃቤ ሕግ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ እንዳሉ መረጃዉ ቢኖረዉም በክልሉ መንግሥት እምቢተኛነት ለሕግ ማቅረብ እንዳልተቻለ” ገልጸዋል። ፟“እኛ ፖለቲካ እና ወንጀልን ለያይተን ነዉ ምናየዉ ጥያቄያችንም ወንጀል ‘ሰርቷል ወይስ አልሰራም’ በሚሉት ጉዳይ ላይ ነዉ፟ ምክንያቱም ለሕግ የበላይነት መከበር ጠንክረን መሥራት ስላለብን ነዉ።” በማለት ብርሃኑ በአጽዕኖት ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕጉ በክልሎች እየታየ ባለዉ ወንጀለኛን የመደበቅ ሁኔታ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቋም ወስዶ ዉሳኔ እንዲያሳልፍም ጠይቀዋል። የቀድሞ የድኅንነት ኃላፊ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እጃቸው መኖር አለመኖሩ ላይ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ የተሰራ እንደሆነ መሆኑን የገለጹት ብርሃኑ በቁጥጥር ስር ለማዋል ግን ችግር እንደገጠማቸዉ ገልፀዋል። “አንድ ግለሰብ ለመያዝ ተታኩሰን ወደ ጦርነት በመግባት የሰው ነብስ አናጠፋም” ሲሉም አክለዋል። በወንጀል ተጠርጥረዉ ከአገር የወጡ ግለሰቦች ደግሞ በቁጥጥር ስር ዉለው ተላልፈዉ የሚሰጡበትን መንገድ እየተመቻቸ እንደሆነ እና ከአገራትም ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን በሪፖርቱ ተገልጿል።
በመጨረሻም ዐቃቤ ሕጉ በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩትን የጦር መሳሪያም ሆነ ገንዘብ የመቆጣጠር ሥራዉ ከመቼዉም ጊዜ በተለየ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዉ የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝዉዉር ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ የቁጥጥር ሒደቱን በሚገባ ያግዛል ብለዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011